በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋን አመስግኑ!

እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋን አመስግኑ!

እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋን አመስግኑ!

“እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት። . . . [እናንት] ወጣት ወንዶችና ደናግል።”—መዝሙር 148:7, 12

1, 2. (ሀ) ብዙ ወጣቶች ምን ዓይነት እገዳዎች እንደተጣሉባቸው ያውቃሉ? (ለ) ወጣቶች ወላጆቻቸው የሚጥሉባቸውን እገዳዎች መጥላት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

 ወጣቶች እንዲያደርጉ የማይፈቀድላቸውን ነገር በአብዛኛው ጠንቅቀው ያውቃሉ። አብዛኞቹ ለብቻቸው መንገድ ማቋረጥ፣ ማታ እስከፈለጉበት ሰዓት ድረስ ማምሸት ወይም መኪና መንዳት የሚፈቀድላቸው በስንት ዓመታቸው እንደሆነ ወዲያው ሊነግሯችሁ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ወጣት በጣም ለሚጓጓላቸው ለአብዛኞቹ ነገሮች “ስታድግ ትደርስበታለህ” የሚል ተመሳሳይ መልስ እንደሚሰጠው ይሰማው ይሆናል።

2 እናንት ወጣቶች ወላጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ገደቦች የሚያወጡት ለራሳችሁ ደህንነት አስበው እንደሆነ ልታውቁ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ወላጆቻችሁን ስትታዘዙ ደስ እንደሚሰኝ በሚገባ ታውቃላችሁ። (ቈላስይስ 3:20) ይሁንና ገና መኖር እንዳልጀመራችሁ ሆኖ ተሰምቷችሁ ያውቃል? አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ እስክታድጉ ድረስ ተከልክላችኋል? ሐቁ ፍጹም ከዚህ የተለየ ነው! ለማግኘት ከምትጓጉለት ከማንኛውም መብት የበለጠ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሥራ በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ነው። እናንት ወጣቶች በዚህ ሥራ እንድትካፈሉ ተፈቅዶላችኋል? ከመፈቀድም አልፎ ሉዓላዊው አምላክ ራሱ በሥራው እንድትካፈሉ ግብዣ አቅርቦላችኋል!

3. ይሖዋ ወጣቶች በየትኛው ሥራ እንዲካፈሉ ግብዣ አቅርቦላቸዋል? ቀጥሎ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 እየተናገርን ያለነው ስለ ምን ዓይነት ሥራ ነው? ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተበት ዋና ጥቅስ የያዛቸውን ቃላት ልብ በል:- “እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት። . . . ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት።” (መዝሙር 148:7, 12) ጥቅሱ ይሖዋን የማመስገን ትልቅ መብት እንዳላችሁ ይገልጻል። በወጣትነት ዕድሜያችሁ በዚህ ሥራ መሳተፍ ያስደስታችኋል? ብዙዎች ደስተኞች ናቸው። እንዲህ ሊሰማን የሚገባው ለምን እንደሆነ ለማየት እስቲ ሦስት ጥያቄዎችን እንመርምር። በመጀመሪያ፣ ይሖዋን ማመስገን ያለባችሁ ለምንድን ነው? ሁለተኛ፣ እርሱን በሚገባ ማመስገን የምትችሉት እንዴት ነው? ሦስተኛ፣ ይሖዋን ማመስገን መጀመር የምንችልበት ጥሩ ጊዜ መቼ ነው?

ይሖዋ መመስገን ያለበት ለምንድን ነው?

