በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ታስሮ የነበረው ጴጥሮስ በር ላይ እንደቆመ ሲሰሙ “የእርሱ መልአክ ነው” ያሉት ለምንድን ነው?—የሐዋርያት ሥራ 12:15

ደቀ መዛሙርቱ እንደዚህ ያሉት በር ላይ ቆሞ የነበረው ሰው ጴጥሮስን ወክሎ የተላከ መልአክ መስሏቸው ይሆናል። እስቲ ከጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ታሪክ እንመልከት።

ያዕቆብን ያስገደለው ሄሮድስ፣ ጴጥሮስም እንዲታሰር አደረገ። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ፣ ጴጥሮስ ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥመዋል ብለው ማሰባቸው ምክንያታዊ ነበር። ወኅኒ ቤት የነበረው ጴጥሮስ በሰንሰለት ታስሮ በአራት ፈረቃ በተመደቡ አራት አራት ወታደሮች ይጠበቅ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ሌሊት መልአክ መጣና በተአምራዊ መንገድ እየመራ ከእስር ቤት አስወጣው። በመጨረሻም ጴጥሮስ ምን እንደተፈጸመ ሲገባው “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ።—የሐዋርያት ሥራ 12:1-11

ወዲያውም ጴጥሮስ ብዙ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው ወደነበሩበት ወደ ዮሐንስ ማርቆስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። የውጭውን በር ሲያንኳኳ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ለመክፈት ሄደች። ከዚያም በር ላይ የቆመው ሰው ጴጥሮስ እንደሆነ በድምፁ አወቀችና በሩን እንኳ ሳትከፍትለት ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየሮጠች ሄደች! መጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ በር ላይ የቆመው ሰው ጴጥሮስ እንደሆነ ለማመን አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ “የእርሱ መልአክ” እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 12:12-15

ደቀ መዛሙርቱ፣ ጴጥሮስ ከተገደለ በኋላ መንፈሱ በር ላይ እንደቆመ ተሰምቷቸው ነበር ማለት ነው? ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም የኢየሱስ ተከታዮች ሙታን “ምንም አያውቁም” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ያውቃሉ። (መክብብ 9:5, 10) ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ “የእርሱ መልአክ ነው” ሲሉ ምን ማለታቸው ነበር?

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በታሪክ ዘመናት ሁሉ መላእክት የአምላክን አገልጋዮች በግለሰብ ደረጃ ይረዱ እንደነበር ያውቃሉ። ለምሳሌ ያህል:- ያዕቆብ “ከጒዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ” በማለት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 48:16) በተጨማሪም ኢየሱስ በተከታዮቹ መሃል ትንሽ ልጅ አቁሞ:- “ከእነዚህ ከታናናሾች መካከል አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ እላችኋለሁና፤ በሰማይ ያሉት መላእክታቸው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ሁልጊዜ ያያሉ” ብሏቸው ነበር።—ማቴዎስ 18:10

ያንግስ ሊትራል ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ አጌሎስ (“መልአክ”) የሚለውን ግሪክኛ ቃል “መልእክተኛ” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል። አንዳንድ አይሁዳውያን እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ የራሱ መልአክ ወይም “ጠባቂ መልአክ” እንዳለው አድርገው ያምኑ የነበረ ይመስላል። እርግጥ ነው፣ የአምላክ ቃል እንደዚያ ብሎ በቀጥታ አያስተምርም። ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ “የእርሱ መልአክ ነው” ብለው ሲናገሩ በር ላይ የቆመው ጴጥሮስን ወክሎ የተላከ መልአክ እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል።