በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መልካም ዜና ማብሰር’

‘መልካም ዜና ማብሰር’

‘መልካም ዜና ማብሰር’

‘በተራሮች ላይ የቆሙ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው።’—ኢሳይያስ 52:7

1, 2. (ሀ) በየዕለቱ ምን አሰቃቂ ነገሮች እየተከሰቱ ነው? (ለ) ብዙ ሰዎች ዘወትር ስለሚሰሟቸው መጥፎ ዜናዎች ምን ይሰማቸዋል?

 በዛሬው ጊዜ በየትኛውም የምድር ክፍል መልካም ዜና መስማት ብርቅ እየሆነ መጥቷል። ሰዎች ሬዲዮናቸውን ሲከፍቱ በምድር ላይ ከባድ ስጋት እየፈጠሩ ስላሉት ቀሳፊ በሽታዎች የሚገልጹ አስፈሪ ዘገባዎችን ይሰማሉ። ቴሌቪዥናቸውን ሲከፍቱ ደግሞ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ያሉ በረሃብ የተቆራመዱና ምስላቸው ከአእምሮ የማይጠፋ ሕፃናትን ይመለከታሉ። ጋዜጦችን ሲመለከቱም ሕንፃዎችን ስላወደሙና የበርካታ ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት ስለቀጠፉ ፍንዳታዎች የሚገልጹ ዘገባዎች ያነብባሉ።

2 አዎን፣ በየዕለቱ አሰቃቂ ነገሮች እየተከሰቱ ነው። ያለ ምንም ጥርጥር የዚህ ዓለም መልክ በአስከፊ ሁኔታ እየተለወጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:31 NW) በምዕራብ አውሮፓ እየታተመ የሚወጣ አንድ መጽሔት አንዳንድ ጊዜ መላዋ ዓለም “ልትጋይ የደረሰች” ትመስላለች የሚል አስተያየት ሰጥቷል። በርካታ ሰዎች መጨነቃቸው ምንም አያስደንቅም! በዩናይትድ ስቴትስ የሚቀርቡ የቴሌቪዥን ዜናዎችን በተመለከተ በተደረገ ጥናት ላይ የተጠቀሰ አንድ አስተያየት ሰጪ የተናገረው ቃል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስሜት የሚያስተጋባ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሰው ‘ዜና ከተመለከትኩ በኋላ በጣም እጨነቃለሁ። አንድም ጥሩ ዜና የለም። የሚሰማው ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው’ ሲል ተናግሯል።

ሁሉም ሰው ሊሰማው የሚገባ ዜና

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውጀው ምሥራች ምንድን ነው? (ለ) ለመንግሥቱ ምሥራች ትልቅ ግምት የምትሰጠው ለምንድን ነው?

3 ሐዘን ባጠላበት በዚህ ዓለም ውስጥ መልካም ዜና ሊገኝ ይችላል? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ዜና ወይም ምሥራች የሚያውጅ መሆኑን ማወቁ የሚያጽናና ነው። ይህ ምሥራች የአምላክ መንግሥት በሽታን፣ ረሃብን፣ ወንጀልን፣ ጦርነትንና ማንኛውንም ዓይነት ጭቆና እንደሚያስወግድ የሚገልጽ ዜና ነው። (መዝሙር 46:9፤ 72:12) ታዲያ ይህ ሰዎች ሁሉ ሊሰሙት የሚገባ ዜና አይደለም? የይሖዋ ምሥክሮች እያንዳንዱ ሰው ይህን ዜና መስማት እንደሚያስፈልገው ይሰማቸዋል። በማንኛውም ቦታ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ሁሉ ያለማሰለስ ለመስበክ በሚያደርጉት ጥረት የሚታወቁት ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 24:14

4. በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ሥር የትኞቹን የአገልግሎታችን ገጽታዎች እንመረምራለን?

