በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ዓለም አቀፍ ሥራ ላይ በመካፈሌ ደስተኛ ነኝ

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ዓለም አቀፍ ሥራ ላይ በመካፈሌ ደስተኛ ነኝ

የሕይወት ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ዓለም አቀፍ ሥራ ላይ በመካፈሌ ደስተኛ ነኝ

አና ማቲያኪስ እንደተናገረችው

የሕዝብ ማመላለሻው ጀልባ በእሳት ተያይዟል። መቶ ሰባ አንድ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ግዙፍ ጀልባ ከሰመጠ ደግሞ ወደ ባሕሩ ወለል ይዞኝ መውረዱ አይቀሬ ነው። ኃይለኛውን ሞገድ እየታገልኩ በመዋኘት ከጀልባው ለመራቅ ጥረት አደረግኩ። እንዳልሰምጥ የሚረዳኝ ብቸኛው መፍትሔ አንዲት ሴት የለበሰችውን ሕይወት አድን ጃኬት ሙጭጭ አድርጎ መያዝ ነበር። አምላክ ብርታትና ድፍረት እንዲሰጠኝ በጸሎት ለመንኩት። ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ይህ ነበር።

ይህ የሆነው በ1971 ሲሆን ወደ ሦስተኛው ሚስዮናዊ ምድቤ ወደ ጣሊያን እየተመለስኩ ነበር። በዚህ አደጋ ምክንያት የነበረኝን ንብረት በሙሉ አጥቻለሁ ማለት ይቻላል። ሆኖም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ይኸውም ሕይወቴን፣ ፍቅር የሰፈነበትን ክርስቲያናዊው የወንድማማች ኅብረትና ይሖዋን የማገልገል መብቴን አላጣሁም። በዚህ ልዩ መብት ምክንያት ወደ ሦስት አህጉራት የተጓዝኩ ሲሆን የጀልባው አደጋ በሕይወቴ ካሳለፍኳቸው በርካታ ገጠመኞች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው።

የተወለድኩት በ1922 ሲሆን ቤተሰባችን ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን አቅጣጫ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በራማላ ይኖር ነበር። ወላጆቼ የተወለዱት በቀርጤስ ደሴት ላይ ቢሆንም አባቴ ያደገው በናዝሬት ነው። ሦስት ወንድሞችና አንዲት እህት የነበሩኝ ሲሆን እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ። ለቤታችን ሁለተኛ ልጅ የነበረው ወንድሜ በትምህርት ቤት በተዘጋጀ ሽርሽር ላይ እያለ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰጥሞ በመሞቱ ቤተሰባችን ሐዘን ላይ ወደቀ። እናቴ በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተነሳ በራማላ መኖር ስላስጠላት ቤተሰባችን ወደ አቴንስ፣ ግሪክ ተዛወረ። በዚያን ወቅት የሦስት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ቤተሰባችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሰማ

ግሪክ እንደደረስን ብዙም ሳንቆይ የ22 ዓመት ወጣት የነበረው ትልቁ ወንድሜ ኒኮስ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማሩ ከፍተኛ ደስታ ያስገኘለት ከመሆኑም በላይ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ኃይለኛ ቅንዓት እንዲኖረው አነሳስቶታል። ይህ ሁኔታ አባቴን ስላናደደው ኒኮስን ከቤት አባረረው። ሆኖም አባቴ ወደ ፍልስጤም በሚሄድበት ጊዜ እኔ፣ እናቴና እህቴ ከኒኮስ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንገኝ ነበር። እናቴ በስብሰባዎቹ ላይ ስለሰማቻቸው ነገሮች በጋለ ስሜት ትናገረው የነበረው ነገር አሁን ድረስ በደንብ ትዝ ይለኛል። ሆኖም ብዙም ሳትቆይ በ42 ዓመቷ በካንሰር ተይዛ ሞተች። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት እህቴ አሪያን በፍቅር ተነሳስታ ቤተሰባችንን መንከባከብ ጀመረች። ወጣት የነበረች ቢሆንም ለብዙ ዓመታት እንደ እናት ሆና አሳድጋኛለች።

