በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሁሉም ነገር ታማኝ ናችሁ?

በሁሉም ነገር ታማኝ ናችሁ?

በሁሉም ነገር ታማኝ ናችሁ?

“በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል።”—ሉቃስ 16:10

1. ይሖዋ ታማኝ የሆነበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

 ቀኑ እየገፋ ሲሄድ መሬት ላይ የሚታይ የአንድ ዛፍ ጥላ ምን እንደሚሆን አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? አዎን፣ የጥላው መጠንም ሆነ አቅጣጫ ይቀየራል። የሰዎች ግብና የሚሰጡት ተስፋም አብዛኛውን ጊዜ እንደ ጥላ ተለዋዋጭ ነው። በአንጻሩ ግን ይሖዋ አምላክ ከጊዜ ጋር አይለወጥም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እርሱን ‘የሰማይ ብርሃናት አባት’ ብሎ የጠራው ከመሆኑም ሌላ “በእርሱ ዘንድ መለዋወጥ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም” ብሏል። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ በጥቃቅን ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ወጥ አቋም ያለውና እምነት የሚጣልበት ነው። እርሱ “ታማኝ አምላክ” ነው።—ዘዳግም 32:4

2. (ሀ) ታማኝ መሆን አለመሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ታማኝነትን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 አምላክ አገልጋዮቹ እምነት የሚጣልባቸው በመሆናቸው ምን ይሰማዋል? ዳዊት ታማኝ ሰዎችን በተመለከተ “ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ ዐይኖቼ በምድሪቱ ታማኞች ላይ ናቸው፤ በንጽሕና መንገድ የሚሄድ፣ እርሱ ያገለግለኛል” ሲል የገለጸው ዓይነት አመለካከት አለው። (መዝሙር 101:6) አዎን፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ በሚያሳዩት ታማኝነት ይደሰታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባቸው” ብሎ የጻፈበት በቂ ምክንያት ነበረው። (1 ቆሮንቶስ 4:2) ታማኝ መሆን ምን ያካትታል? ታማኝነት ማሳየት ያለብን በየትኞቹ የሕይወታችን ዘርፎች ነው? “በንጽሕና መንገድ” መሄድ ምን በረከቶች ያስገኛል?

ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

3. ታማኝ መሆናችን የሚታየው በምንድን ነው?

3 ዕብራውያን 3:5 “ሙሴ . . . ታማኝ አገልጋይ ነበር” ይላል። ይህን ነቢይ ታማኝ ያስባለው ነገር ምንድን ነው? ከመገናኛው ድንኳን ሥራ ጋር በተያያዘ “ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው [አድርጓል]።” (ዘፀአት 40:16) የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን እርሱን በታዛዥነት በማገልገል ታማኝነት እናሳያለን። ይህም አስቸጋሪ ፈተናና ከባድ መከራ ሲደርስብን ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መቀጠልን እንደሚጨምር የታወቀ ነው። ይሁንና ከባድ ፈተናዎችን መወጣት መቻላችን ታማኝነታችን የሚለካበት ብቸኛው መሥፈርት አይደለም። ኢየሱስ “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም” ብሏል። (ሉቃስ 16:10) ቀላል በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ታማኝነት ማሳየት ይኖርብናል።

4, 5. “በትንሽ ነገር” ታማኝ መሆናችን ምን ያሳያል?

4 በየዕለቱ “በትንሽ ነገር” ታዛዥ መሆናችን በሁለት ምክንያቶች የተነሳ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለን ያሳያል። በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም በአዳምና በሔዋን ፊት ተደቅኖ ስለነበረው የታማኝነት ፈተና አስብ። የተጣለባቸው ግዴታ በምንም መልኩ አስቸጋሪ አልነበረም። በዔድን ገነት ከሚገኘው ከሁሉም ዓይነት ፍሬ መብላት የተፈቀደላቸው ሲሆን እንዳይበሉ የተከለከሉት ከአንድ ዛፍ ብቻ ይኸውም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይህን ቀላል ትእዛዝ በታማኝነት በማክበር የይሖዋን አገዛዝ እንደሚደግፉ የማሳየት አጋጣሚ ነበራቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ በዕለታዊ ሕይወታችን የይሖዋን መመሪያዎች መከተላችን የእርሱን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ያሳያል።

