ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል
ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል
“ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል።” (መዝሙር 110:3) እነዚህ ቃላት፣ ለ46ቱ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 118ኛ ክፍል ተማሪዎች ልዩ ትርጉም አላቸው። ተማሪዎቹ፣ ወደ ሌላ አገር ሄደው የሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያረኩ ዕጩ ሚስዮናውያን በሚሠለጥኑበት በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ምን ዝግጅት አድርገው ነበር? ማይክና ስቴሲ የተባሉ የ118ኛው ክፍል ተማሪዎች እንዲህ ብለዋል:- “ቀላል ኑሮ ለመምራት ያደረግነው ውሳኔ እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች እንዲቀንሱና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንድናተኩር ረድቶናል። በሥራው ዓለም ያገኘነው ስኬት መንፈሳዊ ግቦችን ወደ ጎን ገሸሽ እንዲያስደርገን ላለመፍቀድ ቆርጠን ነበር።” እንደ ማይክና ስቴሲ ሁሉ ሌሎቹ የዚህ ክፍል ተማሪዎችም ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረብ በአራት አህጉራት ውስጥ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው ለማገልገል ተዘጋጅተዋል።
ቅዳሜ መጋቢት 12, 2005 የተደረገውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት በተከታተሉት 6,843 ተሰብሳቢዎች ፊት ላይ ደስታ ይነበብ ነበር። የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ነው። ከ28 አገሮች ለመጡት እንግዶች ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረገላቸው በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ባለው ዋጋማነት ላይ አተኮረ። ከዚያም ዊልያም ሊዮን ፌልፕስ የተባሉ አሜሪካዊ መምህር “አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ የሚያውቅ ከሆነ በእርግጥም የተማረ ነው ሊባል ይችላል” ብለው መናገራቸውን ወንድም ጃራዝ ጠቀሰ። ዓለማዊ ትምህርት ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ግን ብልጫ አለው። ይህ ትምህርት ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውን የአምላክን እውቀት እንዲቀስሙ ይረዳቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) ወንድም ጃራዝ፣ ተመራቂዎቹ በመላው ዓለም በሚገኙ ከ98,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ከፍተኛ ድርሻ ለማበርከት ፈቃደኞች በመሆናቸው አመሰገናቸው።
ለተመራቂዎቹ የተሰጠ ወቅታዊ ማበረታቻ
ከሊቀ መንበሩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ ዊልያም ሳሙኤልሰን “በአምላክ ቤት ውስጥ፣ እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ በመዝሙር 52:8 ላይ የተመሠረተ ንግግር አቅርቦ ነበር። የወይራ ዛፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የልምላሜ፣ የውበትና የክብር ምሳሌ ተደርጎ እንደተጠቀሰ ተናገረ። (ኤርምያስ 11:16) ተናጋሪው ተማሪዎቹን ከወይራ ዛፍ ጋር በማወዳደር እንዲህ አለ:- “ሚስዮናዊ ሆናችሁ በተመደባችሁባቸው ቦታዎች የመንግሥቱን ስብከት ሥራችሁን በታማኝነት የምታከናውኑ ከሆነ ይሖዋ ውበትና ክብር እንዳላችሁ አድርጎ ይመለከታችኋል።” የወይራ ዛፍ የድርቅን ወቅት ተቋቁሞ ለማለፍ እንዲችል ረጃጅም ሥሮች ሊኖሩት ይገባል፤ በተመሳሳይ ተማሪዎቹ በባዕድ አገር በሚያገለግሉበት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የግድየለሽነት ዝንባሌ፣ ተቃውሞ ወይም ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም መንፈሳዊ ሥሮቻቸውን ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል።—ማቴዎስ 13:21፤ ቆላስይስ 2:6, 7
