በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእስክንድርያው ፊሎ—ቅዱስ ጽሑፉን በመላምት የተነተነ ሰው

የእስክንድርያው ፊሎ—ቅዱስ ጽሑፉን በመላምት የተነተነ ሰው

የእስክንድርያው ፊሎ—ቅዱስ ጽሑፉን በመላምት የተነተነ ሰው

በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ታላቁ እስክንድር ሠራዊቱን ይዞ ወደ ግብጽ ዘመተ። ዓለምን ድል አድርጎ ለመቆጣጠር በስተ ምሥራቅ ጉዞውን ከመቀጠሉ በፊት እስክንድርያ ብሎ የሰየማትን ከተማ ቆረቆረ። በኋላም ከተማዋ የግሪክ ባሕል ማዕከል ሆነች። በ20 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ በዚህችው ከተማ ሌላ ድል አድራጊ የተወለደ ሲሆን የዚህ ሰው መሣሪያ ግን ጎራዴና ጦር ሳይሆን የፍልስፍና አስተሳሰብ ነበር። ይህ ሰው የእስክንድርያው ፊሎ ወይም በትውልዱ አይሁዳዊ በመሆኑ ፊሎ ጁዲየስ ይባላል።

በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተከሰተውን የኢየሩሳሌም ጥፋት ተከትሎ አይሁዶች ወደተለያዩ አገሮች የተበተኑ ሲሆን ብዙዎች በግብጽ ሰፍረው ነበር። ከእነዚህም መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ኑሯቸውን በእስክንድርያ መሠረቱ። ይሁንና በጉርብትና በሚኖሩት አይሁዶችና ግሪኮች መካከል ችግሮች ነበሩ። አይሁዶች የግሪኮችን አማልክት ለማምለክ ፈቃደኛ አልነበሩም፤ ግሪኮች ደግሞ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ይቀልዱ ነበር። ፊሎ በአንድ በኩል የግሪኮችን ትምህርት የተማረ በሌላ በኩል ደግሞ በአይሁድ ሥርዓት ያደገ በመሆኑ በሁለቱ መካከል ያለውን ቅራኔ በሚገባ ያውቃል። የአይሁድ እምነት እውነተኛ ሃይማኖት እንደሆነ ያምን ነበር። ሆኖም ከብዙዎች በተለየ መልኩ ፊሎ አሕዛብ ወደ አምላክ የሚመጡበትን ሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። የአይሁድ እምነት በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ፍላጎት ነበረው።

ለጥንቶቹ ጽሑፎች አዲስ ትርጉም መስጠት

በእስክንድርያ ይኖሩ እንደነበሩት አብዛኞቹ አይሁዶች ሁሉ ፊሎም አፉን የፈታው በግሪክኛ ነበር። ስለዚህ ዋነኛ መማሪያ መጽሐፉ በግሪክኛ የተዘጋጀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሴፕቱጀንት (ወይም የሰብዓ ሊቃናት) ትርጉም ነበር። ፊሎ ሴፕቱጀንትን ሲያጠና ጽሑፉ የፍልስፍና ሐሳቦች መያዙንና ሙሴ ደግሞ “ታላቅ ፈላስፋ” እንደሆነ በእርግጠኝነት አመነ።

ፊሎ ከመነሳቱ ከብዙ ዘመናት በፊት የግሪክ ምሑራን ስለ ሴትና ወንድ አማልክት የሚናገሩትን ታሪኮች (ስለ ጭራቆችና አጋንንት የሚገልጹ ጥንታዊ የግሪኮች አፈ ታሪክ) አምኖ መቀበል ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም እነዚህን የድሮ ታሪኮች በአዲስ መልክ መተንተን ጀመሩ። ስለ ጥንቱ የግሪካውያንና የሮማውያን ዓለም ታሪክ የሚያጠኑት ጄምስ ድረመንድ ምሑራኑ የተጠቀሙበትን ዘዴ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “ፈላስፋው አፈ ታሪኮቹ በውስጣቸው የያዙትን የተሰወረ ትርጉም ለማግኘት ይፈልጋል፤ ከዚያም ደራሲዎቹ የጻፏቸው አስቀያሚና የሚያስቁ ተረቶች በያዟቸው ስሜት ቀስቃሽ ፈሊጣዊ አነጋገሮች ውስጥ አንዳንድ ጥልቅና ግንዛቤ የሚያሰፉ እውነቶች ለማግኘት ጥረት ያደርጋል።” ይህ ዘዴ ውስጠ ወይራ ንግግሮችን መፍታት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ፊሎ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማብራራት የሞከረው በዚህ መንገድ ነው።

በባግስተር የሴፕቱጀንት ትርጉም ላይ “ጌታ አምላክ ለአዳምና ለሚስቱ ከቆዳ ልብስ ሰፍቶ አለበሳቸው” የሚለውን ዘፍጥረት 3:22ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ግሪኮች ልዑል አምላክ ልብስ ይሰፋል መባሉ ክብሩን ዝቅ እንደሚያደርገው ተሰማቸው። ስለዚህ ፊሎ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ምሳሌያዊ አነጋገሮች እንዳሉ በማሰብ እንዲህ አለ:- “የቆዳ ልብስ፣ የሰውነት ቆዳን ማለትም አካላችንን ለማመልከት የተሠራበት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ምክንያቱም አምላክ በመጀመሪያ አእምሮን ሲፈጥር አዳም ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የስሜት ሕዋስ ፈጠረና ሕይወት ብሎ ሰየመው። በመጨረሻም የግድ አስፈላጊ ስለሆነበት አካል ፈጠረና የቆዳ ልብስ በሚል ምሳሌያዊ አገላለጽ ጠራው።” በመሆኑም ፊሎ አምላክ አዳምና ሔዋንን ማልበሱን በጥልቅ ሊታሰብበት የሚገባ የፍልስፍና ጉዳይ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በዔድን ያለው የአትክልት ስፍራ ውኃ ስለሚያገኝበት መንገድና ከዔድን ወጥተው ስለሚፈሱት አራት ወንዞች የሚናገረውን ዘፍጥረት 2:10-14ን ተመልከት። ፊሎ ቃላቱ የያዙትን ስውር ትርጉምና ከመልክአ ምድሩ ባሻገር ያለውን መልእክት ለመረዳት ጥረት አድርጓል። ስለ መሬቱ ሐሳብ ከሰጠ በኋላ “ይህም አንቀጽ ቢሆን ውስጠ ወይራ ትርጉም ሳይኖረው አይቀርም፤ ምክንያቱም አራቱ ወንዞች አራት መልካም ባሕርያትን ያመለክታሉ።” የፊሶን ወንዝ ጥንቃቄን፣ ግዮን ቁም ነገረኛነትን፣ ጤግሮስ ቆራጥነትን፣ ኤፍራጥስ ደግሞ ፍትሕን እንደሚያመለክት ገልጿል። ስለዚህ አንቀጹ የሚገልጸው መልክአ ምድራዊ አካባቢን መሆኑ ቀርቶ ውስጠ ወይራ አነጋገር እንደያዘ ይታሰባል።

ፊሎ ለፍጥረት ዘገባ፣ ቃየን አቤልን እንደገደለ ለሚናገረው ታሪክ፣ በኖኅ ዘመን ለደረሰው ጎርፍ፣ በባቤል ለተከሰተው የቋንቋ መደበላለቅ እንዲሁም በሙሴ ሕግ ውስጥ ለሚገኙት ለአብዛኞቹ መመሪያዎች በውስጠ ወይራ የአነጋገር ዘዴ ትንታኔ ለመስጠት ጥረት አድርጓል። በፊተኛው አንቀጽ ላይ የቀረበው ምሳሌ እንደሚያሳየው ፊሎ አብዛኛውን ጊዜ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የያዘውን ቀጥተኛ ትርጉም የሚቀበል ሲሆን ከዚያም ምሳሌያዊ ትርጉም አለው የሚለው ሐሳቡን እንዲህ በማለት ይከፍታል:- “ምናልባት እነዚህን ነገሮች በውስጠ ወይራ አገላለጽ እንደተነገሩ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል።” ፊሎ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ለምሳሌያዊ ትርጉሞች ከፍተኛ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙት ግልጽ ትርጉም ግን እየተረሳ መምጣቱ የሚያሳዝን ነው።

አምላክ ማን ነው?

ፊሎ አሳማኝ ምሳሌ በመጠቀም የአምላክን መኖር ገልጿል። ስለ መሬት፣ ወንዞች፣ ፕላኔቶችና ከዋክብት ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ደምድሟል:- “ምድር እጅግ የተዋጣለትና ፍጹም እውቀት ያለው አካል የሠራት ከማንኛውም የፍጥረት ሥራ ይልቅ በጣም በሚያምር ሁኔታና በከፍተኛ ጥበብ የተፈጠረች ናት። አምላክ አለ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የተቀበልነው በዚህ መንገድ ነው።” ይህ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነበር።—ሮሜ 1:20

ሆኖም ፊሎ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ባሕርያት ሲገልጽ ከእውነታው በጣም ርቋል። አምላክ “ይህ ነው የሚባል ባሕርይ የሌለው” እንዲሁም “ከመረዳት አቅም በላይ” እንደሆነ ተናግሯል። ፊሎ “የአምላክን ማንነት ወይም ለየት ያሉ ባሕርያቱን ለመመርመር መጣር ከንቱ ልፋት ነው” በማለት አምላክን ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ፋይዳ እንደሌለው ገልጿል። ፊሎ ይህን አመለካከት ያገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን አረማዊ ፈላስፋ ከሆነው ከፕሌቶ ነበር።

ፊሎ፣ አምላክ ከሰው የመረዳት ችሎታ በላይ ስለሆነ እርሱን በግል ስም መጥራት አይቻልም ብሏል። “ስለዚህ ሕያው ለሆነው አምላክ የግል ስም መስጠቱ ተገቢ አይደለም ብሎ ማሰቡ እጅግ ምክንያታዊ ነው” ሲል ተናግሯል። ይህ ከእውነታው በጣም የራቀ ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የግል ስም እንዳለው በግልጽ ይናገራል። ዘፀአት 6:3 (የ1879 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ። በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።” ኢሳይያስ 42:8 ላይ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው” ብሎ መናገሩን ይጠቅሳል። አይሁዳዊው ፊሎ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያወቀ አምላክ ስም የለውም ብሎ ያስተማረው ለምንድን ነው? እርሱ እየተናገረ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጠቀሰው በግልጽ ስለሚታወቀው አምላክ ሳይሆን የግሪክ ፍልስፍና ስለወለደው ስም የለሽና የማይታወቅ አምላክ በመሆኑ ነው።

ነፍስ ምንድን ነች?

ፊሎ ነፍስ ከአካል የተለየች መሆኗን አስተምሯል። ሰው “አካልና ነፍስ ያለው” እንደሆነ ተናግሯል። ነፍስ ልትሞት ትችላለች? ፊሎ የሰጠውን ማብራሪያ ተመልከት:- “በሕይወት በምንኖርበት ጊዜ አካላችን ሕያው ቢሆንም ነፍሳችን ግን ሞታ በመቃብር ያለች ያህል በሰውነታችን ውስጥ ትቀበራለች። [አካላችን] ሲሞት ግን ነፍሳችን ታስራ ከነበረችበት ክፉና ሙት ከሆነው አካል ነጻ ወጥታ ትክክለኛ ሕይወቷን መኖር ትጀምራለች።” በፊሎ አስተሳሰብ የነፍስ ሞት ምሳሌያዊ ነው። ነፍስ ሞታ አትሞትም፤ ያለመሞት ባሕርይ አላት።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ያስተምራል? ዘፍጥረት 2:7 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሰዎች ነፍስ የላቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እነርሱ ራሳቸው ነፍስ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ አትሞትም ብሎ አያስተምርም። ሕዝቅኤል 18:4 እንዲህ ይላል:- “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” ከእነዚህ ጥቅሶች በመነሳት ሰው ነፍስ ነው የሚል ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን። ስለዚህ አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱም ሞተ ማለት ነው።—ዘፍጥረት 19:19 የ1954 ትርጉም a

