በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው”

“ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው”

“ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው”

ወፎች ማለዳ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ለአፍታ ሲንጫጩ ይቆዩና ምግባቸውን ለመፈለግ በረው ይሄዳሉ። ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ደግሞ ወደ ጎጆአቸው ይመለሱና አሁንም ትንሽ ተንጫጭተው ያሸልባሉ። የመራቢያ ወቅቶችን ጠብቀው እንቁላል ይጥላሉ እንዲሁም ጫጩቶቻቸውን ያሳድጋሉ። ሌሎች እንስሳትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዑደት ይከተላሉ።

እኛ ሰዎች ግን ከዚህ የተለየን ነን። እርግጥ ነው እንመገባለን፣ እንተኛለን እንዲሁም መሰሎቻችንን እንተካለን፤ ሆኖም ብዙዎቻችን በእነዚህ ነገሮች ብቻ አንረካም። ወደዚህ ዓለም የመጣነው ለምን እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። እንዲሁም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት እንሻለን። በተጨማሪም መጪውን ጊዜ በተስፋ መጠበቅ እንፈልጋለን። እነዚህ ውስጣዊ ፍላጎቶች የሰውን ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ የሚያደርገውን አንድ ባሕርይ ይጠቁሙናል፤ እኛ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ይኸውም መንፈሳዊ ነገሮችን የመፈለግና የመረዳት ችሎታ አለን።

በአምላክ መልክ ተፈጥረናል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ተፈጥሯዊ ፍላጎት ሊያድርበት የቻለው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ፣ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:27) “በእግዚአብሔር መልክ” ተፈጥረናል ሲባል በኃጢአትና ባለፍጽምና ምክንያት የጎደፍን ብንሆንም እንኳ የአምላክን አንዳንድ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን ማለት ነው። (ሮሜ 5:12) ለአብነት ያህል፣ የፈጠራ ችሎታ አለን። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጥበብን እናንጸባርቃለን፣ የፍትሕ ስሜት አለን፤ እንዲሁም አንዳችን ለሌላው የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እስክናደርግ ድረስ ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ከዚህም በላይ ያለፈውን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብለን መቃኘትና ስለ ወደፊቱ ማቀድ እንችላለን።—ምሳሌ 4:7፤ መክብብ 3:1, 11፤ ሚክያስ 6:8፤ ዮሐንስ 13:34፤ 1 ዮሐንስ 4:8

አምላክን ለማምለክ ያለን ተፈጥሯዊ ፍላጎት መንፈሳዊ ነገሮችን የመፈለግና የመረዳት ችሎታ እንዳለን በግልጽ ያሳያል። ከፈጣሪያችን ጋር የቅርብ ዝምድና በመመሥረት ይህን ፍላጎት እስካላሟላን ድረስ እውነተኛና ዘላቂ ደስታ አናገኝም። ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 NW) ሆኖም ይህን ፍላጎት ማሟላት የሚኖርብን መንፈሳዊ እውነትን በመመገብ ነው፤ ይህም ስለ አምላክ፣ ስለ አቋም ደረጃዎቹና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የተገለጹትን እውነቶች ይጨምራል። ታዲያ መንፈሳዊ እውነት ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው።

“ቃልህ እውነት ነው”

ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የጳውሎስ ሐሳብ ኢየሱስ ለአምላክ ሲጸልይ ከተናገራቸው “ቃልህ እውነት ነው” ከሚሉት ቃላት ጋር ይስማማል። በዛሬው ጊዜ፣ ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ እናውቃለን፤ እምነታችንም ሆነ አቋማችን ከዚህ ቃል ጋር መስማማቱን ለማወቅ መጣራችን ጥበብ ይሆናል።—ዮሐንስ 17:17

የምናምንባቸውን ነገሮች ከአምላክ ቃል ጋር በማነጻጸር፣ የጳውሎስ ትምህርቶች ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር መስማማታቸውን ለማረጋገጥ ይጥሩ የነበሩትን የጥንት የቤርያ ሰዎች ምሳሌ እንኮርጅ። ሉቃስ እነዚህን ሰዎች ከመንቀፍ ይልቅ ላሳዩት ዝንባሌ አወድሷቸዋል። “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጒጒት ተቀብለዋል” ሲል ጽፏል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) ከዚህ አኳያ፣ እርስ በርስ የሚቃረኑ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርቶች በተስፋፉበት በአሁኑ ወቅት አስተዋይ የነበሩትን የቤርያ ሰዎች ምሳሌ መከተላችን አስፈላጊ ነው።

