መቆጣት ሁልጊዜ ስህተት ሊሆን ይችላል?
መቆጣት ሁልጊዜ ስህተት ሊሆን ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 7:9 ላይ ‘የሞኞች ቊጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ነው’ በማለት ይናገራል። ይህ ጥቅስ አንድ ሰው ሲበድለን ከመጠን በላይ ከመበሳጨት ይልቅ ይቅር ባዮች መሆን እንዳለብን ያሳያል።
ይሁን እንጂ መክብብ 7:9 በምንም ነገር ወይም በማንም ላይ መቆጣት እንደሌለብን እየተናገረ ነው? የደረሰብን በደል ምንም ያህል ከባድ ቢሆንና የቱንም ያህል ጊዜ ቢደጋገም ለማስተካከል ምንም ጥረት ሳናደርግ በአጠቃላይ ይቅር ማለት አለብን ማለቱ ነው? የተቀየመ ሰው ይቅርታ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ስለምናውቅ ሌሎችን በአነጋገራችንም ሆነ በድርጊታችን እንዳናስቀይም መጠንቀቅ አያስፈልገንም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም።
ይሖዋ በፍቅሩ፣ በመሐሪነቱ፣ በይቅር ባይነቱና በታጋሽነቱ ምሳሌ የሚሆን አምላክ ነው። ሆኖም ይሖዋ የተቆጣባቸው በርካታ ጊዜያት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በደሉ ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ባስቆጡት ሰዎች ላይ እርምጃ ይወስድ ነበር። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
በይሖዋ ላይ የተፈጸሙ በደሎች
ኢዮርብዓም ‘እስራኤል [ኃጢአት] እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት እግዚአብሔርን ለቊጣ በማነሣሣት’ መበደሉን 1 ነገሥት 15:30 ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ዜና መዋዕል 28:25 ላይ የይሁዳን ንጉሥ አካዝን በተመለከተ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ አነሣሣው።” ሌላው ምሳሌ ደግሞ በመሳፍንት 2:11-14 ላይ ይገኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። . . . እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ . . . እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው።”
ይሖዋ እንዲቆጣና ከባድ እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርጉት ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለአብነት ያህል በዘፀአት 22:18-20 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ። ከእንስሳ ጋር ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽም ሰው ይገደል። ለእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አማልክት የሚሠዋ ይጥፋ።”
ይሖዋ የጥንት እስራኤላውያን እርሱን ማስቆጣታቸውን ካላቆሙና እውነተኛ ንስሐ ካልገቡ ለፈጸሟቸው ከባድ በደሎች እንዲያው ሁልጊዜ ይቅርታ አያደርግላቸውም። ይሖዋ ልባዊ ንስሐ አንገባም ሲሉና ተመልሰው እርሱን መታዘዝ መጀመራቸውን የሚያሳይ እርምጃ ሳይወስዱ ሲቀሩ እንዲጠፉ አድርጓል። ይህ ሁኔታ የተከሰተው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ607 በባቢሎናውያን፣ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ደግሞ በሮማውያን እጅ በብሔር ደረጃ በጠፉበት ጊዜ ነው።
አዎን፣ ይሖዋ ሰዎች በቃላትም ይሁን በድርጊት በሚፈጽሟቸው መጥፎ ነገሮች የሚቆጣ ከመሆኑም በላይ ከባድ ኃጢአት ሠርተው ንስሐ የማይገቡ በደለኞችንም ያጠፋል። ይሁንና እንዲህ ማድረጉ በመክብብ 7:9 ላይ ከተገለጹት ተርታ ያሰልፈዋል? በጭራሽ። ይሖዋ ከባድ ኃጢአቶች ሲፈጸሙ የሚቆጣበት በቂ ምክንያት ያለው ከመሆኑም ባሻገር ፍርዱ ምንጊዜም ትክክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው” በማለት ስለ ይሖዋ ይናገራል።—ዘዳግም 32:4
በግለሰቦች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ በደሎች
አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የሰጠው ሕግ በሌሎች ላይ ከባድ በደሎችን መፈጸም ስለሚያስከትለው ዘፀአት 22:2
አስፈሪ መዘዝ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሌባ፣ ሰው ቤት በሌሊት ቢገባና የቤቱ ባለቤት ቢገድለው ገዳዩ በደም ዕዳ አይጠየቅም ነበር። የቤቱ ባለቤት የከባድ ወንጀል ሰለባ የሆነ ንጹሕ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሌባ በር ሲሰብር ተይዞ ቢደበደብና ቢሞት፣ ተከላካዩ የደም ባለ ዕዳ አይሆንም” የሚለው ለዚህ ነው።—አስገድዶ መድፈር በአምላክ ዓይን በጣም ከባድ ወንጀል እንደመሆኑ መጠን ይህ ጥቃት የደረሰባት ሴት በጣም ብትቆጣ ምንም አያስደንቅም። ሴት አስገድዶ መድፈር “አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ከሚገድል ሰው አድራጎት ጋር የሚመሳሰል” በመሆኑ በሙሴ ሕግ መሠረት ይህን የፈጸመ ወንድ መሞት ነበረበት። (ዘዳግም 22:25, 26) እኛ በዚህ ሕግ ሥር ባንሆንም ይሖዋ ዘግናኝ ስለሆነው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ምን እንደሚሰማው በጥልቅ እንድናስተውል ይረዳናል።