4 የምናገለግለው ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም በጎ ምላሽ በማይገኝበት ክልል ውስጥ ቢሆንም እንኳን ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ አርኪና ትርጉም ያለው ድርሻ ማበርከታችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ እንችላለን? (ሉቃስ 8:15) የስብከት ሥራችንን ሦስት ዋና ዋና ገጽታዎች በአጭሩ መመርመራችን በዚህ ረገድ እንደሚረዳን ምንም አያጠራጥርም። የምንመረምራቸው ሦስት ገጽታዎች (1) የምንሰብክበት ምክንያት ወይም ለምን እንደምንሰብክ፤ (2) መልእክታችን ወይም ምን እንደምንሰብክ እና (3) የምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ወይም እንዴት እንደምንሰብክ ናቸው። ለመስበክ የሚያነሳሳንን ትክክለኛ ምክንያት ባለመዘንጋት፣ መልእክታችንን ግልጽ በማድረግና ውጤታማ የሆኑ የስብከት ዘዴዎችን በመጠቀም የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የሚገልጸውን እጅግ መልካም የሆነ ዜና እንዲሰሙ አጋጣሚ ልንከፍትላቸው እንችላለን። a

ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የምንሳተፈው ለምንድን ነው?

5. (ሀ) በአገልግሎት እንድንሳተፍ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) እንድንሰብክ የተሰጠንን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ማክበራችን ለአምላክ ፍቅር እንዳለን ያሳያል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

5 እስቲ በቅድሚያ የመጀመሪያውን ገጽታ ማለትም ለመስበክ የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ እንመርምር። ምሥራቹን የምንሰብከው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ከሰበከበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው። እርሱ ‘አብን እወደዋለሁ’ በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 14:31፤ መዝሙር 40:8) ስለዚህ እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:37, 38) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው” በማለት አምላክን በመውደድና በአገልግሎት መካከል ዝምድና እንዳለ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 5:3፤ ዮሐንስ 14:21) ታዲያ የአምላክ ትእዛዛት ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ የሚለውን መመሪያ ያካትታሉ? (ማቴዎስ 28:19) እንዴታ! እነዚህን ቃላት የተናገረው ኢየሱስ ቢሆንም ዋነኛ ምንጩ ይሖዋ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:28፤ ማቴዎስ 17:5) ስለዚህ እንድንሰብክ የተሰጠንን ትእዛዝ በማክበር ይሖዋን እንደምንወደው እናሳያለን።

6. ለአምላክ ያለን ፍቅር እንድንሰብክ የሚገፋፋን በምን መንገዶች ነው?

6 በተጨማሪም ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንድንሰብክ ያነሳሳናል፤ ምክንያቱም ሰይጣን በእርሱ ላይ የሚነዛውን ውሸት መቃወም እንፈልጋለን። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን ስለ አምላክ አገዛዝ ትክክለኝነት ጥያቄ አንስቷል። (ዘፍጥረት 3:1-5) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ሰይጣን የአምላክን ስም ለማጥፋት የሚያደርገውን ጥረት በማጋለጡና ስሙ በሰዎች ሁሉ ፊት እንዲቀደስ በማድረጉ ሥራ ላይ ለመካፈል እንጓጓለን። (ኢሳይያስ 43:10-12) ከዚህም በላይ በአገልግሎት የምንሳተፈው የይሖዋን ባሕርያትና መንገዶች በመማራችን ነው። ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ስለሚሰማን ስለ አምላካችን ለሌሎች የመንገር ከፍተኛ ፍላጎት አለን። እንዲያውም የይሖዋ በጎነትና የጽድቅ መንገዶቹ ከፍተኛ ደስታ ስላስገኙልን ስለ እርሱ መናገራችንን ማቆም አንችልም። (መዝሙር 145:7-12) ለሚሰሙ ሰዎች ሁሉ ምሥጋናውንና ‘ታላቅ ሥራውን’ መናገር እንዳለብን ይሰማናል።—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ኢሳይያስ 43:21

7. ለአምላክ ካለን ፍቅር በተጨማሪ በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የሚገፋፋን ሌላው አስፈላጊ ምክንያት ምንድን ነው?