4, 5. (ሀ) በመዝሙር 148 መሠረት ምን አስደናቂ መብት አግኝተናል? (ለ) መናገርም ሆነ ማሰብ የማይችሉ ፍጥረታት ይሖዋን ማመስገን የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ይሖዋን እንድናመሰግነው የሚያደርገን ትልቁ ምክንያት የሁሉ ነገር ፈጣሪ መሆኑ ነው። መዝሙር 148 በዚህ ሐቅ ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። እስቲ አስበው:- ብዙ ሰዎች አንድ ደስ የሚልና ስሜት ቀስቃሽ የሆነ መዝሙር በሕብረት ሲዘምሩ ብትሰማ ምን ዓይነት ስሜት ያድርብሃል? የመዝሙሩ ግጥም የያዛቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን እንዲሁም መልእክቱ አስፈላጊ፣ አስደሳችና መንፈስ የሚያድስ መሆኑን ብታውቅስ? ስንኞቹን ለማጥናትና አብረህ ለመዘመር ፍላጎት አያድርብህም? ይህ የአብዛኞቻችን ስሜት ነው። እንግዲያው 148ኛው መዝሙር አንተም እጅግ ግሩም በሆነ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ያሳያል። መዝሙሩ ይሖዋን በሕብረት ስለሚያመሰግኑ በርካታ ፍጥረታት ይናገራል። መዝሙሩን ስታነብ ግን አንድ ለየት ያለ ነገር ታስተውል ይሆናል። ይህ ምንድን ነው?

5 በመዝሙር 148 ላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ምስጋና አቅራቢዎች መናገርም ሆነ ማሰብ አይችሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ዐመዳይ፣ ነፋስ፣ ተራሮችና ኰረብቶች ይሖዋን እንደሚያመሰግኑ ተገልጿል። እነዚህ ግዑዝ የሆኑ ፍጥረታት እንዴት ይሖዋን ሊያወድሱ ይችላሉ? (ቁጥር 3, 8, 9) ዛፎች፣ የባሕር ውስጥ ፍጥረታትና እንስሳት ምስጋና በሚያቀርቡበት መንገድ ነው። (ቁጥር 7, 9, 10) ፀሐይ ስትጠልቅ ያላትን ውበት ወይም ሙሉ ጨረቃ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስታቋርጥ የተመለከትክበት፣ እንስሳት ሲጫወቱ አይተህ የሳቅህበት አሊያም በጣም የሚያምር መልክአ ምድር አይተህ በአድናቆት የተዋጥክበት ጊዜ የለም? ከሆነ ፍጥረት የሚያቀርበውን የውዳሴ መዝሙር “ሰምተሃል” ማለት ነው። ይሖዋ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ እርሱ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እንደሆነና በመላው አጽናፈ ዓለም የእርሱን ያህል ኃይል ያለው፣ ጥበበኛ ወይም አፍቃሪ የሆነ ማንም እንደሌለ ያስገነዝቡናል።—ሮሜ 1:20፤ ራእይ 4:11

6, 7. (ሀ) መዝሙር 148 እንደሚናገረው ይሖዋን የሚያመሰግኑት ማስተዋል ያላቸው ፍጡራን የትኞቹ ናቸው? (ለ) ይሖዋን ለማመስገን የምንነሳሳው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

6 መዝሙር 148 ማስተዋል ያላቸው ፍጥረታትም ይሖዋን እንደሚያመሰግኑ ይገልጻል። ቁጥር 2 ላይ በሰማይ ያሉት የይሖዋ ‘ሰራዊት’ ማለትም መላእክት እርሱን እንደሚያመሰግኑት እናነባለን። ቁጥር 11 ላይ እንደ ነገሥታትና መሳፍንት ያሉ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ምስጋና እንዲያሰሙ ተጋብዘዋል። ኃያላን መላእክት ይሖዋን በማወደስ የሚደሰቱ ከሆነ አንድ ተራ ሰው እንዲህ ማድረግ ክብሬን ይነካል እንዴት ሊል ይችላል? ከዚያም በቁጥር 12 እና 13 ላይ ወጣቶች ከሌሎች ፍጥረታት ጋር በመተባበር ይሖዋን እንድታመሰግኑ ግብዣ ቀርቦላችኋል። ይህን ለማድረግ ስሜታችሁ ይገፋፋችኋል?

