በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች

አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች

አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች

የሰው ልጆች እውነተኛ የሆኑና አምላክን የሚያስደስቱ ትምህርቶችን ማወቅ እንዲችሉ አምላክ ሐሳቡን ሊገልጽላቸው ይገባል። በተጨማሪም ሐሳቡን ሁሉም ሰው እንዲያገኘው ማድረግ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን የሰው ዘር አምላክ የሚቀበለውን ትምህርት፣ አምልኮ እንዲሁም ምግባር እንዴት ማወቅ ይችላል? አምላክ እንዲህ ያለውን እውቀት ሰጥቶናል? ከሆነስ ይህ እውቀት የሚገኘው በምን መልኩ ነው?

ከጥቂት አሥርተ ዓመታት የማይበልጥ የሕይወት ዘመን ያለው የትኛውም ሰው ቢሆን ከአምላክ የተላከውን መልእክት ለሰው ዘር በሙሉ በማዳረስ እንደ መገናኛ መሥመር ሆኖ ሊያገለግል ይችላል? ይህ የማይሆን ነገር ነው። በጽሑፍ መልክ የሰፈረ ቋሚ መዝገብ ግን ይህን ማድረግ ይችላል። እንግዲያው ከአምላክ የተላከው መልእክት በመጽሐፍ መልክ ቢቀርብልን ተገቢ አይሆንም? በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፉ ከሚገልጹ ጥንታዊ መጻሕፍት አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛ ትምህርቶች ምንጭ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ እስቲ በጥልቀት እንመርምረው።

ከተጻፈ ምን ያህል ቆይቷል?

ዋና ዋና ከሚባሉት ሃይማኖታዊ መጻሕፍት መካከል የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ረጅም ዕድሜ ያለው የለም። የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከተጻፉ 3,500 የሚያህሉ ዓመታት አልፈዋል። መጽሐፉ ተጽፎ ያለቀው በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው 40 በሚያህሉ ሰዎች በ1,600 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቢሆንም በውስጡ የሚገኙት የተለያዩ መጻሕፍት እርስ በርስ አይጋጩም። ይህም ሊሆን የቻለው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ በመሆኑ ነው።

በታሪክ ዘመናት ሁሉ ወደተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በስፋት በመሰራጨት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዳደረው መጽሐፍ የለም። በየዓመቱ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከፊሉ በ60 ሚሊዮን ያህል ቅጂዎች ይሰራጫል። እንዲሁም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የተወሰነው የመጽሐፉ ክፍል ከ2,300 በሚበልጡ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተተርጉሟል። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሙሉውን ወይም ቢያንስ ከፊሉን መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋው ማግኘት ይችላል። ይህ መጽሐፍ እንዳይሰራጭ ብሔራዊ ድንበርም ሆነ የዘርና የጎሣ ልዩነት አላገደውም።

መጽሐፉ የተደራጀው በምን መልኩ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ካለህ መጽሐፉ እንዴት እንደተደራጀ ለማወቅ ለምን ገልጠህ አትመለከተውም? a በመጀመሪያ የርዕስ ማውጫውን ተመልከት። አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች በመግቢያቸው ላይ የእያንዳንዱን መጽሐፍ ስምና የሚገኝበትን ገጽ የሚያመለክት ማውጫ አላቸው። ከማውጫው መመልከት እንደምትችለው መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ስም ያላቸው የበርካታ መጻሕፍት ስብስብ ነው። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ዘፍጥረት ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ ራእይ ወይም አፖካሊፕስ ይባላል። መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት በአብዛኛው የተጻፉት በዕብራይስጥ ቋንቋ በመሆኑ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተብለው ይጠራሉ። ቀሪዎቹ 27 መጻሕፍት ደግሞ በግሪክኛ የተጻፉ ሲሆን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ይባላሉ። አንዳንዶች እነዚህን ሁለት ክፍሎች ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን በማለት ይጠሯቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በቀላሉ ለማውጣት እንዲያመች ምዕራፎችና ቁጥሮች ተዘጋጅቶላቸዋል። በዚህ መጽሔት ውስጥ ጥቅሶች ሲጠቀሱ ከመጽሐፉ ስም ቀጥሎ ያለው የመጀመሪያው ቁጥር ምዕራፉን የሚያመለክት ሲሆን ቀጥሎ ያለው ደግሞ ቁጥሩን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፣ “2 ጢሞቴዎስ 3:16” ሲባል የሁለተኛ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 ማለት ነው። እስቲ ይህንን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማውጣት ሞክር።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ይህንን መጽሐፍ በየዕለቱ ማንበብ ነው ቢባል አትስማማም? አንዳንዶች ከማቴዎስ መጽሐፍ ጀምረው የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን መጀመሪያ ያነብባሉ። በየቀኑ ከሦስት እስከ አምስት ምዕራፎች በማንበብ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጨረስ ትችላለህ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምታነብበው ነገር በእርግጥ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?

