በቅርቡ ድህነት የሌለበት ዓለም ይመጣል
በቅርቡ ድህነት የሌለበት ዓለም ይመጣል
በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ እንደሚታየው ያሉ የገነት ሥዕሎች በድህነት የሚማቅቁ ሰዎችን ትኩረት ይስባሉ። ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለአዳምና ለሔዋን ገነት እውን ነበረች። የመኖሪያ ሥፍራቸው ዔድን ገነት ነበር። (ዘፍጥረት 2:7-23) ምንም እንኳ የመጀመሪያዋ ገነት የጠፋች ቢሆንም ወደፊት በምትኖረው ገነት ድህነት የሌለበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ያለን እምነት ሕልም ብቻ ሆኖ አይቀርም። እንዲህ ያለው እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ተስፋዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ላይ የገባውን ቃል እንመልከት። ከኢየሱስ ጋር የሞተው ክፉ አድራጊ አምላክ ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ችሎታ እንዳለው ያምን ነበር። “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። ይህ ክፉ አድራጊ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛና ሙታን ወደ ሕይወት እንደሚመለሱ እምነት ነበረው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።—ሉቃስ 23:42, 43
መጽሐፍ ቅዱስ በገነት ውስጥ ስለሚኖሩት ሰዎች ሲናገር “ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ” ይላል። (ኢሳይያስ 65:21) አዎን፣ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።”—ሚክያስ 4:4
ታዲያ አምላክ በአሁኑ ጊዜ ድህነት እንዲኖር ለምን ፈቀደ? አምላክ በድህነት ለተጠቁ ሰዎች ምን ዓይነት እርዳታ ይሰጣቸዋል? ድህነት የሚወገደው መቼ ነው?
አምላክ ድህነት እንዲኖር ለምን ፈቀደ?
ሰይጣን ዲያብሎስ ባነሳሳው ዓመፅ ምክንያት አዳምና ሔዋን ይኖሩባት የነበረችው ገነት ጠፍታለች። ሰይጣን እባብን እንደ አፈ ቀላጤ በመጠቀም ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ጥሳ ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ እንድትበላ አደረጋት። ከአምላክ ፈቃድ ውጪ በራሷ መመራት የተሻለ ሕይወት እንደሚያመጣላት በማሳመን አታለላት። ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ አንስታ ስትሰጠው አዳም የአምላክን ትእዛዝ ጥሶ የሚስቱን ቃል በመስማት ፍሬውን በላ።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14
ዓመፀኞቹ ባልና ሚስት ወዲያውኑ ከገነት መባረራቸው የተገባ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ለአምላክ አለመታዘዝ የሚያስከትለው ውጤት እንዲታይ ይሖዋ እስከ ዛሬ ድረስ ሰይጣንን ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች ላይ እንዲገዛ ፈቅዶለታል። ሰብዓዊ አገዛዝ ምድር ላይ ገነትን ለማምጣት እንዳልቻለ የሰው ልጅ ታሪክ አረጋግጧል። (ኤርምያስ 10:23) ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ርቆ በራስ መመራት ድህነትን ጨምሮ ከባድ ችግሮችን አስከትሏል።—መክብብ 8:9
ሆኖም በዚህ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ ድሆች ያለ ረዳት አልተተዉም። በአምላክ መንፈስ
አነሳሽነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ግሩም የሆነ መመሪያ ይዞላቸዋል።“አትጨነቁ”
በርካታ ድሆችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? . . . ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል።”—ማቴዎስ 6:26-33
ድሃ የሆነ ሰው የግድ መስረቅ አያስፈልገውም። (ምሳሌ 6:30, 31) በሕይወቱ ውስጥ አምላክን ካስቀደመ የሚያስፈልገው ይሟላለታል። በደቡባዊ አፍሪካ በምትገኘው በሌሶቶ የሚኖረውን ቱኪሶን እንመልከት። በ1998 በመንግሥት ላይ የተነሳውን ዓመፅ ለማስቆም የውጭ አገር ጦር ወደ ሌሶቶ ገባ። በዚህ ጦርነት ምክንያት ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል እንዲሁም ከፍተኛ የምግብ እጥረት ነበር።
ቱኪሶ የሚኖረው በዋና ከተማው ውስጥ በጣም ድሃ በሆነው አካባቢ ነው። በርካታ ጎረቤቶቹ ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ሱቆችን ዘርፈዋል። ቱኪሶ ወደ ባለአንድ ክፍል መኖሪያ ቤቱ ሲመለስ አብራው የምትኖረው ማሴሶ የሰረቀችውን በጣም ብዙ ሸቀጣ ሸቀጥ አየ። ቱኪሶ “ይህንን ነገር ከዚህ አውጪው” ካላት በኋላ መስረቅ ከአምላክ ሕግ ጋር እንደሚቃረን አስረዳት። ማሴሶም እንደተባለችው አደረገች። ጎረቤቶቹ በእነሱ ላይ ካፌዙባቸው በኋላ የተሰረቀውን ምግብ ለራሳቸው ወሰዱት።
