በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መዳን የሚገኘው በሥራ ብቻ ሳይሆን በጸጋው ነው

መዳን የሚገኘው በሥራ ብቻ ሳይሆን በጸጋው ነው

መዳን የሚገኘው በሥራ ብቻ ሳይሆን በጸጋው ነው

“በእምነት . . . ድናችኋልና፤ . . . ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም።” —ኤፌሶን 2:8, 9

1. ስኬትን በተመለከተ ክርስቲያኖች በጥቅሉ ከሌሎች ሰዎች የሚለዩት እንዴት ነው? ለምንስ?

 በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ባገኙት ስኬት በእጅጉ ከመኩራራታቸውም በላይ ስለ ራሳቸው በጉራ ለመናገር ይቸኩላሉ። ክርስቲያኖች ግን እንዲህ መሆን አይገባቸውም። በእውነተኛው አምልኮ ረገድ ቢሆንም እንኳን ያገኟቸውን ስኬቶች እያነሱ አጋንነው ከመናገር ይቆጠባሉ። የይሖዋ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ባገኙት ስኬት ቢደሰቱም ለተገኘው ውጤት በግለሰብ ደረጃ ያከናወኑትን ነገር በማጋነን አያወሩም። በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር አንድ ሰው ያከናወነው ሥራ ሳይሆን ያንን ሥራ ለመሥራት ያነሳሳው ውስጣዊ ግፊት መሆኑን ይገነዘባሉ። ማንም ሰው ቢሆን ወደፊት የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው በግሉ ባገኛቸው ስኬቶች ሳይሆን በእምነትና በአምላክ ጸጋ ወይም ይገባናል በማንለው ደግነቱ ነው።—ሉቃስ 17:10፤ ዮሐንስ 3:16

2, 3. ጳውሎስ የተመካው በምን ነበር? ለምንስ?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ሐቅ በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ከነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ለመገላገል ሦስት ጊዜ ከጸለየ በኋላ ይሖዋ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” የሚል መልስ ሰጠው። ጳውሎስ የይሖዋን ውሳኔ በትሕትና በመቀበል “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ” ብሏል። ይህንን የመሰለውን የጳውሎስን ትሕትና ልንኮርጅ ይገባናል።—2 ቆሮንቶስ 12:7-9

3 ጳውሎስ የሚደነቁ ክርስቲያናዊ ተግባሮችን ያከናወነ ቢሆንም ስኬት ያገኘው ባሉት ልዩ ችሎታዎች እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። “ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ” በማለት በትሕትና ተናግሯል። (ኤፌሶን 3:8) ይህ አነጋገሩ ጉረኛና ተመጻዳቂ እንዳልነበረ ያሳየናል። “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (ያዕቆብ 4:6፤ 1 ጴጥሮስ 5:5) በትሕትና ራሳችንን ከወንድሞቻችን ሁሉ እንደምናንስ አድርገን በመቁጠር የጳውሎስን ምሳሌ እንከተላለን?

‘ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ ቊጠሩ’

4. አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን መቁጠር የሚከብደን ለምን ሊሆን ይችላል?

4 ጳውሎስ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቊጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በተለይ ሥልጣን ካለን ይህን ማድረጉ ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ምናልባት ትሑት ለመሆን የተቸገርነው በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው የውድድር መንፈስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጽዕኖ አሳድሮብን ይሆናል። ወይም ደግሞ በልጅነታችን በቤት ውስጥ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አሊያም በትምህርት ቤት ከሚገኙት የክፍል ጓደኞቻችን ጋር እንድንፎካከር ተምረን ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የትምህርት ቤታችን ኮከብ ተማሪ ወይም ታዋቂ ስፖርተኛ በመሆን ስማችንን እንድናስጠራ ያለማቋረጥ ግፊት ተደርጎብን ይሆናል። በእርግጥ አግባብነት ያለውን ማንኛውንም ሥራ ለማከናወን አቅማችን የፈቀደውን ያህል ጥረት ማድረጋችን የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች እንዲህ የሚያደርጉት ከሥራው ሙሉ ጥቅም ለማግኘትና ምናልባትም ሌሎችን ለመጥቀም ብለው እንጂ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ለማግኘት አይደለም። ሁልጊዜ ቀዳሚውን ደረጃ አግኝቶ ለመወደስ መፈለግ አደገኛ ሊሆን ይችላል። እንዴት?