አሁንም ቢሆን አስገድዶ መድፈር ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ትልቅ ወንጀል ነው። ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሰዎች ጉዳዩን ለፖሊስ የማስታወቅ ሙሉ መብት አላቸው። በዚህ መንገድ፣ በደል የፈጸመው ሰው ከሚመለከታቸው ባለ ሥልጣናት ተገቢውን ቅጣት ያገኛል። የጥቃቱ ሰለባዎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ከሆኑ ደግሞ ወላጆች ተገቢውን ፍርድ ለማግኘት አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዱ ይሆናል።
ቀላል በደሎች
ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት በደል በባለ ሥልጣናት ያስቀጣል ማለት አይደለም። በመሆኑም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ አነስተኛ በሆኑ ሌሎች በሚፈጽሟቸው ስህተቶች ከመጠን በላይ ከመቆጣት ይልቅ ይቅር ባዮች ማቴዎስ 18:21, 22
መሆን ይገባናል። ይቅር ማለት የሚኖርብን ስንት ጊዜ ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስ ሲመልስ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው።—በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን የምናስቀይምበትን አጋጣሚ ለመቀነስ የሚረዱንን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለማሳደግ ዘወትር ጥረት ልናደርግ ይገባል። ለምሳሌ ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ የምትናገረው እንዳመጣልህ ወይም ደግሞ ብልሃት በጎደለው አሊያም በሚያበሳጭ መንገድ ነው? እንዲህ ባለ መንገድ መናገር ሊያስቆጣ ይችላል። በደሉን የፈጸመው ሰው፣ ተጎጂው በመቆጣቱ ምክንያት ከመንቀፍና ይቅርታ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ከማሰብ ይልቅ ለሰውየው መቆጣት መንስኤ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል። ከመጀመሪያውም ቢሆን በደሉን የፈጸመው ግለሰብ ድርጊቱንና ንግግሩን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ሌላውን ሰው እንዳያበሳጭ መጠንቀቅ ነበረበት። እንዲህ ያለውን ጥረት ማድረግ የሌሎችን ስሜት በተደጋጋሚ ከመጉዳት እንድንቆጠብ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ያሳስበናል። (ምሳሌ 12:18) ሆን ብለን ባይሆንም እንኳ ሌሎችን በምናስቀይምበት ጊዜ ይቅርታ መጠየቃችን ለችግሩ እልባት ለማግኘት የሚረዳን ውጤታማ መንገድ ነው።
የአምላክ ቃል “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት” ማድረግ እንዳለብን ይገልጻል። (ሮሜ 14:19) ዘዴኛና ደግ ከሆንን “ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው” የሚለውን በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በተግባር እናውላለን። (ምሳሌ 25:11) እንዴት የሚያስደስት አባባል ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል” ስለሚል በለስላሳ አንደበትና በዘዴ የተነገረ ቃል የሌሎችን ግትር አስተሳሰብ እንኳ ሊቀይር ይችላል።—ምሳሌ 25:15
በዚህ ምክንያት የአምላክ ቃል “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን” በማለት ይመክረናል። (ቈላስይስ 4:6) “በጨው እንደ ተቀመመ” ሲባል ሌሎች ለቁጣ የሚነሳሱበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ንግግራችን እንዲጣፍጥ ማድረግ ማለት ነው። ክርስቲያኖች በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው “ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማሳሰቢያ በሥራ ላይ ለማዋል ይጥራሉ።—1 ጴጥሮስ 3:11
ስለዚህ መክብብ 7:9 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ ጥቃቅን የሆኑ በደሎች ሲፈጸሙብን ከመቆጣት መታቀብ እንዳለብን መናገሩ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። እነዚህ ጥቃቅን በደሎች ከሰው አለፍጽምና የመነጩ ወይም ሆን ተብለው የተደረጉ ሊሆኑ ቢችሉም ያን ያህል የጎሉ አይደሉም። ይሁን እንጂ የተፈጸመው በደል ከባድ ከሆነ የተበደለው ሰው ሊቆጣና ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ የሚችልበት በቂ ምክንያት አለው።—ማቴዎስ 18:15-17
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ንስሐ ያልገባው የእስራኤል ብሔር በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮማውያን እንዲጠፋ አድርጓል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ባግባቡ የተነገረ ቃል” እንደ “ወርቅ እንኮይ ነው”