በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን መንገድ መማር

የይሖዋን መንገድ መማር

የይሖዋን መንገድ መማር

‘አንተን ዐውቅህ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ።’—ዘፀአት 33:13

1, 2. (ሀ) ሙሴ አንድ ግብፃዊ አንድን ዕብራዊ ሲበድል አይቶ ዕብራዊውን ለማስጣል የተነሳሳው ለምንድን ነው? (ለ) ሙሴ ለይሖዋ አገልግሎት ብቁ እንዲሆን ምን መማር አስፈልጎት ነበር?

 ሙሴ ያደገው በፈርዖን ቤት ውስጥ ሲሆን የግብፅ ገዢ መደብ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ጥበብ ተምሮም ነበር። ይሁንና ሙሴ ግብፃዊ አለመሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገነዘበ። ወላጆቹ ዕብራውያን ነበሩ። አርባ ዓመት ሲሆነው እስራኤላውያን ወንድሞቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማየት እነርሱ ወዳሉበት ሄደ። አንድ ግብፃዊ በአንድ ዕብራዊ ላይ ግፍ ሲፈጽም አይቶ ዝም ብሎ ማለፍ ስላልቻለ ግብፃዊውን መትቶ ገደለው። ሙሴ ከይሖዋ ሕዝብ ጎን መሆን የመረጠ ከመሆኑም ሌላ ወንድሞቹን ነጻ ለማውጣት አምላክ እየተጠቀመበት እንዳለ ተሰምቶት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 7:21-25፤ ዕብራውያን 11:24, 25) ያደረገው ነገር ይፋ ሲወጣ የግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ ሙሴን እንደ ዓመፀኛ ቆጠረው። እርሱም ሕይወቱን ለማዳን አካባቢውን ጥሎ ለመሸሽ ተገደደ። (ዘፀአት 2:11-15) ሙሴ አምላክ መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀምበት የይሖዋን መንገድ ከበፊቱ በበለጠ ማወቅ ያስፈልገው ነበር። ታዲያ ሙሴ ለመማር ፈቃደኛ ይሆን?—መዝሙር 25:9

2 በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ሙሴ በስደት እረኛ ሆኖ ኖረ። ዕብራውያን ወንድሞቹ በአድናቆት ስላልተቀበሉት በብስጭት ከመዋጥ ይልቅ አምላክ የፈቀደውን በጸጋ ተቀብሏል። ሙሴ ምንም ዓይነት እውቅና ሳያገኝ ብዙ ዓመታት ቢያልፉም ይሖዋ እንዲቀርጸው ፈቃደኛ ሆኗል። በራሱ ሐሳብ ሳይሆን በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር” ሲል ከጊዜ በኋላ ጽፏል። (ዘኁልቁ 12:3) ይሖዋ ሙሴን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። እኛም ትሕትናን የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋ ይባርከናል።—ሶፎንያስ 2:3

ሙሴ ተልእኮ ተሰጠው

3, 4. (ሀ) ይሖዋ ለሙሴ የሰጠው ተልእኮ ምንድን ነው? (ለ) ሙሴ ምን ዓይነት እርዳታ አግኝቷል?

3 የይሖዋ ወኪል የሆነ መልአክ አንድ ቀን በሲና ባሕረ ገብ መሬት፣ በኮሬብ ተራራ አቅራቢያ ሙሴን አናገረው። ለሙሴ የመጣለት መልእክት ይህ ነበር:- “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ። ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው . . . ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።” (ዘፀአት 3:2, 7, 8) ከዚህ ጋር በተያያዘ አምላክ ለሙሴ የሚሰጠው ሥራ አለ፤ ሆኖም ሥራው መሠራት ያለበት በይሖዋ መንገድ ነው።

4 በመቀጠል የይሖዋ መልአክ “በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ” አለው። ሙሴ ለሥራው ብቁ እንዳልሆነ ስለተሰማው ተልእኮውን ለመቀበል አቅማማ፤ ደግሞም በራሱ ችሎታ ሊፈጽመው የሚችለው ሥራ አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” የሚል ዋስትና ሰጠው። (ዘፀአት 3:10-12) ይሖዋ፣ ሙሴ በእርግጥ በእርሱ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጡ ተአምራዊ ምልክቶች እንዲያሳይ ኃይል ሰጠው። የሙሴ ወንድም አሮን ቃል አቀባዩ ሆኖ አብሮት እንዲሄድ ተደረገ። እንዲሁም ምን መናገርና ማድረግ እንዳለባቸው ይሖዋ ሊያስተምራቸው ነው። (ዘፀአት 4:1-17) ሙሴ የተሰጠውን ተልእኮ በታማኝነት ይወጣ ይሆን?

