“በእምነቱ ምክንያት የተሰደደ”
“በእምነቱ ምክንያት የተሰደደ”
በሰሜን ኢጣሊያ ቼርኖብዮ በሚባል ከተማ በአንድ መናፈሻ ውስጥ ሰብዓዊ መብታቸው የተጣሰባቸውን ሰዎች ለማስታወስ የመታሰቢያ ቦታ ተዘጋጅቷል። ለመታሰቢያነት ከተሠሩት ሐውልቶች አንዱ ለናርሲሶ ሪት ተብሎ የተዘጋጀ ነው። በጀርመን አገር የተወለደውና ወላጆቹ ጣሊያናውያን የሆኑት ናርሲሶ ሪት በ1930ዎቹ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በሂትለር አገዛዝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ለሂትለር ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ የበለጠ ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብዙ ስደት ደርሶባቸዋል።
ሪት የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ወደ ማጎሪያ ካምፖች እንደሚያስገባ ጌስታፖዎች ስላወቁበት ወደ ቼርኖብዮ ሸሸ። እዚያ እያለም መጠበቂያ ግንብን ወደ ጣሊያንኛ ከተረጎመ በኋላ በአቅራቢያው ለሚገኙ የእምነት ወንድሞቹ እንዲያሰራጭ ተጠየቀ። ሆኖም በትጋት ያከናውን የነበረው ሥራ ከእይታ አላመለጠም። የኤስ ኤስ ኃላፊውና ወታደሮቹ ወደ ሪት ቤት በድንገት ገቡና ያዙት፤ እንዲሁም ሁለት መጽሐፍ ቅዱሶችና ጥቂት ደብዳቤዎችን “በወንጀል” ማስረጃነት ወሰዱ። ሪትን ወደ ጀርመን ከወሰዱት በኋላ በዳካው ማጎሪያ ካምፕ አሰሩት፤ ከዚያም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ተገደለ። በቼርኖብዮ የተሠራው የመታሰቢያ ሐውልት ላይ “በእምነቱ ምክንያት የተሰደደ” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል።
የናርሲሶ ሪትና በናዚ አገዛዝ ወቅት ስደት የደረሰባቸው የሌሎች በርካታ ምሥክሮች እምነት በአሁኑ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ አምልኮ የሚገባው ብቸኛው አካል ለሆነው ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንዲቆሙ ያበረታታቸዋል። (ራእይ 4:11) ኢየሱስ “ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው” ብሏል። አምላክ ሥራቸውን የሚያስታውስ ከመሆኑም በላይ በድፍረት ላከናወኑት ሥራ ወሮታ ይከፍላቸዋል።—ማቴዎስ 5:10፤ ዕብራውያን 6:10