በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥራ በረከት ነው ወይስ እርግማን?

ሥራ በረከት ነው ወይስ እርግማን?

ሥራ በረከት ነው ወይስ እርግማን?

“ለሰው . . . በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም።”—መክብብ 2:24

“በቀኑ መጨረሻ ላይ ኃይሌ ሙጥጥ ብሎ ያልቃል።” በቅርቡ በተካሄደ ጥናት ከሦስት ሠራተኞች አንዱ አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ እንደሚሰማው ተናግሯል። ሰዎች በውጥረት የተሞላ ሕይወት በሚመሩበት በዚህ ዓለም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መኖሩ አያስገርምም። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ለረጅም ሰዓታት የሚሠሩ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ሥራ ይዘው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፤ ያም ሆኖ ግን አለቆቻቸው አንድም የምስጋና ቃል ከአፋቸው አይወጣም።

ብዙ ሠራተኞች ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት በሚመረትባቸው ግዙፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ ከቁጥር የሚገባ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ተነሳሽነትና የፈጠራ ችሎታ ይጠፋል። ይህ ደግሞ ሰዎች ለሥራ ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው። ሠራተኛው ለሥራው የሚኖረው ፍቅር ይሞታል፤ በሙያው የላቀ ችሎታ ለማዳበር ያለው ፍላጎትም ታፍኖ ይቀራል። እነዚህ ነገሮች ሰዎች ሥራቸውን እንዳይወዱት ምናልባትም እንዲጠሉት ሊያደርጓቸው ይችላሉ።

አመለካከታችንን መመርመር

የሥራችንን ሁኔታ መለወጥ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም አመለካከታችንን ማስተካከል እንችላለን ቢባል አትስማማም? ለሥራ ያለህ አሉታዊ አመለካከት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጽዕኖ እንዳሳደረብህ ከተሰማህ አምላክ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከትና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን መመርመርህ ይጠቅምሃል። (መክብብ 5:18) ብዙዎች እንዲህ በማድረጋቸው በሥራቸው ደስታና እርካታ ማግኘት ችለዋል።

አምላክ ተወዳዳሪ የሌለው ሠራተኛ ነው። ስለ አምላክ በዚህ መንገድ አስበን አናውቅ ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ ሠራተኛ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጀመሪያ ራሱን ያስተዋወቀው በዚህ መንገድ ነው። የዘፍጥረት ዘገባ የመክፈቻ ቃላት ይሖዋ ሰማይንና ምድርን እንደፈጠረ ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 1:1) አምላክ የፍጥረት ሥራውን ሲጀምር በርካታ የሥራ ድርሻዎች እንደነበሩት አስታውስ። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ንድፍ አውጪ፣ መሃንዲስ፣ የሥነ ጥበብ ባለሞያ፣ ቀማሚ፣ የሥነ ሕይወትና የሥነ እንስሳት ባለሞያ፣ ፕሮግራም አርቃቂና የቋንቋ ሊቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሥራውን ያደራጅ፣ ተስማሚ የግንባታ ቁሳቁሶችን ይመርጥ እንዲሁም የሥራውን ሂደት ይከታተል ነበር።—ምሳሌ 8:12, 22-31

አምላክ ያከናወነው ሥራ ጥራቱ ምን ይመስል ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሥራው “መልካም” እንዲሁም “እጅግ መልካም” እንደነበር ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:4, 31) በእርግጥም የፍጥረት ሥራዎች “የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤” እኛም ይሖዋን ልናወድሰው ይገባል።—መዝሙር 19:1፤ 148:1

ሆኖም አምላክ ግዑዙን ሰማይና ምድር እንዲሁም የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ፈጥሮ ሥራውን አላበቃም። የይሖዋ ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 5:17) በእርግጥም ይሖዋ ለፍጥረታቱ የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ፣ የፍጥረት ሥራውን በመንከባከብና ታማኝ አገልጋዮቹን በማዳን መሥራቱን ቀጥሏል። (ነህምያ 9:6፤ መዝሙር 36:6፤ 145:15, 16) እንዲያውም አምላክ ሰዎች ‘ከእርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ’ በማድረግ አንዳንድ ሥራዎችን ለማከናወን ይጠቀምባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 3:9

ሥራ በረከት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ እርግማን እንደሆነ ይገልጽ የለም? በዘፍጥረት 3:17-19 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ስንመለከት አዳምና ሔዋን በማመጻቸው ምክንያት አምላክ አድካሚ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ የቀጣቸው ይመስላል። ይሖዋ በእነዚህ ሁለት ሰዎች ላይ ሲፈርድ አዳምን “ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ” ብሎት ነበር። ይህ ፍርድ ሥራ በአጠቃላይ እርግማን እንደሆነ የሚያሳይ ነው?