7 መስበካችንን እንድንቀጥል የሚገፋፋን ሌላም አስፈላጊ ምክንያት አለ። ይህም ሥፍር ቁጥር በሌላቸው መጥፎ ዜናዎች የሚረበሹም ሆኑ በተለያየ ምክንያት ስቃይ የሚደርስባቸው ግለሰቦች እፎይታ እንዲያገኙ ያለን ልባዊ ፍላጎት ነው። በዚህ ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል እንጥራለን። ለምሳሌ ያህል በማርቆስ ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን ታሪክ እንመልከት።

8. በማርቆስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘው ዘገባ ኢየሱስ ለሕዝቡ ምን ስሜት እንደነበረው ያሳያል?

8 ሐዋርያት ከስብከት ዘመቻ ሲመለሱ የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ለኢየሱስ ተረኩለት። ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንደደከማቸው ስለተገነዘበ አብረውት ወደ አንድ ቦታ ሄደው ‘ጥቂት እንዲያርፉ’ ነገራቸው። ከዚያም ጀልባ ተሳፍረው ጸጥ ወዳለ ሥፍራ ተጓዙ። ይሁንና ሕዝቡ በባሕሩ ዳርቻ በመሮጥ ቀደማቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ? ዘገባው “ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር” ይላል። (ማርቆስ 6:31-34) ኢየሱስ ደክሞት የነበረ ቢሆንም ለሕዝቡ የነበረው አዘኔታ ምሥራቹን መናገሩን እንዲቀጥል አነሳስቶታል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሰዎቹ ሁኔታ አንጀቱን በልቶታል። በሌላ አነጋገር ከልብ ራርቶላቸው ነበር።

9. በማርቆስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘው ዘገባ ለስብከት የምንነሳሳበትን ምክንያት በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

9 ከዚህ ዘገባ ምን እንማራለን? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታ እንዳለብን ይሰማናል። አምላክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” ስለሚፈልግ ምሥራቹን የማወጅ ኃላፊነት እንደተጣለብን እንገነዘባለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ይሁን እንጂ አገልግሎታችንን የምናከናውነው እንዲያው ግዴታ እንዳለብን ተሰምቶን ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ስለምንራራ ነው። ልክ እንደ ኢየሱስ ለሰዎች ከአንጀት የምናዝን ከሆነ ልባችን ምሥራቹን መናገራችንን ለመቀጠል የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ይገፋፋናል። (ማቴዎስ 22:39) እንዲህ ያሉት ግሩም ምክንያቶች ምሥራቹን ያለማሰለስ እንድንሰብክ ያነሳሱናል።

ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የሚገልጸው መልእክታችን

10, 11. (ሀ) ኢሳይያስ የምንሰብከውን መልእክት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘መልካም ዜና ያበሰረው’ እንዴት ነበር? በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮችስ የኢየሱስን ምሳሌ የተከተሉት እንዴት ነው?

10 ስለ ሁለተኛው የአገልግሎታችን ገጽታ ማለትም ስለ መልእክታችን ይዘትስ ምን ለማለት ይቻላል? የምንሰብከው ምንድን ነው? ነቢዩ ኢሳይያስ የምናውጀውን መልእክት እንዲህ በማለት ግሩም አድርጎ ገልጾታል:- “በተራሮች ላይ የቆሙ፣ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ ድነትን የሚያውጁ፣ ጽዮንንም፣ ‘አምላክሽ ነግሦአል’ የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።”—ኢሳይያስ 52:7

