በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ የሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች

በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ የሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች

“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው”

በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ የሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች

በስፔይን የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ሴት “አብዛኞቻችን ትዳር ባንመሠርትም በጣም ደስተኞች ነን” ብላለች። ደስተኛ ልትሆን የቻለችበት ምክንያት ምንድን ነው? “ትዳር ከሚያመጣቸው ጭንቀቶች ነፃ ሆነን ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ማገልገል በመቻላችን ደስተኞች ነን” ስትል አክላ ተናግራለች።

የዚህች እህት አመለካከት የአምላክ ቃል ነጠላነትን አስመልክቶ ከሰጠው ሐሳብ ጋር ይስማማል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ መንፈስ ባገኘው ማስተዋል ትዳርን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ግን እንዲህ እላለሁ፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው።” ጳውሎስ ራሱ አላገባም ነበር። ሳያገቡ መኖርን ያበረታታበት ምክንያት ምን ነበር? ያገባ ሰው ልቡ እንደሚከፈልና ያላገባው ወንድ ወይም ሴት ግን ‘ስለ ጌታ ነገር እንደሚያስቡ’ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:8, 32-34) ያላገባ ሰው ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት እንዲመራ የሚያስችለው ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ማገልገሉ ነው።

ለተከበረ ዓላማ ብሎ በነጠላነት መኖር

ለጋብቻና ቤተሰብ ለማፍራት ከፍ ያለ ቦታ በሚሰጡ አንዳንድ ባሕሎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጳውሎስ ያቀረበው ሐሳብ ግራ የሚያጋባ ሊሆንባቸው ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ያላገባ ቢሆንም ደስታና እርካታ የነበረው ሲሆን በነጠላነት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይህን አጋጣሚ ለተከበረ ዓላማ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ገልጿል። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”—ማቴዎስ 19:12

ከዚህ ዓረፍተ ነገር ጋር በሚስማማ መልኩ ብዙዎች ባለማግባታቸው በትዳር ዓለም ያሉት ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮች ሳያጋጥሟቸው ይሖዋን ለማገልገል እንደቻሉ ተገንዝበዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:35) በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛ ሳይኖራቸው ይሖዋን በደስታ ያመልኩታል፤ እንዲሁም ሌሎችን ከልብ በመርዳት ደስታ ያገኛሉ። a

ብዙ ያላገቡ ክርስቲያኖች ደስታ ላገቡት ብቻ እንዳልሆነ እንዲሁም በነጠላነት የሚኖሩ ሁሉ ደስተኞች አይደሉም ሊባል እንደማይችል ተገንዝበዋል። ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ደስታና ሐዘን ያጋጥማቸዋል። ለነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ትዳር ራሱ “ብዙ ችግር” እንዳለው ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 7:28

በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት በነጠላነት መኖር

ብዙዎች ያላገቡት በምርጫቸው ሳይሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት ነው። በትዳር ውስጥ የሚኖረውን ፍቅር፣ ጓደኝነትና አሳቢነት ማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። ሆኖም አንዳንዶች በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ትዳር መመሥረት አልቻሉም። ተወዳጅ የሆኑ ብዙ መንፈሳዊ እህቶቻችንን ጨምሮ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጋብቻ “በጌታ መሆን” እንዳለበት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ በማድረጋቸው ሳያገቡ ቀርተዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ለይሖዋ ታማኝ በመሆን፣ ማግባት የሚፈልጉት ራሳቸውን ከወሰኑና ከተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ብቻ ነው።

አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ያላገቡ ሰዎች ብቸኝነት ይሰማቸዋል። አንዲት ያላገባች ክርስቲያን እንደዚህ እንደሚሰማት ከገለጸች በኋላ እንዲህ ብላለች:- “የይሖዋን ሕግ ስለምናውቅ በምንም መንገድ ይሖዋን ማሳዘን አንፈልግም። ከእኛ ጋር የሚሆን የኑሮ አጋር እንዲኖረን እንፈልግ ይሆናል፤ የዓለም ሰዎች ከሌሎች ጋር ‘ሊያጣምሩን’ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም እኛ ግን በአቋማችን እንጸናለን። የማያምኑ ወንዶች ወይም ሴቶች ጓደኞቻችን እንኳ እንዲሆኑ አንፈልግም።” እንደነዚህ የመሳሰሉ ክርስቲያኖች በነጠላነት በመኖራቸው ስሜታቸው ቢጎዳም እንኳ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ስለሚያውሉና ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎቹን ስለሚጠብቁ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።

ይሖዋ ከፍተኛ እርዳታ ይሰጠናል

ይሖዋ እርሱን የማያገለግሉ ሰዎችን ባለማግባት ታማኝነታቸውን ለጠበቁ ክርስቲያኖች እርሱም ታማኝ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት “ከታማኙ ጋር ታማኝ ትሆናለህ” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (መዝሙር 18:25) አምላክ በታማኝነት ለሚታዘዙት “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል። (ዕብራውያን 13:5) በታማኝነት የአምላክን ቃል ለሚታዘዙ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ያላገቡ ክርስቲያኖች አድናቆታችንን በመግለጽ ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ያሉባቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመው ለመኖር እንዲችሉ ይሖዋ ጥንካሬ እንዲሰጣቸው መጸለይም እንችላለን።—መሳፍንት 11:30-40

በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ ሙሉ በሙሉ መሳተፋቸው ሕይወታቸው ትርጉም እንዲኖረው አስችሏቸዋል። ለምሳሌ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘውንና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ወይም አቅኚ የሆነችውን ፓትሪሽያ የተባለች ነጠላ እህት እንመልከት። እንዲህ ትላለች:- “ከነጠላነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎች ቢኖሩም አለማግባቴ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ለማገልገል አስችሎኛል። ያላገባሁ እንደመሆኔ መጠን ለጥናት የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ፕሮግራሜን እንደ አስፈላጊነቱ መለዋወጥ ችያለሁ። በተለይ በአስቸጋሪ ጊዜያት ይበልጥ በይሖዋ ላይ መታመንን ተምሬያለሁ።”

እንደዚህ ያለው አመለካከት “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አጽናኝ ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው። (መዝሙር 37:5) በእርግጥም ያገቡም ሆኑ ያላገቡ የይሖዋ ታማኝ አምላኪዎች በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” ከሚሉት ቃላት ማጽናኛና ብርታት ያገኛሉ።—መዝሙር 121:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ሐምሌ/ነሐሴ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሰኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል።”—1 ቆሮንቶስ 7:32

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከነጠላነት ደስታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይቻላል?

ነጠላ የነበረው ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 4:34

ፊልጶስ “ትንቢት የሚናገሩ” አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።—የሐዋርያት ሥራ 21:8, 9

የመንግሥቱን መልእክት የሚያውጁ ያላገቡ ክርስቲያን እህቶች ‘ትእዛዙን ከሚያውጁት ብዙ [“የሴቶች፣” NW] ሰራዊት’ መካከል ናቸው።—መዝሙር 68:11