5 በሁለተኛ ደረጃ “በትንሽ ነገር” የምናሳየው ባሕርይ “በትልቁም” ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን በምንሰጠው ምላሽ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ዳንኤልና ታማኝ ባልንጀሮቹ የሆኑት አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የሚባሉ ሦስት ዕብራውያን ምን እንዳጋጠማቸው ተመልከት። በ617 ከክርስቶስ ልደት በፊት በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወስደው ነበር። ገና ወጣት እያሉ፣ ምናልባትም በአሥራዎቹ ዕድሜ ሊሆን ይችላል እነዚህ አራት ዕብራውያን በንጉሥ ናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት እንዲኖሩ ተደረገ። በዚያም ንጉሡ “በየዕለቱ የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማዕድ ድርጎ እንዲሰጣቸው አደረገ፤ [እነርሱም] ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ናቸው።”—ዳንኤል 1:3-5

6. ዳንኤልና ሦስቱ ዕብራውያን በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ ምን ዓይነት ፈተና ተደቅኖባቸው ነበር?

6 ሆኖም የባቢሎን ንጉሥ እንዲቀርብላቸው ያዘዘው ምግብ ለአራቱ ዕብራውያን ወጣቶች ፈተና ሆነባቸው። ለንጉሡ ከሚዘጋጁት ምግቦች መካከል በሙሴ ሕግ የተከለከሉ ምግቦች ሳይኖሩ አይቀሩም። (ዘዳግም 14:3-20) ለመብል የሚታረዱት እንስሳት ደማቸው በአግባቡ ያልፈሰሰ ሊሆን ይችላል፤ እንዲህ ዓይነት ሥጋ መብላት ደግሞ የአምላክን ሕግ ያስጥሳል። (ዘዳግም 12:23-25) ባቢሎናውያን በአምልኮ ወቅት በኅብረት ከመመገባቸው በፊት ምግቡን ለጣዖቶቻቸው መሥዋዕት አድርገው የማቅረብ ልማድ ስለነበራቸው ምግቡ ለዚያ ዓላማ የዋለም ሊሆን ይችላል።

7. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ታዛዥ መሆናቸው ምን ያሳያል?

7 በባቢሎን ንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ ከአንዳንድ የምግብ ዓይነቶች የመራቅ አስፈላጊነት ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳልሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁን እንጂ ዳንኤልና ጓደኞቹ አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ የከለከላቸውን ምግቦች በመመገብ ራሳቸውን ላለማርከስ በልባቸው ቆርጠው ነበር። ይህ ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት የሚመለከት ጉዳይ ነበር። ስለዚህ አትክልትና ውኃ እንዲቀርብላቸው የጠየቁ ሲሆን ይህም ተፈቀደላቸው። (ዳንኤል 1:9-14) በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አራቱ ወጣቶች የወሰዱት እርምጃ ተራ ነገር መስሎ ይታያቸው ይሆናል። ሆኖም ለአምላክ ታዛዥ መሆናቸው የይሖዋን ሉዓላዊነት አስመልክቶ በተነሳው ጥያቄ ምን አቋም እንዳላቸው አሳይቷል።

8. (ሀ) ሦስቱ ዕብራውያን ታማኝነትን በተመለከተ ያጋጠማቸው ከባድ ፈተና ምንድን ነው? (ለ) የፈተናው ውጤት ምን ነበር? ይህስ ምን ያሳያል?