5. የፉክክር መንፈስ ቁጥጥር ካልተደረገበት ወዴት ሊያመራ ይችላል?

5 አንድ ሰው ያለበትን የፉክክር ወይም የኩራት መንፈስ ካልተቆጣጠረ በስተቀር ሌሎችን ወደ መናቅና ወደ እብሪተኝነት ሊያመራ ይችላል። ምናልባትም ሌሎች ባላቸው ችሎታና ባገኙት መብት መቅናት ይጀምር ይሆናል። ምሳሌ 28:22 (የ1954 ትርጉም) “ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኩላል ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም” ይላል። ሌላው ቀርቶ የማይገባውን ቦታ ለማግኘት አጉል ይዳፈር ይሆናል። እያደረገ ያለውን ነገር ትክክል ለማስመሰል ማጉረምረምና ሌሎችን መንቀፍ ይጀምራል፤ እነዚህ ደግሞ ክርስቲያኖች ሊያስወግዷቸው የሚገቡ ባሕርያት ናቸው። (ያዕቆብ 3:14-16) ያም ሆነ ይህ፣ እንዲህ ያለው ሰው ‘እኔ ልቅደም’ የሚለውን አደገኛ ዝንባሌ ወደ ማፍራቱ እያመራ ነው።

6. መጽሐፍ ቅዱስ የፉክክር መንፈስን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

6 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችን እየተጎነታተልንና [“እየተፎካከርንና፣” NW] እየተቀናናን በከንቱ ውዳሴ አንመካ” በማለት ክርስቲያኖችን ያስጠነቅቃል። (ገላትያ 5:26) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ያለው ዝንባሌ ስለተጠናወተው አንድ ክርስቲያን ባልንጀራው ሲናገር “ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጽፌ ነበር፤ ነገር ግን መሪ መሆን የሚወደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ” ብሏል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ መግባቱ እንዴት የሚያሳዝን ነው!—3 ዮሐንስ 9, 10

7. የፉክክር መንፈስ በተጠናወተው የዘመናችን የሥራ ዓለም አንድ ክርስቲያን ምንን ማስወገድ ይኖርበታል?

7 አንድ ክርስቲያን ሙሉ ለሙሉ የፉክክርን መንፈስ ያስወግዳል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ እንዳልሆነ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል ሰብዓዊ ሥራው፣ ተመሳሳይ ምርት ከሚያመርቱ አሊያም ደግሞ የእርሱ ዓይነት አገልግሎት ከሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የገበያ ውድድር እንዲያደርግ ያስገድደው ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ባሉ ጊዜያትም ጭምር ሥራውን የሚያከናውነው በአክብሮት፣ በፍቅርና በአሳቢነት ሊሆን ይገባዋል። ሕገ ወጥና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ተግባሮችን ከመፈጸም ይቆጠባል፤ እንዲሁም በይበልጥ የሚታወቀው በተፎካካሪነቱ እንዳይሆን ይጠነቀቃል። በሕይወት ውስጥ ትልቁ ጉዳይ በማንኛውም እንቅስቃሴ አንደኛ ሆኖ መገኘት እንደሆነ አድርጎ አያስብም። አንድ ክርስቲያን ለሰብዓዊ ሥራው እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ መያዝ የሚያስፈልገው ከሆነ በአምልኮው ውስጥ ይህንን መንፈስ በይበልጥ ማሳየት አይገባውም?

‘ከሌላ ሰው ጋር ራስን አለማወዳደር’

8, 9. (ሀ) የጉባኤ ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩበት ምክንያት የላቸውም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አንደኛ ጴጥሮስ 4:10 በሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚሠራው ለምንድን ነው?