5. የእስራኤላውያን ዝንባሌ ለሙሴ አስቸጋሪ የሆነበት ለምን ነበር?

5 የእስራኤል ሽማግሌዎች መጀመሪያ ላይ ሙሴና አሮንን አምነው ተቀበሏቸው። (ዘፀአት 4:29-31) ብዙም ሳይቆይ ግን “እስራኤላውያን ኀላፊዎች” ፈርዖንና ሹማምንቱ “እንዲጠየፉን አደረጋችሁ” በማለት ሙሴንና ወንድሙን ነቀፏቸው። (ዘፀአት 5:19-21፤ 6:9) እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው በሚወጡበት ጊዜ የግብፅ ሠረገሎች እያሳደዷቸው እንዳሉ ሲያዩ ተደናገጡ። ከፊታቸው ቀይ ባሕር ከኋላቸው ደግሞ የጦር ሠረገሎች በመኖራቸው አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ስለተሰማቸው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? እስራኤላውያን ባሕሩን የሚሻገሩበት ጀልባ ባይኖራቸውም እንኳ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሙሴ ጓዛቸውን ጠቅልለው ለጉዞ እንዲዘጋጁ ነገራቸው። ከዚያም አምላክ ቀይ ባሕርን ወደኋላ እንዲሸሽ አደረገው፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ተሻገሩ።—ዘፀአት 14:1-22

ከእነርሱ ነጻ መውጣት የበለጠ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ

6. ይሖዋ ለሙሴ ተልእኮ ሲሰጠው አበክሮ የገለጸው ነገር ምንድን ነው?

6 ይሖዋ ለሙሴ ተልእኮ ሲሰጠው የመለኮታዊውን ስም አስፈላጊነት አበክሮ ገልጾለታል። ለዚህ ስምና ስሙ ለሚወክለው አካል አክብሮት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነበር። ሙሴ ይሖዋን ስለ ስሙ ሲጠይቀው “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ” በማለት መለሰለት። ከዚህ በተጨማሪ ሙሴ ለእስራኤላውያን ይህን መልእክት እንዲያደርስ ተነገረው:- “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ወደ እናንተ ልኮኛል።” በመቀጠልም ይሖዋ “ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው” አለ። (ዘፀአት 3:13-15) ዛሬም ቢሆን በምድር ዙሪያ የሚኖሩ አገልጋዮቹ አምላክን የሚያውቁት ይሖዋ በሚለው ስሙ ነው።—ኢሳይያስ 12:4, 5፤ 43:10-12

7. ፈርዖን ትዕቢተኛ ቢሆንም አምላክ ሙሴን ምን እንዲያደርግ አሳስቦታል?

7 ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት ቀርበው ከይሖዋ የመጣውን መልእክት ነገሩት። ይሁንና ፈርዖን በትዕቢት እንዲህ አለ:- “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር ማነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም።” (ዘፀአት 5:1, 2) ፈርዖን ልበ ደንዳናና አታላይ መሆኑን በግልጽ ቢያሳይም ይሖዋ መልእክት እንዲያደርስለት ሙሴን በተደጋጋሚ ላከው። (ዘፀአት 7:14-16, 20-23፤ 8:1, 2, 20) ፈርዖን በጉዳዩ በጣም መናደዱን ሙሴ ተረድቷል። ታዲያ በድጋሚ እርሱ ዘንድ መሄዱ የሚያስገኘው ጥቅም አለ? እስራኤላውያን ነጻ ለመውጣት በጣም ጓጉተዋል፤ ፈርዖን ደግሞ አልለቅም በሚለው አቋሙ ጸንቷል። አንተ ሙሴን ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

8. ይሖዋ ከፈርዖን ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ጉዳይ የወሰደው እርምጃ ምን ጥቅም አስገኝቷል? እነዚህ ነገሮች በእኛ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድሩ ይገባል?