8 ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች ተራ በሚመስሉ ጉዳዮች ረገድ ታማኝ መሆናቸው ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው እንዲቋቋሙ አስችሏቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3ን አውጡና እነዚህ ሦስት ዕብራውያን ንጉሥ ናቡከደነፆር ያቆመውን ከወርቅ የተሠራ ምስል ለማምለክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሞት እንደተፈረደባቸው የሚገልጸውን ታሪክ አንብቡ። ንጉሡ ፊት ባቀረቧቸው ጊዜ ከአቋማቸው ንቅንቅ እንደማይሉ እንዲህ በማለት በድፍረት ተናግረዋል:- “ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” (ዳንኤል 3:17, 18) ታዲያ ይሖዋ አድኗቸዋል? ሦስቱን ወጣቶች ወደ እቶን እሳት ውስጥ የጣሏቸው ወታደሮች ሲሞቱ እነዚህ ታማኝ ዕብራውያን ግን የእቶኑ ከፍተኛ ሙቀት እንኳ ምንም ጉዳት ሳያደርስባቸው በሕይወት ወጡ! ለረጅም ጊዜ ሲከተሉ የቆዩት የታማኝነት ጎዳና በዚህ ከባድ ፈተና ወቅት ታማኝ እንዲሆኑ አዘጋጅቷቸዋል። ታዲያ ይህ በትንንሽ ነገሮች ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት አያሳይም?

“በዓመፃ ገንዘብ” ረገድ ታማኝ መሆን

9. ኢየሱስ በሉቃስ 16:10 ላይ በተናገራቸው ቃላት ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምንድን ነው?

9 ኢየሱስ ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች ታማኝ የሆነ ሰው ከበድ ባሉ ጉዳዮችም ታማኝ ይሆናል የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ከመናገሩ በፊት ለአድማጮቹ ይህን ምክር ሰጥቷቸው ነበር:- “የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፣ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ።” ቀጥሎም በትንሽ ነገር ታማኝ ስለመሆን ተናገረ። ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? . . . ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፣ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”—ሉቃስ 16:9-13 የ1954 ትርጉም

10. “የዓመፃ ገንዘብ” አጠቃቀማችንን በተመለከተ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ በሉቃስ 16:10 ላይ በዋነኝነት እየተናገረ የነበረው ‘የዓመፃ ገንዘብን’ ማለትም ቁሳዊ ሀብታችንን ወይም ንብረታችንን እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ መሆኑን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ያሳያል። ቁሳዊ ሀብት በተለይ ደግሞ ገንዘብ የዓመጻ ንብረት የተባለው ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች እጅ ስለሚገኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ሀብት ለማግኘት መመኘት ዓመጽ ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። ባሉን ቁሳዊ ንብረቶች በጥበብ በመጠቀም ታማኝ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ሀብታችንን ለራስ ወዳድነት ዓላማዎች ከማዋል ይልቅ የስብከቱን ሥራ ለመደገፍና የተቸገሩ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንፈልጋለን። በዚህ መንገድ ታማኝ በመሆን “በዘላለም ቤቶች” ሊቀበሉን ከሚችሉት ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት እንመሠርታለን። እነርሱም በሰማይ ወይም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ወደነዚህ ቤቶች እንድንገባ ይፈቅዱልናል።

11. ጽሑፍ ላበረከትንላቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ የምናከናውነውን ሥራ ለመደገፍ የሚያደርጉትን መዋጮ እንደምንቀበል ከመግለጽ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

11 ለሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ነግረናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስናበረክትላቸው እንዲሁም የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑትን ሥራ ለመደገፍ የሚያደርጉትን መዋጮ እንደምንቀበል ስንገልጽላቸው ምን ዓይነት አጋጣሚ እየሰጠናቸው እንዳለም አስብ። ቁሳዊ ሀብታቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙበት አጋጣሚ እየከፈትንላቸው አይደለም? ምንም እንኳ ሉቃስ 16:10 በዋነኝነት የቁሳዊ ሀብትን አጠቃቀም የሚመለከት ቢሆንም እዚያ ላይ የሰፈረው መሠረታዊ ሥርዓት ለሌሎች የሕይወት ዘርፎችም ይሠራል።