11 እዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “አምላክሽ ነግሦአል” የሚለው ዋና ሐሳብ ልናውጀው የሚገባንን መልእክት ይጠቁመናል። ይህ መልእክት የአምላክ መንግሥት ወንጌል ወይም ምሥራች ነው። (ማርቆስ 13:10) እንዲሁም ጥቅሱ የመልእክታችን ዋና ጭብጥ በመልካም ነገሮች ላይ ያተኮረ መሆኑን እንደሚጠቁም ልብ በል። ኢሳይያስ “ድነት፣” “የምሥራች፣” “ሰላም፣” እና “መልካም ዜና” እንደሚሉ ያሉ መግለጫዎችን ተጠቅሟል። ኢሳይያስ ከኖረበት ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት ቆይቶ ይኸውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና ማለትም የአምላክን መንግሥት መምጣት በቅንዓት በማብሰር ይህን ትንቢት በላቀ ደረጃ ፈጽሟል። (ሉቃስ 4:43) በዘመናችን በተለይ ደግሞ ከ1919 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ስላቋቋመው መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች የሚገልጸውን ምሥራች በቅንዓት በማወጅ የኢየሱስን ግሩም ምሳሌ ተከትለዋል።

12. ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መቀበላቸው ምን ያስገኝላቸዋል?

12 ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መቀበላቸው ምን ያስገኝላቸዋል? በኢየሱስ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም ምሥራቹ ተስፋና ማጽናኛ ያስገኛል። (ሮሜ 12:12፤ 15:4) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን በሚሰሙበት ጊዜ ተስፋቸው የሚለመልመው ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳለ ስለሚማሩ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እንዲህ ያለው ተስፋ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት እንዲይዙ በእጅጉ ይረዳቸዋል። መዝሙራዊው እንዲህ ያሉ ሰዎች ‘ክፉ ወሬ እንደማያሸብራቸው’ ገልጿል።—መዝሙር 112:1, 7

‘ልባቸው የተሰበረውን የሚጠግን’ መልእክት

13. ነቢዩ ኢሳይያስ ምሥራቹን የሚቀበሉ ሰዎች ወዲያውኑ የሚያገኟቸውን በረከቶች የገለጸው እንዴት ነው?

13 በተጨማሪም የምንሰብከውን ምሥራች የሚቀበሉ ሰዎች ወዲያውኑ እፎይታና ሌሎች በረከቶችን ያገኛሉ። እንዴት? ነቢዩ ኢሳይያስ የመንግሥቱ መልእክት ከሚያስገኛቸው በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንዲህ ሲል በትንቢት ተናግሯል:- “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛል። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል፤ የተወደደውን የእግዚአብሔርን ዓመት፣ የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል።”—ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:16-21

14. (ሀ) “ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን” የሚለው አገላለጽ ስለ መንግሥቱ መልእክት ምን ይጠቁማል? (ለ) ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ያለውን የአሳቢነት መንፈስ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 በዚህ ትንቢት መሠረት ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበክ ‘ልባቸው የተሰበረውን ይጠግናል።’ እዚህ ላይ ኢሳይያስ ሐሳቡን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው ‘መጠገን’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ብዙውን ጊዜ ቁስል ላይ መድኃኒት አድርጎ በፋሻ ‘በማሰር’ መፈወስን ለማመልከት ያገለግላል።” አሳቢ የሆነች አንዲት ነርስ የተጎጂው የቆሰለ አካል ድጋፍ እንዲያገኝ በፋሻ ወይም በጨርቅ ታስርለት ይሆናል። በተመሳሳይ አሳቢ የሆኑ አስፋፊዎች የመንግሥቱን መልእክት በሚሰብኩበት ጊዜ በአንድ በሆነ ነገር እየተሰቃዩ ላሉና ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጉላቸዋል። ችግር ላይ የወደቁትን በመደገፍ የይሖዋን የአሳቢነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ። (ሕዝቅኤል 34:15, 16) መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቊስላቸውንም ይጠግናል” ብሏል።—መዝሙር 147:3

የመንግሥቱ መልእክት ምን ለውጥ ያመጣል?

