‘አስተዋይ ርምጃውን ያስተውላል’
‘አስተዋይ ርምጃውን ያስተውላል’
አስተዋይ የሆነ ሰው በሥራው የተዋጣለትና ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጥሩ ችሎታ ያለው፣ ብልህ፣ ትክክለኛ የማመዛዘን ችሎታ ያለው፣ አርቆ አሳቢ፣ ነገሮችን በንቃት የሚከታተልና ጥበበኛ ነው። እንዲህ ያለው ሰው አታላይም ሆነ ተንኮለኛ አይደለም። ምሳሌ 13:16 “አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል” ይላል። አዎን፣ አስተዋይነት አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው።
በዕለት ተዕለት ሕይወታችን አስተዋይ መሆናችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን? በምናደርጋቸው ውሳኔዎች፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እንዲሁም የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በምንወስደው እርምጃ ይህ ባሕርይ በግልጽ ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው? አስተዋዮች ምን በረከቶች ያገኛሉ? ከየትኞቹስ ችግሮች ይጠበቃሉ? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ለእነዚህ ጥያቄዎች ተግባራዊ የሆኑ መልሶችን በምሳሌ 14:12-25 ላይ ሰጥቶናል። a
የምትከተለውን ጎዳና በጥበብ ምረጥ
ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ለማድረግና የተሳካ ሕይወት ለመምራት መልካሙን ከክፉው የመለየት ችሎታ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:12) በዚህም የተነሳ ትክክል መስሎ የሚታየንን ነገር በእርግጥ ትክክል ከሆነው እንዴት መለየት እንደምንችል መማር ይኖርብናል። ይህ ጥቅስ እንደ በኩረ ጽሑፉ ‘ወደ ሞት የሚያደርሱ መንገዶች’ እንዳሉ የሚገልጽ ሲሆን ይህም ብዙ አሳሳች ጎዳናዎች መኖራቸውን ይጠቁማል። በዚህ ረገድ ልናውቃቸውና ልንርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንመልከት።
በዓለም ያሉ ሀብታምና ታዋቂ ሰዎች አድናቆት ሊቸራቸው እንደሚገባና የተከበሩ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በማኅበራዊ ሕይወታቸው ስኬታማና ባለጠጋ በመሆናቸው በትክክለኛው ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሊመስሉ ይችላሉ። ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ ሀብት ወይም ዝና ለማግኘት ስለሚጠቀሙበት መንገድስ ምን ለማለት ይቻላል? መንገዳቸው ሁልጊዜ ቀና እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርን የተከተለ ነው? ለእምነታቸው የሚደነቅ ቅንዓት የሚያሳዩ አንዳንድ ግለሰቦችም አሉ። ይሁን እንጂ ያላቸው ቅንዓት እምነታቸው ትክክል መሆኑን ያሳያል?—ሮሜ 10:2, 3
አካሄዳችን ትክክል መስሎ የታየን ራሳችንን እያታለልን ሊሆንም ይችላል። ለራሳችን ትክክል መስሎ በሚታየን ነገር ላይ ተመሥርተን ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ አታላይ በሆነው ልባችን እንመራለን ማለት ነው። (ኤርምያስ 17:9) ትክክለኛ እውቀት የሌለውና ሥልጠና ያላገኘ ሕሊና የተሳሳተውን ጎዳና ቀና እንደሆነ አድርገን እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል። ታዲያ ትክክለኛውን ጎዳና ለመምረጥ ምን ሊረዳን ይችላል?
‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳችንን ማስለመድ’ እንድንችል በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ እውነቶች በትጋት ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር የማዋል ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። (ዕብራውያን 5:14) ትክክል መስሎን የተከተልነው ጎዳና ‘ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን ቀጭን መንገድ’ እንድንስት እንዳያደርገን መጠንቀቅ አለብን።—ማቴዎስ 7:13, 14
‘ልብ በሚተክዝበት’ ጊዜ
ውስጣዊ ሰላም ሳይኖረን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን? ሥር የሰደደ ሥቃይን በሣቅና በጨዋታ ማቃምሳሌ 14:13ሀ
ለል እንችላለን? ጭንቀትን ለማስወገድ ብሎ የአልኮል መጠጥ፣ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መውሰድ ወይም የሴሰኝነት አኗኗር መከተል አስተዋይነት ነው? መልሱ አይደለም ነው። ጥበበኛው ንጉሥ “በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል” ብሏል።—ምናልባት ሣቅ የሚሰማንን ሥቃይ ይደብቅ ይሆናል፤ ከናካቴው ሊያስወግደው ግን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” ይላል። “ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው” የሚለው አባባል እውነት ነው። (መክብብ 3:1, 4) ሥር የሰደደ ጭንቀት በሚያጋጥመን ጊዜ “መልካም ምክር” በመጠየቅ መፍትሔ ለማግኘት እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ምሳሌ 24:6) b ሣቅና ደስታ ጥቅም እንዳለው ባይካድም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ግን ጠቀሜታው አነስተኛ ነው። ሰሎሞን ተገቢ ያልሆኑና ከመጠን ያለፉ መዝናኛዎችን በተመለከተ “ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል” በማለት አስጠንቅቋል።—ምሳሌ 14:13ለ
ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱና ደጎች ወሮታ የሚያገኙት እንዴት ነው?