ቱኪሶ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ባገኘው እውቀት ምክንያት ይህንን ዓይነት እርምጃ ሊወስድ ችሏል። ታዲያ ለአምላክ ሕግ በመታዘዙ ምክንያት ተራበ? በፍጹም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እሱ በሚሰበሰብበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ምግብ ይዘውለት መጡ። እንዲያውም ጎረቤት አገር በሆነችው በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሶቶ ለሚኖሩ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ከሁለት ቶን በላይ እርዳታ ልከዋል። ማሴሶ፣ ቱኪሶ ለአምላክ ባሳየው ታዛዥነትና ጉባኤው በፍቅር ተነሳስቶ ባደረገላቸው እርዳታ ስሜቷ ስለተነካ እሷም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በመጨረሻም፣ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ካደረጉ በኋላ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን በቁ። እስከ አሁን ድረስ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ይሖዋ አምላክ ለድሆች ያስባል። (“አምላክ ለድሆች ያለው አመለካከት ምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሖዋ እንደ ቱኪሶና ማሴሶ ያሉ ሰዎች
ስለ እሱ ብዙ ነገር እንዲያውቁ ለመርዳት ፍቅራዊ ዝግጅቶችን አድርጓል። ከዚህም በላይ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙንን ተግባራዊ ምክሮች ሰጥቶናል።ግሩም የሆኑ ዝግጅቶች
የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ለድሆች ያለውን አሳቢነት ምንጊዜም ለማንጸባረቅ ይጥራሉ። (ገላትያ 2:10) ብዙውን ጊዜ በአንድ አካባቢ አደጋ ተከስቶ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጉዳት ሲደርስባቸው አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት አንዳንድ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። ከሁሉም በላይ ምሥክሮቹ የሚያሳስባቸው ድሆችን ጨምሮ ሰዎችን ሁሉ በመንፈሳዊ የመርዳቱ ጉዳይ ነው። (ማቴዎስ 9:36-38) ላለፉት 60 ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን በባዕድ አገር ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ቱኪሶና ማሴሶ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የረዷቸው የሴሶቶን ቋንቋ የተማሩ ከፊንላንድ የመጡ ሚስዮናውያን ናቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ የመሰለው የሚስዮናዊነት ሥራ በበለጸጉ አገሮች ምቾት ያለውን ኑሮ ትቶ ድሃ ወደሆኑ አገሮች መምጣትን ይጠይቃል።
ለመኖር ሲባል መስረቅ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ ምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ አምላክ ባለው የመስጠት ችሎታ ላይ እምነት አላቸው። (ዕብራውያን 13:5, 6) ይሖዋ ሕዝቡን የሚንከባከብበት አንደኛው መንገድ እርስ በርስ በሚተሳሰቡ አምላኪዎቹ በተዋቀረው ዓለም አቀፋዊ በሆነው ድርጅቱ በኩል ነው።
ይሖዋ ድሆችን የሚረዳበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ በዕለታዊ ሕይወታቸው ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ተግባራዊ ምክሮችን በመስጠት ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ኤፌሶን 4:28) ሥራ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አትክልት እንደ መትከልና መንከባከብ የመሳሰሉ የጉልበት ሥራዎችን በማከናወን ለራሳቸው ሥራ መፍጠር ችለዋል። ሠርተው የሚያገኙትን ገንዘብ እንዳያባክኑ መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መውሰድን የመሳሰሉ መጥፎ ልማዶችን እንዲያስወግዱ ያስተምራቸዋል።—ኤፌሶን 5:18
ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። (ድህነት የሌለበት ዓለም የሚመጣው መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያመለክተው የምንኖረው በሰይጣን አገዛዝ “መጨረሻው ዘመን” ላይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰው ልጆች ላይ እንዲፈርድ በቅርቡ ይልከዋል። በዚያን ጊዜ ምን ይሆናል? ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ መልሱን ሰጥቷል። እንዲህ ብሏል:- “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እርሱም፣ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል።”—ማቴዎስ 25:31-33