በፕሮግራሙ ከተካፈሉት ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት መካከል አንዱ የሆነው ጆን ባር “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቅርቦ ነበር። (ማቴዎስ 5:13) ወንድም ባር፣ ጨው ምግብን ከብልሽት እንደሚጠብቅ ሁሉ ሚስዮናውያኑ ስለ አምላክ መንግሥት መስበካቸው ሰሚ ጆሮ ያላቸውን ሰዎች ከሥነ ምግባርና ከመንፈሳዊ ብልሽት በመጠበቅ ሕይወት አድን ውጤት እንደሚያመጣ ገለጸላቸው። ከዚያም ከሌሎች ጋር “ተስማሙ” በማለት ለተመራቂዎቹ አባታዊ ምክር ሰጣቸው። (ማርቆስ 9:50) አክሎም “የመንፈስ ፍሬዎችን አዳብሩ፤ ምንጊዜም ጸባያችሁና ንግግራችሁ ደግነትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ይሁን” በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው።
“ጥልቅ በሆነ ባሕር ላይ ካለው መርከብ አትውረዱ” የሚለውን ጭብጥ ያጎላው ደግሞ ከጊልያድ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ነበር። በጥልቅ ባሕር ላይ ያለ መርከብ ትክክለኛ አቅጣጫውን ይዞ መጓዝ ይችላል። በተመሳሳይ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” ማለትም ከእርሱ ዓላማ ጋር የተያያዙትን እውነቶችና ዓላማው እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ መረዳት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ይረዳል። (1 ቆሮንቶስ 2:10) “የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት” ብቻ በማወቃችን ረክተን ጥልቀት በሌለው መንፈሳዊ ውኃ ላይ የምንቆይ ከሆነ እድገታችን ሊገደብ አልፎ ተርፎም “ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደሚጠፋ መርከብ [እምነታችን]” የመጥፋቱ አጋጣሚ ከፍ ሊል ይችላል። (ዕብራውያን 5:12, 13፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19) ወንድም ሊቨረንስ “‘ጥልቅ የሆነው የእግዚአብሔር ጥበብና ዕውቀት ባለጠግነት’ በሚስዮናዊ አገልግሎታችሁ ይደግፋችሁ” በማለት ንግግሩን ደመደመ።—ሮሜ 11:33
ማርክ ኑሜር የተባለ ሌላ የጊልያድ አስተማሪ ደግሞ “ያገኛችሁትን ውርስ ጠብቃችሁ ትኖራላችሁ?” በሚል ርዕስ ንግግር አቅርቦ ነበር። ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፣ የትምህርት ቤቱ ተመራቂዎች በሚሰጡት ግሩም ‘ምስክርነት’ ምክንያት ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት ተአማኒነት እንዳተረፈና መልካም ስም እንደያዘ ሊቆይ ችሏል። (ዘፍጥረት 31:48) ይህ ውርስ ለ118ኛው ክፍል ተማሪዎችም ተላልፏል። ወንድም ኑሜር ተማሪዎቹ በነህምያ ዘመን የነበሩትን የቴቁሐ ሰዎች እንዲኮርጁና በተመደቡበት አገር ካለው ጉባኤም ሆነ ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር በትሕትና እንዲተባበሩ አበረታታቸው። ተመራቂዎቹ ነህምያ እንደጠቀሳቸው ‘መኳንንት’ ኩሩ እንዳይሆኑና የሚሠሯቸውን ነገሮች በታይታ መንፈስ ከማከናወን መራቅ እንደሚገባቸው ጥብቅ ምክር ተሰጥቷቸዋል።—ነህምያ 3:5
ትምህርት ሰጪ ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች
ቀጣዩ ፕሮግራም ደግሞ “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ” የሚል ርዕስ ነበረው። (የሐዋርያት ሥራ 6:7) የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ሎውረንስ ቦወን ባቀረበው በዚህ ክፍል ላይ ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት በመስክ አገልግሎት ሲካፈሉ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ አሳዩ። ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል በቅንዓት እንደሰበኩና ይሖዋም ጥረታቸውን አብዝቶ እንደባረከላቸው ከተሞክሮዎቹ መረዳት ተችሏል።
