ሥራን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው የተለያየ አመለካከት
ሥራን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው የተለያየ አመለካከት
“መሥራት—መሥራት! ሥራ ማቆሚያ እንደሌለው ማወቁ በጣም ያስደስታል።”—ካትሪን ማንስፊልድ የተባሉ ደራሲ (1888-1923)
ለሥራ ቀና አመለካከት የነበራቸው እኚህ ደራሲ በሰጡት ሐሳብ ትስማማለህ? አንተ በግልህ ለሥራ ምን አመለካከት አለህ? ዘና ብለህ ከምታሳልፈው ቅዳሜና እሁድ በኋላ የሚመጣ የማይገፋና አሰልቺ ነገር እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ ሥራህን በጣም ከመውደድህ የተነሳ ሱስ እየሆነብህ ነው?
ብዙ ሰዎች በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በሥራ ነው። የምንኖርበትን ቦታና አኗኗራችንን የሚወስነው ሥራችን ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ሙሉ ሰው ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ጡረታ እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሥራቸው መሆኑን ተገንዝበዋል። አንዳንዶቻችን ከሥራችን ከፍተኛ እርካታ እናገኛለን። ሌሎች ደግሞ የሥራቸውን ዋጋማነት የሚመዝኑት በሚያገኙት ገቢ ወይም ክብር ሲሆን በሌላ በኩል ሥራቸውን ከጊዜ ማሳለፊያነት ለይተው የማይመለከቱ አሊያም ጊዜያቸውን እንደሚያባክንባቸው የሚሰማቸው ሰዎችም አሉ።
ለመኖር ብለው የሚሠሩ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ለመሥራት ሲሉ የሚኖሩም አሉ። አንዳንዶች በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ወይም በሥራቸው ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል። ለአብነት ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በሥራ ምክንያት ለበሽታና ለሞት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር “በጦርነት ወይም አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን እንዲሁም የአልኮል መጠጥን አለአግባብ በመውሰድ” ሳቢያ ከሚታመሙትና ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። ዘ ጋርዲያን የተባለው የለንደን ጋዜጣ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “በየዓመቱ ከሥራ ጋር በተያያዙ አደጋዎች ወይም በሽታዎች ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሞታሉ . . . ለአቧራ፣ ለኬሚካሎች፣ ለከፍተኛ ድምፅ እንዲሁም ለጨረር መጋለጥ ካንሰርና የልብ ሕመም እያስከተለ [ነው]።” የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና በግዳጅ የሚከናወን የጉልበት ሥራ በዛሬው ጊዜ በሥራው ዓለም የሚታዩ አስከፊ እውነታዎች ናቸው።
ከዚህም በላይ የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ስቲቨን ቤርግለስ እንደተናገሩት አንዳንዶች ‘በጣም ከመዛላቸው የተነሳ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ያጋጥማቸዋል።’ ቤርግለስ በሥራው ትልቅ ቦታ ላይ የደረሰ ትጉህ ሠራተኛ “ማምለጫ በሌለውና ሥነ ልቦናዊ እርካታ በማያስገኝለት ሙያ እንደተጠመደ ሲሰማው ከፍተኛ ፍርሃት፣ ውጥረት፣ የተስፋ ማጣት ስሜት ወይም ጭንቀት” እንደሚያድርበት ገልጸዋል።
ትጉህ ሠራተኛና የሥራ ሱሰኛ በመሆን መካከል ያለው ልዩነት
ብዙዎች በርካታ ሰዓታት በሥራ ተጠምደው በሚያሳልፉበት በዚህ ዓለም፣ በትጉህ ሠራተኞችና የሥራ ሱሰኛ በሆኑ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቁ ጠቃሚ ነው። የሥራ ሱስ ያለባቸው ብዙ ሰዎች አስተማማኝ ባልሆነው ዓለም ውስጥ ሥራቸውን እንደ መሸሸጊያ ይመለከቱታል፤ ለትጉህ
ሠራተኞች ግን ሥራ አስፈላጊና አንዳንዴም እርካታ የሚያስገኝ ኃላፊነት ነው። የሥራ ሱሰኞች በሥራቸው በጣም ስለሚጠመዱ በሕይወታቸው ሌላ ምንም ነገር ለማድረግ ጊዜ አይኖራቸውም፤ ትጉህ ሠራተኞች ግን መቼ ሥራ ማቆምና ለሌሎች ነገሮች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ለምሳሌ ያህል የጋብቻቸውን ቀን እንደ ማክበር ላሉ ጉዳዮች ጊዜ ይመድባሉ። የሥራ ሱሰኞች ከመጠን በላይ በመሥራት የሚረኩ ከመሆኑም በላይ ይህ የበለጠ ለመሥራት ያነሳሳቸዋል፤ ትጉህ ሠራተኞች ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም።በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ ከመጠን በላይ መሥራት ተፈላጊ ነገር ተደርጎ ስለሚታይ ተግቶ በመሥራትና የሥራ ሱሰኛ በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ያስቸግራል። ሞባይል ስልኮችና ሌሎች ተመሳሳይ መሣሪያዎች የሥራ ቦታን ከመኖሪያ ቤት መለየት አዳጋች እንዲሆን አድርገዋል። በየትኛውም ቦታ ሆነ በማንኛውም ሰዓት መሥራት የሚቻል በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ጤንነታቸው እስኪቃወስ ድረስ ራሳቸውን በሥራ ያስጠምዳሉ።
እንደዚህ ስላለው ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት አንዳንድ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል? የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብት ከመጠን በላይ በሥራ በተጠመዱና ውጥረት በሚበዛባቸው ሰዎች ዘንድ መንፈሳዊ ነገሮችን ወደ ሥራ ቦታቸው የማምጣትና ሃይማኖታቸውን ከሙያቸው ጋር የማጣመር ዝንባሌ እንደሚታይ አስተውለዋል። ሳን ፍራንሲስኮ ኤግዛምነር የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው “መንፈሳዊነትን ከሥራ ጋር ማጣመር በሕዝቡ ዘንድ እየተለመደ መጥቷል።”
በዩናይትድ ስቴትስ በቴክኖሎጂ በተራቀቁ መሣሪያዎች የሚጠቀሙ ድርጅቶች የሚገኙበትን ሲሊከን ቫሊ የሚባል አካባቢ አስመልክቶ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በሠራተኞች ቅነሳ ሳቢያ በሥራ ቦታ ክፍት የሆኑ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ምሽት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚደረግባቸው ቦታዎች ግን መኪና ማቆሚያ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።” ይህ የሆነበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለሥራ ባላቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይሰማቸዋል፤ ይህም ሕይወታቸውን ይበልጥ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመምራት አስችሏቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው? በዘመናዊው የሥራ ቦታ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችሉን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ይኖሩ ይሆን? ቀጣዩ ርዕስ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነው።