በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥንት ክርስትና ተስፋፍቶ በነበረባት አገር የተገኘ እድገት

ጥንት ክርስትና ተስፋፍቶ በነበረባት አገር የተገኘ እድገት

ጥንት ክርስትና ተስፋፍቶ በነበረባት አገር የተገኘ እድገት

የቦት ጫማ ቅርጽ ባላትና ባህረ ገብ መሬት በሆነችው በኢጣሊያ የተፈጸሙት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክንውኖች በዓለም ታሪክ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ማራኪ በሆነው መልክአ ምድሯ፣ በጣፋጭ ምግቦቿ እንዲሁም በታዋቂ የጥበብ ሥራዎቿ ተስበው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ወደ እርሷ ይጎርፋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኢጣሊያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እድገት ያደረገባት ቦታ ናት።

እውነተኛው ክርስትና በወቅቱ የዓለም ኃያል የነበረችው የኢጣሊያ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሮም የደረሰው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስትናን የተቀበሉት አይሁድና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ ከኢየሩሳሌም ወደ አገራቸው በተመለሱበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢጣሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘው በ59 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ነው። በፑቲዮሉስ የባህር ዳርቻ የእምነት ‘ወንድሞችን አግኝቷል።’—የሐዋርያት ሥራ 2:5-11፤ 28:11-16

ኢየሱስና ሐዋርያት እንደተነበዩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ከሃዲዎች እውነተኛውን ክርስትና ቀስ በቀስ ትተው መውጣት ጀምረው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት እውነተኛዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመንግሥቱን ምሥራች ኢጣሊያን ጨምሮ በመላው ዓለም እየሰበኩ ነው።—ማቴዎስ 13:36-43፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3-8፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3

ተስፋ አስቆራጭ ጅምር

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ይጠራሉ) የሚያካሂዱትን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1891 አንዳንድ የኢጣሊያ ከተማዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጎብኝቶ ነበር። የጉብኝቱ ውጤት ያን ያህል ተስፋ ሰጪ እንዳልነበረ ሲገልጽ:- “በኢጣሊያ ውጤት እናገኛለን ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርገን ነገር አላገኘንም” ብሏል። በ1910 የበልግ ወራት ወንድም ራስል ወደ ኢጣሊያ ተመልሶ በሮም በሚገኝ አንድ የስፖርት ማዕከል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር አቀረበ። ውጤቱስ ምን ነበር? “ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ስብሰባው ተስፋ አስቆራጭ ነበር” ብሏል።

እርግጥ ነው፣ ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኢጣሊያ የምሥራቹ ስብከት ያስገኘው ውጤት አዝጋሚ ነበር፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች በፋሽስታዊ አምባገነኖች ይደርስባቸው የነበረው ስደት ነው። በወቅቱ በአገሪቱ ይገኙ የነበሩት ምሥክሮች ቁጥር ከ150 የማይበልጥ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኞቹ እውነትን በሌላ አገር ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ወይም ከጓደኞቻቸው የሰሙ ነበሩ።

አስደናቂ እድገት

ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በርካታ ሚስዮናውያን ወደ ኢጣሊያ ተላኩ። ሆኖም በመንግሥት ቤተ መዛግብት የተገኙት ደብዳቤዎች እንደሚያመለክቱት የቫቲካን ከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች መንግሥት ሚስዮናውያኑን ከአገር እንዲያስወጣቸው ጠይቀው ነበር። በዚህም ምክንያት ከጥቂቶች በስተቀር ሚስዮናውያኑ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ።

እንቅፋቶች ቢኖሩም በኢጣሊያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ የአምልኮ “ተራራ” መጉረፍ ጀመሩ። (ኢሳይያስ 2:2-4) ባለፉት ዓመታት ምሥክሮቹ ያደረጉት እድገት አስደናቂ ነው። በ2004 ከፍተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎች ቁጥር 233,527 የደረሰ ሲሆን ይህም ማለት ከ248 ሰዎች መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክር ነበር። እንዲሁም በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 433,242 ያህል ሰዎች ተገኝተዋል። በአገሪቱ 3,049 ጉባኤዎች ምቾት ባላቸው የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ስብሰባቸውን ያካሂዳሉ። በቅርቡ በተለይ አንዳንድ የማኅበረሰቡ ክፍሎች በብዛት እውነትን ተቀብለዋል።

በበርካታ ቋንቋዎች መስበክ

ብዙ ሰዎች ከአፍሪካ፣ ከእስያ እንዲሁም ከምሥራቅ አውሮፓ ሥራ ወይም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ አሊያም አስከፊ ሁኔታዎችን ሸሽተው ወደ ኢጣሊያ በስደት ይመጣሉ። እነዚህን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንፈሳዊ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

በኢጣሊያ የሚኖሩ ብዙ ምሥክሮች እንደ ሲንሃላ፣ ቤንጋሊ፣ ታጋሎግ፣ ቻይንኛ፣ የአልባኒያ ቋንቋ፣ አማርኛ፣ አረብኛ እና ፑንጃቢ የመሳሰሉትን ከባድ ቋንቋዎች ለመልመድ ጥረት እያደረጉ ነው። ለእነዚህ በፈቃደኝነት ራሳቸውን ላቀረቡ ምሥክሮች ከ2001 ጀምሮ በውጭ አገር ቋንቋ መስበክ እንዲችሉ የቋንቋ ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ለ3,711 ምሥክሮች 79 ኮርሶች በ17 ቋንቋዎች ተሰጥተዋል። በዚህም የተነሳ አዳዲስ ጉባኤዎችና ቡድኖችን በማቋቋምና የነበሩትንም በማጠናከር በ25 ቋንቋዎች የሚካሄዱ 146 ጉባኤዎችና 274 ቡድኖች ማግኘት ተችሏል። ይህም ብዙ ቅን የሆኑ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዲጀምሩ ምክንያት ሆኗል። ውጤቱም ቢሆን ከተጠበቀው በላይ ነው።

ጆርጅ ከሕንድ የመጣ የማላያላም ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን አንድ የይሖዋ ምሥክር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረዋል። ምንም እንኳ ከፍተኛ የሥራ ጫና ያለበት ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። ከጥቂት ቀናት በኋላ የጆርጅ ጓደኛ የሆነውና የፑንጃቢ ቋንቋ የሚናገረው ጊል በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ጊል ደግሞ ዴቪድ የተባለውን የቴሉጉ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሕንዳዊ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አስተዋወቀው። ብዙም ሳይቆይ ዴቪድ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ሶኒ እና ሹባሽ የሚባሉ ሁለት ሕንዳውያን ከዴቪድ ጋር አንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የማራቲ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ዳሊፕ ለይሖዋ ምሥክሮች ስልክ ደውሎ “እኔ የጆርጅ ጓደኛ ነኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ልታስተምሩኝ ትችላላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ሌላው ደግሞ የታሚል ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ሱሚት ሲሆን እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በመጨረሻም ሌላኛው የጆርጅ ጓደኛ ስልክ በመደወል መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደሚፈልግ ተናገረ። ቀጥሎ ደግሞ ጆርጅ፣ ማክስ የተባለ ወጣት ወደ መንግሥት አዳራሽ ይዞ የመጣ ሲሆን እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑት ጠየቀ። በአሁኑ ወቅት ስድስት ለሚያክሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተመራላቸው ሲሆን አራቱን ጥናት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ጥናቱ የሚካሄደው በእንግሊዝኛ ቢሆንም በሂንዲ፣ በማላያላም፣ በማራቲ፣ በታሚል፣ በቴሉጉ፣ በኡርዱ እና በፑንጃቢ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይጠቀሙባቸዋል።

መስማት የተሳናቸው ምሥራቹን “ሰሙ”

በኢጣሊያ ከ90,000 በላይ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይገኛሉ። በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ትኩረታቸውን እነዚህን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወደ ማስተማር ዘወር አደረጉ። በቅድሚያ አንዳንድ መስማት የተሳናቸው ምሥክሮች በዚህ ረገድ እርዳታ ለማበርከት ለሚፈልጉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የኢጣሊያን የምልክት ቋንቋ አስተማሯቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት አሳዩ። በዛሬው ጊዜ ከ1,400 የሚበልጡ የኢጣሊያን የምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ ሰዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በኢጣሊያ የምልክት ቋንቋ የሚደረጉ አሥራ አምስት ጉባኤዎችና 52 ቡድኖች አሉ።

መጀመሪያ ላይ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መስበክ ባብዛኛው በግለሰብ ምሥክሮች ጥረት ላይ የተመካ ነበር። ይሁን እንጂ በኢጣሊያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በ1978 መስማት ለተሳናቸው ትላልቅ ስብሰባዎችን ማዘጋጀት ጀመረ። በዚያው ዓመት በግንቦት ወር፣ በሚላን በሚደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ መስማት ለተሳናቸው ፕሮግራም እንደተዘጋጀ የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። መስማት ለተሳናቸው የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ የተደረገው የካቲት 1979 ሚላን በሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነበረ።

