በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በአሁኑ ሕይወቴ’ ሙሉ በሙሉ ተደስቻለሁ!

‘በአሁኑ ሕይወቴ’ ሙሉ በሙሉ ተደስቻለሁ!

የሕይወት ታሪክ

‘በአሁኑ ሕይወቴ’ ሙሉ በሙሉ ተደስቻለሁ!

ቴድ በኪንግሃም እንደተናገረው

ለስድስት ዓመት ያህል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተካፈልኩና ትዳር ከያዝኩ ከስድስት ወራት በኋላ በፖሊዮ በሽታ ድንገት ተያዝኩ። ይህ የሆነው በ1950 ሲሆን በወቅቱ ገና የ24 ዓመት ወጣት ነበርኩ። በሆስፒታል በቆየሁባቸው ዘጠኝ ወራት ስለ ሕይወቴ በቁም ነገር አስብ ነበር። የአካል ጉዳተኛ ከሆንኩ በኋላ እኔና ባለቤቴ ጆይስ የወደፊቱን ሕይወታችንን እንዴት እንገፋው ይሆን?

ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያልነበረው አባቴ በ1938 መንግሥት የተባለው መጽሐፍ ደረሰው። a መጽሐፉን እንዲወስድ የገፋፋው የፖለቲካው አለመረጋጋትና ጦርነት ይጀምር ይሆናል የሚለው ግምት ሳይሆን አይቀርም። እኔ እስከማውቀው ድረስ አባቴ መጽሐፉን በጭራሽ ገልጦት አያውቅም፤ ሆኖም አጥባቂ ሃይማኖተኛ የነበረችው እናቴ ታነበው ነበር። ከዚያም ካነበበችው መልእክት ጋር የሚስማማ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን ለቅቃ ከመውጣቷም በላይ አባቴ ይቃወማት የነበረ ቢሆንም ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ በ1990 እስከ ሞተችበት ዕለት ድረስ ታማኝነቷን ጠብቃ ኖራለች።

እናቴ ከለንደን በስተ ደቡብ በሚገኘው ኤፕሰም ከተማ በሚደረግ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወሰደችኝ። ጉባኤው ይደረግ የነበረው ቀደም ሲል በመጋዘንነት ሲያገለግል በቆየ ቤት ውስጥ ነበር። በዚያም በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ሲመራ የነበረውን የጄ ኤፍ ራዘርፎርድን በሸክላ የተቀዳ ንግግር አዳመጥን፤ በንግግሩ ልቤ በእጅጉ ተነካ።

በለንደን ላይ የሚዘንበው ከባድ የቦምብ ውርጅብኝ አስጊ እየሆነ መጣ። ስለሆነም አባቴ በ1940 ከለንደን በስተ ምዕራብ 45 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኝ ከአደጋ ነፃ ወደሆነች ሜድንሄድ የተባለች አነስተኛ ከተማ ቤተሰቡን ይዞ ለመሄድ ወሰነ። በዚያ የሚገኘው 30 አባላትን ያቀፈ ጉባኤ ግሩም የብርታት ምንጭ ሆኖልን ስለነበር ወደዚያ መዛወራችን በእጅጉ ጠቅሞናል። በ1917 የተጠመቀ ፍሬድ ስሚዝ የተባለ ደፋር ክርስቲያን ትኩረት ሰጥቶ ውጤታማ ሰባኪ እንድሆን አሠልጥኖኛል። ስለተወልኝ ግሩም ምሳሌነትና ስላደረገልኝ ፍቅራዊ እርዳታ አሁንም ቢሆን ትልቅ ባለውለታዬ ነው።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ

በ1941 መጋቢት ወር አንድ ቀዝቃዛ ቀን በ15 ዓመቴ በቴምዝ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅሁ። በዚህ ጊዜ፣ ታላቅ ወንድሜ ጂም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ በመሆን ያገለግል ነበር። ከባለቤቱ ከማጅ ጋር በመላው እንግሊዝ እየተዘዋወሩ አብዛኛውን ዕድሜያቸውን በወረዳና በአውራጃ ሥራ ላይ ካሳለፉ በኋላ አሁን መኖሪያቸውን በበርሚንግሃም አድርገዋል። ታናሽ እህቴ ሮቤና እና ባለቤቷ ፍራንክ ደግሞ አሁን ድረስ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በወቅቱ በአንድ የልብስ ፋብሪካ ውስጥ በሒሳብ ሠራተኛነት እሠራ ነበር። አንድ ቀን የፋብሪካው ዋና ዲሬክተር ወደ ቢሮው አስጠራኝና ጥሩ ጥቅም ሊያስገኝ ወደሚችለው የፋብሪካው እቃ ግዢ ክፍል እንድዛወር ግብዣ አቀረበልኝ። ሆኖም የወንድሜን ፈለግ ለመከተል አስቤ ስለነበር ምክንያቴን ጭምር በመናገር ግብዣውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን በትህትና ገለጽኩለት። በጣም የሚገርመው፣ ጠቃሚ በሆነ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመካፈል በመፈለጌ ከልቡ አመሰገነኝ። ከዚያም በ1944 ኖርዝሃምፕተን በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆንኩ።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደብኩት በዴቨን ግዛት በምትገኘው ኤክሰተር የምትባል ከተማ ሲሆን ከተማዋ በጦርነቱ ወቅት በቦምብ ድብደባ ከደረሰባት ጉዳት ቀስ በቀስ እያገገመች ነበር። በዚያም ፍራንክና ሩት ሚደልተን ከሚባሉ ሁለት አቅኚዎች ጋር በአንድ አፓርታማ ውስጥ አብሬ መኖር ጀመርኩ፤ እነርሱም በጣም ያስቡልኝ ነበር። በወቅቱ ገና የ18 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ልብስ በማጠብም ሆነ ምግብ በማብሰል እምብዛም ልምድ አልነበረኝም። የኋላ ኋላ ልምድ እያዳበርኩ ስሄድ ሁኔታዎቹም እየተሻሻሉ መጡ።

የአገልግሎት ጓደኛዬ ከ1920ዎቹ ጀምሮ በምሥክርነቱ ሥራ ሲካፈል የነበረው የ50 ዓመቱ አየርላንዳዊ ቪክተር ገርድ ነበር። እርሱም ጊዜዬን ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንዴት እንደምከፋፍል፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እንዴት ፍቅር ማዳበር እንደምችልና የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማመሳከር ያለውን ጥቅም እንዳስተውል ረድቶኛል። በእነዚያ ወሳኝ ዓመታት ያስፈልገኝ የነበረው ልክ እንደ ቪክተር ያለ የጽናት ምሳሌ ነበር።

በገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት የደረሰብኝ ፈተና

ጦርነቱ ወደማብቃቱ እየተቃረበ ቢሆንም ባለ ሥልጣናቱ በውትድርና አገልግሎት እንዲሳተፉ ወጣቶችን መመልመል አላቆሙም ነበር። በ1943 ሚድንሄድ በሚገኝ ችሎት ፊት በመቅረብ የወንጌል አገልጋይ በመሆኔ ከማንኛውም ወታደራዊ ግዳጅ ነፃ መሆን እንደምፈልግ በግልጽ አስረዳሁ። ጥያቄዬ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ አገልግሎቴን ለመቀጠል ወደ ኤክሰተር ተጓዝኩ። ሆኖም ወደዚያ ከሄድኩ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በከተማው ፍርድ ቤት እንድቀርብ መጥሪያ ወረቀት ደረሰኝ። ዳኛው ረዘም ላለ ጊዜ የማሰር ፍቃድ እንዳልተሰጠው በቁጭት በመግለጽ ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር የስድስት ወር እስራት በየነብኝ። ስድስት ወሩን ጨርሼ ስወጣም ለተጨማሪ አራት ወር በድጋሚ ወደ እስር ቤት ተላክሁ።

በእስር ቤቱ ውስጥ ያለሁት የይሖዋ ምሥክር እኔ ብቻ በመሆኔ ጠባቂዎቹ ጅሆቫ እያሉ ይጠሩኝ ነበር። በስም ጥሪ ወቅት እንዲህ ተብዬ ስጠራ ግድ ሆኖብኝ አቤት እላለሁ እንጂ ይከብደኝ ነበር፤ ሆኖም በየዕለቱ የአምላክ ስም በአደባባይ ሲጠራ መስማት እንዴት የሚያስደስት ነበር! በተጨማሪም አጋጣሚው ሌሎች እስረኞች የታሰርኩት የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን ኅሊናዬን ለመጣስ ፈቃደኛ ባለመሆኔ ምክንያት መሆኑን እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል። ከጊዜ በኋላ ኖርማን ካስትሮ እኔ ወዳለሁበት እስር ቤት መጣ፤ በዚህ ጊዜ ሁኔታው ተለውጦ ሁለታችንን ሙሴና አሮን ብለው ይጠሩን ጀመር።

ከዚያም ከኤክሰተር ወደ ብሪስትል በመጨረሻም ወደ ዊንችስተር እስር ቤት እንድዛወር ተደረገ። ሁኔታዎች ሁልጊዜ አስደሳች ባይሆኑም እንኳ ተጫዋች መሆኔ ጠቅሞኛል። እኔና ኖርማን የመታሰቢያውን በዓል በዊንችስተር አብረን ማክበር በመቻላችን በጣም ተደስተን ነበር። በዚህ ወቅት ሊጠይቀን ወደ እስር ቤት መጥቶ የነበረው ፍራንሲስ ኩክ ግሩም ንግግር ሰጥቶናል።

ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት ያጋጠሙኝ ለውጦች

“እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለ መጽሐፍ በወጣበት ዓመት ይኸውም በ1946 ብሪስትል ውስጥ በተካሄደ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በዴቨን አቅኚ ሆና ስታገለግል ከነበረች ጆይስ ሞር የምትባል ቆንጆ እህት ጋር ተዋወቅሁ። ጓደኝነታችን እየተጠናከረ ሄዶ ከአራት ዓመት በኋላ ቴቨርተን ከተማ ውስጥ ጋብቻችንን ፈጸምን፤ ከ1947 ጀምሮ የምኖረው በዚህ ከተማ ነበር። ከዚያም በሳምንት 15 ሽልንግ (9 ብር ገደማ) የሚከፈልበት ቤት ተከራይተን መኖር ጀመርን፤ እጅግ የሚያስደስት ሕይወት ነበር!

በተጋባንበት ዓመት እንደገና ተዛወርንና ማራኪ የወደብ ከተማ ወደሆነችው ወደ ብሪክስሃም ሄድን፤ ከጀልባ ኋላ የታሰረ መረብ በመጠቀም ዓሣን የማስገር ዘዴ የተጀመረው በዚህች ከተማ እንደነበር ይነገራል። ሆኖም በዚያ የቆየነው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ለስብሰባ ወደ ለንደን በመጓዝ ላይ ሳለን በፖሊዮ በሽታ ተያዝኩ፤ በጊዜው ራሴን ስቼ ነበር። በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ለዘጠኝ ወራት ያህል ሆስፒታል ቆየሁ፤ የቀኝ እጄና ሁለቱም እግሮቼ በጣም ከመጎዳታቸው የተነሳ ለመንቀሳቀስ ምርኩዝ መያዝ አስፈልጎኝ ነበር። እርግጥ እጄና እግሮቼ አሁንም እንደዚያው ናቸው። ሆኖም ሁልጊዜ ፈገግታ የማይለያት ውዷ የትዳር ጓደኛዬ ከጎኔ መሆኗና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል መቻሏ አበረታቶኛል። ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ ምን ይውጠን ይሆን? ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ እጅ ፍጹም አጭር እንዳልሆነች ለማየት ቻልኩ።

በቀጣዩ ዓመት ለንደን በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በዚህ ጊዜ ያለ ምርኩዝ መሄድ ጀምሬ ነበር። በስብሰባው ላይ በእንግሊዝ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት ይመራ ከነበረው ፕሪስ ሂዩዝ ጋር ተገናኘን። እሱም እንዳየኝ “የወረዳ የበላይ ተመልካች እንድትሆን እንፈልጋለን!” አለኝ። እንደዚያ ቀን ተበረታትቼ አላውቅም! ሆኖም ጤንነቴ ይፈቅድልኝ ይሆን? ይህ ጥያቄ እኔንም ሆነ ጆይስን አሳስቦን ነበር። ይሁንና ለአንድ ሳምንት ያህል ከሠለጠንኩ በኋላ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ወደተመደብኩበት ደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ አመራን። በጊዜው ገና የ25 ዓመት ወጣት ብሆንም አሁንም ድረስ በደግነትና በትዕግሥት እርዳታ ያበረከቱልኝን ወንድሞች በአድናቆት ኣስታውሳቸዋለሁ።

እኔና ጆይስ ከተካፈልንባቸው የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች መካከል ጉባኤዎችን የመጎብኘትን ያህል ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ይበልጥ ያቀራረበን ሥራ የለም። መኪና ስላልነበረን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የምንጓዘው በባቡር አሊያም በአውቶቡስ ነበር። ከሕመሜ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የአቅም ገደቦች የነበሩብኝ ቢሆንም እስከ 1957 ድረስ በዚህ ልዩ የአገልግሎት መብት ላይ ቆይተናል። በጣም አስደሳች ሕይወት አሳልፈን በዚህ ዓመት ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ ገጠመን።

ሚስዮናዊ ሆንኩ

በጊልያድ 30ኛውን ክፍል እንድንከታተል ስንጋበዝ ደስታችን ወሰን አልነበረውም። የፖሊዮ በሽታ ካስከተለብኝ አካላዊ ችግር አገግሜ ስለነበር እኔም ሆንኩ ጆይስ ጥሪውን በደስታ ተቀበልን። ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ እስከጣርን ድረስ ሁልጊዜ ብርታት እንደሚሰጠን ከተሞክሮ ተምረናል። በኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ፣ ሳውዝ ላንሲንግ በተባለ በጣም ውብ አካባቢ በሚገኘው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የወሰድነው የአምስት ወር ጥልቀት ያለው ሥልጠና ሳይታወቀን አለፈ። አብዛኞቹ ተማሪዎች በወረዳና በአውራጃ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባልና ሚስቶች ነበሩ። በውጪ አገር በሚደረገው ሚስዮናዊ አገልግሎት ለመካፈል የሚፈልጉ እንዳሉ በተጠየቀ ጊዜ ፈቃደኝነታቸውን ከገለጹት መካካል እኛም እንገኝ ነበር። የት እንመደብ ይሆን? በምሥራቅ አፍሪካ በምትገኘው ኡጋንዳ ተመደብን!

በወቅቱ በኡጋንዳ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ ስለነበር ሰብዓዊ ሥራ በመያዝ ኑሮ ብጀምር የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ ቀረበልኝ። ከዚያም በባቡርና በጀልባ ረዥም ጉዞ ካደረግን በኋላ ካምፓላ፣ ኡጋንዳ ደረስን። የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናቱ በእኛ ወደዚያ መሄድ ደስተኞች አልነበሩም፤ ስለዚህ ጥቂት ወራት ብቻ እንድንቆይ ፈቀዱልን። ከዚያ ከአገሪቱ እንድንወጣ ታዘዝን። በኋላም ከዋናው መሥሪያ ቤት በደረሰን መመሪያ መሠረት ወደ ሰሜን ሮዴዥያ (አሁን ዛምቢያ) አቀናን። በዚያም አብረውን በጊልያድ ሲማሩ የነበሩትን ፍራንክና ካሪ ሉዊስን እንዲሁም ሄይስና ሀሪየት ሃዝኪንዝን በማግኘታችን በጣም ተደሰትን። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ደቡብ ሮዴዥያ (አሁን ዚምባብዌ) እንድናገለግል ተመደብን።

በባቡር ወደ ቡለወዮ ከተማ በምንጓዝበት ወቅት አስደናቂ የሆነውን የቪክቶሪያ ፏፏቴ የማየት አጋጣሚ አግኝተናል። በዚያም ከወንድም መክለኪ ቤተሰብ ጋር ለጥቂት ቀናት ሰነበትን፤ ይህ ቤተሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አካባቢው ከመጡት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ነው። በቀጣዮቹ 16 ዓመታት ከእነርሱ ጋር በይበልጥ የመተዋወቅ አጋጣሚ በማግኘታችን ተደስተናል።