አባቴ አቴንስ እስካለ ድረስ ሁልጊዜ ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይወስደኝ የነበረ ሲሆን እርሱ ከሞተ በኋላም አልፎ አልፎ ቢሆንም መሄዴን አላቋረጥኩም ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ምዕመናኑ አምላካዊ ፍርሃት እንደሌላቸው እየተመለከትኩ በመምጣቴ ቤተ ክርስቲያን መሄዴን አቆምኩ።

አባቴ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ጥሩ ሥራ አገኘሁ። ወንድሜ ግን የመንግሥቱን ወንጌል በመስበኩ ሥራ ራሱን በማስጠመድ በግሪክ ለብዙ ዓመታት አገልግሏል። በ1934 ደግሞ ወደ ቆጵሮስ ተዛወረ። በጊዜው በደሴቲቱ የሚኖር አንድም የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ስላልነበረ የስብከቱ ሥራ እድገት እንዲያደርግ የመርዳት መብት አገኘ። ሚስት ካገባ በኋላ ባለቤቱ ገላቲያም ለበርካታ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍላለች። a ወንድማችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መጽሐፎችንና መጽሔቶችን ደጋግሞ ቢልክልንም አንብበናቸው አናውቅም ነበር። ኒኮስ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የኖረው በቆጵሮስ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የራሴ አደረግሁ

አቴንስ ውስጥ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር የነበረ ጆርጅ ዱራስ የሚባል አንድ የኒኮስ ጓደኛ በ1940 መጥቶ ጠየቀንና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ቤቱ ውስጥ በሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንድንገኝ ጋበዘን። እኛም ግብዣውን በደስታ ተቀበልን። ብዙም ሳይቆይ ስለተማርናቸው ነገሮች ለሌሎች መናገር ጀመርን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ማግኘታችን እኔም ሆንኩ እህቴ ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስን ያነሳሳን ሲሆን አሪያን በ1942፣ እኔ ደግሞ በ1943 ተጠመቅን።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ኒኮስ ወደ ቆጵሮስ እንድንመጣ ግብዣ አቀረበልን። በዚህም ምክንያት በ1945 ኒኮሲያ መኖር ጀመርን። በቆጵሮስ የስብከቱ ሥራ እንደ ግሪክ እገዳ አልተጣለበትም። ከቤት ወደ ቤት ብቻ ሳይሆን በመንገድም ላይ እንደልብ እናገለግል ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ አሪያን ወደ ግሪክ መመለስ ግድ ሆነባት። እዚያም እያለች በኋላ ካገባችው አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በመተዋወቋ አቴንስ ለመቆየት ወሰነች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እህቴና ባለቤቷ ወደ ግሪክ ተመልሼ በዋና ከተማዋ በአቴንስ ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል አበረታቱኝ። ከበፊት ጀምሮ አቅኚ ሆኖ የማገልገል ግብ ስለነበረኝ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ አቴንስ ተመለስኩ።

አዲስ የሥራ በር ተከፈተልኝ

ኅዳር 1, 1947 አቅኚ ሆኜ ማገልገል የጀመርኩ ሲሆን በስብከቱ ሥራ በየወሩ 150 ሰዓታት አሳልፍ ነበር። የጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በእግሬ ብዙ መጓዝ ነበረብኝ። ያም ሆኖ ብዙ በረከቶች አግኝቻለሁ። ፖሊሶች ሲሰብክም ሆነ ሲሰበሰብ ያገኙትን ማንኛውንም የይሖዋ ምሥክር ያስሩ ስለነበር ብዙም ሳልቆይ ታሰርኩ።

የሰዎችን ሃይማኖት ለማስቀየር ሞክራለች በሚል ተከሰስኩ፤ በወቅቱ ይህ ድርጊት እንደ ከባድ ወንጀል ይቆጠር ነበር። አቴንስ ውስጥ በሚገኘው አቬሮፍ የሴቶች ወኅኒ ቤት ሁለት ወር እንድታሰር ተፈረደብኝ። እዚያም ከእኔ ቀደም ብላ ታስራ ከነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘሁ። ሁለታችንም በእስር ላይ የነበርን ቢሆንም እንኳ አስደሳችና ገንቢ የሆነ ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ለመመሥረት ችለናል። ፍርዴን ካጠናቀቅሁ በኋላ በደስታ አቅኚነቴን ቀጠልኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኋቸው አብዛኞቹ ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሆኑ መቀጠላቸው ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል።

