በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም ወዴት እያመራች ነው?

ዓለም ወዴት እያመራች ነው?

ዓለም ወዴት እያመራች ነው?

ዓለም አቀፍ አንድነት ቢገኝ በጣም ያስደስታል። ይህ ሁሉም ሰው የሚመኘው ነገር አይደለም? አዎን፣ አንድነትን በተመለከተ ብዙ ሲባል ቆይቷል። የዓለም መሪዎች ባደረጓቸው ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ስለዚህ ጉዳይ አንስተው ተወያይተዋል። በነሐሴ 2000 ከ1,000 የሚበልጡ የሃይማኖት መሪዎች የዓመቱን የዓለም ሰላም ጉባኤ ለማድረግ ኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሰብስበው ነበር። በስብሰባው ላይ በዓለም ላሉት ግጭቶች መፍትሄ የሚሆኑ ሐሳቦችን አንስተው ተወያይተዋል። ይሁን እንጂ ስብሰባው ራሱ እየተባባሰ የመጣው በዓለም የሚታየው ግጭት ነጸብራቅ ነበር። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አንድ መፍቲ (የእስልምናን ሕግ የሚያውቁና ትንታኔ የሚሰጡ ሰው)፣ በስብሰባው ላይ የአይሁድ ረቢ (የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪ) ስለሚገኙ በጉባኤው ለመካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሌሎች የስብሰባው ተካፋዮች ደግሞ ቻይና ቅር ትሰኝ ይሆናል በሚል ፍራቻ ዳላይ ላማ (የቲቤት ቡድሂዝም ሃይማኖትና ፖለቲካ መሪ) በስብሰባው የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ላይ እንዲገኙ ባለመጋበዛቸው ተበሳጭተዋል።

የሰላማዊ ውቅያኖስ አዋሳኝ አገሮች በጥቅምት 2003 ታይላንድ ውስጥ ባደረጉት የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ፣ የዓለምን ሰላም በተመለከተ ውይይት አድርገው ነበር። በጉባኤው ላይ የተገኙት 21 አገሮች አሸባሪ ቡድኖችን ለማጥፋት ቃል ከመግባታቸውም በተጨማሪ ዓለም አቀፉን ሰላም ይበልጥ አስተማማኝ ማድረግ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ የጉባኤው ተካፋይ የነበሩ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አይሁዳውያንን ከጥላቻ በመነሳት ወንጅለዋል በሚል ስሜት የበርካታ አገሮች ተወካዮች በስብሰባው ወቅት ሲያጉረመርሙ ተሰምተዋል።

አንድነት ሊገኝ ያልቻለው ለምንድን ነው?

ዓለምን አንድ ስለ ማድረግ ብዙ ውይይቶች ቢደረጉም ይሄ ነው የሚባል ውጤት አላስገኙም። ብዙዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥረት ቢያደርጉም፣ በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን የሚገኙ ሰዎች አንድነት ሊኖራቸው ያልቻለው ለምንድን ነው?

በእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ ከተካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አንዱ የሰጡት አስተያየት ለተነሳው ጥያቄ የተወሰነ መልስ ይሰጣል። “ብሔራዊ ኩራት የሚባል ነገር አለ” በማለት ተናግረዋል። አዎን፣ የሰው ልጆች በብሔረተኝነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቀዋል። እያንዳንዱን ብሔርና ጎሳ የሚያንቀሳቅሰው ኃይል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ፍላጎት ነው። የአገር ሉዓላዊነት፣ ፉክክርና የስስት መንፈስ ተዳምረው አደገኛ ሁኔታ ፈጥረዋል። ከብሔራዊ ጥቅምና ከመላው ዓለም ፍላጎት አንዱን የመምረጥ አጣብቂኝ በሚፈጠርበት ጊዜ በአብዛኛው ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ይሰጣል።

መዝሙራዊው “አሰቃቂ ቸነፈር” በማለት የተናገረው ሐሳብ ብሔራዊ ስሜትን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። (መዝሙር 91:3) ብሔራዊ ስሜት በሰዎች ላይ ልክ እንደ መቅሰፍት ቁጥር ስፍር የሌለው መከራ እያስከተለ ነው። ብሔረተኝነትና ይህንን ተከትሎ የሚመጣው ሌሎች ሕዝቦችን የመጥላት ዝንባሌ ለበርካታ ዘመናት የኖረ ችግር ነው። በአሁኑ ጊዜም ብሔረተኝነት መከፋፈል እንዲባባስ እያደረገ ሲሆን ሰብዓዊ መሪዎች ይህን ችግር ማስቆም አልቻሉም።