በፍጹም አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ አዳምና ሔዋን ታማኝ ባለመሆናቸው ምክንያት ዔድን ገነትን የማስፋፋቱ ሥራ በዚያ ወቅት እንደማይከናወን የሚያሳይ ነበር። አምላክ ምድሪቷን ስለረገማት አንድ ሰው ለመኖር የሚያስፈልገውን ምግብ ለማግኘት ብዙ መልፋት ነበረበት።—ሮሜ 8:20, 21

መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ እርግማን ሳይሆን ልናደንቀው የሚገባ በረከት እንደሆነ ይገልጻል። ከላይ እንደተገለጸው አምላክ ራሱ ትጉህ ሠራተኛ ነው፤ ሰዎችን በአምሳሉ ከፈጠረ በኋላ ምድራዊ ፍጥረታቱን የማስተዳደር ችሎታና ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 1:26, 28፤ 2:15) አምላክ ይህንን ሥራ የሰጣቸው በዘፍጥረት 3:19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ፍርድ ከማስተላለፉ በፊት ነበር። ሥራ እርግማንና መጥፎ ነገር ቢሆን ኖሮ ሰዎች እንዲሠሩ አያበረታታቸውም ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ በፊትም ሆነ በኋላ ብዙ የሚሠሩት ሥራ ነበራቸው። በክርስትና ዘመንም ቢሆን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሠሩ ተመክረዋል።—1 ተሰሎንቄ 4:11

ያም ቢሆን ግን በዛሬው ጊዜ ሥራ አድካሚ ሊሆን እንደሚችል ሁላችንም እናውቃለን። ውጥረት፣ በጤንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ አደገኛ ሁኔታዎች፣ መሰልቸት፣ ያሰቡት ሳይሆን ሲቀር መበሳጨት፣ ፉክክር፣ ማታለል እንዲሁም የፍትሕ መጓደል በሥራ ቦታ እንደ “እሾኽና አሜከላ” ሊሆኑ ከሚችሉት ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ ሥራ በራሱ እርግማን አይደለም። በመክብብ 3:13 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ እና ከሥራ የሚገኘው ውጤት የአምላክ ስጦታዎች መሆናቸውን ይገልጻል።—“ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ውጥረትን መቋቋም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በሥራህ አምላክን ማክበር ትችላለህ። ጥራት ያለውና የላቀ ሥራ ምንጊዜም ቢሆን ይወደሳል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥራት ያለው ሥራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል። አምላክ ራሱ ሥራውን የሚያከናውነው ጥራት ባለው መንገድ ነው። ለእኛም ቢሆን የፈጠራ ችሎታና ተሰጥኦ የሰጠን ሲሆን ይህንንም ጥሩ ነገር ለመሥራት እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። ለአብነት ያህል፣ በጥንቷ እስራኤል የመገናኛው ድንኳን በተሠራበት ወቅት ይሖዋ እንደ ባስልኤልና ኤልያብ ላሉት ሰዎች ለየት ያሉ የሥነ ጥበብ ሥራዎችንና ሌሎች ተግባሮችን እንዲያከናውኑ ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፀአት 31:1-11) ይህም ይሖዋ ለሚያከናውኑት ሥራ፣ ለሙያቸው፣ ለንድፉና ለሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደነበረ ያሳየናል።