ከገጠሙን ለውጦች ጋር ራሳችንን ማስማማት

በአፍሪካ ውስጥ ከሚደረገው የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ ጋር መተዋወቅ እንድችል የሁለት ሳምንት ሥልጠና ካገኘሁ በኋላ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ቁጥቋጦ በሚበዛባቸው የአፍሪካ ገጠሮች ውስጥ ለማገልገል ውኃ፣ ምግብ፣ ብርድ ልብስና አንሶላ፣ ልብስ፣ የፊልም ፕሮጀክተር፣ ጀነሬተር፣ ትልቅ ስክሪን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መገልገያዎችን ይዞ መጓዝ ጠይቆብናል። ይህን ሁሉ ጓዝ ለጉዞ ምቹ ያልሆኑ መንገዶችን የመቋቋም አቅም ባለው መኪና ላይ መጫን ነበረብን።

እኔ የአገሩ ተወላጅ ከሆኑ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር አብሬ በምሠራበት ወቅት ጆይስ ደግሞ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በደስታ ትረዳ ነበር። ከቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተዳምሮ በሣር በተሸፈኑና አለፍ አለፍ ብለው የበቀሉ ቁጥቋጦዎች በሚታዩበት የአፍሪካ ገጠራማ መንገዶች መጓዝ አድካሚ ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ የአየር ጠባይ ያለብኝን አካላዊ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረልኝ በጣም አመስጋኝ ነበርኩ።

ሕዝቡ በአጠቃላይ ሲታይ ድሃ ነው፤ ብዙዎቹ በባህልና በአጉል እምነት የተጠላለፉ እንዲሁም ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ ያላቸው ቢሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ጉባኤ የሚደረገው በትላልቅ ዛፎች ጥላ ሥር ሲሆን ማታ ማታ ብርሃን ለማግኘት በፋኖስ መጠቀም ግድ ነበር። ያም ሆኖ የይሖዋ ዕጹብ ድንቅ ሥራ ከሆነውና በከዋክብት ከተሞላው የተንጣለለ ሰማይ ሥር ሆነን ቃሉን ስናጠና ሁልጊዜ በአድናቆት ስሜት እንዋጣለን።

በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ ፊልሞችን በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች ያሳየንባቸውን ጊዜያት መቼም አልረሳቸውም። በአንድ ጉባኤ የሚሰበሰቡት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 30 ይሆናል ብለን ብንወስድ እንኳ በእነዚህ ወቅቶች ቢያንስ 1,000 ሰዎች እንደሚገኙ በእርግጠኝነት እንጠብቅ ነበር።

በሐሩር ክልል በተደጋጋሚ የጤና ችግር ማጋጠሙ የተለመደ ስለሆነ ሁልጊዜ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ነበረብን። እኔ በወባ በሽታ የተያዝኩባቸው ጊዜያት ሲኖሩ ጆይስ ደግሞ በአሜባ በሽታ ትቸገር ነበር። ሆኖም የሚገጥሙንን የጤና ችግሮች ለመቋቋም ችለናል።

በኋላም በሳልስቤሪ (አሁን ሃራሬ) በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያም ሌስተር ዴቪይ፣ ጆርጅና ሩቢ ብራድሊን ከመሳሰሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር አብረን መሥራት መቻላችን ታላቅ መብት ነበር። ከመንግሥት በተገኘ ፈቃድ መሠረት የጋብቻ ጉዳይ ሹም ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ይህም የአገሬው ተወላጅ ለሆኑ ወንድሞች የጋብቻ ሥርዓት የማስፈጸምና በጉባኤ ውስጥ የጋብቻ ትስስር እንዲጠናከር የመርዳት አጋጣሚ አስገኝቶልኛል። ጥቂት ዓመታት ካለፉ በኋላ ደግሞ በመላው አገሪቱ የሚገኙ በውጪ አገር ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን የመጎብኘት ልዩ መብት አገኘሁ። እኔም ሆንኩ ጆይስ በዚህ መልኩ ያሳለፍናቸው ከአሥር የሚበልጡ ዓመታት ከወንድሞች ጋር ይበልጥ እንድንተዋወቅና በመንፈሳዊ እድገታቸው እንድንደሰት አስችለውናል። በእነዚህ ወቅቶች በቦትስዋናና በሞዛምቢክ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ማየት ችለናል።

ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሄድ

በደቡባዊው አፍሪካ ክልል ብዙ አስደሳች ዓመታትን ካሳለፍን በኋላ በ1975 በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር፣ በሴራሊዮን እንድናገለግል ተመደብን። የተሰጠንን አዲስና አስደሳች ሥራ ለማከናወን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው በመሄድ በዚያው መኖር ጀመርን፤ ሆኖም እዚያ ብዙ መቆየት አልቻልንም። በወባ በሽታ ክፉኛ በመታመሜና ሰውነቴም በመዳከሙ ለሕክምና ወደ ለንደን ሄድኩ። በዚያም ዳግመኛ ወደ አፍሪካ መመለስ እንደሌለብኝ ተነገረኝ። በሁኔታው እጅግ አዘንን፤ ደስ የሚለው ግን ለንደን የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆንን ሲሆን ቤተሰቡም ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገልን። ለንደን በሚገኙ ብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ አፍሪካውያን ወንድሞችን ማግኘታችንም አፍሪካ እንዳለን እንዲሰማን አድርጎናል። ጤንነቴ እየተሻሻለ ሲሄድ በሌሎች የተለመዱ እንቅስቃሴዎች መካፈል ጀመርን፤ እኔም የእቃ ግዢ ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በቀጣዮቹ ዓመታት ያየነው መስፋፋት ሥራውን ይበልጥ አስደሳች አድርጎልኛል።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ውዷ ባለቤቴ ጆይስ ነርቭን በሚያጠቃ በሽታ በመያዟ ታማ ከቆየች በኋላ በ1994 ሕይወቷ አለፈ። ጆይስ በሕይወት በኖረችባቸው ጊዜያት ሁሉ ከሚገጥሙን የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ራሷን ለማስማማት ፈቃደኛ የሆነች አፍቃሪና ታማኝ ሚስት ነበረች። እንዲህ የመሰለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ግልጽ የሆነ መንፈሳዊ አመለካከት መያዝና የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ጠቃሚ እንደሆኑ አስተውያለሁ። በተጨማሪም ስብከትን ጨምሮ ጥሩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያወጣሁትን ፕሮግራም እንድከተል ይሖዋን በጸሎት መጠየቄ አእምሮዬ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አስችሎኛል።—ምሳሌ 3:5, 6

የቤቴል አገልግሎት ልዩ መብት ከመሆኑም በላይ እጅግ አስደሳች የሕይወት መንገድ ነው። ከበርካታ ወጣቶች ጋር አብሬ መሥራትና አስደሳች ጊዜያት ማሳለፍ ችያለሁ። የለንደን ቤቴልን ለመጎብኘት የሚመጡ ብዙ ወንድሞችን ማስተናገድ መቻል ሌላው በረከት ነው። አንዳንድ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እናውቃቸው ከነበሩ ወዳጆቻችን ጋር እገናኝና ያሳለፍኳቸውን አስደሳች ጊዜያት ወደኋላ ተመልሼ በትዝታ እቃኛለሁ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ‘በአሁኑ ሕይወቴ’ ሙሉ በሙሉ እንድደሰትና ‘የሚመጣውን’ ሕይወት በተስፋና በልበ ሙሉነት እንድጠባበቅ አስችለውኛል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1928 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1946 ከእናቴ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1950 ከጆይስ ጋር በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በብሪስትል በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በደቡብ ሮዴዥያ (አሁን ዚምባብዌ) በሚገኝ አንድ ገለልተኛ ቡድንና (ከላይ) አንድ ጉባኤ (በስተ ግራ) ውስጥ ስናገለግል