15, 16. የመንግሥቱ መልእክት ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን እንደሚደግፍና እንደሚያበረታ የሚያሳዩ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን ተናገር።

15 የመንግሥቱ መልእክት በእርግጥም ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን የሚደግፈውና የሚያበረታው እንዴት እንደሆነ በግልጽ የሚያሳዩ በርካታ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎች አሉ። በአንድ ወቅት በሕይወት መኖር አስጠልቷቸው የነበሩትን በደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ ኦሬያነ የሚባሉ አንዲት አረጋዊት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታቸው እየሄደች ትጠይቃቸው እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስንና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ b የተባለውን መጽሐፍ ታነብላቸው ጀመር። በጭንቀት የተዋጡት እኚህ ሴት መጀመሪያ ላይ የሚነበብላቸውን ነገር ያዳምጡ የነበረው ዓይናቸውን ከደን አድርገው አልጋቸው ላይ ጋደም እንዳሉ ሲሆን አልፎ አልፎ ቁና ቁና ይተነፍሱ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እንደምንም ብለው በመነሳት አልጋ ላይ ቁጭ ብለው ማዳመጥ ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ሳሎን ውስጥ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያቸውን መጠበቅ ቻሉ። ከዚያም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከመጀመራቸውም በላይ ከስብሰባዎቹ ባገኙት ትምህርት በመበረታታት በደጃቸው ለሚያልፉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያበረክቱ ጀመር። በኋላም ኦሬያነ በ93 ዓመታቸው ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። የመንግሥቱ መልእክት በሕይወት የመኖር ፍላጎታቸውን አድሶላቸዋል።—ምሳሌ 15:30፤ 16:24

16 የመንግሥቱ መልእክት በበሽታ ምክንያት ሕይወታቸው በአጭር ሊቀጭ እንደደረሰ ለሚያውቁ ሰዎች ጭምር ብርቱ ድጋፍ ይሆናቸዋል። በምዕራብ አውሮፓ የምትኖረውን ማሪያን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በማይድን በሽታ ትማቅቅ የነበረችው ይህች ሴት ተስፋዋ ሁሉ ተሟጥጦ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተገናኘችበት ወቅት በከባድ ጭንቀት ትሰቃይ ነበር። ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ዓላማ ስትማር ሕይወቷ እንደገና ትርጉም ያለው እየሆነ መጣ። ብዙም ሳይቆይ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር የሆነች ሲሆን በስብከቱ ሥራ በትጋት ትሳተፍ ጀመር። ከመሞቷ በፊት በነበሩት የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት በፊቷ ላይ ደስታና ብሩህ ተስፋ ይነበብ ነበር። ማሪያ በትንሣኤ ላይ ጽኑ እምነት እንደያዘች ሕይወቷ አለፈ።—ሮሜ 8:38, 39

17. (ሀ) የመንግሥቱ መልእክት በተቀበሉት ሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ‘የወደቁትን ሁሉ እንደሚያነሳ’ በራስህ ተሞክሮ የተመለከትከው እንዴት ነው?

17 እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች የመንግሥቱ መልእክት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተጠሙ ሰዎች ሕይወት ላይ በእርግጥ ለውጥ እንደሚያመጣ ያሳያሉ። የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሲማሩ ኃይላቸው እንደገና ይታደሳል። (1 ተሰሎንቄ 4:13) ድሆች የሆኑና የቤተሰባቸውን የዕለት ጉርስ ለማሟላት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎች ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ከቶ እንደማይተዋቸው ሲገነዘቡ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ይጨምራል፤ ብርታትም ያገኛሉ። (መዝሙር 37:28) በመንፈስ ጭንቀት ይሰቃዩ የነበሩ በርካታ ሰዎች በይሖዋ እርዳታ ይህን ችግር ለመቋቋም የሚያስፈልጋቸውን ብርታት ያገኙ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ድነዋል። (መዝሙር 40:1, 2) በእርግጥም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ኃይል በመስጠት አሁንም እንኳ ‘የወደቁትን ሁሉ እያነሳ’ ነው። (መዝሙር 145:14) የመንግሥቱ ምሥራች በአገልግሎት ክልላችንና በጉባኤያችን ለሚገኙት ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ማጽናኛ በማስገኘት ላይ መሆኑን ስንመለከት፣ የምንሰብከው መልእክት እጅግ መልካም የሆነ ዜና እንደሆነ ዘወትር እንድናስታውስ ያደርገናል!—መዝሙር 51:17

‘ስለ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን የምለምነው’

18. ጳውሎስ አይሁዳውያን ምሥራቹን አለመቀበላቸው ምን ስሜት አሳድሮበት ነበር? ለምንስ?