መጽሐፍ ቅዱስን ልትተማመንበት ትችላለህ?

ለሁሉም የሰው ዘሮች እንዲሆን ታስቦ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንደሚገባን የሚገልጽ ጊዜ የማይሽረው ምክር ሊሰጠን የሚገባ አይመስልህም? መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኛውም የሰው ዘር ትውልድ በሚጠቅም ሁኔታ የተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ የሚሰጣቸው መመሪያዎች መጀመሪያ በተጻፉበት ወቅት እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ታዋቂ ንግግር በመመልከት የዚህን አባባል እውነተኝነት በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል። ትምህርቱ በማቴዎስ ወንጌል ከምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቀው ይህ ንግግር እውነተኛ ደስታ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን አለመግባባቶችን ስለ መፍታት፣ ስለ ጸሎት፣ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን ስለ ማሟላትና ስለ ሌሎች ነገሮችም ትምህርት ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ንግግርና በሌሎቹም ክፍሎቹ ሁሉ አምላክን ለማስደሰት ብሎም የተሻለ ሕይወት ለመምራት ከፈለግን ምን ማድረግ እንዳለብንና ልናስወግዳቸው የሚገቡት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ በግልጽ ይነግረናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ እንድትተማመን የሚያደርግህ ሌላው ምክንያት ደግሞ ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ በሳይንሳዊ ጉዳዮች ረገድ የሚሰጠው ሐሳብ ትክክል መሆኑ ነው። ለአብነት ያህል፣ አብዛኞቹ ሰዎች ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ያምኑ በነበረበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ምድር ክበብ” ገልጿል። b (ኢሳይያስ 40:22) ከዚህም በላይ ስመ ጥር ሳይንቲስት የሆነው ሰር አይዛክ ኒውተን ፕላኔቶች በሕዋ ላይ ያለምንም ድጋፍ በስበት ኃይል ተንጠልጥለው እንደሚገኙ ከመግለጹ ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ‘ምድር እንዲያው በባዶው ላይ እንደተንጠለጠለች’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ ነበር። (ኢዮብ 26:7) ስለ ምድር የውኃ ዑደት የሚገልጸውን ከ3,000 ዓመታት በፊት የሰፈረ ዘገባም እንመልከት:- “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።” (መክብብ 1:7) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አጽናፈ ዓለምን የፈጠረው አካል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አንጻር ትክክል መሆኑ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ለመጻፉ ማስረጃ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ታሪኮች እንዲሁ ተረቶች አይደሉም። የተፈጸሙበት ጊዜና ቦታ እንዲሁም የሰዎቹ ማንነት በግልጽ ሰፍሯል። ለምሳሌ በሉቃስ 3:1 ላይ “ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ” በነበሩበት ጊዜ ስለተፈጸመው ሁኔታ የሚገልጽ እውነተኛ ዘገባ እናገኛለን።

የጥንት ጸሐፊዎች ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ስለ ገዢዎች ሲጽፉ ያገኙትን ድልና መልካም ባሕርያቸውን ብቻ የሚጠቅሱ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን የራሳቸውን ስሕተቶች እንኳ በሐቀኝነት ዘግበዋል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ . . . የፈጸምሁት ታላቅ የስንፍና ሥራ ነው” በማለት ጥፋቱን ያመነ ሲሆን ይህንንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን። (2 ሳሙኤል 24:10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሙሴም በአምላክ ሳይታመን የቀረበትን አጋጣሚ ዘግቧል።—ዘኍልቍ 20:12

መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላም ማስረጃ አለ። ፍጻሜያቸውን ያገኙት ትንቢቶች ይኸውም በታሪክ ውስጥ ምን እንደሚፈጸም አስቀድመው የተጻፉት ነገሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛነት ማስረጃ ይሆኑናል። ከእነዚህ መካከል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩት ትንቢቶች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ተስፋ የተደረገበት ይህ ሰው “በቤተ ልሔም ይሁዳ” እንደሚወለድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በትክክል ተንብየው ነበር።—ማቴዎስ 2:1-6፤ ሚክያስ 5:2

ሌላም ምሳሌ እንመልከት። በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።” ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ በአጠቃላይ በሰዎች ላይ የሚታየውን ባሕርይ በሚገባ የሚገልጽ አይደለም? እነዚህ ቃላት የተጻፉት በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማለትም ከ1,900 ዓመታት በፊት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?

መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብብ ይህ መጽሐፍ ከፍተኛ ጥበብ የያዘ መሆኑን ትገነዘባለህ። አምላክ ማን ነው? ዲያብሎስ በእርግጥ አለ? ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? መከራና ሥቃይ የኖረው ለምንድን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን? እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። ሰዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡህ መልስ እንደ እምነታቸውና ባሕላቸው የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህና ስለ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች እውነቱን ይናገራል። ከዚህም በላይ መጽሐፉ ሥነ ምግባርን እንዲሁም ለሌሎች ሰዎችና ለበላይ ባለ ሥልጣናት ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት አስመልክቶ የሚሰጠው መመሪያ ተወዳዳሪ አይገኝለትም። c

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምድርንና የሰው ልጆችን በተመለከተ ስላለው ዓላማ ምን ይገልጻል? “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚል ተስፋ ይዟል። (መዝሙር 37:10, 11) “እግዚአብሔር ራሱም [ከሰዎች] ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ጦርነት፣ ወንጀል፣ ዓመጽና ክፋት እንደሚወገዱ ይናገራል። ሕመም፣ እርጅና እንዲሁም ሞት ይቀራሉ። ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይቻላል። ይህ ምንኛ አስደሳች ተስፋ ነው! እነዚህ ተስፋዎች አምላክ ለሰው ዘር ያለውን ፍቅር በተጨባጭ ያሳያሉ!

ምን ለማድረግ አስበሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከፈጣሪያችን የተገኘ ድንቅ ሥጦታ ነው። ይህን መጽሐፍ በተመለከተ ምን ለማድረግ አስበሃል? የሂንዱ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ አንድ ሰው ከአምላክ የመጣ እውቀት ለሰው ሁሉ ጠቃሚ እንዲሆን የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የነበረ መሆን እንዳለበት ያምን ነበር። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጣም ጥንታዊ ከሆነው ቬዳ የተባለ የሂንዱ ጽሑፍ በፊት የተጻፉ መሆናቸውን ሲያውቅ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ይዘቱን ለመመርመር ወስኗል። d በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ደግሞ በዓለም ላይ በስፋት ስለተሰራጨው ስለዚህ መጽሐፍ አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት መጽሐፉን ሊያነቡት እንደሚገባ ተገንዝበዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ትምህርቱን በተግባር ማዋል የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ቃል ስለሚያነብብ ሰው ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” e (መዝሙር 1:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በተማርከው ነገር ላይ ማሰላሰል መንፈሳዊ ፍላጎትህ እንዲሟላ ስለሚያደርግ ደስታ ያስገኝልሃል። (ማቴዎስ 5:3) መጽሐፍ ቅዱስ ስኬታማ የሆነ ሕይወት ለመምራትና ችግሮችን ለመወጣት የሚያስችልህን መንገድ ይጠቁምሃል። አዎን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን የአምላክ ቃል “መጠበቅ ወሮታ አለው።” (መዝሙር 19:11) ከዚህም በላይ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደርህ ዛሬ በረከት የሚያስገኝልህ ሲሆን ስለ ወደፊቱ ጊዜም ብሩህ ተስፋ እንዲኖርህ ያደርጋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 2:2) አንድ ሕፃን በሕይወት ለመኖር መመገብ የሚያስፈልገው ሲሆን ይህ ፍላጎቱ እንዲሟላለትም ሁልጊዜ ይጠይቃል። እኛም በተመሳሳይ ሕይወታችን ከአምላክ በሚገኘው እውቀት ላይ የተመካ ነው። ስለዚህ ለቃሉ ‘ምኞት’ ወይም ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተላኩ እውነተኛ ትምህርቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው። ይህንን መጽሐፍ አዘውትረህ የማጥናት ግብ አውጣ። በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከጥናትህ ጥቅም ማግኘት እንድትችል ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ከእነርሱ ጋር እንድትገናኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። አሊያም ደግሞ ለዚህ መጽሔት አሳታሚዎች መጻፍ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የግልህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለህ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንድትችል ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

b በኢሳይያስ 40:22 ላይ “ክበብ” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቃል “ድቡልቡል” ተብሎ ሊገለጽም ይችላል። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህንን ጥቅስ “በምድር ሉል” (ዱዌይ ቨርሽን) እንዲሁም “ክብ በሆነችው ምድር” (ሞፋት) ብለው ተርጉመውታል።

c ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ስለ እነዚህ ርዕሶች ማብራሪያ ይሰጣል።

d ጥንታዊ የሚባሉት የቬዳ መዝሙሮች ከ3,000 ዓመታት በፊት እንደተቀናበሩና በቃል ሲተላለፉ እንደቆዩ ይታመናል። ሰራትኩመር የተባሉ ደራሲ ኤ ሂስትሪ ኦቭ ኢንዲያ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ቬዳ በጽሑፍ የሰፈረው በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው” ብለዋል።

e ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አምላክ ስም ነው። በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ መዝሙር 83:18 ላይ ይህንን ስም ማግኘት ይቻላል። በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የ1879 ትርጉም ዘፀአት 6:3 ላይ ይገኛል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል “ተመኙ።” መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራችሁ አጥኑ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

NASA photo