በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

“ጻድቃን ሥልጣን ሲይዙ ሕዝብ ሐሤት ያደርጋል፤ ክፉዎች ሲገዙ ግን ሕዝብ ያቃስታል።” (ምሳሌ 29:2) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ የዚህን ምሳሌ እውነተኝነት በግልጽ ያሳያል። መጽሐፉ የሰሎሞንን የሕይወት ታሪክ ይዘግባል፤ በእርሱ የንግሥና ዘመን በእስራኤል ሰላምና ብልጽግና ሰፍኖ ነበር። በተጨማሪም አንደኛ ነገሥት፣ ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ብሔሩ ለሁለት ስለመከፈሉ እንዲሁም ከሰሎሞን በኋላ በእስራኤልና በይሁዳ ስለገዙ 14 ነገሥታት የሚገልጽ ታሪክ ይዟል። ከእነዚህ ነገሥታት መካከል እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ የሆኑት ሁለቱ ብቻ ነበሩ። ከዚህም በላይ ኤልያስን ጨምሮ ስድስት ነቢያት የፈጸሟቸውን ድርጊቶች አስፍሯል።

መጽሐፉን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሆኖ የጻፈው ነቢዩ ኤርምያስ ሲሆን ከ1040 እስከ 911 ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን ወደ 129 የሚጠጉ ዓመታት ታሪኮች ይዟል። ኤርምያስ መጽሐፉን ሲያጠናቅር ‘የሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍን’ የመሳሰሉ ጥንታዊ ጽሑፎችን አገላብጧል። እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች በአሁኑ ጊዜ የሉም።—1 ነገሥት 11:41፤ 14:19፤ 15:7

ጠቢብ ንጉሥ ሰላምና ብልጽግና እንዲሰፍን ያደርጋል

(1 ነገሥት 1:1 እስከ 11:43)

አንደኛ ነገሥት ዘገባውን የሚጀምረው የንጉሥ ዳዊት ልጅ አዶንያስ የአባቱን ንግሥና ያለ አግባብ ለመውረስ ስላደረገው ሙከራ በሚገልጸው የሚያጓጓ ታሪክ ነው። ነቢዩ ናታን በወሰደው ፈጣን እርምጃ ይህ እቅድ ከተጨናገፈ በኋላ ሌላው የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ነገሠ። ይሖዋ አዲስ የተሾመው ንጉሥ ባቀረበው ጥያቄ በመደሰት “ጥበብና አስተዋይ ልቡና” እንዲሁም “ብልጽግናና ክብር” ሰጥቶታል። (1 ነገሥት 3:12, 13) የንጉሡ ጥበብ አቻ የለውም፤ በሀብቱም ቢሆን የሚተካከለው አልተገኘም። ጊዜው ለእስራኤል የሰላምና የብልጽግና ዘመን ሆነላት።

ሰሎሞን ካከናወናቸው የግንባታ ሥራዎች መካከል የይሖዋ ቤተ መቅደስና በርካታ የአስተዳደር ሕንጻዎች ይገኙበታል። ይሖዋ፣ ሰሎሞን በታዛዥነት ከቀጠለ የሚያደርግለትን ሲገልጽ “ዙፋንህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ” ብሎታል። (1 ነገሥት 9:4, 5) እውነተኛውን አምላክ አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን ውጤቶችም ጠቁሞታል። ሆኖም ንጉሡ የኋላ ኋላ በርካታ ባዕዳን ሚስቶችን አገባ። እነዚህ ሚስቶቹ ባደረጉበት ተጽዕኖ በስተርጅናው የሐሰት አምልኮ መከተል ጀመረ። በዚህ ምክንያት ይሖዋ መንግሥቱ እንደሚከፈል በትንቢት ተናገረ። ሰሎሞን በ997 ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም በነገሠ በ40ኛው ዓመት ሞተ። ልጁ ሮብዓምም በእግሩ ተተካ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

