በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማሬ—ጥንታዊቷ የበረሃ ንግሥት

ማሬ—ጥንታዊቷ የበረሃ ንግሥት

ማሬ—ጥንታዊቷ የበረሃ ንግሥት

“የዚያን ዕለት ቀንቶን ስለዋልን ከጓደኞቼ ጋር ስንገባበዝ አምሽተን ወደ መኝታ ክፍሌ ስመለስ ደስታ የምሆነውን አሳጥቶኝ ነበር” በማለት አንድሬ ፓሮ የተባሉት ፈረንሳዊ አርኪኦሎጂስት ገጠመኛቸውን ያስታውሳሉ። በጥር ወር 1934 ፓሮና የሥራ ባልደረቦቻቸው ሶርያ ውስጥ በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ በምትገኘው አቡ ከማል በምትሰኝ አነስተኛ ከተማ አቅራቢያ ባለችው በቴል ሃሪሪ አንድ ሐውልት አገኙ። ሐውልቱ “ላምጊ ማሬ፣ የማሬ ንጉሥ፣ የኢንሊል ሊቀ ካህን” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል። ፓሮና ባልደረቦቻቸው ይህ ግኝት በጣም አስደስቷቸው ነበር።

ማሬ በመባል የምትታወቀው ከተማ በመጨረሻ ተገኘች! ታዲያ የዚህች ከተማ መገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?

ማሬ ትኩረታችንን የምትስበው ለምንድን ነው?

ማሬ የተባለች ከተማ እንደነበረች ከጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ማወቅ ቢቻልም ትክክለኛ ቦታዋ ግን ለረዥም ጊዜ ምስጢር ሆኖ ቆይቷል። ሱሜሪያን ጸሐፊዎች ማሬ፣ በአንድ ወቅት መስጴጦሚያን ባጠቃላይ ያስተዳድር ነበር ተብሎ የሚገመት ሥርወ መንግሥት መቀመጫ እንደነበረች ይገልጻሉ። በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ ላይ የተገነባችው ማሬ የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከአሶር፣ ከመስጴጦሚያ፣ ከአናቶሊያ እንዲሁም ከሜዲትራንያን ጠረፍ አካባቢ ጋር በሚያገናኙት የንግድ መሥመሮች መተላለፊያ ላይ ቁልፍ በሆነ ቦታ ትገኝ ነበር። እንደ እንጨት፣ ብረትና ድንጋይ የመሳሰሉት በመስጴጦሚያ ጨርሶ የማይገኙ ነገሮች በዚህች ከተማ በኩል ያልፉ ስለነበር ማሬ ከቀረጥ የምታገኘው ገቢ እጅግ አበለጸጋት። ይህም አካባቢውን ለመቆጣጠር አስችሏት ነበር። ሆኖም የአካድ ገዥ የነበረው ሳርጎን ሶርያን ሲወርር የማሬ ኃያልነት አከተመ።

ከሳርጎን ወረራ በኋላ ለ300 ዓመታት ያህል ማሬ በተለያዩ ወታደራዊ መንግሥታት ትተዳደር የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅት በተወሰነ መጠን የቀድሞ ብልጽግናዋን ማግኘት ችላለች። ይሁን እንጂ የመጨረሻው የማሬ ንጉሥ በሆነው በዚምሪ ሊም ዘመነ መንግሥት ከተማዋ ወደ ውድቀት እያመራች ነበር። ዚምሪ ሊም ተከታታይ ወታደራዊ ወረራዎችና ስምምነቶች በማድረግ እንዲሁም የጋብቻ ዝምድናዎች በመመሥረት የግዛቱን አንድነት ለማጠናከር ሞክሯል። ሆኖም በ1760 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ የባቢሎኑ ንጉሥ ሃሙራቢ ከተማዋን በመውረር ፓሮ “በጥንቱ ዓለም ከፍተኛ ሥልጣኔ ላይ ከደረሱት” ከተሞች አንዷ እንደሆነች የተናገሩላትን ማሬን አወደማት።