ፊሎ ከሞተ በኋላ አይሁዶች ቦታ ሳይሰጡት ቢቀሩም ሕዝበ ክርስትና ግን ተቀብላዋለች። ዩሴቢየስና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ፊሎ ክርስትናን ተቀብሏል የሚል እምነት አላቸው። ጄሮም ከቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል እንደ አንዱ ይቆጥረዋል። የፊሎ ጽሑፎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረጉት አይሁዳውያን ሳይሆኑ ከሃዲ ክርስቲያኖች ናቸው።

የፊሎ ጽሑፎች ታላቅ ሃይማኖታዊ ለውጥ አምጥተዋል። የእርሱ ተጽዕኖ ክርስቲያን ነን ባዮች ነፍስ አትሞትም የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ መሠረተ ትምህርት እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል። እንዲሁም ፊሎ ስለ ወልድ (ወይም ቃል) ያስተማረው ትምህርት ከሃዲዋ ክርስትና ለተቀበለችው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ቀኖና ይኸውም ለሥላሴ ትምህርት መገኘት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አትታለሉ

ፊሎ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ባደረገው ጥናት “ከተራው ቋንቋ በስተጀርባ የሚገኘው ውስጠ ወይራ ትርጉም ያለው የትኛውም ሐሳብ ሳይብራራ እንዳይታለፍ” ለማድረግ ተጠንቅቆ ነበር። ይሁን እንጂ በዘዳግም 4:2 ላይ እንደምናነበው ሙሴ የአምላክን ሕግ በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከእርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቁ።” ፊሎ ላይ ላዩን ሲታይ ጥሩ ዓላማ የነበረው ቢሆንም በርካታ መላምቶችን በመደርደር በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የያዘውን ግልጽ መመሪያ አድበስብሶታል።

ሐዋርያው ጴጥሮስ “ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ . . . በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:16) ፊሎ ካዘጋጃቸው ጽሑፎች በተለየ ጴጥሮስ ለጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የጻፈው መልእክት በተጨባጭ ሐቅና የአምላክ መንፈስ በሚሰጠው አመራር ይኸውም ወደ እውነት ሁሉ በመራቸው “የእውነት መንፈስ” ላይ የተመሠረተ ነበር።—ዮሐንስ 16:13

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውን አምላክ ማምለክ የምትፈልግ ከሆነ በሰው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ሳይሆን አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት ይኖርብሃል። ስለ ይሖዋና ስለ ፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አለብህ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በቅን ልቦና ለመማር ትሕትና ሊኖርህ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ ትክክለኛ ዝንባሌ ካጠናህ “በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን” ማወቅ ትችላለህ። እንዲህ በማድረግ የአምላክ ቃል ‘ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆነህ እንድትገኝ’ ሊረዳህ እንደሚችል ትገነዘባለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ነፍስን በተመለከተ በ1910 የታተመው ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “አካል ከፈራረሰ በኋላ ነፍስ መኖሯን ትቀጥላለች የሚለው እምነት የፍልስፍና ወይም የሃይማኖታዊ ትምህርት መላምት እንጂ መሠረታዊ እምነት አይደለም። በመሆኑም ቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ በየትኛውም ቦታ በግልጽ ሰፍሮ አይገኝም።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፊሎ የኖረባት ከተማ

ፊሎ የኖረውም ሆነ የሥራ ዘመኑን ያሳለፈው በግብጿ እስክንድርያ ነው። ይህች ከተማ ለበርካታ ዘመናት በመጻሕፍት ማከማቻነትና ምሑራዊ ውይይቶችን በማስተናገድ ረገድ የዓለማችን መዲና ነበረች።

