በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ በሚገኘው እውቀት ችግሮቻቸውን መፍታት የቻሉ ቤተሰቦች

ከአምላክ በሚገኘው እውቀት ችግሮቻቸውን መፍታት የቻሉ ቤተሰቦች

“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው”

ከአምላክ በሚገኘው እውቀት ችግሮቻቸውን መፍታት የቻሉ ቤተሰቦች

“የበርሊን ግንብ።” በአርጀንቲና የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ቤታቸውን ለሁለት ለመክፈል የገነቡትን ግድግዳ እንዲህ በማለት ሰይመውት ነበር! በእነዚህ ባልና ሚስት መካከል የተፈጠረው የከረረ አለመግባባት እርስ በርስ እስከ መጠላላት አድርሷቸው ነበር።

ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው እነዚህ ባልና ሚስት ብቻ አለመሆናቸው ያሳዝናል። ጠብ፣ ታማኝነትን ማጉደል እንዲሁም ጥላቻ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኝ መቅሠፍት ሆኗል። ቤተሰብን ያቋቋመው አምላክ ሆኖ ሳለ እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ያሳዝናል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:23, 24) ቤተሰብ ጥልቅ ፍቅር ለማሳየት የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር መለኮታዊ ስጦታ ነው። (ሩት 1:9) የቤተሰብ አባሎች አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነቶች በመወጣት ይሖዋን ከማስከበርም አልፈው አንዳቸው ለሌላው የደስታ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። a

የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚኖረንን ግንዛቤ እርሱ እንዲቀርጸው መፍቀድ ይኖርብናል። የአምላክ ቃል የቤተሰብ ሕይወት የተሳካ እንዲሆን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ምክሮች ይዟል፤ በተለይ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ እነዚህ ምክሮች እርዳታ ያበረክታሉ። የባሎችን ኃላፊነት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎችም . . . ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል” ይላል። ባልየው ይህን ሲያደርግ ‘ሚስትም ባሏን ማክበር’ የሚያስደስት ነገር ይሆንላታል።—ኤፌሶን 5:25-29, 33

ሐዋርያው ጳውሎስ በወላጆችና በልጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ሲጽፍ:- “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ብሏል። (ኤፌሶን 6:4) ይህም የቤተሰቡ ሕይወት ፍቅር የሰፈነበት እንዲሆን ስለሚያደርግ ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ ቀላል ይሆንላቸዋል።—ኤፌሶን 6:1

ከላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ሕይወት አስመልክቶ አስተማማኝ ምክር እንደሚሰጥ ምሳሌ ይሆናሉ። ብዙ ቤተሰቦች መለኮታዊ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረጋቸው በቤታቸው ውስጥ ደስታ አግኝተዋል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሱትን በአርጀንቲና የሚገኙትን ባልና ሚስት እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለሦስት ወር ያህል ካጠኑ በኋላ ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር በተግባር ላይ ማዋል ጀመሩ። አንዳቸው ለሌላው ሐሳባቸውን የሚገልጹበትን መንገድ ለማሻሻል፣ ራሳቸውን በሌላው ቦታ ለማስቀመጥና ይቅር ባዮች ለመሆን ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። (ምሳሌ 15:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:7፤ 4:8) ንዴታቸውን መቆጣጠርና ሁኔታዎች ከቁጥጥራቸው በላይ በሚሆኑበት ጊዜ የአምላክን እርዳታ በጸሎት መጠየቅ እንደሚችሉ ተማሩ። (ቈላስይስ 3:19) ብዙም ሳይቆይ “የበርሊን ግንብ” ብለው የሰየሙት ግድግዳ ፈረሰ!

