በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ራሳችሁን ፈትኑ”

“ራሳችሁን ፈትኑ”

“ራሳችሁን ፈትኑ”

“በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ።”—2 ቆሮንቶስ 13:5

1, 2. (ሀ) ስለምናምንባቸው ነገሮች መጠራጠር ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ በሚገኝ ጉባኤ የነበሩ አንዳንዶች የትኛውን አቅጣጫ መከተል እንዳለባቸው ግራ እንዲጋቡ ያደረጋቸው ሁኔታ ምንድን ነው?

 ከከተማ ውጪ እየተጓዘ ያለ ሰው አንድ መንታ መንገድ ላይ ደረሰ። ወደሚፈልገው ቦታ የሚያደርሰው መንገድ የትኛው እንደሆነ እርግጠኛ ስላልሆነ በዚያ የሚያልፉትን ሰዎች አቅጣጫ ጠየቃቸው። የተሰጠው መልስ ግን የተለያየ ነበር። በነገሩ ግራ ስለተጋባ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም። እኛም ስለምናምንባቸው ነገሮች ጥርጣሬ ካደረብን ውጤቱ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው የጥርጣሬ ስሜት ውሳኔ የማድረግ ችሎታችንን ስለሚገድብብን በየትኛው መንገድ መጓዝ እንዳለብን ግራ እንድንጋባ ያደርጋል።

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ፣ ግሪክ በሚገኝ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትል የሚችል አንድ ሁኔታ ተከስቶ ነበር። “ታላላቅ ሐዋርያት” የሚባሉት “መልእክቶቹ ከባድና ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነቱ ሲታይ ደካማ፣ ንግግሩም የተናቀ ነው” በማለት የሐዋርያው ጳውሎስን ሥልጣን ተጋፍተዋል። (2 ቆሮንቶስ 10:7-12፤ 11:5, 6) እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች የትኛውን አቅጣጫ መከተል እንዳለባቸው ግራ እንዲጋቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

3, 4. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

3 ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኘውን ጉባኤ ያቋቋመው እዚያ በቆየበት በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። በቆሮንቶስ “የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማራቸው አንድ ዓመት ተኩል” ተቀመጠ። በወቅቱ “ጳውሎስ ሲናገር የሰሙ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ተጠመቁ።” (የሐዋርያት ሥራ 18:5-11) ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቹ መንፈሳዊ ደኅንነት በጥልቅ ያሳስበው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በዚያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ምክር እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጠይቀውት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 7:1) ከዚህ የተነሳ በጣም ግሩም የሆነ ምክር ሰጣቸው።

4 ጳውሎስ “በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” ሲል ጻፈላቸው። (2 ቆሮንቶስ 13:5) በቆሮንቶስ የሚኖሩ ወንድሞች ይህን ምክር በተግባር ቢያውሉ ኖሮ በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ እንዳለባቸው ጥርጣሬ አያድርባቸውም ነበር። በዛሬው ጊዜ ለእኛም ተመሳሳይ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ታዲያ የጳውሎስን ምክር መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲሁም ራሳችንን መፈተን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

“በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ”

5, 6. በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን ለመመርመር የሚረዳን የትኛው መሥፈርት ነው? ይህስ ትክክለኛ መሥፈርት ነው የሚባለው ለምንድን ነው?

5 በምርመራ ሂደት ላይ በአብዛኛው ምርመራ የሚደረግበት ሰው አሊያም አንድ ነገር የሚኖር ከመሆኑም ሌላ ምርመራው የሚከናወንበት መለኪያ ወይም መሥፈርት ያስፈልጋል። አሁን በተነሳው ጉዳይ ላይ ምርመራ የሚካሄድበት ነገር አምነን የተቀበልነው ትምህርት ይኸውም እምነታችን ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ እኛው ራሳችን ነን። ምርመራውን ለማካሄድ የሚያስችል ፍጹም መለኪያ አለን። መዝሙራዊው ዳዊት ያቀናበረው አንድ መዝሙር እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል።” (መዝሙር 19:7, 8) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ፍጹም ሕጎች፣ ትክክለኛ መመሪያዎችና የታመነ ሥርዓት እንዲሁም ብሩህ ትእዛዝ ይዟል። በዚያ ውስጥ የሚገኘው መልእክት አንድን ነገር ለመመርመር የሚያስችል ትክክለኛ መሥፈርት ነው።