የሃሙራቢ ወታደሮች ማሬን ሲያፈራርሱ ሳያውቁት በዛሬው ጊዜ ያሉ አርኪኦሎጂስቶችንና ታሪክ ጸሐፊዎችን የሚጠቅም ሥራ አከናውነዋል። ካልተቃጠለ የጭቃ ጡብ የተሠራውን ግንብ ሲንዱ አንዳንድ ሕንጻዎችን እስከ 5 ሜትር በሚደርስ የፍርስራሽ ክምር ውስጥ የቀበሯቸው ሲሆን ይህም ሕንጻዎቹ ከጊዜ ብዛት ሳይበላሹ እንዳሉ ተጠብቀው እንዲቆዩ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዛሬ አርኪኦሎጂስቶች በቁፋሮ ያገኟቸው የፈራረሱ ቤተ መቅደሶችና ቤተ መንግሥቶች እንዲሁም በርካታ ዕደ ጥበባትና በሺዎች የሚቆጠሩ የተቀረጹ ጽሑፎች ስለ ጥንቱ ዓለም ሥልጣኔ ብዙ ለማወቅ አስችለዋል።

የማሬ ፍርስራሾች ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው? የእስራኤላውያን ቅድመ አያት የሆነው አብርሃም የኖረበትን ዘመን እናስብ። አብርሃም የተወለደው በ2018 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን በዚህ ወቅት ታላቁ የጥፋት ውኃ ከመጣ 352 ዓመታት አልፈው ነበር። አብርሃም የኖረው ከኖኅ በኋላ በአሥረኛው ትውልድ ላይ ነው። አብርሃም አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል የትውልድ ከተማውን ዑርን ለቅቆ ወደ ካራን ተጓዘ። በ1943 ከክርስቶስ ልደት በፊት አብርሃም 75 ዓመት ሲሆነው ከካራን ተነስቶ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። ጣልያናዊው አርኪኦሎጂስት ፓውሎ ማቲይ “አብርሃም ከዑር ተነስቶ [በከነዓን ወደምትገኘው] ወደ ኢየሩሳሌም የፈለሰው በታሪክ ውስጥ ማሬ በነበረችበት ወቅት ነው” ብለዋል። በመሆኑም የማሬ መገኘት የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው አብርሃም የኖረበት ዘመን ምን ይመስል እንደነበረ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል ይረዳናል። aዘፍጥረት 11:10 እስከ 12:4

የከተማዋ ፍርስራሾች ምን ያሳያሉ?

በሌሎች የመስጴጦሚያ ግዛቶች እንደሚደረገው ሁሉ በማሬም ሃይማኖት ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። የሰው ልጅ አማልክትን የማገልገል ግዴታ እንዳለበት የሚታሰብ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ ማንኛውንም ከበድ ያለ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት አማልክቱን ይጠይቅ ነበር። አርኪኦሎጂስቶች የስድስት ቤተ መቅደሶችን ፍርስራሽ አግኝተዋል። ከእነዚህ ቤተ መቅደሶች መካከል የአናብስት ቤተ መቅደስ (አንዳንዶች የዳጋን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው የዳጎን ቤተ መቅደስ እንደሆነ ይናገራሉ) እንዲሁም የመራባት አምላክ የሆነችው የኢሽታርና የፀሐይ አምላክ የሆነው የሻማሽ መቅደሶች ይገኙበታል። በእነዚህ ቤተ መቅደሶች ውስጥ፣ መሥዋዕትና ጸሎት የሚቀርብለት አምላክ ምስል ይገኝ ነበር። አማኞች በገጽታቸው ላይ ፈገግታ የሚነበብባቸውን የራሳቸውን ምስሎች በመሥራት በመቅደሱ ውስጥ ወንበር ላይ ያስቀምጡ የነበረ ሲሆን ይህን የሚያደርጉት ምስላቸው እነርሱን ተክቶ አምልኮ ማቅረቡን ይቀጥላል በሚል እምነት ነበር። ፓሮ እንዳሉት “በዛሬው ጊዜ በካቶሊክ እምነት አምልኮ ለማቅረብ ሻማ እንደሚበራ ሁሉ ምስሉ ደግሞ ከዚህ በላቀ መንገድ የአማኙ ምትክ” እንደሆነ ይታመን ነበር።