የእስራኤል ንጉሥ ቀጥሎ “ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱ የእጃቸውን ሙሉ ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደግ ሰውም ወሮታውን ያገኛል” ብሏል። (ምሳሌ 14:14) ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱና ደጋግ ሰዎች የእጃቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው?
ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ለአምላክ መልስ ስለመስጠቱ አያስብም። ስለዚህ እንዲህ ያለው ሰው በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ማድረግ አስፈላጊ አይመስለውም። (1 ጴጥሮስ 4:3-5) እንዲህ ዓይነቱ ሰው እርካታ የሚያገኘው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ አኗኗሩ በሚያስገኘው ውጤት ነው። (መዝሙር 144:11-15ሀ) በሌላው በኩል ደግ ሰው በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ማድረግ ይፈልጋል። በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ቅድሚያ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ይሖዋ አምላኩ ስለሆነና የሉዓላዊው ጌታ አገልጋይ በመሆኑ ወደር የሌለው ደስታ ስለሚያገኝ እርካታ ይኖረዋል።—መዝሙር 144:15ለ
‘ሁሉን አትመን’
የተላላ ሰውንና የአስተዋይን መንገድ በማነጻጸር ሰሎሞን “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 14:15) አስተዋይ ሰው በቀላሉ አይደለልም። የሰማውን ሁሉ ከማመን ወይም በሌሎች አመለካከት ከመመራት ይልቅ አካሄዱን በጥበብ ይመለከታል። መረጃዎችን በማሰባሰብ በእውቀት ላይ ተመሥርቶ እርምጃ ይወስዳል።
“አምላክ አለ?” የሚለውን ጥያቄ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ተላላ ሰው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ወይም ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች የሚያምኑትን ነገር ወደ መቀበል ያዘነብላል። በሌላው በኩል ግን አስተዋይ የሆነ ሰው ጊዜ ወስዶ መረጃዎችን ይመረምራል። በሮሜ 1:20 እና በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ያጤናል። አስተዋይ ሰው መንፈሳዊ ነገርን በተመለከተ የሃይማኖት መሪዎች የተናገሩትን ሐሳብ ብቻ ከመቀበል ይልቅ ‘መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን ይመረምራል።’—1 ዮሐንስ 4:1
‘ሁሉን ነገር ማመን’ እንደሌለብን የተሰጠንን ምክር መከተል ምንኛ ጥበብ ነው! በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሌሎችን የመምከር ኃላፊነት ለተጣለባቸው ሰዎች ይህ ልብ ሊሉት የሚገባ ቁም ነገር ነው። ምክር ሰጪው ወንድም ምን እንደተፈጸመ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ምክሩ ጥበብ የጎደለውና ለአንድ ወገን ያደላ እንዳይሆን በጥንቃቄ ማዳመጥና መረጃዎችን ከሁሉም አቅጣጫ ማሰባሰብ ይኖርበታል።—ምሳሌ 18:13፤ 29:20
“መሠሪም ሰው አይወደድም”
የእስራኤል ንጉሥ በጠቢብና በተላላ መካከል ያለውን ተጨማሪ ልዩነት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ጠቢብ ሰው ጥንቁቅ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ ተላላ ግን ችኩልና ደንታ ቢስ ነው [“ራሱን ታምኖ ይኰራል፣” የ1954 ትርጉም]። ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል፤ መሠሪም ሰው አይወደድም።”—ምሳሌ 14:16, 17
ጠቢብ ሰው የተሳሳተ ጎዳና መከተል የሚያስከትለውን መዘዝ ይፈራል። ጠንቃቃ ከመሆኑም በላይ ክፋትን ለማስወገድ የሚረዳውን ማንኛውንም ምክር ያደንቃል። ሰነፍ ግን ይህ ዓይነቱ ፍራቻ የለውም። በራሱ ስለሚተማመን የሌሎችን ምክር በትዕቢት ይንቃል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው በቀላሉ የሚቆጣ በመሆኑ የቂልነት ተግባር ይፈጽማል። ሆኖም መሠሪ ሰው የማይወደደው ለምንድን ነው?