6 አምላክ በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈውን ይህን መልእክት በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) አዎን፣ የአምላክ ቃል ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም ልባችንን ሊመረምር ይችላል። ይህን እንደ ስለት ዘልቆ የሚወጋና ለሥራ የሚያነሳሳ መልእክት በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙራዊው “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል” በማለት በዘመረ ጊዜ ይህ ምን ማድረግ እንደሚጠይቅ በግልጽ አስፍሮልናል። (መዝሙር 1:1, 2) ‘የይሖዋ ሕግ’ በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይገኛል። የይሖዋን ቃል የማንበብ ፍቅር ሊኖረን ይገባል። በእርግጥም፣ ቃሉን በተመስጦ ለማንበብ ወይም በቃሉ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ በጽሑፍ የሰፈረው ነገር እንዲመረምረን መፍቀድ አለብን።

7. በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የምንችልበት ዋናው መንገድ ምንድን ነው?

7 ስለዚህ በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የምንችልበት ዋናው መንገድ የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል እንዲሁም ካነበብነው ነገር ጋር ምን ያህል ተስማምተን እንደምንኖር ማጤን ነው። የአምላክን ቃል ለመረዳት የሚያስችለን ብዙ እርዳታ ስላለልን ደስተኞች መሆን እንችላለን።

8. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን ለመመርመር ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ይሖዋ፣ “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አማካኝነት ትምህርትና መመሪያ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ይሖዋ ቅረብ በተባለው መጽሐፍ በአብዛኞቹ ምዕራፎች መጨረሻ ላይ የሚገኘውን “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። a ይህ የመጽሐፉ ገጽታ ቆም ብለን ለማሰብ የሚረዳ ግሩም አጋጣሚ ይሰጠናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችም በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን እንድንመረምር ይረዱናል። በቅርብ ጊዜ በወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የሚገኙ በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የቀረቡ ማብራሪያዎችን የያዙ ርዕሶችን በተመለከተ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “እነዚህን ርዕሶች በጣም ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ንግግሬ፣ ባሕርዬና ዝንባሌዬ በእርግጥ ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ይስማማ እንደሆነ ለማወቅ ራሴን እንድመረምር ረድተውኛል።”

9, 10. በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን እንድንመረምር የሚያስችሉን ይሖዋ ያደረገልን ዝግጅቶች ምንድን ናቸው?

9 በተጨማሪም በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ትምህርትና ከፍተኛ ማበረታቻ እናገኛለን። እነዚህ አምላክ ለአገልጋዮቹ እርዳታ ከሰጠባቸው ዝግጅቶች መካከል አንዳንዶቹ ሲሆኑ ኢሳይያስ እነርሱን በተመለከተ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ። ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ . . . እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጐዳናውም እንሄዳለን።’” (ኢሳይያስ 2:2, 3) የይሖዋን መንገድ በተመለከተ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ማግኘት በእርግጥ በረከት ነው።

10 የጉባኤ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ክርስቲያኖች የሚሰጡንን ምክር ችላ ማለት የለብንም። እነርሱን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” (ገላትያ 6:1) እየተስተካከልን እንድንሄድ ለሚያስችለን ለዚህ ዝግጅት በጣም አመስጋኝ ልንሆን ይገባል!

11. በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር ምን ማድረግ ይጠይቃል?

11 ጽሑፎቻችን፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና የተሾሙ ወንዶች ከይሖዋ ያገኘናቸው ግሩም ዝግጅቶች ናቸው። ይሁንና በእምነት መሆናችንን መመርመር የራስን ሁኔታ መገምገምን ይጠይቃል። ስለዚህ ጽሑፎቻችንን ስናነብ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ስናዳምጥ ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘ይሄ ጉዳይ እኔን ይመለከታል? ደግሞስ እኔ የማደርገው ነገር ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በጥብቅ እከተላለሁ?’ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት ለምናገኘው ትምህርት ያለን አመለካከት በመንፈሳዊ ሁኔታችንም ላይ ተጽዕኖ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው” ይላል። “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል።” (1 ቆሮንቶስ 2:14, 15) በመጻሕፍታችን፣ በመጽሔቶቻችንና በሌሎች ጽሑፎች ላይ ለምናነባቸው ነገሮች እንዲሁም በስብሰባዎቻችን ላይና ከሽማግሌዎች ለምንሰማቸው ነገሮች አድናቆት የታከለበት መንፈሳዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ማድረግ አይኖርብንም?