በርካታ ባለ ሥልጣናት ብሔረተኝነትና ራስ ወዳድነት በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች ዋነኛ መንስዔዎች እንደሆኑ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዩ ታንት “በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሙን ያሉት አብዛኞቹ ችግሮች የተሳሳተ አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው። . . . ከእነዚህም መካከል ‘ትክክልም ይሁን ስህተት አገሬ የምትወስደውን እርምጃ እደግፋለሁ’ የሚለው ጠባብ የብሔረተኝነት አስተሳሰብ ይገኝበታል” ብለዋል። አሁንም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ የቆሙ ብሔራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ያላቸው ፍላጎት እያየለ መጥቷል። ከዚህም በላይ ሉዓላዊነታቸውን በትንሹም ቢሆን አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። ለምሳሌ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን ስለ አውሮፓ ኅብረት ሲገልጽ “ፉክክርና አለመተማመን አሁንም ድረስ በአውሮፓ ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። አብዛኞቹ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ሌሎች አቻ አገሮች ጠንከር ያለ ተጽዕኖ እንዲያደርጉና የመሪነቱን ቦታ እንዲይዙ አይፈልጉም” ብሏል።

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላውን የሰው ልጅ አገዛዝ ውጤት በተመለከተ “ሰው ሰውን ለመጒዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ” በማለት ትክክለኛውን ነገር ተናግሯል። (መክብብ 8:9) የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች ዓለምን በብሔር መከፋፈላቸው “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እውነት መሆኑን እንዲያዩ አድርጓቸዋል።ምሳሌ 18:1

ለእኛ የሚበጀንን የሚያውቀው ፈጣሪያችን፣ ሰዎች የራሳቸውን መንግሥታት እንዲያቋቁሙና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዓላማው አልነበረም። ይሁን እንጂ ሰዎች የራሳቸውን አገዛዝ በመመሥረት የአምላክን ዓላማ ችላ ከማለታቸውም በላይ ሁሉም ነገር የእርሱ የመሆኑን እውነታ ዘንግተዋል። መዝሙር 95:3-5 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ታላቅ ንጉሥ ነው። የምድር ጥልቆች በእጁ ናቸው፤ የተራራ ጫፎችም የእርሱ ናቸው። እርሱ ፈጥሮአታልና፣ ባሕር የእርሱ ናት፤ እጁም የብስን አበጀ።” አምላክ ሁሉም ፍጥረቶቹ ሊገዙለት የሚገባ ሉዓላዊ ገዥ የመሆን ሕጋዊ መብት አለው። ብሔራት ግን የራሳቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በመሯሯጥ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።መዝሙር 2:2

ምን ያስፈልጋል?

ዓለም አቀፍ አንድነት ሊገኝ የሚችለው፣ ለሁሉም ሰዎች ፍላጎት የሚያስብና ምድርን አንድ አድርጎ የሚያስተዳድር መንግሥት ሲቋቋም ብቻ ነው። ነገሩ የሚያሳስባቸው ብዙ ሰዎች የዚህን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ይህ እንዲሆን የሚጠብቁት ከተሳሳተ አቅጣጫ ነው። ለምሳሌ ያህል የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፣ ሰዎች ዓለም አቀፍ አንድነት ለማግኘት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተስፋ እንዲያደርጉ ያበረታታሉ። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ያቋቋማቸው ድርጅቶች ምንም ያህል በጎ ዓላማ ቢኖራቸው፣ የሰዎችን ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ፈጽሞ መፍታት አልቻሉም። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰብዓዊ ድርጅቶች በበርካታ አገሮች መካከል ያለውን መከፋፈል የሚያንጸባርቁ እየሆኑ መጥተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” በማለት ከሰብዓዊ ድርጅቶች መፍትሄ እንዳንፈልግ አስጠንቅቋል። (መዝሙር 146:3) እንዲህ ሲባል ታዲያ ዓለም አቀፍ አንድነት ሊመጣ አይችልም ማለት ነው? እንደዚህ ማለት አይደለም። አንድነት የሚገኝበት መንገድ አለ።