18 መልእክታችን እጅግ መልካም የሆነ ዜና የያዘ ቢሆንም ብዙዎች ጆሮ መስጠት አይፈልጉም። ታዲያ ይህ ምን ስሜት ሊያሳድርብን ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ጳውሎስ ለአይሁዳውያን ደጋግሞ የሰበከላቸው ቢሆንም አብዛኞቹ የመዳንን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። አለመቀበላቸው የጳውሎስን ስሜት በእጅጉ ነክቶት ነበር። በመሆኑም “ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ” በማለት የተሰማውን በግልጽ ተናግሯል። (ሮሜ 9:2) ጳውሎስ ይሰብክላቸው ለነበሩት አይሁዳውያን ከአንጀቱ ይራራላቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ምሥራቹን አለመቀበላቸው አሳዝኖታል።

19. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ ብናዝን የሚያስደንቅ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ እንዲቀጥል የረዳው ምን ነበር?

19 እኛም በርኅራኄ ተነሳስተን ምሥራቹን እንሰብካለን። ስለሆነም ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ሲቀሩ ብናዝን የሚያስደንቅ አይሆንም። ይህ ዓይነቱ ስሜት ለምንሰብክላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ደኅንነት ከልብ እንደምናስብ ያሳያል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ጳውሎስን በስብከቱ ሥራ እንዲቀጥል የረዳው ምን ነበር? አይሁዳውያን ምሥራቹን ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸው አሳዝኖትና አስጨንቆት የነበረ ቢሆንም ምንም ተስፋ የላቸውም በሚል ስሜት ከነአካቴው እርግፍ አድርጎ አልተዋቸውም። ከዚህ ይልቅ ክርስቶስን የሚቀበሉ ጥቂት አይሁዳውያን አይጠፉም የሚል ተስፋ ነበረው። ስለሆነም ጳውሎስ “ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው” በማለት ስለ አንዳንድ አይሁዳውያን የነበረውን ስሜት ጽፏል።—ሮሜ 10:1

20, 21. (ሀ) አገልግሎታችንን በተመለከተ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ የትኛው የአገልግሎታችን ገጽታ ይብራራል?

20 ጳውሎስ ጎላ አድርጎ የገለጻቸውን ሁለት ነገሮች ልብ በል። አንዳንድ አይሁዳውያን መዳን እንዲያገኙ ልባዊ ምኞት የነበረው ሲሆን ይህን በተመለከተም አምላክን ለምኗል። ዛሬም በዚህ ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ እንከተላለን። ለምሥራቹ ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ልባዊ ፍላጎት እናዳብራለን። እንዲሁም እንዲህ ያሉ ሰዎችን ማግኘት እንድንችል ወደ ይሖዋ ሳንታክት እንጸልያለን። እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን ማግኘታችን ለመዳን የሚያበቃቸውን እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ያስችለናል።—ምሳሌ 11:30፤ ሕዝቅኤል 33:11፤ ዮሐንስ 6:44

21 ይሁን እንጂ የመንግሥቱን ምሥራች በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ማድረስ እንድንችል ለምን እና ምን እንደምንሰብክ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምንሰብክም ጭምር መመርመር ይኖርብናል። ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ሥር ሁለቱ ገጽታዎች ይብራራሉ። በሚቀጥለው ርዕስ ሥር ደግሞ ሦስተኛው ይብራራል።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• በአገልግሎት እንድንሳተፍ የሚያደርጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

• የስብከታችን ዋነኛ መልእክት ምንድን ነው?

• የመንግሥቱን መልእክት የተቀበሉ ሰዎች ምን በረከቶች አግኝተዋል?

• በአገልግሎታችን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ መልእክት ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ብርታት ይሰጣል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎት በአገልግሎታችን እንድንጸና ይረዳናል