ሪቻርድ አሽ ከትምህርት ቤቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለሚሠሩ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር። የተሰጠው አስተያየት እንደሚያመለክተው የጊልያድ ተማሪዎች ከትምህርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ትልቅ እርዳታ ያደርጉላቸው ነበር። ከዚያም ጄፍሪ ጃክሰን ከጥቂት የቀድሞ የጊልያድ ተመራቂዎች ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። እነዚህ ወንድሞች ሚስዮናውያን ለይሖዋ ምስጋናና ክብር ለማምጣት የሚያስችሏቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉ ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ሚስዮናዊ ሆናችሁ የምታከናውኑትን እያንዳንዱን ነገር ይከታተላሉ። ያዳምጣሉ፣ ይመለከታሉ እንዲሁም ያስታውሳሉ።” በመሆኑም ተማሪዎቹ በማንኛውም ጊዜ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን እንዲጥሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ግሩም ምክር ወደፊት በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው አያጠራጥርም።
ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት “‘የሕይወትን ውሃ’ ማካፈላችሁን ቀጥሉ” የሚል ርዕስ ያለውን የመደምደሚያ ንግግር አቀረበ። (ዮሐንስ 7:38) ተማሪዎቹ ላለፉት አምስት ወራት የአምላክን ቃል እውነት እስኪረኩ ድረስ በመጠጣት ይህ ነው የማይባል ጥቅም እንዳገኙ ገለጸ። ይሁን እንጂ የቀሰሙትን እውቀት እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል? ወንድም ሌት ተመራቂዎቹ ይህን መንፈሳዊ ውኃ ምንም ሳይሰስቱ ለሌሎች እንዲያካፍሉ አጥብቆ አሳሰባቸው፤ እንዲህ ካደረጉ ሌሎች “የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ” እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። (ዮሐንስ 4:14) አክሎም “‘ሕያው የውሃ ምንጭ ለሆነው’ ለይሖዋ የሚገባውን ክብርና ምስጋና መስጠታችሁን አትዘንጉ። ድርቅ የመታትን ታላቂቱን ባቢሎን ለቅቀው የሚወጡ ሰዎችን በምታስተምሩበት ጊዜ ትዕግሥት ይኑራችሁ” ብሏል። (ኤርምያስ 2:13) ከዚያም ተመራቂዎቹ መንፈሱንና ሙሽራይቱን በቅንዓት በመኮረጅ “ና” ማለታቸውንና “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ ማቅረባቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታታት ንግግሩን ደመደመ።—ራእይ 22:17
ወንድም ጃራዝ ከተለያዩ አገሮች የተላኩ ሰላምታዎችን በማንበብ ፕሮግራሙን ደመደመ። ከዚህ በኋላ ከተመራቂዎቹ አንዱ የምስጋና ደብዳቤ አነበበ።
አንተስ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደህ ለማገልገል ራስህን በፈቃደኝነት ማቅረብ ትችላለህ? ከሆነ ተመራቂዎቹ እንዳደረጉት መንፈሳዊ ግቦችህን ለማሳካት ተጣጣር። ሚስዮናዊ ሆነህ በውጪ አገር በማገልገል ወይም ደግሞ በመኖሪያ አካባቢህ በማገልገል፣ ራስን በፈቃደኝነት ለአምላክ አገልግሎት ማቅረብ የሚያስገኘውን ደስታና እርካታ ቅመስ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 8
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 19
የተማሪዎቹ ብዛት:- 46
አማካይ ዕድሜ:- 33.0
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16.5
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.9
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 118ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ብሮክማይር አኒታ፣ መሎኒ ስቴሲ፣ ሲመንድዝ ኑንሲያ፣ ሎፔዝ ኢሴላ፣ ሃዋርድ ካሚል (2) ጃዝድሬብስኪ ትዊያ፣ ብራውን ዳንየል፣ ሄርናንዴስ ሄለን፣ ማላጎን አይሪን፣ ጆንስ አራሴሊስ፣ ኮኔል ሊኔት (3) ሃዋርድ ጆዲ፣ ላሩ ኢስተር፣ ሻምስ ቢትረስ፣ ሄየስ ሳሻ፣ ብራውን ኦስካር (4) በረል ጄኒፈር፣ ሃመር ሜላኒ፣ ሜየር አሊግዛንድራ፣ ኪም ኬ፣ ስታንሊ ሬቸል፣ ሬኒ ሮዛሊያ (5) ጃዝድሬብስኪ ፕዮተር፣ ዚለቬትዝ ካሪ፣ ፌረስ ሼሊ፣ ቶሬስ ቤለን፣ ቶሬስ ፌርናንዶ (6) ኮኔል ጆሴፍ፣ ሄርናንዴስ ራፋኤል፣ መሎኒ ማይክል፣ ማላጎን ሆርሄ፣ ሻምስ ሬዛ፣ ሄየስ ጄሲ (7) ፌረስ አለን፣ ሃመር ጆን፣ ስታንሊ ግራንት፣ ኪም ቻርሊ፣ ሲመንድዝ ስቴፈን፣ ሎፔዝ ዳንየል፣ በረል ዴሪክ (8) ብሮክማይር ዶነቨን፣ ሜየር ዩርገን፣ ሬኒ ሻነን፣ ዚለቬትዝ ስቴፈን፣ ጆንስ ራየን፣ ላሩ ጆኤል