መንፈሳዊ እውነትን ለመለየት የምንችልበት ሌላው መንገድ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያሳደረውን ተጽዕኖ በመመልከት ነው። (ማቴዎስ 7:17) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምቶ መኖሩ የተሻለ ባል ወይም የተሻለ አባት እንዲሆን ያደርገዋል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ የተሻለች ሚስት ወይም የተሻለች እናት እንድትሆን ያስችላታል። ይህም ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለእያንዳንዳቸው እርካታ ያስገኝላቸዋል። ኢየሱስ “ብፁዓንስ [“ደስተኞችስ፣” NW] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” ሲል ተናግሯል።—ሉቃስ 11:28

እነዚህ የኢየሱስ ቃላት በሰማይ የሚኖረው አባቱ ለጥንት እስራኤላውያን የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሱናል:- “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።” (ኢሳይያስ 48:17, 18) በጎነትንና ጽድቅን የሚወዱ ሁሉ በዚህ ፍቅራዊ ግብዣ ስሜታቸው እንደሚነካ አያጠራጥርም!

አንዳንዶች ‘ጆሮአቸውን የሚኮረኩርላቸው’ ይፈልጋሉ

አምላክ ለእስራኤላውያን በኢሳይያስ በኩል ይህን ዓይነት ልባዊ ግብዣ ያቀረበው በሃይማኖታዊ ውሸቶች ተታልለው ስለነበር ነው። (መዝሙር 106:35-40) እኛም እንዲህ በመሰሉ ውሸቶች እንዳንታለል መጠንቀቅ ይገባናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ነን ስለሚሉ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው [“ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው፣” NW] በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

ሃይማኖታዊ መሪዎች የሰዎችን ጆሮ የሚኮረኩሩት ዝሙት፣ ምንዝር፣ ግብረ ሰዶምና ስካር የመሳሰሉት መጥፎ ድርጊቶች ሲፈጸሙ አይተው እንዳላዩ በማለፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን የሚደግፉም ሆኑ የሚያደርጉ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ” በግልጽ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ሮሜ 1:24-32

እርግጥ ነው፣ በተለይ ፌዝን ተቋቁሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ድፍረት ይጠይቃል፤ ሆኖም ማድረግ ይቻላል። ቀደም ሲል የዕፅ ሱሰኛ፣ ሰካራም፣ ወሮበላ፣ ሌባ እንዲሁም ሐሰተኛ የነበሩ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ይገኛሉ። የሚገርመው ግን፣ አሁን የአምላክን ቃል ተግባራዊ በማድረግና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ‘ለጌታ እንደሚገባ ለመኖር’ ሕይወታቸውን ለውጠዋል። (ቆላስይስ 1:9, 10፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11) በተጨማሪም ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረታቸው ውስጣዊ ሰላም እንዲሁም ቀጥለን እንደምንመለከተው መጪውን ጊዜ በተመለከተ እውነተኛ ተስፋ አስገኝቶላቸዋል።

የመንግሥቱ ተስፋ

ታዛዥ ሰዎች ዘላቂ ሰላም እንደሚያገኙ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው። ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብሏል። (ማቴዎስ 6:10) አዎን፣ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የምታደርገው የአምላክ መንግሥት ብቻ ናት። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ሉዓላዊነት በምድር ላይ የሚረጋገጠው በክርስቶስ በምትመራው በዚህች ሰማያዊ መንግሥት በኩል ስለሆነ ነው።—መዝሙር 2:7-12፤ ዳንኤል 7:13, 14

ኢየሱስ የዚህች ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ተብትቦ ከያዛቸው ከአዳም ኃጢአትና ውጤቶቹ ከሆኑት ሕመምና ሞት በተጨማሪ ከማንኛውም ዓይነት ባርነት ያላቅቃቸዋል። ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ . . . እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”

በመላው ምድር ላይ ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል። ይህ እንደሚሆን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ኢሳይያስ 11:9 ምክንያቱን ሲገልጽ “[የመንግሥቲቱ ዜጎች] በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” በማለት ይናገራል። አዎን፤ በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ይኖረዋል፤ ለእርሱም ይታዘዛል። ይህ የወደፊት ተስፋ ልብህን ደስ አያሰኘውም? ከሆነ፣ ውድ የሆነውን ‘የእግዚአብሔር እውቀት’ ለማግኘት ጊዜው አሁን ነው።

የመንግሥቱን መልእክት ታዳምጣለህ?