8 “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል” የሚሉት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቃላት ክርስቲያኖች በአምልኳቸው ረገድ ሊያንጸባርቁ የሚገባቸውን አስተሳሰብ ይገልጻሉ። (ገላትያ 6:4) የጉባኤ ሽማግሌዎች እርስ በርስ በሚፎካከሩበት መድረክ ላይ እንዳልሆኑ በመገንዘብ እንደ አንድ አካል ሆነው በኅብረት ይሠራሉ። ለመላው ጉባኤ ደህንነት እያንዳንዱ ሽማግሌ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ይደሰታሉ። በዚህ መልኩ የሚከፋፍል የፉክክር መንፈስን አስወግዶ አንድነትን በማስፈን በኩል ለቀሪው የጉባኤ አባላት ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ።

9 አንዳንድ ሽማግሌዎች በዕድሜያቸው፣ ባካበቱት ተሞክሮ ወይም በተፈጥሯቸው ከሌሎች የተሻለ ችሎታ አሊያም ደግሞ ላቅ ያለ ማስተዋል ይኖራቸው ይሆናል። በመሆኑም ሽማግሌዎች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶች አሏቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው ከመፎካከር ይልቅ “እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል” የሚለውን ምክር ያስታውሳሉ። (1 ጴጥሮስ 4:10) ይህ ጥቅስ በሁሉም ክርስቲያኖች ላይ እንደሚሠራ የተረጋገጠ ነው፤ ምክንያቱም በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ትክክለኛ እውቀት የተሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በክርስቲያናዊ አገልግሎት የመካፈል መብት አላቸው።

10. ቅዱስ አገልግሎታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው በምን መልኩ ከቀረበ ብቻ ነው?

10 ይሖዋ በቅዱስ አገልግሎታችን የሚደሰተው አገልግሎቱን የምናቀርበው ከሌሎች ከፍ ብለን ለመታየት በመፈለግ ሳይሆን ለእርሱ ካለን ጥልቅ ፍቅር ተነሳስተን ከሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ስለምናደርገው እንቅስቃሴ ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን በጣም አስፈላጊ ነው። ማንም ሰው ስለ ሌሎች ውስጣዊ ግፊት ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ባይችልም “ልብን የሚመረምር” ይሖዋ ግን ይህን ማድረግ ይችላል። (ምሳሌ 24:12፤ 1 ሳሙኤል 16:7) ስለዚህ ‘በይሖዋ አገልግሎት እንድካፈል የሚያነሳሳኝ ምንድን ነው?’ እያልን በየጊዜው ራሳችንን ብንጠይቅ መልካም ነው።—መዝሙር 24:3, 4፤ ማቴዎስ 5:8

ለእምነት ሥራዎች ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት

11. የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን በተመለከተ ምን ምክንያታዊ ጥያቄዎችን እንመረምራለን?

11 በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ወሳኝ የሆነው ነገር ለሥራ የሚያንቀሳቅሰን ውስጣዊ ግፊት ከሆነ ስለ እምነት ሥራዎች መጨነቅ ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው? አገልግሎታችንን የምናከናውነው ከትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስተን እስከሆነ ድረስ ምን እንዳከናወንን ወይም ምን ያህል እንዳገለገልን መመዝገቡ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ይበልጥ ትኩረት መስጠት የምንፈልገው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን በተመለከተ ለሚቀርቡት አኃዛዊ መረጃዎች ወይም ጥሩ ሪፖርት ለማቅረቡ ጉዳይ ሳይሆን በይሖዋ አገልግሎት ለምናከናውነው ሥራ ነው።

12, 13. (ሀ) የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን መመዝገብ አስፈላጊ የሆነባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? (ለ) ዓለም አቀፍ የስብከት እንቅስቃሴያችንን በተመለከተ የሚቀርቡትን ሪፖርቶች ስናይ እንድንደሰት የሚያደርጉን ነገሮች ምንድን ናቸው?