‘መሠሪ’ ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቃል ሁለት ትርጉም አለው። አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሲሠራበት አስተዋይ ወይም ብልህ ማለት ነው። (ምሳሌ 1:4፤ 2:11፤ 3:21) ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ቃሉ ክፋትን ወይም መሠሪነትን ሊያመለክት ይችላል።—መዝሙር 37:7፤ ምሳሌ 12:2፤ 24:8
‘መሠሪ’ ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያ ቃል ተንኮል የሚያውጠነጥንን ሰው የሚገልጽ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለምን እንደሚጠላ ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። ሆኖም አስተዋይ የሆነ ሰውም ጭምር ይህንን ባሕርይ በማያሳዩ ሰዎች ሲጠላ እንመለከት የለም? ለምሳሌ፣ የማሰብ ችሎታቸውን በመጠቀም ‘ከዓለም ላለመሆን’ የሚመርጡ ሰዎች በዓለም ይጠላሉ። (ዮሐንስ 15:19) የማገናዘብ ችሎታቸውን የሚጠቀሙና እኩዮች የሚያሳድሩትን ጤናማ ያልሆነ ተጽዕኖ በመቋቋም ከመጥፎ ባሕርይ የሚርቁ ክርስቲያን ወጣቶች ይፌዝባቸዋል። እውነተኛ አምላኪዎች በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም መጠላታቸው የሚጠበቅ ነው።—1 ዮሐንስ 5:19
“ክፉዎች በደጎች ፊት . . . ያጐነብሳሉ”
አስተዋዮች ብስለት ከሌላቸው ሰዎች የሚለዩበት ሌላም መንገድ አለ። “ብስለት የሌላቸው ተላላነትን ይወርሳሉ፤ አስተዋዮች ግን ዕውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።” (ምሳሌ 14:18) ብስለት የሌላቸው ሰዎች ማስተዋል ስለሚጎድላቸው የሞኝነት አካሄድ የሚመርጡ ሲሆን ሕይወታቸውንም የሚመሩት በዚሁ መንገድ ይሆናል። በሌላው በኩል ደግሞ ዘውድ ንጉሥን እንደሚያስከብረው ሁሉ እውቀትም አስተዋዮችን ያስውባቸዋል።
ጠቢቡ ንጉሥ “ክፉዎች በደጎች ፊት፣ ኀጥኣንም በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ” ብሏል። (ምሳሌ 14:19) ይህም ውሎ አድሮ ደጎች በክፉዎች ላይ ድልን ይጎናጸፋሉ ማለት ነው። የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ ያገኙትን ከፍተኛ ጭማሪና ያላቸውን የላቀ የአኗኗር ዘይቤ መመልከት ይቻላል። አንዳንድ ተቃዋሚዎች የአምላክ አገልጋዮች ያገኙትን በረከት ሲመለከቱ በምድር ላይ ያሉትን በመንፈስ የተቀቡ ቀሪዎች ለምታመለክተው በሰማይ ለምትገኘው ምሳሌያዊት ሴት ‘ለማጐንበስ’ ይገደዳሉ። እነዚህ ተቃዋሚዎች በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በሰማይ ያለውን ድርጅቱን እንደሚወክል ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም በአርማጌዶን ጦርነት ግን ይህን ሐቅ ለመገንዘብ ይገደዳሉ።—ኢሳይያስ 60:1, 14፤ ገላትያ 6:16፤ ራእይ 16:14, 16
“ለተቸገሩት የሚራራ”
ሰሎሞን ስለ ሰው ተፈጥሮ በሚገባ ካስተዋለ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ድኾችን ወዳጆቻቸው እንኳ ይጠሏቸዋል፤ ባለጠጎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው።” (ምሳሌ 14:20) ይህ አባባል ኃጢአተኞች በሆኑት የሰው ልጆች ላይ በትክክል ይሠራል! የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ስላላቸው ሀብታሞችን ከድሆች አስበልጠው የመመልከት አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ሀብታሞች ብዙ ጓደኞች ቢኖሯቸውም እነዚህ ወዳጆቻቸው ልክ እንደ ሀብታቸው ዘላቂ አይደሉም። ታዲያ በገንዘብ ወይም በመሸንገል ወዳጅነት ለማፍራት ከመሞከር መራቅ አይኖርብንም?