7 አንድ ምሳሌ ተመልከት። አንድ የቅርብ ጓደኛህ በስፖርት፣ በሥዕል ወይም በሙዚቃ የላቀ ችሎታ ቢኖረው ይህን ለቤተሰብህና ለሌሎች ጓደኞችህ አትነግራቸውም? እንዴታ። እንግዲያው፣ ይሖዋ ስላደረጋቸው ነገሮች ማወቃችንም በእኛ ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 19:1, 2 በከዋክብት የተሞሉት ሰማያት ‘እንደሚናገሩ’ ይገልጻል። እኛም ብንሆን ይሖዋ ስላከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ስናስብ ለሌሎች ስለ አምላካችን ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።

8, 9. ይሖዋ እርሱን እንድናመሰግነው የሚፈልገው በየትኞቹ ምክንያቶች የተነሳ ነው?

8 ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርገን ሌላው ዐቢይ ምክንያት እንዲህ እንድናደርግ የሚፈልግ መሆኑ ነው። ለምን? ከሰዎች ምስጋና ማግኘት ስለሚያስፈልገው ነው? አይደለም። እኛ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ መመስገን ያስፈልገን ይሆናል፤ ይሖዋ ግን ከእኛ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 55:8) ስለ ራሱ ማንነት ወይም ስለ ባሕርያቱ የሚጠራጠረው ነገር የለም። (ኢሳይያስ 45:5) ሆኖም እርሱን እንድናወድሰው ይፈልጋል፤ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ደስ ይለዋል። ለምን? ሁለት ምክንያቶችን ተመልከቱ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እርሱን ልናመሰግነው እንደሚገባ ያውቃል። ሲፈጥረን መንፈሳዊ ፍላጎት ማለትም የማምለክ ዝንባሌ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 5:3) ወላጆቻችሁ ለሰውነታችሁ ጠቃሚ የሆነ ምግብ ስትመገቡ እንደሚደሰቱ ሁሉ ይሖዋም ለዚህ ፍላጎታችን ትኩረት ስንሰጥ ይደሰታል።—ዮሐንስ 4:34

9 በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ ሌሎች ሰዎች እርሱን ስናመሰግን መስማት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል:- “ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) አዎን፣ ለሌሎች ስለ ይሖዋ አምላክ በማስተማር እርሱን ስታመሰግኑ እነርሱም ይሖዋን ሊያውቁ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ እውቀት የዘላለም ደህንነት ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ዮሐንስ 17:3

10. አምላካችንን የማመስገን ግዴታ እንዳለብን የሚሰማን ለምንድን ነው?

10 ይሖዋን እንድናመሰግነው የሚያደርገን ሌላም ምክንያት አለ። ልዩ ችሎታ ስላለው ጓደኛህ የጠቀስነውን ምሳሌ አስታውስ። ሌሎች ስለ እርሱ ውሸት በመናገር መልካም ስሙን ሲያጠፉ ብትሰማ እርሱን ለማመስገን ከበፊቱ የበለጠ ቆርጠህ አትነሳም? በተመሳሳይ፣ ይሖዋ በዚህ ዓለም ውስጥ ስሙ በእጅጉ ጎድፏል። (ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 12:9) በመሆኑም ለእርሱ ፍቅር ያላቸው ሰዎች ውሸቱን በማጋለጥ ስለ እርሱ እውነቱን የመናገር ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እናንተስ ለይሖዋ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት መግለጽ እንዲሁም ከቀንደኛ ጠላቱ ከዲያብሎስ ይልቅ እርሱ ገዥያችሁ እንዲሆን እንደምትመርጡ ማሳየት ትፈልጋላችሁ? ይሖዋን በማመስገን ይህን ሁሉ ማድረግ ትችላላችሁ። ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ እንዴት? የሚል ይሆናል።

አንዳንድ ወጣቶች ይሖዋን ያመሰገኑት እንዴት ነው?