8 ሙሴ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” በማለት አሁንም ለፈርዖን ነገረው። በተጨማሪም አምላክ እንዲህ አለው:- “አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር። ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ።” (ዘፀአት 9:13-16) ይሖዋ ልበ ደንዳና በሆነው በፈርዖን ላይ በሚወስደው እርምጃ አማካኝነት እርሱን ለሚዳፈሩት በሙሉ ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸው ኃይሉን የማሳየት ዓላማ ነበረው። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከጊዜ በኋላ “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ለጠራው ለሰይጣን ዲያብሎስም ማስጠንቀቂያ ይሆናል። (ዮሐንስ 14:30፤ ሮሜ 9:17-24) አስቀድሞ እንደተነገረው የይሖዋ ስም በመላው ምድር ላይ ታወጀ። ትዕግሥት ማሳየቱ እስራኤላውያንና ይሖዋን በማምለክ የተባበሯቸው እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ እንዲተርፉ አስችሏል። (ዘፀአት 9:20, 21፤ 12:37, 38) ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ስም መታወጁ እውነተኛውን አምልኮ የተቀበሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ጠቅሟል።

አስቸጋሪ የሆነን ሕዝብ መምራት

9. እስራኤላውያን ለይሖዋ አክብሮት ሳያሳዩ የቀሩት እንዴት ነው?

9 ዕብራውያኑ መለኮታዊውን ስም ያውቁ ነበር። ሙሴ ዕብራውያኑን ሲያነጋግር በዚያ ስም ይጠቀም የነበረ ቢሆንም እነርሱ ግን ለስሙ ባለቤት ተገቢውን አክብሮት ሳያሳዩ የቀሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ በተአምር ካወጣቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚጠጣ ውኃ ወዲያው ባለማግኘታቸው የተከሰተው ነገር ምን ነበር? በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ቀጥሎም ስለ ምግብ አማርረው ተናገሩ። ሙሴ የሚያጉረመርሙት በእርሱና በአሮን ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ እንደሆነ በመንገር አስጠነቀቃቸው። (ዘፀአት 15:22-24፤ 16:2-12) ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤላውያን ሕጉን የሰጣቸው ሲሆን በወቅቱም ተአምራዊ ምልክቶችን አሳይቷቸዋል። እስራኤላውያን ግን መመሪያውን በመጣስ የሚያመልኩት የወርቅ ጥጃ ሠርተው “ለእግዚአብሔር በዓል” እንደሆነ ተናገሩ።—ዘፀአት 32:1-9

10. በዘፀአት 33:13 ላይ ለሚገኘው ሙሴ ላቀረበው ልመና በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ትኩረት ሊሰጡ የሚገባው ለምንድን ነው?

10 ይሖዋ ራሱ አንገተ ደንዳና ብሎ የጠራውን ሕዝብ ሙሴ መምራት የሚችለው እንዴት ነው? ሙሴ “በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ” ሲል ይሖዋን ተማጽኗል። (ዘፀአት 33:13) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚመሯቸው በዚህ ዘመን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ከእስራኤላውያን በተለየ እጅግ ትሑት ናቸው። ይሁንና እነዚህ የበላይ ተመልካቾችም “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ” የሚል ተመሳሳይ ጸሎት ያቀርባሉ። (መዝሙር 25:4) የበላይ ተመልካቾች የይሖዋን መንገድ ማወቃቸው ለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ከአምላክ ቃል ጋር በሚስማማና ከባሕርዩ ጋር በሚጣጣም ሁኔታ መፍትሔ እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል።

ይሖዋ ከሕዝቡ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

11. ይሖዋ ለሙሴ የሰጠው መመሪያዎች ምንድን ናቸው? እኛስ ለእነዚህ መመሪያዎች ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ ከሕዝቡ የሚጠብቀው ነገር ምን እንደሆነ ሲና ተራራ አጠገብ ሳሉ በቃል ተነግሯቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ሙሴ አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ተሰጡት። ከተራራው ሲወርድ እስራኤላውያን ቀልጦ የተሠራውን ጥጃ ሲያመልኩ ተመልክቶ በንዴት ጽላቶቹን ወርውሮ ሰባበራቸው። ይሖዋ፣ ሙሴ ባዘጋጃቸው የድንጋይ ጽላቶች ላይ አሥርቱን ትእዛዛት እንደገና ጻፈለት። (ዘፀአት 32:19፤ 34:1) እነዚህ ትእዛዛት መጀመሪያ ከተጻፉበት ጊዜ አንስቶ አልተለወጡም። ሙሴ ትእዛዛቱን እንዲያከብር ይጠበቅበት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ አምላክ ማንነቱን ለሙሴ በሚገባ ስለገለጸለት የይሖዋ ወኪል ሆኖ ሲሠራ እንዴት መኖር እንዳለበት አሳውቆታል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። ሆኖም ይሖዋ ለሙሴ የነገረው ነገር እስካሁን ድረስ ያልተለወጡና ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሁሉ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ቁልፍ የሆኑ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። (ሮሜ 6:14፤ 13:8-10) እስቲ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።