1:5—አዶንያስ ዳዊት ገና በሕይወት እያለ ለመንገሥ የሞከረው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚገልጸው ነገር የለም። የአዶንያስ ታላላቅ ወንድሞች የሆኑት አምኖን፣ አቤሴሎምና ምናልባትም ኪልአብ በዚያን ጊዜ በሕይወት አልነበሩም። በመሆኑም አዶንያስ ከቀሩት የዳዊት ወንዶች ልጆች ትልቁ እርሱ እንደመሆኑ መጠን ዙፋኑን የመውረስ መብት እንዳለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። (2 ሳሙኤል 3:2-4፤ 13:28, 29፤ 18:14-17) አዶንያስ፣ ኃያሉ የጦር መሪ ኢዮአብና ከፍተኛ ተሰሚነት የነበረው ሊቀ ካህኑ አብያታር ድጋፍ ስላደረጉለት ሙከራው የሚሳካለት ሳይመስለው አልቀረም። ዳዊት ዙፋኑን ለሰሎሞን የማውረስ እቅድ እንዳለው አዶንያስ የሚያውቀው ነገር መኖር አለመኖሩን መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ይሁን እንጂ ‘መሥዋዕት’ በሠዋበት ጊዜ ሰሎሞንንና ሌሎች ታማኝ የዳዊት ደጋፊዎችን አልጠራም። (1 ነገሥት 1:9, 10) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አዶንያስ ሰሎሞንን እንደ ተቀናቃኝ አድርጎ ይመለከተው ነበር።

1:49-53፤ 2:13-25ሰሎሞን አዶንያስን ይቅር ካለው በኋላ እንዲሞት ያደረገው ለምንድን ነው? ቤርሳቤህ ነገሩን አትገንዘበው እንጂ አዶንያስ አቢሳን ለማግባት ንጉሡን እንድትጠይቅለት አማላጅነት የላካት ለምን እንደሆነ ሰሎሞን ተረድቶ ነበር። ዳዊት ውብ ከነበረችው አቢሳ ጋር ምንም ግንኙነት ያላደረገ ቢሆንም እንደ ቁባቱ ተደርጋ ትታይ ነበር። በወቅቱ በነበረው ልማድ መሠረት አቢሳ የምትገባው ለዳዊት ሕጋዊ ወራሽ ብቻ ነበር። አዶንያስ እርሷን ካገባ ለመንገሥ በድጋሚ ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል አስቦ ሊሆን ይችላል። ሰሎሞን የአዶንያስ ጥያቄ የመንገሥ ምኞት ያለው መሆኑን እንደሚያሳይ ተገንዝቦ ይቅርታውን አነሳ።

6:37–8:2—ቤተ መቅደሱ የተመረቀው መቼ ነበር? የቤተ መቅደሱ ግንባታ የተጠናቀቀው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1027 በስምንተኛው ወር ማለትም በሰሎሞን 11ኛ የንግሥና ዘመን ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱ ቁሳቁሶችን ለማስገባትና ሌሎች ዝግጅቶችን ለማድረግ 11 ወራት ሳይፈጅ አልቀረም። ስለዚህ ምርቃቱ የተደረገው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1026 በሰባተኛው ወር መሆን አለበት። ዘገባው በወቅቱ የነበረውን የግንባታ ፕሮግራም በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለመስጠት የቤተ መቅደሱ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለ ምርቃቱ ከመናገሩ በፊት ስለተከናወኑት ሌሎች ግንባታዎች ይገልጻል።—2 ዜና መዋዕል 5:1-3

9:10-13—ሰሎሞን በገሊላ የሚገኙ 20 ከተሞችን ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም መስጠቱ ከሙሴ ሕግ ጋር አይጋጭም? በወቅቱ በዘሌዋውያን 25:23, 24 ላይ የተጠቀሰው ሕግ የሚሠራው እስራኤላውያን ለሚኖሩባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ይሆናል። ሰሎሞን ለኪራም የሰጣቸው ከተሞች በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘፀአት 23:31) ሰሎሞን የወሰደው እርምጃ ‘ብዙ ፈረሶችን ለራሱ በማብዛትና’ በርካታ ሚስቶችን በማግባት ሕጉን እንደጣሰ ሁሉ በተሟላ መልኩ ሕጉን እንዳልታዘዘ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (ዘዳግም 17:16, 17) ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኪራም በስጦታው አልረካም። ምናልባት አረማዊ የሆኑት ነዋሪዎች ከተሞቹን ጥሩ አድርገው አልያዟቸው ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ከተሞቹ አመቺ ቦታ ላይ አይገኙ ይሆናል።

11:4—ሰሎሞን ዕድሜው ሲገፋ ታማኝነቱን እንዲያጓድል ያደረገው መጃጀቱ ነው? ምክንያቱ ይሄ የነበረ አይመስልም። ሰሎሞን መግዛት ሲጀምር በጣም ወጣት ስለነበር ለ40 ዓመታት ቢገዛም መጃጀት ደረጃ ላይ አይደርስም። ከዚህም በላይ ይሖዋን ማምለኩን ሙሉ ለሙሉ አልተወም ነበር። ከዚህ ይልቅ ሃይማኖትን ለመቀላቀል ሳይሞክር አልቀረም።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

