“በቃ ተገላገልን”
“በቃ ተገላገልን”
የይሖዋ ምሥክሮች በ2002 በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ እምባንዳካ በምትባል ከተማ ውስጥ የአውራጃ ስብሰባ አድርገው ነበር። በስብሰባው ላይ የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በሊንጋላ ቋንቋ ታትሞ እንደወጣ ማስታወቂያ ሲነገር ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ከደስታቸው የተነሳ ቃል በቃል የዘለሉ ነበሩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የደስታ እንባ አንብተዋል። በኋላ ላይ ሰዎቹ “ባሱኪ ባሳምብዊ” ማለትም “በቃ ተገላገልን! ከእንግዲህ አንገታቸውን ይድፉ!” እያሉ አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ በደንብ ለማየት በፍጥነት ወደ መድረኩ ሄዱ።
ተሰብሳቢዎቹ ይህን ያህል የተደሰቱት ለምን ነበር? “በቃ ተገላገልን!” ሲሉስ ምን ማለታቸው ነበር? እምባንዳካ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሊንጋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አይችሉም ነበር። ለምን? ምክንያቱም አብያተ ክርስቲያናት ለይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለመሸጥ ፈቃደኞች ስላልነበሩ ነው። ወንድሞችና እህቶች መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት ከፈለጉ ሌላ ሰው እንዲገዛላቸው መጠየቅ ነበረባቸው። አብያተ ክርስቲያናት ከአሁን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያገኙ ሊከለክሏቸው ስለማይችሉ በጣም ተደስተዋል።
ከአዲሱ ትርጉም ተጠቃሚ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡ በአጠቃላይ ነው። መኖሪያ ቤቱ ሆኖ በድምፅ ማጉያዎች ፕሮግራሙን ያዳመጠ አንድ ግለሰብ ለይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በመውጣቱ በጣም ተደስቻለሁ። ብዙ እውቀት ያስገኝልናል። እኔ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም፤ ሆኖም ይህን መጽሐፍ ቅዱስ የማገኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።”
የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሙሉ ለሙሉ በ32 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ደግሞ ሊንጋላን ጨምሮ በ18 ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል። የዚህ ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቅጂ እንዲኖርህ ከፈለግህ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጠየቅ ትችላለህ።