12. ይሖዋ እርሱ ብቻ መመለክ እንዳለበት ማዘዙ እስራኤላውያን ምን እንዲያደርጉ ይጠይቅባቸው ነበር?

12 ይሖዋን ብቻ አምልኩ። ይሖዋ እርሱ ብቻ መመለክ እንዳለበት ሲገልጽ የእስራኤል ብሔር በቀጥታ ሰምቷል። (ዘፀአት 20:2-5) እስራኤላውያን ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎች አይተዋል። (ዘዳግም 4:33-35) ሌሎች ብሔራት ምንም ዓይነት ልማድ ቢኖራቸው ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ወይም የመናፍስትነት ሥራ ሕዝቦቹ እንዲያከናውኑ እንደማይፈቅድ በግልጽ ተናግሯል። ለእርሱ የሚያቀርቡት አምልኮ ለታይታ የሚደረግ መሆን የለበትም። ሁሉም ይሖዋን በሙሉ ልባቸው፣ በሙሉ ነፍሳቸውና በሙሉ ኃይላቸው መውደድ ነበረባቸው። (ዘዳግም 6:5, 6) ይህ ንግግራቸውንም ሆነ ባሕርያቸውን ጨምሮ ማንኛውንም የሕይወታቸውን ገጽታ ይመለከታል። (ዘሌዋውያን 20:27፤ 24:15, 16፤ 26:1) ኢየሱስ ክርስቶስም ይሖዋ እርሱ ብቻ መመለክ እንደሚፈልግ በግልጽ ተናግሯል።—ማርቆስ 12:28-30፤ ሉቃስ 4:8

13. እስራኤላውያን አምላክን በጥብቅ መታዘዝ የነበረባቸው ለምንድን ነው? እኛስ እርሱን እንድንታዘዘው የሚያነሳሳን ምን መሆን አለበት? (መክብብ 12:13)

13 የይሖዋን ትእዛዛት በጥብቅ አክብሩ። እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን በገቡበት ወቅት እርሱን በጥብቅ ለመታዘዝ የገቡትን ቃል የሚያስታውሳቸው አስፈልጓቸው ነበር። በግለሰብ ደረጃ ሰፊ ነጻነት የነበራቸው ቢሆንም ይሖዋ ትእዛዝ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ግን ትእዛዙን በጥብቅ ማክበር ነበረባቸው። እንዲህ ማድረጋቸው ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ የሚያወጣቸው መመሪያዎች በሙሉ ለደኅንነታቸው ስለሆኑ እነርሱንም ሆነ ዘሮቻቸውን ይጠቅማቸዋል።—ዘፀአት 19:5-8፤ ዘዳግም 5:27-33፤ 11:22, 23

14. አምላክ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ የመስጠትን አስፈላጊነት ለእስራኤላውያን አበክሮ የገለጸላቸው እንዴት ነበር?

14 ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ስጡ። እስራኤላውያን ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በመሯሯጥ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ትኩረት መስጠት እንዲሳናቸው መፍቀድ አልነበረባቸውም። እስራኤላውያን ሕይወታቸው ተራ ጉዳዮችን በማሳደድ ላይ ብቻ ማተኮር አልነበረበትም። ይሖዋ በሳምንቱ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ የተቀደሰ እንዲሆንና ለእውነተኛው አምላክ ከሚቀርበው አምልኮ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ እንዲውል መድቦ ነበር። (ዘፀአት 35:1-3፤ ዘኍልቊ 15:32-36) በየዓመቱ ለሚካሄዱት ቅዱስ ስብሰባዎች ተጨማሪ ጊዜ እንዲመድቡ ተነግሯቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 23:4-44) እነዚህ ስብሰባዎች የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ለማውሳት፣ መንገዱን በተመለከተ ማሳሰቢያ ለማግኘትና ለጥሩነቱ በሙሉ ምስጋና ለማቅረብ አጋጣሚ ይሰጣሉ። እስራኤላውያን ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን ሲያሳዩ ለእርሱ ያላቸው ፍርሃትና ፍቅር የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ በመንገዱ ለመሄድ እርዳታ ያገኛሉ። (ዘዳግም 10:12, 13) በእነዚህ መመሪያዎች ውስጥ የታቀፉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በዛሬው ጊዜ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች ጠቃሚ ናቸው።—ዕብራውያን 10:24, 25