11. ወጣቶች ይሖዋን በማመስገን ረገድ የተሳካላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶች ይሖዋን በማመስገን ረገድ በአብዛኛው በጣም የተዋጣላቸው እንደሆኑ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ሶርያውያን ማርከው የወሰዷት አንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ነበረች። ይህቺ ልጅ የይሖዋ ነቢይ ስለነበረው ስለ ኤልሳዕ ለእመቤቷ በድፍረት መሠከረች። እርሷ የተናገረችው ነገር ተአምር እንዲፈጸም ምክንያት ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ምሥክርነት እንዲሰጥ አስችሏል። (2 ነገሥት 5:1-17) ኢየሱስም ልጅ እያለ በድፍረት መሥክሯል። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሊሰፍሩ ከሚችሉ ኢየሱስ በልጅነቱ ካደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ይሖዋ የመረጠው አንዱን ብቻ ነው። ይህም ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ እያለ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያሉትን የሃይማኖት አስተማሪዎች በድፍረት ሲጠይቃቸው እንደነበረና እነርሱም ስለ ይሖዋ ቃል በነበረው እውቀት እንደተገረሙ የሚገልጸው ዘገባ ነው።—ሉቃስ 2:46-49

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ቤተ መቅደሱ ውስጥ ምን አድርጓል? ይህስ በሰዎቹ ላይ ምን ዓይነት ስሜት አሳድሯል? (ለ) ኢየሱስ ልጆቹ ያቀረቡትን ምስጋና እንዴት ተመለከተው?

12 ኢየሱስ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላም ልጆች ይሖዋን ለማመስገን እንዲነሳሱ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የተወሰነ ጊዜ አሳልፎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ “ታምራት” ማድረጉን ይናገራል። ይህን ቅዱስ ቦታ የወንበዴዎች ዋሻ ያደረጉትን ሰዎች ከዚያ አባረራቸው። ከዚህ በተጨማሪ ዐይነ ስውሮችንና ሽባዎችን ፈወሰ። በዚያ የነበሩ ሁሉ በተለይ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቹ ይሖዋንና መሲሑን ልጁን ለማመስገን መገፋፋት ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ግን በዚያ ዘመን የነበሩ ብዙዎች እንዲህ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ኢየሱስ በአምላክ የተላከ መሆኑን አውቀዋል፤ ሆኖም የሃይማኖት መሪዎቹን ፈርተው ዝም አሉ። ይሁንና በድፍረት የተናገረ አንድ ቡድን ነበር። እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን [ኢየሱስ] ያደረጋቸውን ታምራትና፣ ‘ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ’ እያሉ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቊጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ ‘እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ’ አሉት።”—ማቴዎስ 21:15, 16፤ ዮሐንስ 12:42

13 እነዚህ ካህናት ኢየሱስ እያመሰገኑት የነበሩትን ልጆች ዝም ያሰኛቸዋል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ታዲያ ዝም አሰኛቸው? በጭራሽ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን? ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’” ኢየሱስና አባቱ ልጆቹ ባቀረቡት ምስጋና እንደተደሰቱ ግልጽ ነው። እነዚህ ልጆች ያደረጉት በዚያ የነበሩ ትልልቅ ሰዎች በሙሉ ሊያደርጉ የሚገባውን ነገር ነው። በዚያ በልጅነት አእምሯቸው ነገሩ ሁሉ በግልጽ ገብቷቸው ነበር። ይህ ሰው ታምራት ሲያደርግ አይተዋል፣ በድፍረትና በእምነት ሲናገር ሰምተዋል እንዲሁም ለአምላክና ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አስተውለዋል። ተስፋ የተደረገበት ‘የዳዊት ልጅ’ መሲሑ መሆኑን በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም አሳይቷል። ልጆቹ ከነበራቸው እምነት የተነሳ አንድ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ የማድረግ ልዩ አጋጣሚ በማግኘት ተባርከዋል።—መዝሙር 8:2

14. ወጣቶች በተፈጥሮ ያገኙት ስጦታ ይሖዋን ለማመስገን የሚያስችላቸው እንዴት ነው?

