በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጎ ነገር ከማድረግ አትታክት

በጎ ነገር ከማድረግ አትታክት

በጎ ነገር ከማድረግ አትታክት

 ሐዋርያው ጴጥሮስ “በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ” በማለት አጥብቆ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 2:12) “መልካም” ወይም “በጎ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ውብ፣ ጥሩ፣ ክቡርና ግሩም” የሆነን ነገር ያመለክታል። በጥቅሉ ሲታይ በዚህ ዘመን ሰዎች ጥሩ ወይም የሚያስከብር ባሕርይ ያሳያሉ ብሎ መጠበቁ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ይመስላል። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ የጴጥሮስን ማሳሰቢያ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም የሚታወቁት በመልካም ጠባያቸው ነው።

በዚህ ‘አስጨናቂ ጊዜ’ መከራና ጭንቀት እየደረሰብንም እንኳ እንዲህ ያለ ባሕርይ ማሳየታችን የሚደነቅ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) መከራ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ሲሆን በክርስቲያናዊ የሕይወት ጎዳና ስንጓዝ ተቃውሞ ማጋጠሙም እንግዳ አይደለም። በተጨማሪም አንዳንድ ችግሮች ወዲያውኑ ሲያልፉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ሊዘልቁ እንዲያውም እየተባባሱ ሊሄዱ ይችላሉ። የሆነ ሆኖ ሐዋርያው ጳውሎስ “በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን” በማለት አጥብቆ አሳስቧል። (ገላትያ 6:9) ታዲያ አሳዛኝ መከራና የማይረግብ ጥላቻ እየደረሰብንም እንኳ አሁንም ሆነ ወደፊት መልካም የሆነውን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በጎ የሆነውን ለማድረግ የሚረዱ ነገሮች

“ጥሩ፣ ክቡር፣ ግሩም” የሚሉት ቃላት የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ወይም የልብ ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። ስለሆነም በመከራና በችግር ወቅት መልካም ባሕርይ ማሳየት የሚቻለው እንዲያው በደመ ነፍስ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ዘወትር በመከተልና ተግባራዊ በማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የሚረዱን ነገሮች ምንድን ናቸው? ቀጥሎ ያሉትን ሐሳቦች ተመልከት።

የክርስቶስን አስተሳሰብ አዳብር። ኢፍትሐዊ የሚመስሉ ጉዳዮችን መታገሥ ትሕትና ይጠይቃል። ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ሰው የሚደርስበትን በደል ይታገሣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ሆኖም ኢየሱስ “ራሱን ዝቅ አደረገ፤ . . . እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:5, 8) እኛም የእርሱን ፈለግ በመከተል ‘ሳንዝል ወይም ተስፋ ሳንቆርጥ’ ቅዱስ አገልግሎታችንን ማቅረብ እንችላለን። (ዕብራውያን 12:2, 3) በጉባኤህ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ካላቸው ወንድሞች ጋር በፈቃደኝነት በመተባበር ታዛዥነትን አዳብር። (ዕብራውያን 13:17) ለሌሎች ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት ከአንተ “እንደሚሻሉ” አድርገህ መመልከትን ተማር።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

ይሖዋ እንደሚወድህ አስታውስ። ይሖዋ ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ የሚሰጥ’ አምላክ መሆኑን ማመን አለብን። (ዕብራውያን 11:6) ከልብ ያስብልናል፣ እንዲሁም ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ማጥፋት የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ማስታወሳችን በመከራ ወቅት ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።—ሮሜ 8:38, 39

በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ታመን። በተለይ ችግሮች ማቆሚያ የሌላቸው ወይም ለሕይወት አስጊ በሚመስሉበት ጊዜ በይሖዋ መታመናችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ‘ከምንችለው በላይ’ የሆነ ምንም ዓይነት ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ፣ ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ ‘መውጫውን እንደሚያዘጋጅልን’ ሙሉ በሙሉ መተማመን አለብን። (1 ቆሮንቶስ 10:13) በእርሱ ከታመንን ሕይወታችንን የማጣት ፈተና ቢገጥመን እንኳ በድፍረት ልንጋፈጠው እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 1:8, 9

በጸሎት ጽና። ከልብ የመነጨ ጸሎት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 12:12) ልባዊ ጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ከሚያስችሉን መንገዶች መካከል አንዱ ነው። (ያዕቆብ 4:8) ከግል ተሞክሯችን እንዳየነው “ማንኛውንም ነገር . . . ብንለምን እርሱ ይሰማናል” ለማለት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 5:14) ይሖዋ፣ ከአቋማችን ፍንክች የማንል መሆናችንን ለመፈተን የሚደርስብን መከራ እንዲቀጥል ከፈቀደ ለመጽናት እንዲረዳን እንጸልያለን። (ሉቃስ 22:41-43) ጸሎት ፈጽሞ ብቻችንን እንዳልሆንን እንድንገነዘብ ያደርገናል፤ ይሖዋ ከጎናችን እንዳለ እንዲሰማን ስለሚያደርግ ሁልጊዜ ድል እንነሳለን።—ሮሜ 8:31, 37

በጎ ሥራ—‘ክብርና ውዳሴ ያስገኛል’

ሁሉም ክርስቲያኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ “ብዙ ዐይነት ፈተና” ስለሚደርስባቸው ማዘናቸው አይቀርም። ያም ሆኖ ግን ‘በጎ ነገር ከማድረግ መታከት’ የለብንም። አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ታማኝነትህ የኋላ ኋላ ‘ክብርንና ውዳሴን እንደሚያስገኝልህ’ በማወቅ በርታ። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) ይሖዋ እምነትህ እንዲጠናከር ለመርዳት ባደረጋቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። እርዳታ ሲያስፈልግህ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኛ፣ አስተማሪና አማካሪ ሆነው ወደሚያገለግሉት ወንድሞች መሄድ ትችላለህ። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ በሚያነቃቁን’ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር ተገኝ። (ዕብራውያን 10:24) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብህና የግል ጥናት ማድረግህ ንቁና በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድትሆን ይረዳሃል፤ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ አዘውትረህ መካፈልህም መንፈሳዊ ጥንካሬ ያስገኝልሃል።—መዝሙር 1:1-3፤ ማቴዎስ 24:14

ይሖዋ አፍቃሪና አሳቢ አምላክ መሆኑን ባየህ መጠን ‘መልካም የሆነውን በማድረግ ለመትጋት’ ያለህ ፍላጎትም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። (ቲቶ 2:14) ‘የሚድነው እስከ መጨረሻ የሚጸና’ መሆኑን አትዘንጋ። (ማቴዎስ 24:13) አዎን፣ ‘በጎ ነገር ከማድረግ አለመታከት’ ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን!

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ‘ከምንችለው በላይ’ የሆነ ምንም ዓይነት ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ፣ ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ ‘መውጫውን እንደሚያዘጋጅልን’ ሙሉ በሙሉ መተማመን አለብን

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን የሚደርሱብንን ችግሮች ለመወጣት ዝግጁ ያደርገናል