በዚህ ምሳሌ ላይ በጎች ተብለው የተጠሩት ለኢየሱስ ንግሥና የሚገዙ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስን እንደ እረኛቸው አድርገው ስለሚከተሉት በበጎች መመሰላቸው ተገቢ ነው። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ በግ መሰል ሰዎች በኢየሱስ ፍጹም አገዛዝ ሥር ሕይወት ያገኛሉ። ድህነት በሌለበት አዲስ ዓለም ውስጥ አስደሳች ሕይወት ይኖራቸዋል። የኢየሱስን ንግሥና የሚቃወሙ ፍየል መሰል ሰዎች ግን ለዘላለም ይጠፋሉ።—ማቴዎስ 25:46
የአምላክ መንግሥት ክፋትን ስታስወግድ ድህነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል። በምትኩ ምድር እርስ በርሳቸው በሚዋደዱና በሚተሳሰቡ ሰዎች ትሞላለች። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ዓለም አቀፍ የወንድማማች መዋደድ አዲሱ ዓለም እንደሚመጣ ያሳያል፤ ይህን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:35
[በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አምላክ ለድሆች ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ፈጣሪ “ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ” እንደሆነ ይገልጻል። (መዝሙር 146:7) አምላክ ለድሆች እንደሚያስብ የሚገልጹ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሕጉን ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር በሰጣቸው ጊዜ በእስራኤል ውስጥ የሚገኙትን ገበሬዎች በእርሻቸው ዳርና ዳር ያለውን ሰብል እንዳያጭዱት እንዲሁም የወይራ ዛፍና የወይን ተክል ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰው እንዳይሄዱ አዟቸው ነበር። እነዚህ ሕጎች ለመጻተኞች፣ ወላጆች ለሌሏቸው፣ ለመበለቶች እንዲሁም ለድሆች ተብለው የተደረጉ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ነበሩ።—ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19-21
በተጨማሪም አምላክ እስራኤላውያንን እንዲህ በማለት አዟቸዋል:- “ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ። ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ። ቊጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የለሽ ይሆናሉ።” (ዘፀአት 22:22-24) ባለጠጋ የሆኑት ብዙ እስራኤላውያን ግን ይህንን መመሪያ ሳይታዘዙ መቅረታቸው ያሳዝናል። ለዚህና ለሌላው ክፉ ሥራቸው ይሖዋ አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 10:1, 2፤ ኤርምያስ 5:28፤ አሞጽ 4:1-3) በመጨረሻም አምላክ አሦራውያን ከዚያም ባቢሎናውያን እስራኤልን ድል አድርገው እንዲይዙ አድርጓል። ብዙ እስራኤላውያን የተገደሉ ሲሆን የተረፉት ደግሞ ምርኮኞች ሆነው ወደ ባዕድ አገር ተወስደዋል።
የአምላክ ውድ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አባቱ ለድሆች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል። ኢየሱስ የአገልግሎቱን ዓላማ ሲናገር “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና” ብሏል። (ሉቃስ 4:18) ይህን ሲል ግን የኢየሱስ አገልግሎት ለድሆች ብቻ የተወሰነ ነበር ማለት አይደለም። ባለጠጋ የሆኑትንም ሰዎች በፍቅራዊ ሁኔታ ረድቷቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ባለጠጋዎችን ቢረዳም ብዙውን ጊዜ የድሆች ደህንነት እንደሚያሳስበው ይገልጽ ነበር። ለምሳሌ ለአንድ ባለጠጋ አለቃ “ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” የሚል ምክር ሰጥቶታል።—ሉቃስ 14:1, 12-14፤ 18:18, 22፤ 19:1-10
ይሖዋ አምላክና ልጁ ለድሆች በጥልቅ ያስባሉ። (ማርቆስ 12:41-44፤ ያዕቆብ 2:1-6) በሚሊዮን የሚቆጠሩ በሞት ያንቀላፉ ድሆችን ይሖዋ የሚያስታውሳቸው መሆኑ ለድሆች ያለውን አሳቢነት ያሳያል። እነዚህ ሁሉ ከሞት ተነስተው ከድህነት ነጻ በሆነ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።—የሐዋርያት ሥራ 24:15
[ሥዕሎች]
በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት አዲሱ ዓለም እንደሚመጣ ያሳያል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቱኪሶና ማሴሶ፣ ቱኪሶን መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናው ሚስዮናዊ ጋር
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማሴሶ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናቻት ሚስዮናዊት ጋር በቤቷ ደጃፍ ላይ