ለይሖዋ ባሕርያት አድናቆት ማዳበር

15. (ሀ) ሙሴ ለይሖዋ ባሕርያት አድናቆት ማዳበሩ የሚጠቅመው ለምንድን ነው? (ለ) በእያንዳንዱ የይሖዋ ባሕርይ ላይ በጥልቅ እንድናስብ የሚረዱን ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

15 ሙሴ የይሖዋን ባሕርያት ማድነቁ ከሕዝቡ ጋር ላለው ግንኙነትም ይጠቅመዋል። ዘፀአት 34:5-7 አምላክ በሙሴ ፊት እንዳለፈና እንዲህ ብሎ እንዳወጀ ይገልጻል:- “እግዚአብሔር ሩኅሩኅ ቸር አምላክ [“መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣” የ1954 ትርጉም] እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።” ጊዜ ወስደህ በእነዚህ ቃላት ላይ አሰላስል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘እያንዳንዱ ባሕርይ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋ ባሕርያቱን ያንጸባረቀው እንዴት ነው? ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? የእያንዳንዳችንን አድራጎት እንዴት ሊነካው ይገባል?’ እስቲ ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት።

16. አምላክ ለሚያሳየው የምሕረት ባሕርይ አድናቆታችንን ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

16 ይሖዋ ‘መሐሪና ሞገስ ያለው አምላክ’ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው የማመሳከሪያ ጽሑፍ ካለህ “መሐሪ” በሚለው ሥር የቀረበውን ሐሳብ ለምን አታነብም? ወይም ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን ወይም በሲዲ የሚገኘውን ዎችታወር ላይብረሪ በመጠቀም ምርምር አድርግ። a መሐሪ የሚል ቃል የሠፈረባቸውን ጥቅሶች ለማግኘት በጥቅሶች ማውጫ (ኮንኮርዳንስ) ተጠቀም። እንዲህ በማድረግ የይሖዋ ምሕረት አንዳንድ ጊዜ ቅጣት ከማቅለል በተጨማሪ ርኅራኄ ማሳየትንም እንደሚያካትት ትገነዘባለህ። ይህ ባሕርይ አምላክ ሕዝቡን ከችግር ለማዳን እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። አምላክ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸው መሆኑ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። (ዘዳግም 1:30-33፤ 8:4) ይሖዋ ስህተት ሲፈጽሙ ምሕረት በማሳየት ይቅር ብሏቸዋል። ለጥንት ሕዝቦቹ ምሕረት አሳይቷቸዋል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹ አንዳቸው ለሌላው ምሕረት ማሳየታቸው ምንኛ ተገቢ ነው!—ማቴዎስ 9:13፤ 18:21-35

17. ይሖዋ ሞገስ የሚያሳይ መሆኑን መረዳታችን ለእውነተኛው አምልኮ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?

17 የይሖዋ ምሕረት ለሌሎች ሞገስ ከማሳየቱ ጋር የተሳሰረ ነው። ‘ሞገስ’ እና ‘ሞገስ ያለው’ የሚሉትን ቃላት እንዴት ትገልጻቸዋለህ? የቃሉን ፍቺ ይሖዋ ሞገስ የሚያሳይ እንደሆነ ከሚናገሩት ጥቅሶች ጋር አስተያይ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚያሳየው ሞገስ በሕዝቡ መካከል ላሉት ችግረኞች የሚያሳየውን ከፍቅር የመነጨ አሳቢነት እንደሚያካትት ይጠቁማል። (ዘፀአት 22:26, 27) በየትኛውም አገር ቢሆን መጻተኞችም ሆኑ ሌሎች በደል ይፈጸምባቸው ይሆናል። ይሖዋ እንደዚህ ባሉ ሰዎች ላይ አድልዎ እንዳይፈጽሙና ደግነት እንዲያሳዩ ለሕዝቡ ትምህርት ሲሰጥ እነርሱም በግብፅ መጻተኞች እንደነበሩ አስታውሷቸዋል። (ዘዳግም 24:17-22) በዛሬው ጊዜ ያለን የአምላክ ሕዝቦችስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለሌሎች ሞገስ ማሳየታችን ይኸውም ሌሎችን በአክብሮት መያዛችን በመካከላችን አንድነት እንዲኖርና ሌሎች ወደ ይሖዋ አምልኮ እንዲሳቡ ያስችላል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ራእይ 7:9, 10