ይህ ችሎታዎቻችንንና የሥራ ልማዳችንን በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል። እነዚህ ነገሮች ከአምላክ ያገኘናቸው ስጦታዎች መሆናቸውንና አቅልለን ልናያቸው እንደማይገባ እንድንገነዘብ ያስችለናል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ሥራቸውን አምላክ እንደሚመለከተው በማሰብ እንዲያከናውኑ የሚከተለው ምክር ተሰጥቷቸዋል:- “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት።” (ቈላስይስ 3:23) የይሖዋ አገልጋዮች ሥራቸውን በጥንቃቄና በትጋት እንዲያከናውኑ የታዘዙ ሲሆን እንዲህ ማድረጋቸው ክርስቲያናዊው መልእክት በሥራ ባልደረቦቻቸውም ሆነ በሌሎች ዘንድ ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ያደርገዋል።—“በሥራ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

የምናከናውነው ነገር አምላክን ሊያስከብር እንደሚችል ካወቅን ሥራችንን በትጋትና በጥራት እየተወጣን መሆን አለመሆናችንን ራሳችንን መጠየቁ አስፈላጊ ነው። ሥራችንን የምናከናውንበት መንገድ አምላክን ያስደስታል? እርካታስ እያስገኘልን ነው? ካልሆነ ማሻሻያ ማድረግ እንችላለን ማለት ነው።—ምሳሌ 10:4፤ 22:29

ሥራና መንፈሳዊነትን በሚዛናዊነት አከናውን። ጠንክሮ መሥራት የሚደነቅ ነገር ቢሆንም በሥራችንና በሕይወታችን ለመርካት የሚያስፈልገን ሌላም ቁልፍ ነገር አለ። ይህም መንፈሳዊነታችን ነው። ንጉሥ ሰሎሞን ትጉህ ሠራተኛ ከመሆኑም በላይ በሕይወቱ ሊያገኝ የሚችለው ሀብትና ምቾት ሁሉ የነበረው ቢሆንም በመጨረሻ “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና” ወደሚል መደምደሚያ ደርሷል።—መክብብ 12:13

ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ማንኛውንም ሥራ ስናከናውን የአምላክን ፈቃድ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። የምንሠራው ሥራ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነው ወይስ የሚጋጭ? አምላክን ለማስደሰት እየጣርን ነው ወይስ ራሳችንን ለማስደሰት ብቻ ነው የምንሮጠው? የአምላክን ፈቃድ የማናደርግ ከሆነ ውሎ አድሮ ለተስፋ መቁረጥ፣ ለብቸኝነትና ለባዶነት ስሜት እንዳረጋለን።

ስቲቨን ቤርግለስ ከፍተኛ ድካም የሚሰማቸው አለቆች ‘የሚወዱትን ሥራ ቢይዙና የሕይወታቸው ክፍል ቢያደርጉት’ የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ አቅርበዋል። ትርጉም ያለው ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ተሰጥኦና ችሎታ የለገሰንን ፈጣሪ ከማገልገል የሚበልጥ ሥራ የለም። ፈጣሪያችንን የሚያስደስት ሥራ የምንሠራ ከሆነ እርካታ እናገኛለን። ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሰጠው ሥራ ልክ እንደ ምግብ ጠቃሚ፣ አርኪና መንፈስ የሚያድስ ሆኖለታል። (ዮሐንስ 4:34፤ 5:36) ከዚህም በላይ ተወዳዳሪ የሌለው ሠራተኛ የሆነው አምላክ ከእርሱ ጋር ‘አብረን እንድንሠራ’ ጋብዞናል።—1 ቆሮንቶስ 3:9

ይሖዋን ማምለክና መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እርካታ የሚያመጣ ሥራ ለመሥራትና ኃላፊነት ለመቀበል ያዘጋጀናል። በሥራው ዓለም ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል እንዲሁም ግጭትና ውጥረት ያጋጥማቸዋል፤ በመሆኑም ጠንካራ እምነትና መንፈሳዊነት ማዳበራችን የተሻልን ሠራተኞች ወይም አሠሪዎች ለመሆን በምናደርገው ጥረት በጣም የሚያስፈልገንን ብርታት ያስገኝልናል። በሌላ በኩል ደግሞ ለአምላክ አክብሮት በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ የምናያቸው ነገሮች እምነታችንን ልናጠናክርባቸው የሚገቡ መስኮችን ይጠቁሙናል።—1 ቆሮንቶስ 16:13, 14