ሐቀኝነት በጣም አስፈላጊ ነው

12, 13. ሐቀኝነት ማሳየት የምንችልባቸው መስኮች የትኞቹ ናቸው?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ “በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር [“በሐቀኝነት፣” NW] ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18) “በሁሉም መንገድ” የሚለው አባባል ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ጉዳይ እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። የተበደርነውን ገንዘብም ሆነ መክፈል ያለብንን ቀረጥ በወቅቱና በሐቀኝነት እንከፍላለን። ለምን? እንዲህ የምናደርገው ለኅሊናችን ብለን ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት ለአምላክ ፍቅር ስላለን ብሎም የእርሱን መመሪያ መታዘዝ ስለምንፈልግ ነው። (ሮሜ 13:5, 6) የጠፋ ዕቃ ብናገኝ ምን እናደርጋለን? ለባለቤቱ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የግለሰቡን ንብረት ለመመለስ ያነሳሳን ምን እንደሆነ ስንገልጽ እግረ መንገዳችንን ግሩም ምሥክርነት የመስጠት አጋጣሚ እናገኛለን!

13 በሁሉም መንገድ ታማኝና ሐቀኛ መሆን በሥራ ቦታችንም ሐቀኛ መሆንን ይጨምራል። በሥራ ልማዳችን ሐቀኛ መሆናችን የምናመልከው አምላክ ማንነት እንዲታወቅ ያደርጋል። ልግመኛ በመሆን የሥራ ሰዓት ‘አንሰርቅም።’ ከዚህ ይልቅ ይሖዋን እንደምናገለግል ቆጥረን በትጋት እንሠራለን። (ኤፌሶን 4:28፤ ቈላስይስ 3:23) በአንድ የአውሮፓ አገር የተገኘ ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳየው የሐኪም ፈቃድ እንዲሰጣቸው ከሚጠይቁ ሠራተኞች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ፈቃድ የሚያገኙት በማጭበርበር ነው። እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ከሥራ ለመቅረት ብለው የውሸት ምክንያት አያቀርቡም። አንዳንድ ጊዜ፣ አሠሪዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ሐቀኝነትና ትጋት በመመልከት በሥራ ቦታቸው እድገት ይሰጧቸዋል።—ምሳሌ 10:4

በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ታማኝነት ማሳየት

14, 15. በክርስቲያናዊ አገልግሎት ታማኝ መሆናችንን የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

14 በአደራ በተሰጠን አገልግሎት ረገድ ታማኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ” ይላል። (ዕብራውያን 13:15) በአገልግሎት ታማኝነታችንን የምናሳይበት ዋናው መንገድ በሥራው አዘውታሪ በመሆን ነው። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው ሳንመሠክር አንድ ወር እንዲያልፈን እንዴት እንፈቅዳለን? እንዲሁም በስብከቱ ሥራ አዘውትረን መካፈላችን ችሎታችንና ውጤታማነታችን እንዲሻሻል ይረዳናል።

15 በአገልግሎት ታማኝነት ማሳየት የምንችልበት ሌላው ግሩም መንገድ በመጠበቂያ ግንብ እና በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ነው። የተሰጡንን የመግቢያ ሐሳቦች ወይም ተስማሚ የሆኑ ሌሎች መግቢያዎች ተዘጋጅተን ስንጠቀምባቸው አገልግሎታችን ይበልጥ ፍሬያማ አይሆንም? ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳየ ሰው ስናገኝ ፍላጎቱን ለማሳደግ ወዲያው ተከታትለን እንረዳዋለን? ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የጀመርንላቸውን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተመለከተስ እንዴት ነን? በቋሚነት እነርሱን በመርዳት ረገድ እምነት የሚጣልብንና ታማኞች ነን? በአገልግሎት ታማኝ መሆናችን ለእኛም ሆነ ለሚሰሙን ሰዎች ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16

ከዓለም የተለዩ መሆን

16, 17. ከዓለም የተለየን መሆናችንን በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?