14 እንደዚህ ካሉት ምሳሌዎች ምን እንማራለን? ወጣቶች ይሖዋን በሚገባ ማመስገን እንደሚችሉ እናያለን። አብዛኛውን ጊዜ እውነትን በግልጽና ሳይጠራጠሩ የመቀበል እንዲሁም እምነታቸውን በቅንነትና በቅንዓት የመግለጽ ተሰጥኦ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ “የጎልማሶች ክብር ብርታታቸው . . . ነው” በማለት በምሳሌ 20:29 ላይ የተጠቀሰው ስጦታም አላቸው። አዎን፣ እናንት ወጣቶች ይሖዋን ለማመስገን የሚያስችላችሁ እንደ ሀብት የሚቆጠር ጥንካሬና ጉልበት አላችሁ። እነዚህን ስጦታዎች ጥሩ አድርጋችሁ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

ይሖዋን ማመስገን የምትችለው እንዴት ነው?

15. ይሖዋን በተገቢው መንገድ ለማመስገን በምን ዓላማ መነሳሳት ይኖርብሃል?

15 ይሖዋን በጥሩ ሁኔታ ለማመስገን መነሻው ልብ ነው። ይሖዋን የምታመሰግነው ሌሎች እንድታደርግ ስለሚፈልጉ ብለህ ብቻ ከሆነ እርሱን በትክክለኛ መንገድ ልታመሰግነው አትችልም። ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ” የሚለው መሆኑን አስታውስ። (ማቴዎስ 22:37) ቃሉን በግልህ በማጥናት ይሖዋን በቅርብ ማወቅ ችለሃል? በዚህ መንገድ ቃሉን ማጥናትህ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርብህ ያደርጋል። ይህን ፍቅር መግለጽ የምትችልበት ትክክለኛ መንገድ እርሱን ማመስገን ነው። ይሖዋን የምታመሰግንበት ግልጽና ጠንካራ ምክንያት ካለህ እርሱን በቅንዓት ለማመስገን ዝግጁ ነህ ማለት ነው።

16, 17. ይሖዋን በማመስገን ረገድ ባሕርያችን ምን ድርሻ ሊኖረው ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

16 ስለዚህ ምን እንደምትናገር ከማሰብህ በፊት ምን እንደምታደርግ አስብ። በኤልሳዕ ዘመን የነበረችው እስራኤላዊቷ ልጃገረድ ሥርዓት የሌላት፣ ሰው የማታከብር ወይም አታላይ ብትሆን ኖሮ ሶርያውያን ጌቶቿ ስለ ይሖዋ ነቢይ የነገረቻቸውን የሚቀበሏት ይመስልሃል? ላይቀበሏት ይችሉ ነበር። በተመሳሳይ ሰው አክባሪ፣ ሐቀኛና ጨዋ መሆንህን ሰዎች ከተመለከቱ አንተን የመስማት አጋጣሚያቸው ሰፊ ይሆናል። (ሮሜ 2:21) አንድ ምሳሌ ተመልከት።

17 በፖርቱጋል የምትኖር አንዲት የ11 ዓመት ልጅ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናዋን በሚያስጥሱ በዓላት ላይ እንድትገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ግፊት ይደረግባት ነበር። ለአስተማሪዋ በበዓሉ ላይ መሳተፍ የማትፈልግበትን ምክንያት በአክብሮት ብታስረዳትም እርሷ ግን አሾፈችባት። በሌላ ጊዜም አስተማሪዋ ሃይማኖቷን በመተቸት ልጅቷን ለማሳፈር ተደጋጋሚ ጥረት አደረገች። ይሁንና ይህች ልጅ ለአስተማሪዋ አክብሮት ማሳየቷን ቀጠለች። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይህች ወጣት እህት የዘወትር አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነች። በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የጥምቀት ሥርዓት ሲከናወን ከተጠማቂዎቹ መካከል አንዷን እንደምታውቃት ተገነዘበች። ሴትየዋ የድሮ አስተማሪዋ ነበረች! ተቃቅፈው ከተላቀሱ በኋላ መምህሯ ለአቅኚዋ፣ ተማሪ እያለች ታሳይ የነበረውን አክብሮት የተሞላበት ባሕርይ ፈጽሞ እንደማትረሳው ነገረቻት። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ምሥራቹን ስትሰብክላት አስተማሪዋ ስለ ቀድሞ ተማሪዋ ባሕርይ ነገረቻት። በዚህም ምክንያት ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ እውነትን ለመቀበል በቃች። አዎን፣ የምታሳዩት ባሕርይ ለይሖዋ ከፍተኛ ምስጋና ሊያመጣ ይችላል!