2:26, 27, 35 ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ሁልጊዜ ፍጻሜውን ያገኛል። የዔሊ ተወላጅ የሆነው አብያታር መባረሩ ‘እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት የተናገረው ቃል’ ፍጻሜ ነበር። በዘኁልቁ 25:10-13 ባለው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ደግሞ በአብያታር ፋንታ ሳዶቅ ተተክቷል።—ዘፀአት 6:25፤ 1 ሳሙኤል 2:31፤ 3:12፤ 1 ዜና መዋዕል 24:3

2:37, 41-46 የይሖዋን ሕግ እየጣሱ ከቅጣት አመልጣለሁ ብሎ ማሰብ በጣም አደገኛ ነው! ሆን ብለው ‘ወደ ሕይወት ከሚያደርሰው ቀጭን መንገድ’ የሚወጡ ሰዎች ይህ መጥፎ አካሄድ የሚያመጣባቸውን መዘዝ ይቀምሳሉ።—ማቴዎስ 7:14

3:9, 12-14 ይሖዋ አገልጋዮቹ የእርሱን ሥራ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ጥበብ፣ ማስተዋልና መመሪያ እንዲሰጣቸው ለሚያቀርቡት ልባዊ ጸሎት መልስ ይሰጣል።—ያዕቆብ 1:5

8:22-53 ሰሎሞን ይሖዋን ለፍቅራዊ ደግነቱ እንዲሁም የገባውን ቃል የሚፈጽምና ጸሎት ሰሚ አምላክ በመሆኑ ከልብ አመስግኖታል! ሰሎሞን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ በማሰላሰል፣ ለእነዚህና ለሌሎቹም የአምላክ ባሕርያት ያለንን አድናቆት ከፍ ማድረግ እንችላለን።

11:9-14, 23, 26 ሰሎሞን በእርጅና ዘመኑ ታዛዥ ሳይሆን ሲቀር ይሖዋ ጠላቶች አስነስቶበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ብሏል።—1 ጴጥሮስ 5:5

11:30-40 አኪያ ስለ ኢዮርብዓም በተናገረው ትንቢት ምክንያት ንጉሥ ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ፈልጎ ነበር። ይህ የንጉሡ ፍላጎት ከ40 ዓመት በፊት አዶንያስንና ሌሎች ሴረኞችን ላለመበቀል ከነበረው አቋም ፈጽሞ የተለየ ነበር! (1 ነገሥት 1:50-53) እንዲህ ያለ የአስተሳሰብ ለውጥ ያደረገው ከይሖዋ በመራቁ ምክንያት ነው።

አንድ የነበረ መንግሥት ለሁለት ተከፈለ

(1 ነገሥት 12:1 እስከ 22:53)

ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ወደ ንጉሥ ሮብዓም በመሄድ አባቱ ሰሎሞን የጫነባቸውን ቀንበር ቀለል እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። ሮብዓም ለጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከበፊቱ የባሰ ሸክም እንደሚጭንባቸው ዛተ። በመሆኑም አሥሩ ነገዶች በማመጽ ኢዮርብዓምን ንጉሣቸው አድርገው ሾሙ። በዚህ መንገድ መንግሥቱ ተከፈለ። ሮብዓም በስተ ደቡብ በሚገኙት የይሁዳና የብንያም ነገዶች ላይ ሲነግሥ ኢዮርብዓም በስተ ሰሜን ባሉት አሥሩ የእስራኤል ነገዶች ላይ መግዛት ጀመረ።

ኢዮርብዓም ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመከላከል ሲል ሁለት የወርቅ ጥጃዎች አዘጋጅቶ አንዱን ዳን ውስጥ ሌላውን ደግሞ በቤቴል አቆማቸው። ከኢዮርብዓም በኋላ በእስራኤል ከገዙት ነገሥታት መካከል ናዳብ፣ ባኦስ፣ ኤላ፣ ዘምሪ፣ ታምኒ፣ ዖምሪ፣ አክዓብና አካዝያስ ይገኙበታል። ከሮብዓም በኋላ በይሁዳ የተነሱት ነገሥታት ደግሞ አብያ፣ አሳ፣ ኢዮሣፍጥና ኢዮራም ናቸው። በእነዚህ ነገሥታት ዘመን የነበሩት ነቢያት አኪያ፣ ሳማያ፣ በስም ያልተጠቀሰ አንድ የእግዚአብሔር ሰው እንዲሁም ኢዩ፣ ኤልያስና ሚክያስ ናቸው።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