ሥራ በረከት የሚሆንበት ጊዜ

በአሁኑ ጊዜ አምላክን በትጋት የሚያገለግሉ ሰዎች ይሖዋ ምድርን እንደገና ገነት የሚያደርግበትንና የሚያረካ ሥራ ብቻ የሚኖርበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ። ኢሳይያስ የተባለው የይሖዋ ነቢይ በዚያን ጊዜ ስለሚኖረው ሕይወት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።”—ኢሳይያስ 65:21-23

በዚያን ጊዜ ሥራ በረከት ይሆናል! አምላክ ምን እንደሚፈልግብህ በመማርና ከተማርከው ነገር ጋር ተስማምተህ በመኖር ይሖዋ ከባረካቸው ሕዝቦች መካከል ለመሆን እንዲሁም ‘በምትደክምበት ሁሉ ርካታን ለማግኘት’ ያብቃህ።—መክብብ 3:13

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ ተወዳዳሪ የሌለው ሠራተኛ ነው:- ዘፍጥረት 1:1, 4, 31፤ ዮሐንስ 5:17

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሥራ በረከት ሊሆን ይችላል:- ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15፤1 ተሰሎንቄ 4:11

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሥራህ አምላክን ማክበር ትችላለህ:- ዘፀአት 31:1-11፤ ቈላስይስ 3:23

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሥራና መንፈሳዊነትን በሚዛናዊነት አከናውን:- መክብብ 12:13፤ 1 ቆሮንቶስ 3:9

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ውጥረትን መቋቋም

የሕክምና ባለሞያዎች በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ውጥረትን በጤንነት ላይ ጉዳት ከሚያመጡ ሁኔታዎች መካከል ፈርጀውታል። በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ውጥረት የሆድ ዕቃ ቁስለትና የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትል አልፎ ተርፎም ራስን ወደ ማጥፋት ሊመራ ይችላል። ጃፓኖች ይህን ሁኔታ ካሮሺ በማለት የሚጠሩት ሲሆን “ከመጠን በላይ በመሥራት የሚከሰት ሞት” ማለት ነው።

ከሥራ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች አንድን ሰው ለውጥረት ሊዳርጉት ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል የሥራ ሁኔታ ወይም ሰዓት መለወጥ፣ ከአለቆች ጋር አለመስማማት፣ የኃላፊነት ወይም የሥራ ለውጥ፣ ጡረታ መውጣት እንዲሁም ከሥራ መባረር ይገኙበታል። አንዳንዶች እንደዚህ ካለው ውጥረት ለማምለጥ ሲሉ ሥራቸውን ወይም አካባቢውን ይቀይራሉ። ሌሎች ደግሞ ችግሩን ችለው ለመኖር ይመርጡ ይሆናል፤ ሆኖም ውጥረቱ ያስከተለው ስሜት በሌሎች የሕይወታቸው ክፍሎች (አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰብ ሕይወታቸው) ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንዳንዶች ደግሞ የስሜት መቃወስ ስለሚያጋጥማቸው ለጭንቀትና ለተስፋ መቁረጥ ይዳረጋሉ።

ክርስቲያኖች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን ውጥረቶች መቋቋም እንዲችሉ በሚገባ የታጠቁ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን መንፈሳዊና ስሜታዊ ጤንነታችን ሳይቃወስ ችግሩን መወጣት እንድንችል የሚረዱ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ብሏል። እዚህ ላይ የተሰጠን ማበረታቻ ስለ ቀጣዩ ቀን ችግሮች ከማሰብ ይልቅ በዕለቱ ችግር ላይ ብቻ እንድናተኩር የሚያሳስብ ነው። ይህም ችግሮቻችን ከመጠን በላይ ገዝፈው እንዲታዩን በማድረግ ይበልጥ ከመጨነቅ እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ማቴዎስ 6:25-34

ክርስቲያኖች በራሳቸው ጥንካሬ ሳይሆን በአምላክ መታመናቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ነገሮች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ ሲሰማን አምላክ የልብ ሰላምና ደስታ ሊሰጠን እንዲሁም ማንኛውንም ፈተና ለመወጣት የሚያስችለንን ጥበብ ሊሰጠን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ” በማለት ጽፏል።—ኤፌሶን 6:10፤ ፊልጵስዩስ 4:7