18. አንድ ወጣት ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ይሖዋ አምላክ ውይይት መጀመር የሚያስፈራው ከሆነ ምን ማድረግ ይችላል?

18 ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ እምነትህ ውይይት ለመጀመር አስቸጋሪ የሚሆንብህ ጊዜ አለ? እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ሆኖም ሌሎች ስለ እምነትህ እንዲጠይቁህ የሚያደርግ ሁኔታ ማመቻቸት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ወደ ትምህርት ቤት ይዞ መምጣት የማይከለከል ከሆነ ጽሑፍ ይዘህ ሄደህ በምሳ ሰዓት ወይም አመቺ በሆነ በሌላ ወቅት ለምን አታነብም? አብረውህ የሚማሩ ልጆች የምታነበው ነገር ምን እንደሆነ ይጠይቁህ ይሆናል። ለጥያቄያቸው መልስ በመስጠት አሊያም ከምታነበው ርዕስ ወይም መጽሐፍ ላይ የወደድከውን ነገር በመንገር ሳታስበው ጥሩ ውይይት ልትጀምሩ ትችላላችሁ። አብረውህ የሚማሩ ልጆች ምን እምነት እንዳላቸው ለማወቅ ጥያቄዎች መጠየቅህን አትዘንጋ። በአክብሮት አዳምጣቸው፤ ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርከውን ነገር አካፍላቸው። በገጽ 29 ላይ የቀረቡት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ብዙ ወጣቶች በትምህርት ቤት አምላክን ያመሰግናሉ። ይህ ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝላቸው ከመሆኑም በላይ ብዙዎች ይሖዋን ማወቅ እንዲችሉ ይረዳል።

19. ወጣቶች ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ይበልጥ ውጤታማ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ይሖዋን ለማመስገን የሚያስችል እጅግ ውጤታማ የሆነ መንገድ ነው። በዚህ አገልግሎት መካፈል ካልጀመርክ ለምን ግብ አድርገህ አትይዘውም? ከቤት ወደ ቤት የምትሄድ ከሆነ ደግሞ ምን ሌሎች ግቦች ማውጣት ትችላለህ? ለምሳሌ ያህል፣ በእያንዳንዱ በር ላይ ተመሳሳይ ነገር ከመናገር ይልቅ ከወላጆችህና ልምድ ካላቸው ከሌሎች ምክር በመጠየቅ ማሻሻል የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆች ለማድረግና ጥናት ለማስጀመር በመጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ መጠቀም የምትችልበትን መንገድ ተማር። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) በእነዚህ መንገዶች ለይሖዋ የምታቀርበው ምስጋና በጨመረ መጠን ውጤታማነትህም በዚያው መጠን ያድጋል፤ እንዲሁም አገልግሎቱን ይበልጥ እየወደድከው ትሄዳለህ።

ይሖዋን ማመስገን መጀመር ያለባችሁ መቼ ነው?

20. ወጣቶች ይሖዋን ለማመስገን ልጅ ነኝ ብለው ማሰብ የሌለባቸው ለምንድን ነው?