አምላክ በመንግሥቲቱ አማካኝነት የሰይጣንን ሥራ ሁሉ ያስወግዳል፤ ሰዎች የጽድቅ መንገዶቹን እንዲማሩም ያደርጋል። በዚህ የተነሳ የኢየሱስ ትምህርት ዋነኛ ትኩረት ያረፈው በመንግሥቲቱ ላይ መሆኑ አያስደንቅም። ኢየሱስ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል” ካለ በኋላ ምክንያቱን ሲገልጽ “የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” ብሏል። (ሉቃስ 4:43) ደቀ መዛሙርቱንም ይህንኑ መልእክት ለሌሎች እንዲናገሩ አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) የመጨረሻው ጊዜ በጣም ቀርቧል፤ በመሆኑም ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ሁሉ ይህን ሕይወት አድን ምሥራች ማዳመጣቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!

በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው አልበርት፣ ባለቤቱና ወንድ ልጁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በመጀመራቸው እርሱም የመንግሥቱን መልእክት ሰማ። አልበርት መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ አድሮበት ነበር። እንዲያውም በአካባቢው ወደሚገኙ አንድ ቄስ በመሄድ የይሖዋ ምሥክሮች ሐሰተኛ መሆናቸውን ለባለቤቱና ለልጁ እንዲያስረዱለት ጠይቋቸው ነበር። ሆኖም ቄሱ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። ስለዚህ አልበርት ስህተት ለማግኘት ሲል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በሚደረገው ውይይት ላይ ተገኝቶ ለማዳመጥ ወሰነ። በመጀመሪያው ውይይት ላይ ከተገኘ በኋላ ግን ተጨማሪ ነገሮችን ለመማር ጉጉት ስላደረበት በጥናቱ ውስጥ መሳተፍ ጀመረ። በኋላ ላይ አመለካከቱን ለምን እንደቀየረ ሲገልጽ “ስፈልገው የኖርኩት ይህንኑ ነበር” ብሏል።

በመጨረሻ፣ አልበርት መንፈሳዊ ፍላጎቱን ማርካት ቻለ፤ ባደረገው ውሳኔም ፈጽሞ ቆጭቶት አያውቅም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወቱን ሙሉ ሲፈልጋቸው የነበሩትን ነገሮች እንዲያገኝ ማለትም በኅብረተሰቡ ውስጥ ለተንሰራፋው የፍትሕ መጓደልና ምግባረ ብልሹነት መፍትሔው ምን እንደሆነ እንዲሁም የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ እንደያዘ እንዲያውቅ ረድቶታል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ውስጣዊ ሰላም አስገኝቶለታል። ያንተስ መንፈሳዊ ፍላጎት ረክቷል? ታዲያ በገጽ 6 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ጥቂት ጊዜ ወስደህ ለምን አታነብም? ተጨማሪ መረጃ የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[በገጽ  6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መንፈሳዊ ፍላጎትህ ረክቷል?

በምታገኘው መንፈሳዊ ምግብ ረክተሃል? የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንድታነብና በትክክል መልስ ልትሰጥበት በቻልከው ነጥብ ላይ ምልክት እንድታደርግ እንጋብዝሃለን።

አምላክ ማን ነው? ስሙስ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? መሞት ያስፈለገውስ ለምንድን ነው? የእርሱ መሞት የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

ዲያብሎስ አለ? ካለስ ከየት መጣ?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

አምላክ ምን የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን አውጥቷል?

በቤተሰብ ውስጥ አምላክ ለባልና ለሚስት የሰጠው ቦታ ምንድን ነው? ለቤተሰብ ደስታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ምንድን ናቸው?

ከላይ ለተጠየቁት ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ካላወቅህ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር እንዲላክልህ መጠየቅ ትችላለህ። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ ብሮሹር 300 በሚጠጉ ቋንቋዎች የታተመ ሲሆን ከላይ የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ጨምሮ 16 ለሚያህሉ ዋና ዋና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ይሰጣል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ልጅ ከእንስሳ በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ፍላጎት አለው

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3 NW

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ታሰፍናለች