በመጨረሻም፣ ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችም እንኳ መልካም ነገር ሊያስገኙ እንደሚችሉ እናስታውስ። ችግሮች ወደ ይሖዋ ዘወር እንድንል፣ እንድንፈልገውና በእርሱ እንድንታመን ሊያደርጉን ይችላሉ። ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማፍራታችንን እንድንቀጥልና ተጽዕኖዎች ቢያጋጥሙንም የመጽናት ችሎታ እንድናዳብር ያስችሉናል። ጳውሎስ “በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን [ያስገኛል]” በማለት መክሮናል።—ሮሜ 5:3, 4

እንግዲያው ውጥረት የሚያስከትል ሁኔታም እንኳ በተስፋ መቁረጥና በሐዘን እንድንዋጥ ከማድረግ ይልቅ በመንፈሳዊ እንድናድግ ሊያነሳሳን ይችላል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሥራ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ

አንድ ክርስቲያን ለሥራው ያለው አመለካከትና የሚያሳየው ባሕርይ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሥራ ባልደረቦቹም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ማራኪ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ በዛሬው ጊዜ ተቀጥረው ከሚሠሩ ሰዎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ላይ የነበሩ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “ባሮች [ለአሠሪዎቻቸው] በማንኛውም ነገር እንዲገዙ፣ ደስ እንዲያሰኟቸው፣ የአጸፋ ቃል እንዳይመልሱላቸው አስተምር፤ አይስረቁ፤ ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው።”—ቲቶ 2:9, 10

ለአብነት ያህል፣ አንድ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የላከውን የሚከተለውን ደብዳቤ ተመልከት:- “ይህን ደብዳቤ የጻፍኩላችሁ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመቅጠር እንድችል ፈቃድ ለመጠየቅ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችን መቅጠር የፈለግሁት እነርሱ ታማኝ፣ ቅንና እምነት የሚጣልባቸው ከመሆናቸውም በላይ አሠሪያቸውን ስለማያታልሉ ነው። መተማመን የምችለው በይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነው። እባካችሁ እርዱኝ።”

ካይል የተባለች አንዲት ክርስቲያን በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ እንግዳ ተቀባይ ሆና ትሠራለች። ከአንዲት የሥራ ባልደረባዋ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሳቢያ ሴትየዋ ተማሪዎች ባሉበት ካይልን ሰደበቻት። ካይል “በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ላለማምጣት መጠንቀቅ ነበረብኝ” በማለት ታስታውሳለች። በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ካይል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችል ስታውጠነጥን ቆየች። ካሰበችባቸው መመሪያዎች መካከል በሮሜ 12:18 ላይ የሚገኘው “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለው ጥቅስ ይገኝበታል። ከዚያም ካይል ለሥራ ባልደረባዋ በኢ-ሜይል መልእክት በመላክ በመካከላቸው ስለተፈጠረው አለመግባባት ይቅርታ ጠየቀቻት። እንዲሁም ከሥራ በኋላ ቢሮ ቆይተው ስለ ጉዳዩ በመወያየት ችግሩን እንዲፈቱ ሐሳብ አቀረበችላት። ይህንንም በማድረጋቸው የካይል የሥራ ባልደረባ ቁጣዋ የበረደላት ሲሆን ካይል የወሰደችው እርምጃ ጥሩ መሆኑንም አምናለች። ካይልን “ይህን እንድታደርጊ ያነሳሳሽ ሃይማኖትሽ መሆን አለበት” ካለቻት በኋላ ሲሰነባበቱ ሞቅ ባለ ስሜት እቅፍ አደረገቻት። ካይል ምን ተሰማት? “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ካደረግን ፈጽሞ አንሳሳትም” ብላለች።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ሠራተኞች ግዙፍ በሆነው ድርጅት ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ ከቁጥር የሚገባ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል

[ምንጭ]

የጃፓን የመረጃ ማዕከል፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የጃፓን ጠቅላይ ቆንስላ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሉል:- NASA photo