በ1949 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ16ኛው ክፍል ላይ እንድካፈል ተጋበዝኩ፤ ጊልያድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ለሚስዮናዊነት የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት ነው። ከዚህም የተነሳ እኔም ሆንኩ ዘመዶቼ በደስታ ፈነደቅን። በ1950 የበጋ ወራት ኒው ዮርክ በሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከተካፈልኩ በኋላ በዚያው ወደ ጊልያድ ለመግባት ዝግጅት አደረግሁ።

ዩናይትድ ስቴትስ ከደረስኩ በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ለጥቂት ወራት የጽዳት ሥራ የመሥራት ልዩ መብት አገኘሁ። እዚያ ሁሉ ነገር ንጹሕ፣ አስደሳችና መንፈስን የሚያድስ ከመሆኑም በተጨማሪ ፈገግታ ከማይለያቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር እኖር ነበር። በቤቴል ያሳለፍኳቸውን ስድስት ወራት ሳስታውስ ልቤ ሁልጊዜ በሐሴት ይሞላል። ከዚያም በጊልያድ ትምህርት ጀመርን፤ ለአምስት ወራት የዘለቀው ጥልቅ ምርምር የታከለበት የትምህርት ጊዜ ሳይታወቀኝ አለፈ። በጊዜው የነበርነው ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ምን ያህል ውድና ግሩም እንደሆነ ተገንዝበናል፤ ይህም ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደረገልን ከመሆኑም በላይ ሕይወት ሰጪ የሆነውን የእውነት እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ያለንን ጉጉት አሳድጎልናል።

ሚስዮናዊ ሆኜ የተመደብኩበት የመጀመሪያው ቦታ

በጊልያድ ትምህርት ቤት ሳለን ምድብ ቦታችንን ከማወቃችን በፊት የአገልግሎት ጓደኛ እንድንመርጥ አጋጣሚ ተሰጥቶን ነበር። ሩት ሄሚግ (አሁን ቦስሃርት) የምትባል ግሩም እህት የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆነች። እኔና ሩት አውሮፓና እስያ በሚገናኙባት በቱርክ፣ ኢስታንቡል ከተማ እንደተመደብን ስናውቅ ደስታችን ወደር አልነበረውም! የስብከቱ ሥራችን በአገሪቷ ሕጋዊ እውቅና እንደሌለው እናውቅ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ እንደሚደግፈን እርግጠኞች ነበርን።

ኢስታንቡል ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ልዩ ልዩ ባሕል ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት ውብ ከተማ ናት። ኢስታንቡል በብዙ ሰዎችና ሸቀጦች የተጨናነቁ ገበያዎችን፣ የተለያዩ አገሮች ምርጥ የባሕል ምግቦችን፣ ማራኪ ቤተ መዘክሮችን እንዲሁም ደስ የሚሉ ጎረቤቶችንና ሁልጊዜም ቀልብ የሚስበውን የባሕር ዳርቻ ያቀፈች ከተማ ነች። ከሁሉ የሚበልጠው ግን ስለ አምላክ መማር የሚፈልጉ ቅን ሰዎች መኖራቸው ነበር። በዚህች ከተማ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን በአብዛኛው አርመኖችን፣ ግሪኮችንና አይሁዶችን ያቀፈ ነበር። ሆኖም ብዙ የውጪ አገር ዜጎች ስለነበሩ የቱርክን ቋንቋ ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን ለመግባባት ያህል መልመድ አስፈላጊ ነበር። የተለያየ አገር ዜጎች የሆኑ እውነትን የተጠሙ ሰዎች በማግኘታችን እጅግ ተደስተናል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል።

የሚያሳዝነው ሩት የመኖሪያ ፍቃዷን ማደስ ስላልቻለች አገሩን ለቅቃ መውጣት ግድ ሆነባት። ስዊዘርላንድ ሄዳ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈሏን ቀጠለች። እነዚህ ሁሉ ዓመታት አልፈውም እንኳ አስደሳችና የሚያንጸው ወዳጅነቷ ይናፍቀኛል።