20 በዚህ ርዕስ ውስጥ ከቀረቡት ሦስት ጥያቄዎች መካከል የዚህ የመጨረሻ ጥያቄ መልስ በጣም ቀላል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ግልጽ መልስ ተመልከት:- “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።” (መክብብ 12:1) አዎን፣ ይሖዋን ማመስገን የምትጀምሩበት ጊዜ አሁን ነው። “ይሖዋን ለማመስገን ዕድሜዬ ገና አልደረሰም። ምንም ችሎታ የለኝም። እስካድግ ድረስ መቆየት አለብኝ” ማለት በጣም ቀላል ነው። እንዲህ ዓይነት ስሜት ቢሰማህ አንተ የመጀመሪያው ሰው አይደለህም። ለምሳሌ ያህል ወጣቱ ኤርምያስ ለይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና።” ይሖዋ የሚፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ በመናገር ኤርምያስን አበረታታው። (ኤርምያስ 1:6, 7) በተመሳሳይ እኛም ይሖዋን ስናመሰግን እንድንፈራ የሚያደርገን አንዳች ምክንያት የለም። ይሖዋ ሊያስወግደው የማይችለው ምንም ዓይነት ጉዳት ሊደርስብን አይችልም።—መዝሙር 118:6

21, 22. ይሖዋን የሚያመሰግኑ ወጣቶች በጠል የተመሰሉት ለምንድን ነው? እንዲህ መባሉ የሚያበረታታ የሆነውስ ለምንድን ነው?

21 በመሆኑም ወጣቶች፣ ይሖዋን ከማመስገን ወደኋላ አትበሉ ብለን እናሳስባችኋለን! በምድር ዙሪያ በመከናወን ላይ ባለው እጅግ አስፈላጊ ሥራ መሳተፍ የምትችሉበት ከሁሉ የተሻለ ጊዜ ይህ የወጣትነታችሁ ወቅት ነው። እንዲህ ስታደርጉ ይሖዋን የሚያመሰግነው የአጽናፈ ዓለሙ ቤተሰብ ክፍል የመሆን ግሩም መብት ይኖራችኋል። ይሖዋ ይህ ቤተሰብ እናንተንም የሚጨምር በመሆኑ በጣም ይደሰታል። መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት ለይሖዋ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት:- “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤ ከንጋት ማሕፀን፣ በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣ የጐልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ [“እንደ ጠል ያሉ ወጣቶች አብረውህ ይሆናሉ፣” NW]።”—መዝሙር 110:3

22 የማለዳ ፀሐይ ጠል ላይ ሲያርፍ የሚፈጠረውን አንጸባራቂ ውበት የማያደንቅ ማን አለ? ጠል መንፈስ የሚያድስና አንጸባራቂ ከመሆኑም ሌላ ብዛቱም ለቁጥር ያታክታል። ይሖዋም በዚህ አስጨናቂ ዘመን እርሱን በታማኝነት እያወደሳችሁት ያላችሁትን ወጣቶች የሚመለከታችሁ በዚህ መንገድ ነው። ይሖዋን ለማመስገን መምረጣችሁ ልቡን ደስ እንደሚያሰኘው ምንም ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 27:11) በመሆኑም እናንት ወጣቶች ይሖዋን ከማመስገን ወደኋላ አትበሉ!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉን አንዳንድ ዐበይት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

• ወጣቶች ይሖዋን በማመስገን ረገድ የተዋጣላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

• በዛሬው ጊዜ ወጣቶች ይሖዋን ማመስገን የሚችሉት እንዴት ነው?

• ወጣቶች ይሖዋን ማመስገን መጀመር ያለባቸው መቼ ነው? ለምንስ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጓደኛህ ልዩ ችሎታ ቢኖረው ይህን ለሌሎች አታወራለትም?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብረውህ የሚማሩ ልጆች ስለ እምነትህ መስማት ያስደስታቸው ይሆናል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አገልግሎትህን ማሻሻል ከፈለግህ ጥሩ ልምድ ያለው የይሖዋ ምሥክር ሐሳብ እንዲሰጥህ ጠይቅ