“ራሳችሁን ፈትኑ”

12. ራስን መፈተን ምን ማድረግን ያካትታል?

12 ራሳችንን መፈተን የራስን አቋም መመዘንን ይጨምራል። አዎን፣ እውነት ውስጥ ልንሆን እንችላለን፤ ሆኖም መንፈሳዊ አቋማችን ምን ያህል ጠንካራ ነው? ራስን መፈተን በሳል መሆናችንንና ለመንፈሳዊ ዝግጅቶች ልባዊ አድናቆት እንዳለን ማሳየትን ያጠቃልላል።

13. በዕብራውያን 5:14 መሠረት ጎልማሳ መሆናችን የሚታየው በምንድን ነው?

13 ጎልማሳ ክርስቲያን መሆናችን የሚታየው በምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ጠንካራ ምግብ . . . መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 5:14) የማስተዋል ችሎታችንን ስናሠለጥን ብስለት ያለን ይኸውም ጎልማሳ ክርስቲያኖች መሆናችን ይታያል። አንድ አትሌት በሚወዳደርበት የስፖርት ዘርፍ የላቀ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ተደጋጋሚ ሥልጠና በማድረግ ጡንቻውን ማለማመድ እንዳለበት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድም የማስተዋል ችሎታችን ሥልጠና ማግኘት ይኖርበታል።

14, 15. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች ለማጥናት ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

14 ይሁንና የማስተዋል ችሎታችንን ለማሠልጠን በመጀመሪያ እውቀት ማግኘት ይኖርብናል። ለዚህም ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት ወሳኝ ነገር ነው። አዘውትረን የግል ጥናት ካደረግን በተለይ ደግሞ የአምላክን ቃል ጥልቅ ነገሮች ከመረመርን ብስለት እያገኘን ወይም የማስተዋል ችሎታችን እየዳበረ ይሄዳል። ባለፉት ዓመታት በመጠበቂያ ግንብ ላይ ጥልቀት ያላቸው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተብራርተዋል። ጥልቀት ያለው ትምህርት የያዙ ርዕሶች ሲያጋጥሙን ምን እናደርጋለን? እነዚህ ርዕሶች “በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች” ስለያዙ ብቻ ወደ ጎን ገሸሽ እናደርጋቸዋለን? (2 ጴጥሮስ 3:16) ከዚህ ይልቅ ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት ለመረዳት ተጨማሪ ጥረት እናደርጋለን።—ኤፌሶን 3:18

15 ይሁንና ማጥናት የማንወድ ቢሆንስ? የማጥናት ፍቅር ለማዳበር ወይም ለመኮትኮት ጥረት ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። b (1 ጴጥሮስ 2:2) ወደ ጉልምስና ለመድረስ የአምላክ ቃል የያዛቸውን ጥልቅ ትምህርቶች ማለትም ጠንካራ ምግብ በመመገብ መንፈሳዊነታችንን መገንባት ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን የማስተዋል ችሎታችን አንድ ቦታ ላይ ተገድቦ ይቀራል። ይሁን እንጂ ብስለት ወይም ጉልምስና እንዳለን የሚታየው የማስተዋል ችሎታ በማዳበር ብቻ አይደለም። ትጋት በተሞላበት የግል ጥናት አማካኝነት ያገኘነውን እውቀት በዕለታዊ ሕይወታችን በሥራ ማዋል ይኖርብናል።

16, 17. ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ‘የቃሉ አድራጊዎች’ ስለመሆን የሰጠው ምክር ምንድን ነው?