18:21—ኤልያስ እስራኤላውያን ይሖዋን አሊያም ደግሞ በኣልን እንዲያመልኩ ሲጠይቃቸው ዝም ያሉት ለምንድን ነው? ምናልባት እርሱ ብቻ ሊመለክ የሚገባውን ይሖዋን አለማምለካቸውን በመገንዘባቸው የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ኅሊናቸው ከመጠን በላይ በመደንዘዙ ምክንያት ይሖዋንም እያመለኩ በኣልንም ማምለክ እንደሚቻል ተሰምቷቸው ይሆናል። “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” ብለው የተናገሩት ይሖዋ ኃይሉን ካሳየ በኋላ ነው።—1 ነገሥት 18:39

20:34—አክዓብ በይሖዋ እርዳታ ሶርያውያንን ድል ካደረገ በኋላ ንጉሣቸውን ቤን ሀዳድን የማረው ለምንድን ነው? አክዓብ ንጉሥ ቤን ሀዳድን በመግደል ፈንታ በሶርያ ዋና ከተማ በደማስቆ የራሱን ገበያ ለማቋቋም ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አደረገ። ቀደም ብሎ የቤን ሀዳድ አባት ሰማርያ ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ ንግድ አቋቁሞ ነበር። በመሆኑም አክዓብ ቤን ሀዳድን በነጻ የለቀቀው በደማስቆ ገበያ ለማቋቋም ሲል ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

12:13, 14 በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን ስናደርግ መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቀው የሚያውቁ እንዲሁም የአምላክን መመሪያዎች ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ጥበበኛና የበሰሉ ሰዎችን ማማከር ይገባናል።

13:11-24 ምክር ያገኘነው የሚያስቡልን ከሚመስሉ የእምነት ወንድሞቻችን ቢሆንም እንኳን ምክሩ ወይም ሐሳቡ አጠያያቂ ከሆነ፣ ትክክለኛ መመሪያ በያዘው በመጽሐፍ ቅዱስ ልንመዝነው ይገባል።—1 ዮሐንስ 4:1

14:13 ይሖዋ በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ለማግኘት በጥንቃቄ ይመረምረናል። እርሱን ለማገልገል የተቻለንን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ፣ ያለን መልካም ነገር ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን እያደገ እንዲሄድ ይረዳናል።

15:10-13 ክህደትን በድፍረት መቃወምና እውነተኛውን አምልኮ ማስፋፋት ይገባናል።

17:10-16 የሰራፕታዋ መበለት ኤልያስ ነቢይ እንደሆነ በማመን ለነቢይ የሚገባውን መስተንግዶ አድርጋለታለች፤ ይሖዋም ይህንን የእምነት ሥራዋን ባርኮላታል። በተመሳሳይ ዛሬም ይሖዋ የእምነት ሥራዎቻችንን ልብ ብሎ ይመለከታል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ሥራ በተለያዩ መንገዶች ለሚደግፉ ተገቢውን ዋጋ ይከፍላል።—ማቴዎስ 6:33፤ 10:41, 42፤ ዕብራውያን 6:10

19:1-8 ከባድ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ይሖዋ እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7-9

19:10, 14, 18 እውነተኛ አምላኪዎች በጭራሽ ብቻቸውን አይደሉም። ይሖዋና በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻቸው ከጎናቸው ናቸው።

19:11-13 ይሖዋ እንዲያው የተፈጥሮ ኃይል አይደለም።

20:11 ቤን ሀዳድ ሰማርያን እንደሚያጠፋ ጉራውን ሲነዛ የእስራኤል ንጉሥ “ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው” በውጊያ ድል አድርጎ በመመለስ “የጦር ትጥቁን እንደ ፈታ ሰው መደንፋት የለበትም” የሚል መልስ ሰጥቶት ነበር። አዲስ ሥራ ለመሥራት በምንዘጋጅበት ወቅት ከመጠን በላይ በራሳችን በመተማመን ጉራችንን መንዛት የለብንም።—ምሳሌ 27:1፤ ያዕቆብ 4:13-16

ከመጽሐፉ የምናገኘው ጥቅም

ሙሴ በሲና ተራራ ሕጉ የተሰጠበትን ሁኔታ ለእስራኤላውያን ሲገልጽ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤ በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፣ መርገሙ ደግሞ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የማትፈጽሙ፣ . . . እኔ ከማዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው።”—ዘዳግም 11:26-28

የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ ይህን አስፈላጊ እውነት በግልጽ አስገንዝቦናል! በተጨማሪም መጽሐፉ ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶችንም እንደሚሰጥ ተመልክተናል። በእርግጥም የያዘው መልእክት ሕያውና የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤተ መቅደሱና ሰሎሞን ያስገነባቸው ሌሎች ሕንጻዎች

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን “እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” ብለው በመደነቅ የተናገሩት ይሖዋ ኃይሉን ካሳየ በኋላ ነው