ተማሪዎች በከተማዋ በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በታዋቂ ምሑራን የመማር አጋጣሚ አግኝተዋል። በእስክንድርያ የሚገኘው ቤተ መጻሕፍት በዓለም ዙሪያ የታወቀ ነበር። የቤተ መጻሕፍቱ ኃላፊዎች የማንኛውንም ጽሑፍ ቅጂ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ስለነበር ቤተ መጻሕፍቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ስብስብ ነበረው።

ከጊዜ በኋላ እስክንድርያ በዓለም ዙሪያ የነበራት ክብር እየከሰመ የሄደ ከመሆኑም ሌላ የጽሑፍ ክምችቱም ቀስ በቀስ ተመናመነ። የሮም ንጉሠ ነገሥታት ለራሳቸው ከተማ ቅድሚያ በመስጠታቸው የባሕል ማዕከል የነበረው ቦታ ወደ አውሮፓ ተሸጋገረ። እስክንድርያ ያከተመላት በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወራሪዎች ከተማዋን ድል ካደረጓት በኋላ ነበር። በዛሬው ጊዜም እንኳ የታሪክ ምሑራን የዚህ ዝነኛ ቤተ መጻሕፍት መውደም የሚያንገበግባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም ሥልጣኔ በ1,000 ዓመት የኋሊት እንደሄደ ይሰማቸዋል።

[ምንጭ]

L. Chapons/Illustrirte Familien-Bibel nach der deutschen Uebersetzung Dr. Martin Luthers

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዛሬም መላምታዊ ትንታኔዎች ይሰጣሉ

አብዛኛውን ጊዜ ውስጠ ወይራ የንግግር ዘይቤ “የሰውን ልጅ ሕልውና ምሳሌያዊ በሆኑ ልብ ወለድ ገጸ ባሕርያትና በእውነት ላይ በተመሠረቱ ድርጊቶች ወይም ጠቅለል ብለው በተቀመጡ ሐሳቦች የሚገልጽ አነጋገር” ነው። ውስጠ ወይራ አገላለጾችን የሚጠቀሙ ዘገባዎች ስውር የሆኑና ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘሉ መልእክቶችን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የሚገልጹ እንደሆኑ ይነገራል። የእስክንድርያው ፊሎ እንዳደረገው ሁሉ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት መላምታዊ ትንታኔዎችን ይሰጣሉ።

ከፍጥረት ዘመን አንስቶ የባቤል ግንብ በተሠራበት ቦታ ሰዎች መበታተናቸውን ስለሚገልጸው የሰው ልጅ ታሪክ ዘፍጥረት ምዕራፍ 1-11 ላይ የሠፈረውን ዘገባ ተመልከት። ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል የተባለው የካቶሊክ ትርጉም ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ጽሑፉን ጠብቀው ማቆየት የነበረባቸው እስራኤላውያን በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሠፈረውን እውነት መረዳት እንዲችሉ በዚያ ወቅት የነበሩ ሰዎች የሚያውቋቸውን ነገሮች መጠቀም የግድ ነው። በዚህም ምክንያት በጽሑፉ ላይ የተገለጹትን እውነቶች ከምሳሌያዊ ልባሳቸው ሙሉ በሙሉ ለይተን ልናያቸው ይገባል።” ይህም ዘፍጥረት ምዕራፍ 1-11ን ቃል በቃል መረዳት የለብንም የማለት ያህል ነው። ልብስ ሰውነትን እንደሚሸፍን ሁሉ ቃላቱም ጥልቅ ትርጉም ያለውን ሐሳብ ይሸፍናሉ።

ኢየሱስ ግን በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ቃል በቃል መወሰድ እንዳለባቸው አስተምሯል። (ማቴዎስ 19:4-6፤ 24:37-39) ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስም ተመሳሳይ ሐሳብ ተናግረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:24-26፤ 2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:6, 7) ልበ ቅን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክ ቃል ከያዘው አጠቃላይ ሐሳብ ጋር የማይስማሙ ማብራሪያዎችን አይቀበሉም።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእስክንድርያው ትልቅ የወደብ መብራት

[ምንጭ]

Archives Charmet/Bridgeman Art Library