ቅርንጫፍ ቢሮው መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ሲል ብዙ የምሥራቹ ሰባኪዎች ያላቸውን የምልክት ቋንቋ ችሎታ እንዲያዳብሩ እያበረታታቸው ነው። ከ1995 ጀምሮ ልዩ አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን) መስማት የተሳናቸውን የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት እንዲያሠለጥኑና ስብሰባዎችን እንዲያደራጁ ወደ ተለያዩ ቡድኖች ተልከዋል። ፕሮግራሙን በደንብ መከታተል እንዲችሉ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የቪዲዮ መሣሪያዎች ያሏቸው ሦስት የስብሰባ አዳራሾች ተዘጋጅተዋል። በተጨማሪም መስማት ለተሳናቸው መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በቪዲዮ ካሴቶች ይገኛሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚጥሩ የታዘቡ ሰዎችም አሉ። የኢጣሊያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር የሚያሳትመው ፓሮሌ ኤ ሴኚ የተባለው መጽሔት ከአንድ የካቶሊክ ጳጳስ የተላከለትን ደብዳቤ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “መስማት የተሳነው ሰው ሁልጊዜም ትኩረት ስለሚሻ የመስማት ችሎታን ማጣት ከባድ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቻውን ያለ ችግር ቢመጣ እንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀርበውን ስብከት ወይም መዝሙር መከታተል እንዲችል የሚተረጉምለት ሰው ያስፈልገዋል።” መጽሔቱ በመቀጠል “ጳጳሱ ቤተ ክርስቲያን ለአካል ጉዳተኞች ያደረገችው ዝግጅት አለመኖሩን ከማመናቸውም በላይ መስማት ለተሳናቸው ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የተሻለ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል” ብሏል።

ምሥራቹ ለእስረኞች ተሰበከ

አንድ ሰው እስር ቤት ውስጥ እያለም ነጻ መውጣት ይችላል? አዎን፣ ምክንያቱም የአምላክ ቃል የሚቀበሉትንና ምክሩን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ‘ነጻ የማውጣት’ ኃይል አለው። ኢየሱስ “ለታሰሩት” የሰበከው መልእክት ከኃጢአትና ከሐሰት ሃይማኖት ነጻ የሚያወጣቸው ነበር። (ዮሐንስ 8:32፤ ሉቃስ 4:16-19) በኢጣሊያ፣ በእስር ቤቶች ውስጥ በመስበክ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል። ወደ 400 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክር አገልጋዮች ለእስረኞቹ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲሰጡ ከመንግሥት ፈቃድ አግኝተዋል። ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ይህን ፈቃድ በመጠየቅና በማግኘት ረገድ የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሌሎች የሚደርሰው ባልተጠበቀ መንገድ ይሆናል። እስረኞቹ እርስ በርስ የይሖዋ ምሥክሮች እያካሄዱት ስላለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ይነጋገራሉ። ከዚያም ከእነዚህ እስረኞች መካከል አንዳንዶቹ ምሥክሮቹ እንዲያናግሯቸው ጥያቄ ያቀርባሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከወኅኒ ቤት ውጭ ያሉ ዘመዶቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጀምሩና እነርሱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ያበረታቷቸዋል። በነፍስ ግድያ አሊያም ሌላ የከፋ ወንጀል በመሥራታቸው ምክንያት ዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው አንዳንዶች ኃጢአታቸውን በመናዘዝ በሕይወታቸው ውስጥ አስደናቂ ለውጥ ያደርጋሉ። ይህም ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ያስችላቸዋል።

በብዙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች ለመስጠት፣ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር እንዲረዱ ተብለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የቪዲዮ ካሴቶች ለማሳየት ዝግጅት ተደርጓል። አብዛኛውን ጊዜ ቁጥራቸው በዛ ያለ እስረኞች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በወኅኒ ቤቶች ለሚገኙት ሰዎች ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ለመስጠት የሕግ ታራሚዎቹን ሊጠቅሙ የሚችሉ መጽሔቶችን በብዛት አሰራጭተዋል። ከእነዚህ መካከል “እስረኞች ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ይቻላል?” የሚል ርዕስ ያለው የግንቦት 2001 ንቁ! እና “በቤተሰብ ውስጥ አደገኛ ዕጽ የሚወስድ ካለ ምን ማድረግ ይቻላል?” የሚል ርዕስ የያዘው የሰኔ 2003 ንቁ! ይገኙበታል። በሺህ የሚቆጠሩ ቅጂዎች በእስረኞች እጅ እንዲገቡ ተደርጓል። በውጤቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕግ ታራሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀምሮላቸዋል። አንዳንድ የወኅኒ ቤት ጠባቂዎችም ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጥሩ ፍላጎት አሳይተዋል።

