በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ዳዊትና ቤርሳቤህ ምንዝር በመፈጸማቸው እነርሱ ሳይገደሉ የተወለደው ልጅ እንዲሞት የተደረገው ለምንድን ነው?

የሙሴ ሕግ “አንድ ሰው፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፣ አብሮአት የተኛው ሰውና ሴቲቱ ሁለቱም ይገደሉ፤ ክፉውን ከእስራኤል ማስወገድ አለብህ” በማለት ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 22:22) ይሖዋ ዳዊትና ቤርሳቤህ ለሠሩት የኃጢአት ድርጊት ሰብዓዊ ዳኞች በሕጉ መሠረት ውሳኔ እንዲሰጡበት ቢያደርግ ኖሮ አመንዝራ የሆኑት ሁለቱም ሰዎች ይገደሉ ነበር። እነዚህ ዳኞች ልብን ማንበብ ስለማይችሉ ውሳኔ የሚሰጡት ግለሰቦቹ በፈጸሙት ድርጊት ላይ ብቻ ተመሥርተው ነው። በሕጉ መሠረት አመንዝራ የሆነ ሰው ሞት ይፈረድበት ነበር። እስራኤላውያን ዳኞች ደግሞ ይህን ኃጢአት ይቅር የማለት ሥልጣን አልነበራቸውም።

ከዚህ በተቃራኒ ግን እውነተኛው አምላክ ልብን በማንበብ የሚገባቸው ሆነው ላገኛቸው ኃጢአትን ይቅር ማለት ይችላል። ጉዳዩ የመንግሥት ቃል ኪዳን የገባለትን ዳዊትን የሚመለከት በመሆኑ ይሖዋ ሁኔታውን ለየት ባለ መንገድ ለመያዝና ፍርድ ለመስጠት መርጧል። (2 ሳሙኤል 7:12-16) “የምድር ሁሉ ዳኛ” እንደዚህ የማድረግ መብት አለው።—ዘፍጥረት 18:25

ይሖዋ የዳዊትን ልብ ሲመረምር ያየው ነገር ምን ይሆን? በመዝሙር 51 አናት ላይ የሰፈረው ሐሳብ፣ መዝሙሩ “ዳዊት ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ፣ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ” የተሰማውን ስሜት የሚገልጽ መሆኑን ያሳያል። መዝሙር 51:1-4 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ። በደሌን ፈጽሞ እጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ። እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው። . . . አንተን፣ በእርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።” ይሖዋ ዳዊት በጣም እንደተጸጸተ የሚያሳየውን ይህንን ልመና እውነተኛ ንስሐ ስለመግባቱ ማስረጃ አድርጎ ተመልክቶት መሆን አለበት። ከዚህም በመነሳት ለጥፋተኞቹ ምሕረት ለማሳየት የሚያበቃ ምክንያት እንዳለ ወስኗል። ከዚህም በላይ ዳዊት ራሱ መሐሪ ነበር፤ ይሖዋ ደግሞ ለመሐሪዎች ምሕረት ያሳያል። (1 ሳሙኤል 24:4-7፤ ማቴዎስ 5:7፤ ያዕቆብ 2:13) ስለዚህም ዳዊት ኃጢአቱን ባመነበት ወቅት ናታን “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም” ብሎታል።—2 ሳሙኤል 12:13

ዳዊትና ቤርሳቤህ የሠሩት የኃጢአት ድርጊት ከሚያስከትልባቸው መዘዝ ሙሉ በሙሉ አምልጠዋል ማለት ግን አይደለም። ናታን ለዳዊት “ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል” ብሎታል። ዳዊት ለሰባት ቀናት ቢጾምና ቢያዝንም ልጃቸው ታሞ መሞቱ አልቀረም።—2 ሳሙኤል 12:14-18

አንዳንዶች ዘዳግም 24:16 “ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ” እያለ ልጁ የሞተበትን ምክንያት ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል። መዘንጋት የሌለብን ነገር ጉዳዩ በሰብዓዊ ዳኞች ታይቶ ቢሆን ኖሮ ወላጆቹም ሆኑ በእናቲቱ ማኅፀን ያለው ጽንስ ይሞቱ ነበር። ከዚህም በላይ የልጁ መሞት ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በፈጸመው ድርጊት ይሖዋ ምን ያህል እንዳዘነ በግልጽ እንዲገነዘብ ረድቶት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ “መንገዱ ፍጹም” ስለሆነ ፍትሐዊ እርምጃ እንደወሰደ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።— 2 ሳሙኤል 22:31

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት እውነተኛ ንስሐ አሳይቷል