12 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ ምን እንደሚል ልብ በል:- “የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በስብከቱ ሥራ የሚታየውን እድገት ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። (ማር. 6:30) በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሲፈስስ በቦታው 120 ሰዎች እንደነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይገልጽልናል። ብዙም ሳይቆይ የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር ወደ 3,000 በኋላም ወደ 5,000 ከፍ ብሏል። . . . (ሥራ 1:15፤ 2:5–11, 41, 47፤ 4:4፤ 6:7) ስለ እነዚህ ጭማሪዎች የሚገልጸው ዜና ደቀ መዛሙርቱን በእጅጉ አበረታቷቸው መሆን አለበት!” በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ፍጻሜ መሠረት እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮች በተመለከተ ትክክለኛ ዘገባዎች ለማስፈር ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 24:14) እንዲህ ያሉት ሪፖርቶች በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ያለውን ነገር ትክክለኛ ገጽታ ያሳያሉ። በተጨማሪም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ክልሎች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት ይበልጥ የሚጠቅሙት ጽሑፎች የትኞቹ እንደሆኑና ምን ያህል ብዛት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማወቅ ይረዳሉ።

13 ስለዚህ ስለ ስብከት እንቅስቃሴያችን ሪፖርት ማቅረባችን የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ተልእኳችንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም ያስችለናል። ከዚህም በላይ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ወንድሞቻችን እያከናወኑ ስላሉት ሥራ ስንሰማ አንበረታታም? በዓለም ዙሪያ ስላለው እድገትና መስፋፋት የምንሰማው ዜና ያስደስተናል፣ ለበለጠ ሥራ ያነሳሳናል እንዲሁም ይሖዋ እየባረከን እንዳለ እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል። በዓለም ዙሪያ ስለሚደረገው እንቅስቃሴ በሚጠናቀረው ሪፖርት ውስጥ የእኛም ሪፖርት መጨመሩን ማወቁ እንዴት ደስ ያሰኛል! ከዓለም አቀፉ ሪፖርት ጠቅላላ ድምር አንጻር ሲታይ በግል የምናከናውነው በጣም ትንሽ ነው፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ያደረግነውን ነገር ይመለከታል። (ማርቆስ 12:42, 43) የአንተ ሪፖርት ካልተጨመረ ዓለም አቀፉ ሪፖርት የተሟላ እንደማይሆን አስታውስ።

14. ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ከስብከቱና ከማስተማሩ ሥራ ሌላ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

14 እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ራሱን መወሰኑ ያስከተለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያከናውናቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ሪፖርት እንደማያደርግ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ሪፖርቱ ዘወትር የሚያደርገውን የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘቱንና ያደረገውን ተሳትፎ፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉበትን ኃላፊነቶች፣ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ የሚያደርገውን እርዳታ፣ ዓለም አቀፉን የመንግሥቱ ሥራ ለመደገፍ የሚሰጠውን የገንዘብ መዋጮና የመሳሰሉትን ነገሮች አይጨምርም። የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ማድረጋችን ቅንዓታችን እንዳይበርድና ቸልተኞች እንዳንሆን በመርዳት በኩል የሚጫወተው ሚና እንዳለ ቢታወቅም ለጉዳዩ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚገባን መሆናችንን የሚያረጋግጥልን መንፈሳዊ የፈቃድ ወረቀት ወይም ፓስፖርት አድርገን ልናየው አይገባም።

‘መልካም የሆነውን ለማድረግ መትጋት’

15. የእምነት ሥራ ብቻውን ሊያድነን ባይችልም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 የእምነት ሥራ ብቻውን ሊያድነን ባይችልም አስፈላጊ መሆኑ ግን አይካድም። ክርስቲያኖች ‘መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚተጋ የእርሱ የሆነው ሕዝብ’ ተብለው የተጠሩትና “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ” የሚል ማበረታቻ የተሰጣቸው ለዚህ ነው። (ቲቶ 2:14፤ ዕብራውያን 10:24) ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ያዕቆብ ደግሞ “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” በማለት ነገሩን ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል።—ያዕቆብ 2:26

16. ከመልካም ሥራዎች ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል?