16 ኢየሱስ ተከታዮቹን በተመለከተ ወደ አምላክ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል:- “ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቶአቸዋል። የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:14-16) እንደ ገለልተኝነት፣ ሃይማኖታዊ በዓላትና ልማዶች እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና በመሳሰሉት አቢይ ጉዳዮች ከዓለም የተለየን ለመሆን ጥብቅና ቆራጥ አቋም እንወስድ ይሆናል። ይሁንና ትንንሽ በሚመስሉ ጉዳዮችስ? ምንም ሳይታወቀን የዓለም መንገድ ተጽዕኖ አሳድሮብን ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ ጠንቃቃ ካልሆንን አለባበሳችን የማያስከብርና ቅጥ ያጣ ሊሆን ይችላል። ታማኝ መሆን በአለባበስና በፀጉር አበጣጠር ረገድ ‘ጨዋነትና ራስን መግዛት’ እንድናሳይ ይጠይቅብናል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) አዎን፣ “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን።”—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4

17 ይሖዋን ለማስከበር ካለን ፍላጎት የተነሳ ወደ ጉባኤ ስብሰባ ስንሄድ ክብር ባለው መንገድ እንለብሳለን። በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ ብዙ ሆነን በምንሰበሰብበት ወቅትም ለአለባበሳችን እንጠነቀቃለን። ልብሳችን ለሁኔታው የሚስማማና ክብር ያለው ሊሆን ይገባል። ይህም ለሚያዩን ሰዎች ምሥክርነት ሊሰጥ ይችላል። መላእክት የጳውሎስንና የክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንቅስቃሴ ይከታተሉ እንደነበር ሁሉ የእኛንም ሥራ ይመለከታሉ። (1 ቆሮንቶስ 4:9) ስለዚህ ምንጊዜም ተገቢ በሆነ ሁኔታ መልበስ ይኖርብናል። በልብስ ምርጫ ረገድ ታማኝነት ማሳየት ለአንዳንዶች ተራ ነገር ይመስላቸው ይሆናል። በአምላክ ዓይን ግን ጉዳዩ ክብደት አለው።

ታማኝነት የሚያስገኛቸው በረከቶች

18, 19. ታማኝ መሆን ምን በረከቶች ያስገኛል?

18 እውነተኛ ክርስቲያኖች “ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ” እንደሆኑ ተነግሯል። በመሆኑም የሚያገለግሉት ‘እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ብርታት ነው።’ (1 ጴጥሮስ 4:10, 11) ከዚህ በተጨማሪ መጋቢ እንደመሆናችን መጠን በአደራ የተሰጠንን አገልግሎት ጨምሮ ወደር ስለማይገኝለት የአምላክ ደግነት የተነገሩት ነገሮች ምንጭ እኛ አይደለንም። ታማኝ መጋቢ ሆነን በመገኘት አምላክ በሚሰጠን “እጅግ ታላቅ ኀይል” እንመካለን። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ወደፊት ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ይህ ግሩም ሥልጠና ይሆነናል!

19 መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል።” (መዝሙር 31:23) ይሖዋ “ለሰዎች ሁሉ በተለይም ለሚያምኑት አዳኝ” መሆኑን ሙሉ በሙሉ በመተማመን ታማኝ ሆነን ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ጢሞቴዎስ 4:10

ታስታውሳለህ?

• “በትንሽ ነገር ታማኝ” መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• ሐቀኝነትን በተመለከተ ታማኝ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

• በአገልግሎት ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• ከዓለም የተለዩ በመሆን ረገድ ታማኝ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትንሹ ታማኝ የሆነ በትልቁም ታማኝ ይሆናል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በሁሉም መንገድ በሐቀኝነት ኑሩ’

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመስክ አገልግሎት ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ታማኝነት የምናሳይበት አንድ ግሩም መንገድ ነው

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአለባበሳችሁና በፀጉር አበጣጠራችሁ ልከኛ ሁኑ