አምላክ ቤተሰብን ሊያጠናክር ይችላል

የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማወቅና በሥራ ላይ ማዋል ቤተሰቦች ተጽዕኖዎች ሲያጋጥሟቸው መቋቋም እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በዛሬው ጊዜ በቤተሰብ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ትንቢት ስለተነገረ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ በዘመናችን ስለሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀትና የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ዝቅጠት ቀደም ብሎ ተናግሯል። “በመጨረሻው ዘመን” ሰዎች ቅድስና የሌላቸው እንደሚሆኑ፣ “[የተፈጥሮ] ፍቅር” እንደማይኖራቸው እንዲሁም ‘ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው’ ልጆችም ጭምር ወላጆቻቸውን እንደማይታዘዙ ገልጾ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

አምላክን ለማስደሰት መሞከር የቤተሰብን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ እንደነዚህ ካሉ ነገሮች ለመራቅ ይረዳል። በርካታ ቤተሰቦች የሚያጋጥሟቸውን አብዛኞቹን ችግሮች ለመወጣት የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል። የቤተሰቡ አባላት ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው ከፈለጉ ከሁሉም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋልና “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” የሚለውን ጥቅስ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 127:1) በቤተሰብ ውስጥ ደስታን ለማስፈን የሚረዳው ትልቁ ነገር አምላክን በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ ነው።—ኤፌሶን 3:14, 15

በሃዋይ የሚገኝ ዴኒስ የተባለ ሰው ይህ እውነት መሆኑን ተመልክቷል። ምንም እንኳን ክርስቲያን ነኝ ይል የነበረ ቢሆንም ስድብና ጥል የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ክፍል ነበር። በጦር ሠራዊት ውስጥ ገብቶ ካገለገለ በኋላማ የባሰ መጥፎና ቁጡ ሰው ሆነ። “ከሰዎች ጋር ሁልጊዜ እጣላ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “ምንም ነገር ቢደርስብኝ ግድ አይሰጠኝም፤ ሞትንም አልፈራም ነበር። በዚህም ምክንያት መሳደቤንና መጣላቴን ቀጠልኩበት። ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክር ስለነበረች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና አበረታታችኝ።”

ዴኒስ ባለቤቱ የምታደርገውን ጥረት አልተቀበለውም። ሆኖም ክርስቲያናዊ አኗኗሯ መጥፎ አመለካከቱን አለሳለሰው። በመጨረሻም ዴኒስ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ጀመረ። በኋላም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለትና ጥሩ እድገት አደረገ። ለ28 ዓመታት ሲጋራ ያጨስ የነበረ ቢሆንም ይህን ልማድ እርግፍ አድርጎ ተወ፤ እንዲሁም ለማሸነፍ የሚፈልጋቸውን መጥፎ ድርጊቶች ከሚፈጽሙ ጓደኞቹ ጋር መሆን አቆመ። ዴኒስ ይሖዋ ላደረገለት ነገር ካለው አድናቆት የተነሳ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የቤተሰቤ ሕይወት እየተሻሻለ ሄደ። በቤተሰብ መልክ ወደ ስብሰባዎችና አገልግሎት አብረን መሄድ ጀመርን። ንዴቴን መቆጣጠር በመማሬና ስድብን ከናካቴው በማስወገዴ ሁለቱ ልጆቼ እኔን መፍራት አቆሙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን በማድረግ እንደሰታለን። መጽሐፍ ቅዱስን ባላጠና ኖሮ በጣም ግልፍተኛ ስለነበርኩ እስካሁን በሕይወት አልቆይም ነበር።”

ቤተሰቦች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የሚጥሩ ከሆነ ደስተኛ መሆን ይችላሉ። በቤተሰቡ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ የሚከተለው አንድ ሰው ብቻ እንኳን ቢሆን ይህን የሚያደርግ አንድም ሰው ከሌለበት ቤተሰብ ይልቅ ሁኔታዎች የተሻሉ እንደሚሆኑ ተሞክሮዎች ያሳያሉ። በክርስትና እምነት የሚመላለስ ቤተሰብ መገንባት ዘዴና ጊዜ ስለሚጠይቅ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ቤተሰብ ለመገንባት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ይሖዋ እንደሚባርካቸው ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል። እነሱም እንደ መዝሙራዊው “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” ማለት ይችላሉ።—መዝሙር 121:2 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ግንቦት/ሰኔ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከአምላክ “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል።”—ኤፌሶን 3:15

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይሖዋ የቤተሰብን ዝግጅት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

“እግዚአብሔርም፣ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት . . .’ ብሎ ባረካቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

“እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ . . . የተባረኩ ናቸው። . . . ሚስትህ በቤትህ፣ እንደሚያፈራ ወይን ናት።”—መዝሙር 128:1, 3