16 መልካም ሥራ መሥራት አስፈላጊ ሊሆን ቢችልም ሥራውን ለማከናወን የሚያነሳሳን ውስጣዊ ግፊት ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በየጊዜው ውስጣዊ ግፊታችንን መመርመራችን መልካም ነው። ሆኖም ማንም ሰው የሌሎችን ውስጣዊ ግፊት በትክክል ማወቅ ስለማይችል በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሌላውን በሚያገለግል ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” የሚል ጥያቄ ካነሳልን በኋላ “እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው” በማለት ግልጽ የሆነ መልስ ይሰጠናል። (ሮሜ 14:4) የሁሉም ጌታ የሆነው ይሖዋና እርሱ ፈራጅ አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ የሚሰጡን በእምነት ሥራዎቻችን ብቻ ላይ ተመሥርተው ሳይሆን ውስጣዊ ግፊታችንን፣ የነበሩንን አጋጣሚዎችና ፍቅራችንን ተመልክተው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ የተመሠከረለት ሠራተኛ፣ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ልታቀርብ ትጋ” ሲል በተናገረው መሠረት ክርስቲያኖች እንዲሠሩት የታዘዙትን ሥራ መሥራት አለመሥራታችንን በትክክል ሊፈርዱ የሚችሉት ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 2 ጴጥሮስ 1:10፤ 3:14

17. አቅማችን የፈቀደውን ያህል ለማድረግ ስንጥር ያዕቆብ 3:17ን በአእምሯችን መያዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው። ያዕቆብ 3:17 ላይ “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ . . . ታጋሽ [“ምክንያታዊ፣” NW]” ጭምር እንደሆነች ተገልጿል። በዚህ ረገድ ይሖዋን መምሰል አስተዋይነት አልፎ ተርፎም እውነተኛ ስኬት አይደለም? ስለዚህ ከራሳችንም ሆነ ከወንድሞቻችን ምክንያታዊ ያልሆኑና ሊደረስባቸው የማይችሉ ነገሮችን መጠበቅ የለብንም።

18. የምናከናውናቸውን የእምነት ሥራዎችና የይሖዋን ጸጋ በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ከያዝን ምን እንደምናገኝ መጠበቅ እንችላለን?

18 ለምናከናውናቸው የእምነት ሥራዎችና ለይሖዋ ጸጋ ሚዛናዊ አመለካከት እስካዳበርን ድረስ፣ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች መለያ ምልክት የሆነውን ደስታችንን እንደያዝን መቀጠል እንችላለን። (ኢሳይያስ 65:13, 14) በግላችን ማድረግ የምንችለው ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋ ለጠቅላላው ሕዝቡ ከሚያፈሰው በረከት ተቋዳሽ በመሆን መደሰት እንችላለን። ይሖዋ አቅማችን የፈቀደውን ማድረግ እንድንችል እንዲረዳን ‘በጸሎት፣ በምልጃና በምስጋና’ አዘውትረን ልንጠይቀው እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ‘ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚጠብቅ’ ምንም ጥርጥር የለውም። (ፊልጵስዩስ 4:4-7) አዎን፣ መዳን የምናገኘው በሥራ ብቻ ሳይሆን በይሖዋ ጸጋ ወይም ይገባናል በማንለው ደግነቱ ጭምር መሆኑን ማወቃችን ያጽናናናል እንዲሁም ያበረታታናል!

ልታብራራ ትችላለህ?

• ክርስቲያኖች በግል ስላገኙት ስኬት በጉራ ከመናገር የሚታቀቡት ለምንድን ነው?

• ክርስቲያኖች የፉክክር መንፈስ ከማሳየት መቆጠብ የሚገባቸው ለምንድን ነው?

• ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎት ስላደረጉት እንቅስቃሴ ሪፖርት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

• ክርስቲያኖች በእምነት ባልንጀሮቻቸው ላይ መፍረድ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጸጋዬ ይበቃሃል”

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች፣ ለመላው ጉባኤ ደኅንነት እያንዳንዱ ሽማግሌ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ይደሰታሉ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእያንዳንዳችሁ ሪፖርት ካልተጨመረ ዓለም አቀፉ ሪፖርት የተሟላ አይሆንም