በቴል ሃሪሪ ከተገኙት ነገሮች ሁሉ በጣም አስደናቂ የሆነው በመጨረሻው የማሬ ንጉሥ በዚምሪ ሊም ስም የሚጠራው ትልቅ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ነው። ልዊ ሁግ ቫንሳን የተባሉት ፈረንሳዊ አርኪኦሎጂስት ይህ ቤተ መንግሥት “የጥንቱ የሩቅ ምሥራቅ ሥነ ሕንፃ ድንቅ ሥራ” እንደሆነ ገልጸዋል። ቤተ መንግሥቱ የታነጸው 2.5 ሄክታር በሚሸፍን ቦታ ላይ ሲሆን 300 ክፍሎችና አደባባዮች አሉት። በጥንቱ ዘመንም እንኳ ይህ ቤተ መንግሥት የዓለም ድንቅ ሥራ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ዦርዥ ሩ ኤንሸንት ኢራክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “[ቤተ መንግሥቱ] ዝናው በጣም የገነነ ከመሆኑ የተነሳ በሶርያ ጠረፍ የምትገኘው የኡጋሪት ንጉሥ ልጁ 600 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ‘የዚምሪ ሊምን ቤት’ እንዲመለከት ለመስደድ አላመነታም።”

ጎብኚዎች ሰፊ ወደሆነው አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት ግራና ቀኝ በግንብ ወደተከለለውና አንድ መግቢያ ብቻ ወዳለው በቀላሉ የማይደፈር ቤተ መንግሥት ይገባሉ። በዚህ ቦታ የመጨረሻው የማሬ ንጉሥ ዚምሪ ሊም ከፍ ባለ መድረክ ላይ በሚገኝ ዙፋን ተቀምጦ ወታደራዊ፣ ንግድ ነክና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮችን ይመለከት እንዲሁም ፍርድ ይሰጥና እንግዶችንና አምባሳደሮችን ይቀበል ነበር። ለእንግዶች ማረፊያ የተዘጋጁ ክፍሎች የነበሩ ሲሆን እንግዶቹም ንጉሡ በሚያደርጋቸው ድል ያሉ ድግሶች ላይ ሁልጊዜ ይገኛሉ። በግብዣው ላይ የተጠበሰ ወይም የተቀቀለ የበሬ፣ የበግ፣ የሜዳ ፍየል፣ የዓሣና የዶሮ ሥጋ በቅመም ከተዘጋጀ የነጭ ሽንኩርት ስጎ እንዲሁም ከተለያየ ዓይነት አትክልትና ከአይብ ጋር ይቀርባል። ከምግብ በኋላ ደግሞ የደረሱ ፍራፍሬዎች፣ በተራቀቀ ቅርጽ የተሠሩ ኬኮች እንዲሁም የደረቁ ወይም ስኳር የተቀቡ ፍራፍሬዎች ይቀርባሉ። እንግዶቹ ጥማቸውን ለማርካት ቢራ ወይም ወይን ይቀርብላቸው ነበር።

በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የንጽሕና ጉዳይም ቢሆን ችላ አልተባለም። በሸክላ የተሠሩ መታጠቢያ ገንዳዎችና መቀመጫ የሌላቸው መጸዳጃ ቤቶች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ወለሎቹና የግድግዳዎቹ የታችኛው ክፍል ውኃ እንዳያስገቡ ቅጥራን ተለቅልቀዋል። ለፍሳሽ ማስወገጃ ከጡብ በተሠሩ ቦዮችና ቅጥራን በተለቀለቁ የሸክላ ቱቦዎች ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን እነዚህ ቦዮች ወደ 3,500 ዓመታት የሚጠጋ ዕድሜ ቢኖራቸውም አሁንም ይሠራሉ። ከንጉሡ ሚስቶችና ቁባቶች መካከል ሦስት ሴቶች የሚገድል በሽታ እንደያዛቸው ሲታወቅ በሽታው እንዳይሰራጭ ለማድረግ ጥብቅ መመሪያ ወጥቶ ነበር። በዚህ በሽታ የተያዘች ሴት ለብቻዋ ተለይታ እንድትኖር ከመደረጉም በላይ “ማንም ሰው በእርሷ መጠጫ እንዳይጠቀም፣ በምትመገብበት ጠረጴዛ ላይ እንዳይመገብ እንዲሁም የምትቀመጥበት ወንበር ላይ እንዳይቀመጥ” የሚል ትእዛዝ ተላልፎ ነበር።

በቁፋሮ ከተገኙት ነገሮች ምን ትምህርት እናገኛለን?