ሌላ አህጉር ተመደብኩ

በ1963 በቱርክ የነበረኝ የመኖሪያ ፍቃድ ሊታደስልኝ አልቻለም። ብዙ ውጣ ውረዶችን ለማሸነፍ እየጣሩ መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ከነበሩ ክርስቲያኖች መለየት ከባድ ነበር። ቤተሰቦቼ እኔን ለማጽናናት ብለው ኒው ዮርክ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድካፈል የትራንስፖርት ወጪዬን በደግነት ሸፈኑልኝ። ቀጣዩን ምድብ ቦታዬን ግን ገና አላወቅኩም ነበር።

ከአውራጃ ስብሰባው በኋላ ሊማ፣ ፔሩ ተመደብኩ። የአገልግሎት ጓደኛዬ ከሆነችው ወጣት እህት ጋር በቀጥታ ከኒው ዮርክ ወደ አዲሱ የአገልግሎት ምድቤ ተጓዝኩ። በፔሩ ስፓንኛ የተማርኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ባለበት ሕንፃ ላይ በላይኛው ፎቅ በሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ መኖር ጀመርኩ። በሊማ መስበክም ሆነ የአገሬው ተወላጅ ከሆኑት ወንድሞችና እህቶች ጋር መተዋወቅ በጣም ያስደስታል።

ሌላ ምድብና ሌላ ቋንቋ

ከጊዜ በኋላ በግሪክ ያሉት ዘመዶቼ ከእርጅናና ከጤና እክል የተነሳ አቅም እያጡ መጡ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን አቋርጬ የራሴን ሕይወት በመጀመር እንድረዳቸው አንድም ቀን ጠይቀውኝ አያውቁም። ሆኖም ብዙ ካሰብኩበትና ከጸለይኩበት በኋላ ወደ ቤተሰቦቼ ቀረብ ብዬ ባገለግል የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ተገነዘብኩ። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችም ያቀረብኩትን ሐሳብ በደስታ ተቀብለው ጣሊያን የመደቡኝ ሲሆን ዘመዶቼ ደግሞ ለመጓጓዣ የሚያስፈልገኝን ወጪ ሸፈኑልኝ። በእርግጥም ጣሊያን ውስጥ ተጨማሪ ወንጌላውያን ያስፈልጉ ነበር።

አሁንም በድጋሚ አዲስ ቋንቋ ማለትም ጣሊያንኛ መማር ነበረብኝ። መጀመሪያ ፎጃ በምትባል ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ። በኋላ ላይ ግን የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ኔፕልስ ተዛወርኩ። የአገልግሎት ክልሌ ኔፕልስ ውስጥ ከሚገኙ በጣም ውብ ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው ፖዚሊፖ ነበር። ክልሉ በጣም ሰፊ ከመሆኑም በላይ በአካባቢው የነበረው አንድ የመንግሥቱ አስፋፊ ብቻ ነበር። ሥራው አስደሳች ነበር፤ ይሖዋም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዳስጀምር ረድቶኛል። ከጊዜ በኋላ በዚህ አካባቢ ትልቅ ጉባኤ ተቋቁሟል።

በመጀመሪያ ሳስጠናቸው ከነበሩት የክልሉ ነዋሪዎች መካከል አንድ እናትና አራት ልጆቿ ይገኙበታል። ይህች እናትና ሁለት ሴት ልጆቿ አሁን ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። አንዲት ትንሽ ልጅ ያለቻቸው ባልና ሚስትም አስጠና ነበር። ሁሉም በእውነት ውስጥ እድገት ያደረጉ ሲሆን ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ ልጅቷ አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ያገባች ሲሆን ሁለቱም አምላክን በቅንዓት እያገለገሉ ነው። ከአንድ ትልቅ ቤተሰብ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ላይ ሳለሁ የአምላክ ቃል ያለውን ከፍተኛ ኃይል ተመልክቻለሁ። አምላክ በምስሎች የሚቀርብለትን አምልኮ እንደማይቀበል የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች እንዳነበብን እናትየው ጥናቱ እስኪያልቅ እንኳ መታገስ አልቻለችም። ወዲያውኑ ተነሳችና ቤቷ ውስጥ ያሉትን ምስሎች በሙሉ አስወገደች!