በርካታ ሰዎች አምላክ ዓለምን አንድ ማድረግ የሚችል መንግሥት እንዳቋቋመ አይገነዘቡም። መጽሐፍ ቅዱስ “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ። ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ” በማለት ስለ ይሖዋ አምላክ ይናገራል። (መዝሙር 2:6, 8) ይሖዋ አምላክ በመዝሙር 2:7 ላይ “ልጄ” ብሎ የጠቀሰውን ‘የራሱን ንጉሥ እንደሾመ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ንጉሥ የአምላክ ታላቅ መንፈሳዊ ልጅ ከሆነውና በሁሉም ብሔራት ላይ ሥልጣን ከተሰጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።

ዓለም አቀፍ አንድነት እውን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

ብዙ ሰዎች አምላክ ስላቋቋመው ስለዚህ ሰማያዊ አገዛዝ አያውቁም። ብሔራት የራሳቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለውበታል። የሆነ ሆኖ አምላክ ሉዓላዊነቱንና ያቋቋመውን መንግሥት ለመቀበል አሻፈረኝ የሚሉትን አይታገሳቸውም። መዝሙር 2:9 አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ለመቀበል እምቢተኛ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ “አንተም [ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ] በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቃቸዋለህ” ይላል። ብሔራት ይወቁትም አይወቁት ከአምላክ ጋር የሚያጋጫቸውን አካሄድ እየተከተሉ ነው። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት’ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ይገልጻል። (ራእይ 16:14) ብሔራትና የፈጠሯቸው ክፍፍሎች በሙሉ ከህልውና ውጪ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ያለ ምንም እንቅፋት ሥራውን እንዲያከናውን መንገድ ይጠርጋል።

የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ ኃይሉን በጥበብ በመጠቀም፣ በልጁ በኩል ዓለም አቀፋዊ አንድነት ለማምጣት አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ያደርጋል። የአምላክ መንግሥት እውነተኛ አንድነት ያመጣል፤ እንዲሁም ጽድቅ ወዳድ የሆኑትን ሁሉ ይባርካል። ለምን ጥቂት ጊዜ ወስደህ ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ መዝሙር ምዕራፍ 72ን አታነብም? ይህ ምዕራፍ በአምላክ ልጅ የሚመራው መስተዳድር ለሰው ዘሮች ምን እንደሚያመጣላቸው ትንቢታዊ መግለጫዎችን ይዟል። የሰው ልጆች እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም እንደ ጭቆና፣ የጭካኔ ተግባር፣ ድህነትና የመሳሰሉት ሌሎች ችግሮቻቸው በሙሉ ይወገዱላቸዋል።

በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ይህን የመሰለ ተስፋ ሊጨበጥ እንደማይችል ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ብሎ ማሰቡ ፈጽሞ ስህተት ነው። አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሳይፈጸሙ ቀርተው አያውቁም፤ ለወደፊቱ ቃል የገባቸው ነገሮችም እንዲሁ መፈጸማቸው አይቀርም። (ኢሳይያስ 55:10, 11) እንዲህ ያለውን ለውጥ ማየት ትፈልጋለህ? ፍላጎቱ ካለህ ለማየት ትችላለህ። በዛሬው ጊዜ ያንን ለውጥ ለማየት የሚያስፈልገውን ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ቢሆኑም እርስ በርሳቸው አይዋጉም፤ ከዚህ ይልቅ አንድ ሆነው ለአምላክ ሉዓላዊነት እየተገዙ ናቸው። (ኢሳይያስ 2:2-4) እነዚህ እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ይባላሉ። ለምን በስብሰባዎቻቸው ላይ አትገኝም? ለአምላክ ሉዓላዊነት እንድትገዛ ሊረዱህ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት መመሥረትህና ከእነርሱ ጋር ለዘላለም የማይከስም አንድነት ማግኘትህ እንደሚያስደስትህ የተረጋገጠ ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች አንድነት ባለው ዓለም ውስጥ ለመኖር ዝግጅት እያደረጉ ነው

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Saeed Khan/AFP/Getty Images

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሐዘን የደረሰባት ሴት:- Igor Dutina/AFP/Getty Images; የተቃውሞ ሰልፈኞች:- Said Khatib/AFP/Getty Images; ብረት ለበስ መኪናዎች:- Joseph Barrak/AFP/Getty Images