18. ይሖዋ እስራኤላውያን የሌሎች ብሔራትን አካሄድ እንዳይከተሉ ከሰጠው መመሪያ ምን ትምህርት እናገኛለን?

18 ይሁንና እስራኤላውያን ለሌሎች ሕዝቦች የሚያሳዩት አሳቢነት ለይሖዋና ለሥነ ምግባር ደንቦቹ ካላቸው ፍቅር መብለጥ የለበትም። በመሆኑም እስራኤላውያን በአካባቢያቸው ያሉትን ብሔራት አካሄድ እንዳይከተሉ፣ ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውንና የረከሰ አኗኗራቸውን እንዳይኮርጁ ትምህርት ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፀአት 34:11-16፤ ዘዳግም 7:1-4) ይህ መመሪያ በዛሬው ጊዜ እኛንም ይመለከታል። አምላካችን ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እኛም ቅዱስ ሕዝብ እንድንሆን ይጠበቅብናል።—1 ጴጥሮስ 1:15, 16

19. ይሖዋ ለኃጢአት ያለውን አመለካከት መረዳታቸው ለሕዝቦቹ ጥበቃ የሚሆንላቸው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ ኃጢአትን የሚፈቅድ ባይሆንም እንኳ ለቁጣ የዘገየ መሆኑን ለሙሴ በመግለጽ መንገዱን መረዳት እንዲችል አድርጓል። ሰዎች ብቃቶቹን እንዲማሩና ከዚያም ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ጊዜ ይሰጣቸዋል። አንድ ሰው ንስሐ ከገባ ይሖዋ ኃጢአቱን ይቅር የሚልለት ቢሆንም ከባድ ኃጢአት መፈጸም ከሚያስከትለው ቅጣት ግን እንዲያመልጥ አያደርገውም። እስራኤላውያን የሚያደርጉት ነገር በመጪዎቹ ትውልዶች ላይ በጎ ወይም ጎጂ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ሙሴን አስጠንቅቆት ነበር። የአምላክ ሕዝቦች ለይሖዋ መንገድ አድናቆት ማሳደራቸው በራሳቸው ጥፋት ለደረሰባቸው ችግር አምላክን ከመውቀስ ወይም ቸልተኛ ነው ብለው ከመደምደም እንዲቆጠቡ ያስችላቸዋል።

20. ከእምነት ባልንጀሮቻችንና በአገልግሎት ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? (መዝሙር 86:11)

20 ስለ ይሖዋና ስለ መንገዱ ያላችሁን እውቀት ማሳደግ ከፈለጋችሁ ምርምር ማድረጋችሁንና መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ጊዜ ማሰላሰላችሁን ቀጥሉ። የተለያዩ አስደናቂ ገጽታዎች ያሉትን የይሖዋን ባሕርይ በጥንቃቄ መርምሩ። አምላክን እንዴት መምሰል እንደምትችሉና ሕይወታችሁን ከዓላማው ጋር እንዴት በተሟላ መልኩ ማስማማት እንደምትችሉ በጸሎት አስቡበት። እንዲህ ማድረጋችሁ አደጋዎችን እንድትርቁ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራችሁ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ድንቅ የሆነውን አምላካችንን እንዲያውቁና እንዲያፈቅሩ ለመርዳት ያስችላችኋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሁሉም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ሙሴ ትሑት መሆኑ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? ለእኛስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• የይሖዋን ቃል ለፈርዖን በተደጋጋሚ መንገሩ ምን ጥቅም ነበረው?

• ሙሴ የተማራቸውና ለእኛም አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ላቅ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?

• ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያለንን ግንዛቤ ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴ ከይሖዋ የተቀበለውን መልእክት ለፈርዖን በታማኝነት አድርሷል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የአቋም ደረጃዎቹን ለሙሴ ነግሮታል

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ባሕርያት ላይ አሰላስሉ