የባሕር አደጋ

ከጣሊያን ወደ ግሪክ ስመላለስ ሁልጊዜ የምጓዘው በመርከብ ነበር። እንዲህ ያለው ጉዞ ብዙውን ጊዜ አስደሳች ነው። ሆኖም በ1971 በጋ ላይ ያደረግሁት ጉዞ ለየት ያለ ነበር። ኤሌና በተባለ የመጓጓዣ ጀልባ ወደ ጣሊያን በመመለስ ላይ ነበርኩ። ነሐሴ 28 ማለዳ ላይ በጀልባው ኩሽና ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ተነሳ። እሳቱ እየተዛመተ ሲመጣ በተሳፋሪዎቹ መሃል ድንጋጤ ተፈጠረ። ሴቶች ራሳቸውን ስተው ይወድቁ ጀመር፣ ልጆች ደግሞ ያለቅሳሉ፣ ወንዶችም በብስጭት ይጮኹና ይቆጡ ነበር። ሰዎች ሕይወት አድን ጀልባዎች ወደሚገኙባቸው አቅጣጫዎች ይሮጡ ጀመር። ሆኖም የነበሩት መንሳፈፊያ ጃኬቶች በቂ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ ጀልባዎቹን ወደ ባሕሩ የሚያወርደው መሣሪያ በደንብ አይሠራም ነበር። መንሳፈፊያ ጃኬት አልነበረኝም፤ እንደዚያም ሆኖ እሳቱ ይበልጥ እየተባባሰ በመምጣቱ የነበረኝ ብቸኛ አማራጭ ወደ ባሕሩ ዘልሎ መግባት ነበር።

ባሕሩ ውስጥ እንደገባሁ በአቅራቢያዬ መንሳፈፊያ ጃኬት የለበሰች አንዲት ሴት ውኃው ላይ ተንሳፍፋ ተመለከትኩ። መዋኘት እንደማትችል ስለጠረጠርኩ እየሰጠመ ከነበረው ጀልባ ለማራቅ ስል ክንዷን ይዤ ጎተትኳት። የባሕሩ ሞገድ እያየለ በመምጣቱ ተንሳፍፌ ለመቆየት የማደርገው ጥረት እጅግ አድካሚ ሆነብኝ። ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጠኝ ደጋግሜ በመለመኔ ብርታት አገኘሁ። ሁኔታው ሐዋርያው ጳውሎስ ያጋጠመውን የመርከብ አደጋ እንዳስታውስ አደረገኝ።—የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 27

ትንሽ ብርታት ሳገኝ እየዋኘሁ እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳኝ እየጮኽኩ ሴትየዋን ሙጭጭ አድርጌ ይዤ ለአራት ሰዓታት ያህል ከሞገዱ ጋር ታገልኩ። መጨረሻ ላይ አንድ ትንሽ ጀልባ ወደ እኛ ሲቃረብ ተመለከትኩ። ሰዎች የደረሱልን ቢሆንም ሴትየዋ ግን ሞታ ነበር። በሕይወት የተረፍነው ጣሊያን፣ ባሪ ከተማ እንደደረስን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ እንዲደረግልኝ ወደ አንድ ሆስፒታል ተወሰድኩ። በሆስፒታሉ በቆየሁባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እየመጡ የጠየቁኝ ሲሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ በደግነት አሟልተውልኛል። በሆስፒታሉ ተኝተው የነበሩ ሌሎች ሰዎች ወንድሞችና እህቶች ያሳዩኝ በነበረው ክርስቲያናዊ ፍቅር በእጅጉ ተነክተው ነበር። b

