ከስሜትህ ጋር እየታገልክ ነው?
ከስሜትህ ጋር እየታገልክ ነው?
ሊና አብዛኛውን ዕድሜዋን ያሳለፈችው ለራሷ ካላት አፍራሽ ስሜት ጋር ትግል በማድረግ ነው። “በልጅነቴ ለዓመታት ሲፈጸምብኝ የነበረው የወሲብ ጥቃት ለራሴ ሊኖረኝ የሚገባውን አክብሮት ከሞላ ጎደል ገድሎታል። ፈጽሞ የማልረባ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። ሲሞንም የወጣትነት ጊዜዋን መለስ ብላ በማስታወስ “በውስጤ የባዶነትና የእርባና ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለውን ስሜት ተከትሎ የሚመጣው ደስታ የማጣት ችግር በጣም እየተስፋፋ ያለ ይመስላል። በጉርምስና ዕድሜ ለሚገኙ ልጆች በስልክ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ድርጅት ከሚደውሉት ወጣቶች መካከል ግማሽ የሚያህሉት “ዘወትር የዋጋ ቢስነት ስሜት” እንደሚሰማቸው ተናግሯል።
እንደ አንዳንዶቹ የሕክምና ዶክተሮች አባባል ሰዎች ‘ለምንም ነገር ብቁ አይደለሁም’ የሚለው ስሜት የሚፈጠርባቸው የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነገር ሲፈጸምባቸው ነው። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የሚመነጨው አንድ ሰው በተደጋጋሚ ሲነቀፍ፣ ከልክ በላይ ሲተች ወይም ግፍ ሲፈጸምበት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይህ ስሜት ቅስምን የሚሰብር አልፎ ተርፎም ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል። በቅርብ የተደረገ አንድ የሕክምና ጥናት እንዳመለከተው ስለራሳቸው አፍራሽ አመለካከት ያላቸው ሰዎች
ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ማመን ስለሚከብዳቸው ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቀስ በቀስ ያበላሻሉ። “በሌላ አነጋገር በጣም ይፈሩት የነበረውን ሁኔታ በገዛ እጃቸው ‘ይፈጥራሉ።’”እንደዚህ የሚሰማቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አብዛኛውን ጊዜ ‘በውስጣቸው ጭንቀት’ የቆሰሉ ናቸው። (መዝሙር 94:19) ለምንም ነገር ብቁ እንደሆኑ አይሰማቸውም። አንድ ነገር ባልተሳካ ቁጥር ቶሎ ብለው ራሳቸውን መኮነን ይቀናቸዋል። ስኬታማ ለሆኑበት ነገር ሌሎች ቢያመሰግኗቸው እንኳ ይዋል ይደር እንጂ መጋለጡ የማይቀር አስመሳይ ሰው እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ብዙዎቹ ለደስታ እንዳልተፈጠሩ ሆኖ ስለሚሰማቸው ራሳቸውን ለጎጂ ባሕርያት ያጋልጣሉ፤ እንዲሁም እነዚህን ጎጂ ባሕርያት ፈጽሞ ማሸነፍ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊና ለራሷ ካላት ዝቅተኛ ግምት የተነሳ ከፍተኛ የአመጋገብ መዛባት ችግር አጋጥሟት የነበረ ሲሆን “ችግሩ ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች።
‘የውስጣቸው ጭንቀት’ የሚያሰቃያቸው ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን እንዲህ እየተሰማቸው ይኖራሉ ማለት ነው? ይህን ዓይነቱን ስሜት ለማሸነፍ ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ? መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች ይህን ትግል እንዲያሸንፉ የረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ምክሮችን ይዟል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? የስሜት ቁስል ያለባቸውን ሰዎች ደስታ እንዲያገኙ የረዷቸውስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን በተመለከተ ማብራሪያ ይሰጣል።