ራሳችንን በሐቀኝነት ስንመረምር የባለጠጋ ሰዎች ወዳጅነትን በመሻት ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን እንደምንንቅ ብንገነዘብስ? እንደዚህ ዓይነት ወገናዊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘ መሆኑን መገንዘብ አለብን። የአምላክ ቃል “ጎረቤቱን የሚንቅ ኀጢአት ይሠራል፤ ለተቸገሩት የሚራራ ግን ቡሩክ ነው” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 14:21
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ላሉ ሰዎች አሳቢነት ማሳየት አለብን። (ያዕቆብ 1:27) ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ‘ባለን ሀብት’ ይኸውም በገንዘብ፣ በምግብ፣ በመጠለያና በልብስ ረገድ የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ልዩ ትኩረት በመስጠት ነው። (1 ዮሐንስ 3:17) መጽሐፍ ቅዱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ስለሚል ለእንደነዚህ ዓይነት ግለሰቦች የሚራሩ ደስተኞች ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
አስተዋይና ተላላ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል?
“ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” የሚለው መሠረታዊ መመሪያ ለአስተዋዩም ሆነ ለተላላው ሰው ይሠራል። (ገላትያ 6:7) አስተዋዩ ጥሩ ነገር ሲሠራ ተላላው ግን ተንኮል ይሸርባል። ጠቢቡ ንጉሥ “ክፉ ነገር የሚያቅዱ ከትክክለኛው መንገድ ይወጡ የለምን?” በማለት ጠይቋል። አዎን፣ መንገዳቸውን “ይስታሉ።” (የ1954 ትርጉም) “በጎ ነገር የሚያቅዱ ግን ፍቅርንና ታማኝነትን ያተርፋሉ።” (ምሳሌ 14:22) በጎ ነገር የሚሠሩ በሌሎች ዘንድ ተወዳጅነት ከማትረፋቸውም በላይ የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት ያገኛሉ።
ሰሎሞን ጠንክሮ መሥራት ስኬት እንደሚያስገኝ እንዲሁም ብዙ ማውራትና ሥራ ፈት መሆን ለውድቀት እንደሚዳርግ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ለፍተው የሠሩት ሁሉ ትርፍ ያስገኛል፤ ከንቱ ወሬ ግን ወደ ድኽነት ያመራል።” (ምሳሌ 14:23) ይህ መሠረታዊ መመሪያ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን በተመለከተም ይሠራል። በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ጠንክረን ስንሠራ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ የሆነውን እውነት ለሌሎች ማካፈል የሚያመጣውን በረከት እናጭዳለን። ምንም ዓይነት ቲኦክራሲያዊ ሥራ ቢሰጠን በታማኝነት የምንወጣው ከሆነ ደስታና እርካታ እናገኛለን።
ምሳሌ 14:24 ላይ “ጠቢባን ብልጥግና ዘውዳቸው ነው፤ የተላሎች ተላላነት ግን ፍሬው ከንቱነት ነው” ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለጥበበኞች ሀብት የሚሆናቸው ጥረው የሚያገኙት ጥበብ ሲሆን ይህም ዘውድ ይሆንላቸዋል ወይም ያስጌጣቸዋል ማለት ሊሆን ይችላል። በሌላው በኩል የተላሎች ተላላነት ግን ፍሬው ከንቱነት ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ምሳሌ ሲፈታው “ሀብት በሚገባ ለተጠቀሙበት ጌጥ ነው . . . ሞኞች ግን ሞኝነታቸውን ይዘው ይቀራሉ” ብሏል። ያም ሆነ ይህ የጥበበኛ ሰው መጨረሻ ከሞኙ የተሻለ ይሆናል።
የእስራኤል ንጉሥ ቀጥሎም እንዲህ በማለት ይናገራል:- “እውነተኛ ምስክር ሕይወት ያድናል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን አባይ ነው።” (ምሳሌ 14:25) ይህ ጥቅስ በፍርድ ረገድ የሚሠራ ቢሆንም በአገልግሎታችንም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ስለ መንግሥቱ የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራችን በአምላክ ቃል ውስጥ ስላለው እውነት መመሥከርንም ያጠቃልላል። ምሥክርነቱ ቅን ልብ ያላቸውን ግለሰቦች ከሐሰት ሃይማኖት ነጻ የሚያወጣ ከመሆኑም በላይ የሰዎችን ሕይወት ይታደጋል። ለራሳችንና ለትምህርታችን በመጠንቀቅ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ይህንን በማድረግ በሁሉም የሕይወታችን ክፍል አስተዋይነትን ለማንጸባረቅ ንቁ እንሁን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በምሳሌ 14:1-11 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-29 ተመልከት።
b የጥቅምት 22, 1987 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 11-16 ተመልከት።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልካሙን ከክፉው ለመለየት እንድንችል ጥልቀት ያላቸውን እውነቶች በትጋት ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ አኗኗር እውነተኛ እርካታ ያመጣልናል?