ሙሉ ለሙሉ ካገገምኩ በኋላ ሮም ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚህ ጊዜ የተሰጠኝ ክልል በመሃል ከተማ ውስጥ የሚገኘው የንግድ አካባቢ ሲሆን በይሖዋ እርዳታ ለአምስት ዓመታት ያህል ሠርቼበታለሁ። ጣሊያን ውስጥ በአጠቃላይ 20 አስደሳች ዓመታት በአገልግሎት አሳልፌያለሁ፤ ጣሊያናውያንንም ወድጃቸዋለሁ።

አቅኚነት ወደጀመርኩበት ተመለስኩ

የአሪያንና የባለቤቷ ጤንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጣ። ወደ እነሱ ይበልጥ ቀረብ ብዬ ብኖር በፍቅር ተነሳስተው ላደረጉልኝ ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን ውለታቸውን መክፈል እንደምችል ተሰማኝ። በእውነቱ ጣሊያንን ለቅቆ መሄድ በጣም ከብዶኝ ነበር። ሆኖም በኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች ፈቅደውልኝ፣ ከ1985 የበጋ ወራት አንስቶ በ1947 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በጀመርኩበት በአቴንስ አቅኚ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ።

በተመደብኩበት ጉባኤ ክልል ውስጥ እያገለገልኩ በመሃል ከተማ በሚገኝ የንግድ አካባቢ መስበክ እችል እንደሆነ ቅርንጫፍ ቢሮውን ጠየቅሁ። ይህንንም ከአንዲት አቅኚ ጋር ሆኜ ለሦስት ዓመት ያህል ሠራሁ። በመኖሪያ ቤታቸው ብዙም ለማይገኙ ሰዎች መጠነ ሰፊ ምሥክርነት ለመስጠት ችለናል።

ዕድሜዬ እየገፋ ሲሄድ ለማገልገል ያለኝ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም አካላዊ ጥንካሬዬ ግን እየተዳከመ ነው። በአሁን ሰዓት የእህቴ ባል በሞት አንቀላፍቷል። እንደ እናት ሆና ያሳደገችኝ አሪያን ደግሞ ማየት ተስኗታል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኩባቸው ጊዜያት ጥሩ ጤንነት ነበረኝ። በቅርቡ ግን ከአንድ የእምነበረድ ደረጃ ላይ በመውደቄ ቀኝ እጄ ተሰበረ። ከዚያ በኋላ ደግሞ እንደገና ወድቄ የዳሌዬ አጥንት ተሰበረ። ቀዶ ሕክምና ማድረግ የነበረብኝ ሲሆን ለረጅም ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ሆኜ ነበር። አሁን እንደልቤ መሄድ አልችልም። ምርኩዝ የምጠቀም ሲሆን ከቤት ለመውጣት ግን የሰው ድጋፍ ያስፈልገኛል። ሆኖም አካላዊ ጤንነቴ እየተሻሻለ እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ የቻልኩትን ያህል ከማድረግ ወደኋላ አልልም። መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ በመጠኑም ቢሆን የማደርገው ተሳትፎ አሁንም ዋነኛ የደስታና የእርካታ ምንጭ ሆኖልኛል።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን አስደሳች ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ልቤ ለይሖዋ ባለው የአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። ይሖዋና ድርጅቱ የሚሰጡኝ አስተማማኝ መመሪያና ወደር የማይገኝለት ድጋፍ ምንጊዜም አልተለየኝም። ይህም እርሱን በሙሉ አቅሜ እንዳገለግል አስችሎኛል። አሁንም ቢሆን የልቤ ምኞት ይሖዋ ብርታት ሰጥቶኝ እርሱን ማገልገል እቀጥል ዘንድ ነው። ይሖዋ በሚመራው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ዓለም አቀፋዊ ሥራ ላይ ትንሽም ቢሆን አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ ደስታ ይሰማኛል።—ሚልክያስ 3:10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የ1995 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 73-89 ተመልከት።

b ለተጨማሪ ማብራሪያ ንቁ! የካቲት 8, 1972 (እንግሊዝኛ) ገጽ 12-16 ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ጊልያድ ልሄድ ስል፣ ከእህቴ ከአሪያንና ከባለቤቷ ከሚካሊስ ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ሩት ሄሚግ ኢስታንቡል፣ ቱርክ ተመደብን

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጣሊያን

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሁን ከእህቴ ከአሪያን ጋር