በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፍ አንድነት የሌለው ለምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ አንድነት የሌለው ለምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ አንድነት የሌለው ለምንድን ነው?

“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ኅብረተሰብ አንድ ሆኗል። . . . ስለዚህ የዓለም ኅብረተሰብ፣ ይህንን አጋጣሚ ሲጠበቅ የነበረውን አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማምጣት ሊጠቀምበት ይገባል።”

ይህንን የተናገሩት በ1990ዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩ ሰው ናቸው። በወቅቱ የነበረው የዓለም ሁኔታ ዓለም አቀፍ አንድነት የሚገኝበት ጊዜ የተቃረበ እንዲመስል አድርጎ ነበር። አምባገነን መንግሥታት ተራ በተራ እየወደቁ ነበር። የበርሊን ግንብ መፍረሱ ደግሞ ለአውሮፓ የአዲስ ዘመን መባቻ ነበር። እንዲሁም በበርካታ ምዕራባውያን አገሮች ዘንድ የዓለም አቀፍ ግጭቶች ቆስቋሽ እንደሆነች ተደርጋ ትታይ የነበረችው ሶቪዬት ኅብረት ዓለምን ባስገረመ መልኩ ከህልውና ውጪ ሆነች። ቀዝቃዛው ጦርነት ከማክተሙም በተጨማሪ የኑክሌርና የሌሎች የጦር መሣሪያዎች ቅነሳን የሚመለከቱ ተስፋ ሰጪ ውይይቶች ይደረጉ ጀመር። እርግጥ ነው፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት ተነስቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት አብዛኛው ሕዝብ ለዓለም ሰላም ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ያነሳሳ ጊዜያዊ ችግር ብቻ ነበር።

አዎንታዊ ምልክቶች የታዩት በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኑሮ መስኮች ጭምር ነው። በበርካታ አገራት የሰዎች የኑሮ ደረጃ ተሻሽሎ ነበር። በሕክምናው መስክ የተገኘው እድገት ሐኪሞች ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት እንደ ተአምር ይታዩ የነበሩ ነገሮችን እንዲሠሩ አስችሏቸዋል። መላው ዓለም ወደ ብልጽግና የሚያመራ እስኪመስል ድረስ ብዙ አገሮች ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አድርገው ነበር። በጥቅሉ ሲታይ፣ ሁኔታዎች ትክክለኛ አቅጣጫቸውን የያዙ ይመስል ነበር።

እነዚህ ክንውኖች ከተፈጸሙ ብዙ ዓመታት ባያልፉም እንኳ ‘ምን ተፈጠረ? ተስፋ የተደረገው ዓለም አቀፍ አንድነት የት አለ?’ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። እንዲያውም ዓለም በተቃራኒው አቅጣጫ እየተጓዘች ያለች ትመስላለች። ጋዜጦች አጥፍቶ ጠፊዎች ስላደረሱት የቦምብ ፍንዳታ፣ አሸባሪዎች ስለሰነዘሩት ጥቃት፣ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች እየተመረቱ ስለመሆናቸውና ስለ ሌሎች አስፈሪ ክስተቶች መዘገባቸው የተለመደ ሆኗል። እነዚህን የመሰሉ ክስተቶች ዓለምን ይበልጥ ከአንድነት እያራቋት መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። በቅርቡ አንድ ስመ ጥር ባለ ሀብት “ሳንወድ በግዳችን ይበልጥ እየተባባሰ በሚሄድ የጭካኔ ተግባር እሽክርክሪት ውስጥ ገብተናል” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ አንድነት ወይስ ክፍፍል?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቋቋመበት ጊዜ ከነበሩት ዓላማዎች አንዱ “የሕዝቦችን የመብት እኩልነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መርህ በማክበር በብሔራት መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ” ነው። ወደ ስልሳ ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ እንዲህ ያለው ከፍተኛ ግብ ላይ መድረስ ተችሎ ይሆን? በፍጹም! እንዲያውም ብሔራትን ይበልጥ የሚማርካቸው “ወዳጃዊ ግንኙነት” ሳይሆን ‘የራስን ዕድል በራስ መወሰን’ የሚለው ጉዳይ ነው። እውቅና ለማግኘትና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የሚታገሉ ሕዝቦችና ጎሳዎች ዓለም የባሰ እንድትከፋፈል እያደረጉ ነው። በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተቋቋመበት ጊዜ 51 አባል አገራት ብቻ የነበሩት ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ 191 ደርሷል።

ቀደም ብለን እንዳየነው በ1990ዎቹ ብዙዎች ዓለም አቀፍ አንድነት በቅርቡ እውን ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የዓለም ኅብረተሰብ ከቀን ወደ ቀን እየተከፋፈለ ሲመጣ ይህ ተስፋ እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ዩጎዝላቪያ በጦርነት መገነጣጠሏ፣ በቼችንያና በሩሲያ መካከል የተፈጠሩት ግጭቶች፣ የኢራቅ ጦርነትና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ የመጣው ደም መፋሰስ ዓለም ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ እየተከፋፈለች መምጣቷን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉት አብዛኞቹ ጥረቶች ከቅን ልቦና እንደሚመነጩና በጎ ዓላማ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህም ሆኖ ዓለም አቀፍ አንድነት የሕልም እንጀራ የሆነ ይመስላል። ብዙዎች ‘ዓለም አቀፍ አንድነት አልጨበጥ ያለው ለምንድን ነው? ዓለም ወዴት እያመራች ነው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/Lionel Cironneau

Arlo K. Abrahamson/AFP/ Getty Images