በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

አልበርት ደስታ የሰፈነበት ትዳርና ሁለት የሚያማምሩ ልጆች ያሉት ሰው ነበር። ያም ሆኖ በሕይወቱ ውስጥ የሚጎድለው ነገር እንዳለ ይሰማው ነበር። ሥራ ለማግኘት ጥረት በሚያደርግበት አንድ ወቅት ላይ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መካፈል ጀመረና የሶሻሊዝምን ጽንሰ ሐሳብ ተቀበለ። እንዲያውም በአካባቢው የሚገኝ የአንድ ኮሚኒስት ፓርቲ አባል በመሆን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ።

ሆኖም ብዙ ሳይቆይ አልበርት ኮሚኒዝም እንደጠበቀው እንዳልሆነለት ተገነዘበ። ስለዚህ በፖለቲካ ውስጥ የሚያደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ አቋረጠና ሙሉ ትኩረቱን ቤተሰቡ ላይ አደረገ። እንዲያውም ቤተሰቡን ማስደሰት የሕይወቱ ዋነኛ ዓላማ ሆነ። ይሁን እንጂ አልበርት የሚሰማው የባዶነት ስሜት ከውስጡ ሊጠፋ አልቻለም። እውነተኛ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት አልሆነለትም።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው አልበርት ብቻ አይደለም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ሲሉ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳቦችን፣ ፍልስፍናዎችን እንዲሁም ሃይማኖቶችን ሞክረዋል። በ1960ዎቹ ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ብቅ ብሎ የነበረው የሂፒዎች ንቅናቄ ዘመናት ያስቆጠሩትን ሥነ ምግባራዊና ማኅበራዊ እሴቶች የሚጻረር ነበር። በተለይ ደግሞ ወጣቶች አስተሳሰብን የሚያዛቡ ዕፆችን በመውሰድ እንዲሁም የንቅናቄው መንፈሳዊ መሪዎች በሚያራምዱት ፍልስፍና በመመራት ደስታና የሕይወት ትርጉም ለማግኘት ይጥሩ ነበር። የሆነ ሆኖ የሂፒዎች ንቅናቄ እውነተኛ ደስታ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል። ከዚህ ይልቅ ዕፅ ሱሰኞችንና ሴሰኛ ወጣቶችን በማፍራት ኅብረተሰቡ ያለበት የሥነ ምግባር ግራ መጋባት እንዲባባስ አድርጓል።

ለበርካታ መቶ ዘመናት ብዙዎች ከሀብት፣ ከሥልጣን ወይም ከከፍተኛ ትምህርት ደስታን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም እንዲህ ያለው ጥረት ውሎ አድሮ ወደ ሐዘን መምራቱ አይቀርም። ኢየሱስ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ” አለመሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 12:15) ከዚህ ይልቅ ሀብት ለማጋበስ ቆርጦ መነሳት ብዙውን ጊዜ ለሐዘን ይዳርጋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ . . . ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ሲል ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

ታዲያ አንድ ሰው ውስጣዊ ሰላም ማግኘትና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የሚችለው እንዴት ነው? ጨለማ ውስጥ የተቀመጠን ዒላማ ለመምታት ጥረት የማድረግን ያህል እንዲያው በሙከራ የሚገኝ ነው? እንዲህ ባለመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው መፍትሔው የሰው ልጆች ብቻ ያላቸውን አንድ አስፈላጊ ፍላጎት ማሟላት መቻል ነው።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀብት፣ ሥልጣን፣ አሊያም ትምህርት ማሳደድ ውስጣዊ ሰላም እንድታገኝ ይረዳሃል?