ፓሮና ባልደረቦቻቸው የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት በአካድያን ቋንቋ የተጻፉ 20,000 ጽላቶች አግኝተዋል። በእነዚህ ጽላቶች ላይ ደብዳቤዎች እንዲሁም አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸው ጽሑፎች ሰፍረዋል። በቁፋሮ ከተገኙት ከእነዚህ ጽላቶች መካከል ለሕትመት የበቁት አንድ ሦስተኛ ያህሉ ብቻ ቢሆኑም እነዚህ ራሳቸው 28 ጥራዞች ሆነዋል። እነዚህ ግኝቶች ምን ጥቅም አላቸው? በማሬ የተካሄደውን አርኪኦሎጂያዊ ሥራ የመሩት ዣን ክሎድ ማርገሮን እንዲህ ብለዋል:- “በማሬ ያሉት ቅርሶች ከመገኘታቸው አስቀድሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ስለነበረው የመስጴጦሚያና ሶርያ ታሪክ፣ የሕዝቡ ማኅበራዊ ግንኙነትና ልማድ እንዲሁም ዕለታዊ ሕይወት ምንም አናውቅም ነበር ማለት ይቻላል። እነዚህ [ጽላቶች] የነበረንን የተሳሳተ አመለካከት ለማረምና በርከት ያለ ተጨማሪ ታሪክ ለመጻፍ ስላስቻሉን ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።” ፓሮ እንደተናገሩት በቁፋሮ የተገኙት ነገሮች “በወቅቱ ስለነበሩት ሰዎች የያዙት ታሪክ በብሉይ ኪዳን ላይ ስለ ዕብራውያን አባቶች ዘመን ከሰፈረው ዘገባ ጋር በሚያስገርም መንገድ ይመሳሰላል።”

ከዚህም በላይ በማሬ የተገኙት ጽላቶች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግልጽ እንዲሆኑልን ያደርጋሉ። ለአብነት ያህል፣ የጠላትን ሚስቶችና ቁባቶች መውሰድ “በወቅቱ በነበሩ ነገሥታት ዘንድ የተለመደ” እንደሆነ በጽላቶቹ ላይ ተገልጿል። ስለዚህ ከሃዲው አኪጦፌል የንጉሥ ዳዊት ልጅ አቤሴሎም ከአባቱ ቁባቶች ጋር እንዲተኛ የሰጠው ምክር አዲስ ሐሳብ አልነበረም።—2 ሳሙኤል 16:21, 22

ከ1933 ወዲህ በቴል ሃሪሪ 41 አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮዎች ተደርገዋል። ያም ሆኖ ግን ማሬ ከነበረችበት 110 ሄክታር የሚሸፍን ቦታ ውስጥ እስካሁን ድረስ ምርምር የተካሄደበት 8 ሄክታር የሚሆነው ብቻ ነው። ወደፊት በጥንታዊቷ የበረሃ ንግሥት በማሬ በርካታ አስደናቂ ግኝቶች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከወደመች በኋላ ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን በፈራረሰችው የማሬ ከተማ ዳርቻ አልፈው ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የፋርስ ባሕረ ሰላጤ

ዑር

መስጴጦሚያ

የኤፍራጥስ ወንዝ

ማሬ

አሶር

ካራን

አናቶሊያ

ከነዓን

ኢየሩሳሌም

የሜዲትራንያን ባሕር (ታላቁ ባሕር)

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ ጽላት ላይ የማሬ ንጉሥ የነበረው ያህዱን ሊም ስላከናወነው የግንባታ ሥራ በጉራ ገልጿል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ የላሚጊ ማሬ ምስል መገኘቱ ማሬን በእርግጠኝነት ለማወቅ አስችሏል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማሬ ተቆጣጣሪ የሆነው ኢቢሂል ሲጸልይ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የተገኘው ይህ መድረክ የአንዲት አምላክ ምስል ተቀምጦበት የነበረ ሊሆን ይችላል

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል12]

ባልተቃጠለ የጭቃ ጡብ ይሠራ የነበረውን ግንባታ የሚያሳይ የማሬ ፍርስራሽ

[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል12]

በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኝ መታጠቢያ ቤት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሬን የወረራት ናራም ሲን ስላገኘው ድል የሚገልጽ ሐውልት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተ መንግሥቱ ፍርስራሾች ውስጥ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ 20,000 ያህል ጽላቶች ተገኝተዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Mission archéologique française de Tell Hariri - Mari (Syrie)

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ጽላት:- Musée du Louvre, Paris; ሐውልት:- © Mission archéologique française de Tell Hariri - Mari (Syrie)

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ምስል:- Musée du Louvre, Paris; መድረኩና መታጠቢያ ቤቱ:- © Mission archéologique française de Tell Hariri - Mari (Syrie)

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የድል ሐውልት:- Musée du Louvre, Paris; የቤተ መንግሥት ፍርስራሽ:- © Mission archéologique française de Tell Hariri - Mari (Syrie)