16 ለእውነት ያለንን አድናቆት የምንገልጽበት መንገድ ይኸውም የምናከናውናቸው የእምነት ሥራዎችም የእኛን ማንነት ያሳያሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አሳማኝ ምሳሌ በመጠቀም በዚህ ረገድ ራሳችንን እንዴት መመዘን እንደምንችል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል።”—ያዕቆብ 1:22-25

17 ያዕቆብ እንዲህ ማለቱ ነበር:- ‘እንደ መስተዋት የሆነውን የአምላክን ቃል በመመልከት ራሳችሁን ገምግሙ። እንዲህ በማድረግ ጽኑ፤ እንዲሁም ከአምላክ ቃል ላይ ባገኛችሁት ሐሳብ ራሳችሁን መርምሩ። ከዚያም ያያችሁትን ነገር ወዲያውኑ አትርሱ። አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጉ።’ ይህን ምክር መከተል አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆን ይችላል።

18. ያዕቆብ የሰጠውን ምክር መከተል ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?

18 ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ የመካፈልን አስፈላጊነት ተመልከት። ጳውሎስ “የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 10:10) በአፋችን መሥክረን ለመዳን በርካታ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልገናል። በስብከቱ ሥራ መካፈል ለአብዛኞቻችን ቀላል ነገር አይደለም። በዚህ ሥራ በቅንዓት መካፈልና በሕይወታችን ውስጥ ለሥራው ተገቢውን ቦታ መስጠት ብዙ ለውጦች ማድረግና መሥዋዕቶች መክፈል ይጠይቃል። (ማቴዎስ 6:33) ሆኖም አምላክ በሰጠን በዚህ ሥራ መካፈል ከጀመርን ይሖዋ በሥራው ስለሚከበር ደስ ይለናል። ታዲያ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ነን?

19. የምናከናውነው የእምነት ሥራ ምን ነገሮችን ሊያጠቃልል ይገባል?

19 የምናከናውነው የእምነት ሥራ ምን ያህል ስፋት ሊኖረው ይገባል? ጳውሎስ “ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማናቸውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 4:9) የተማርነውን፣ የተቀበልነውን፣ የሰማነውንና ያየነውን ነገር በተግባር ስናውል በሌላ አባባል በክርስትና ሕይወት ራስን መወሰንና ደቀ መዝሙር መሆን የሚያካትታቸውን ነገሮች ስናደርግ የእኛ ማንነት ይታያል። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል መመሪያ ሰጥቷል።—ኢሳይያስ 30:21

20. ለጉባኤው ትልቅ በረከት የሚሆኑት ምን ዓይነት ግለሰቦች ናቸው?

20 የአምላክ ቃል ትጉ ተማሪዎች፣ የምሥራቹ ቀናተኛ ሰባኪዎችና የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች የሆኑ እንዲሁም ክርስቲያናዊ አቋማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች ለጉባኤው ትልቅ በረከት ናቸው። የእነርሱ መኖር ላሉበት ጉባኤ ጥንካሬ ይጨምራል። በተለይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በጣም ብዙ አዳዲስ ክርስቲያኖች ስላሉ ለጉባኤው ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታሉ። ጳውሎስ “በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” ሲል የሰጠውን ምክር በጥንቃቄ የምንከተል ከሆነ እኛም በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር እንችላለን።

የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ተደሰቱ

21, 22. የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

21 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 40:8) ዳዊት የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር። ለምን? የይሖዋ ሕግ በዳዊት ልብ ውስጥ ስለነበረ ነው። ዳዊት የትኛውን አቅጣጫ ተከትሎ መጓዝ እንዳለበት ጥርጣሬ አልተሰማውም።

22 የአምላክ ሕግ በልባችን ውስጥ ከተቀመጠ በየትኛው መንገድ መጓዝ እንዳለብን ጥርጣሬ አይገባንም። የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እንደሰታለን። በመሆኑም ይሖዋን ከልባችን ስናገለግል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ‘ጥረት’ እናድርግ።—ሉቃስ 13:24

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b የአጠናን ዘዴን በተመለከተ ጠቃሚ ሐሳቦች ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 27-32 ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?

• ራስን መፈተን ምን ማድረግን ያካትታል?

• ክርስቲያናዊ ጉልምስና እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

• የምናከናውናቸው የእምነት ሥራዎች ማንነታችንን እንድንገመግም የሚረዱን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእምነት መሆንህን ለማወቅ ራስህን መመርመር የምትችልበት ዋናው መንገድ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማስተዋል ችሎታችንን ስንሠራበት ጎልማሳ ክርስቲያኖች መሆናችን ይታያል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን የቃሉ አድራጊዎችም በመሆን’ ማንነታችን ይታያል