ኮስታንቲኖ የተባለ የሕግ ታራሚ ከባለ ሥልጣናት ፈቃድ ስላገኘ በሳን ሬሞ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ 138 የሚያክሉ የአካባቢው ምሥክሮች በተገኙበት ተጠምቋል። ኮስታንቲኖ ፊቱ ላይ የደስታ ስሜት እየተነበበ “በዚያ የተገኙ ሁሉ ፍቅራቸውን ገለጹልኝ” በማለት ተናግሯል። በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው የወኅኒ ቤቱ ተቆጣጣሪ እንዲህ ብለዋል:- “ፈቃድ የሰጠነው . . . በከፍተኛ ደስታ ነበር። የአንድ እስረኛ ማኅበራዊና የግል ሕይወት እንዲሁም መንፈሳዊነት እንዲሻሻል የሚያደርግ ማንኛውም ነገር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።” የኮስታንቲኖ ባለቤትና ሴት ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ሕይወቱን እንዴት እንደለወጠው ሲመለከቱ በጣም ተደንቀዋል። “ያደረገው ለውጥ በእርሱ እንድንኮራ አድርጎናል። ሰላማዊ ከመሆኑ ባሻገር ለእኛ ያለው አሳቢነት እየጨመረ ሄዷል። በእርሱ ላይ ያለን እምነትና ለእርሱ ያለን አክብሮት ጨምሯል” ብለዋል። እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩ ሲሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ ይገኛሉ።

ሰርጆ በሌብነት፣ በመሣሪያ አስፈራርቶ በመዝረፍ፣ በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች አዘዋዋሪነት እንዲሁም በነፍስ ግድያ ወንጀል በመከሰሱ እስከ 2024 ድረስ እንዲታሰር ተፈርዶበት ወኅኒ የወረደ ሰው ነው። ለሦስት ዓመታት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ካጠና በኋላ ግን በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ በማድረግ ለመጠመቅ ወሰነ። በኤልባ ደሴት በሚገኘው በፖርቶ አትሱሮ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከተጠመቁት እስረኞች መካከል 15ኛው ነው። የጥምቀት ሥርዓቱ የተከናወነው በወኅኒ ቤቱ የስፖርት ሜዳ ላይ ተንቀሳቃሽ ገንዳ በመጠቀም ሲሆን ብዙ እስረኞችም ተገኝተዋል።

ሊዮናርዶ ለ20 ዓመታት የተፈረደበት እስረኛ ሲሆን በፓርማ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ለመጠመቅ እንዲችል ልዩ ፈቃድ አግኝቷል። ሊዮናርዶ በአካባቢው ከሚታተም አንድ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የወሰነው ከጨለማው የወኅኒ ቤት ሕይወት ለመውጣት ሳይሆን በጣም አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ብሎ መሆኑን ግልጽ ማድረግ” እንደፈለገ ተናግሯል። ሊዮናርዶ በመቀጠልም “ሕይወቴ የተበላሸ ነበር፣ አሁን ያንን እርግፍ አድርጌ በመተው ለውጥ አድርጌያለሁ። ይህ ግን በአንድ ጀምበር ያደረግሁት ለውጥ አይደለም። ወደፊትም ቢሆን ትክክል የሆነውን ማድረጌን መቀጠል አለብኝ” ብሏል።

ሳልቫቶሬ በነፍስ ግድያ ወንጀል በመከሰሱ በስፔልቶ በሚገኝ ከፍተኛ ቁጥጥር በሚደረግበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ያለ ሰው ነው። የተጠመቀው እዚያው እስር ቤት ውስጥ ሲሆን ያደረገው ውሳኔም ብዙዎችን አስደንቋል። የወኅኒ ቤቱ ኃላፊ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የሕግ ታራሚዎች የባሕርይ ለውጥ በማድረግ ለሁሉም ሰው ጥሩ እንዲሆኑ የሚረዳቸው ምርጫ ማድረጋቸው ማኅበራዊ ጠቀሜታ ስላለው ሊበረታታ የሚገባ ነገር ሲሆን ይህም ለእስረኞችም ሆነ ለሌላው ማኅበረሰብ ጥቅም ያለው ነገር ነው።” የሳልቫቶሬ ሚስትና ሴት ልጁ ለውጡን ካዩ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረዋል። በተጨማሪም ሳልቫቶሬ የመሰከረለት ሌላ እስረኛ የተጠመቀ የይሖዋ አገልጋይ ሆኗል።

በጥንት ዘመን ክርስትና ከተስፋፋባቸው አገሮች አንዷ ኢጣሊያ ነበረች። (የሐዋርያት ሥራ 2:10፤ ሮሜ 1:7) ጳውሎስና ክርስቲያን ባልደረቦቹ ምሥራቹን ለመስበክ በደከሙበት አገር ላይ በዘመናችንም ቢሆን መንፈሳዊ እድገት እየተገኘ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 23:11፤ 28:14-16

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኢጣሊያ

ሮም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቢቶንቶ የሚገኘው የትልልቅ ስብሰባዎች አዳራሽና በሮም ያለው የኢጣሊያ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስረኞች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት ‘ነጻ እየወጡ’ ነው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንት ክርስትና ተስፋፍቶ የነበረባት አገር በመንፈሳዊ እድገት ማድረጓን ቀጥላለች