በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ትምህርቶችን ከየት ማግኘት ይቻላል?

እውነተኛ ትምህርቶችን ከየት ማግኘት ይቻላል?

እውነተኛ ትምህርቶችን ከየት ማግኘት ይቻላል?

 በቲቤት የሚኖር አንድ ሰው አነስተኛ ከበሮ የሚመስልና በውስጡ ጸሎቶች የተጻፉበት ዕቃ በእንጨት ላይ ሰክቶ ሲያሽከረክር ይታያል። ሰውየው ዕቃውን ባሽከረከረው ቁጥር ጸሎቶቹ ይደገማሉ የሚል እምነት አለው። ሕንድ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ቤት ፑጃ በመባል የሚታወቀውን አምልኮ ለማከናወን ተብሎ የተዘጋጀ አነስተኛ ክፍል አለ፤ የአምልኮ ሥርዓቱ ለተለያዩ የወንድና የሴት አማልክት ምስሎች ዕጣን፣ አበባና ሌሎች ነገሮችን ማቅረብን ሊያካትት ይችላል። በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው በኢጣሊያ ደግሞ መቁጠሪያ የያዘች አንዲት ሴት ባማረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኢየሱስ እናት በማርያም ምስል ፊት ተንበርክካ ትጸልያለች።

አንተም ሃይማኖት በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስተውለህ ይሆናል። ዘ ዎርልድስ ሪሊጅንስ—አንደርስታንዲንግ ዘ ሊቪንግ ፌዝስ የሚለው መጽሐፍ “ሃይማኖት . . . ባለፉት ዓመታት ሁሉ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ማኅበረሰቦች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና የነበረው ሲሆን ወደፊትም ይኸው ሁኔታ ይቀጥላል” ይላል። ጆን ቦከር የተባሉት ደራሲ ጎድ—ኤ ብሪፍ ሂስትሪ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በአምላክ የሚያምን ኅብረተሰብ ያልነበረበት ዘመን የለም ለማለት ይቻላል፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ የገዢነት ወይም የፈጣሪነት ቦታ ይሰጠዋል። በአምላክ መኖር በማያምኑ አገሮች ውስጥ እንኳ እንዲህ ያለው ሁኔታ ይታያል።”

በእርግጥም ሃይማኖት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ ሁኔታ የሰው ዘር መንፈሳዊ ፍላጎትና ጥማት እንዳለው የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አይደለም? ስመ ጥር የሥነ ልቦና ምሑር የሆኑት ዶክተር ካርል ጉስታቭ ጀንግ ዚ አንዲስከቨርድ ሰልፍ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በሰው ዘር ታሪክ ሁሉ አንድን ታላቅ ኃይል የማምለክ ፍላጎት” እንደነበረ ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰዎች በአምላክ አያምኑም፤ ለሃይማኖትም ግድ የላቸውም። አምላክ መኖሩን የሚጠራጠሩ ወይም እስከ ጭራሹ መኖሩን የማይቀበሉ አንዳንዶች እንዲህ ያለው መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት የሚያውቋቸው ሃይማኖቶች መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ሊያረኩላቸው አለመቻላቸው ነው። ሃይማኖት “ለአንድ ሥርዓት ያደሩ መሆን፣ ፍጹም ታማኝነት፣ በሕሊና መመራት፣ የአምልኮ ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሟል። በዚህ ትርጉም መሠረት አምላክ የለም ባዮችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ለሚያምንባቸው ደንቦች ያደረ በመሆኑ አንድ ዓይነት ሃይማኖት አለው ማለት ይቻላል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን በሚሸፍነው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ፍላጎቱን ለማርካት ሲል የተለያዩ ዓይነት አምልኮዎችን ሞክሯል። ይህም በዓለም ላይ የምንመለከታቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሃይማኖታዊ አመለካከቶች እንዲኖሩ አድርጓል። ለአብነት ያህል፣ ሁሉም ሃይማኖቶች ማለት ይቻላል በአንድ ታላቅ ኃይል ያምናሉ፤ ሆኖም ስለዚህ ኃይል ማንነት ወይም ምንነት ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአብዛኞቹ እምነቶች ውስጥ መዳን ወይም ነጻ መውጣት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። መዳን ምንድን ነው? እንዴትስ ይገኛል? ሲባል ግን የሚያስተምሩት ትምህርት የተለያየ ነው። ከእነዚህ ሁሉ እምነቶች መካከል አምላክን የሚያስደስቱትን እውነተኛ ትምህርቶች ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?