በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር” በይሖዋ ተቆጥሯል

“የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር” በይሖዋ ተቆጥሯል

“የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር” በይሖዋ ተቆጥሯል

“አንዲቷ [ድንቢጥ] እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው።”—ማቴዎስ 10:29, 30

1, 2. (ሀ) ኢዮብ አምላክ እንደተወው ሆኖ የተሰማው ለምን ነበር? (ለ) የኢዮብ አነጋገር የአምላክ ተቃዋሚ ወደ መሆን እንዳዘነበለ ያመለክታል? አብራራ።

 “እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ነገር ግን አልመለስህልኝም፤ በፊትህም ቆምሁ፤ አንተ ግን ዝም አልኸኝ። ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በክንድህም ብርታት አስጨነቅኸኝ።” እነዚህን ቃላት የተናገረው ሰው በጣም ተጨንቆ ነበር፤ ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም! ምክንያቱም መተዳደሪያውን አጥቷል፣ ድንገተኛ አደጋ ልጆቹን በሞት ነጥቆታል፣ ከዚያ ደግሞ እርሱ ራሱ በከባድ በሽታ ይሰቃይ ጀመር። ሰውየው ኢዮብ የሚባል ሲሆን የደረሰበት አሰቃቂ መከራ ለእኛ ጥቅም ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል።—ኢዮብ 30:20, 21

2 የኢዮብ አነጋገር የአምላክ ተቃዋሚ ወደ መሆን ያዘነበለ ቢያስመስለውም ሁኔታው ግን እንዲህ አልነበረም። ኢዮብ የውስጡን ጭንቀት እየገለጸ ነበር። (ኢዮብ 6:2, 3) ችግር እየደረሰበት ያለው በሰይጣን ምክንያት መሆኑን ስላላወቀ ‘አምላክ ትቶኛል’ ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ደርሶ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋን “ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? እንደ ጠላትህስ ለምን ትቈጥረኛለህ?” እስከ ማለት ደርሷል። aኢዮብ 13:24

3. መከራ ሲደርስብን ምን ሊሰማን ይችላል?

3 በዛሬው ጊዜ በርካታ የይሖዋ ሕዝቦች በጦርነት፣ በፖለቲካዊ ወይም በማኅበራዊ አለመረጋጋት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በዕድሜ መግፋት፣ በጤና ማጣት፣ በከባድ ድህነትና በመንግሥታዊ እገዳዎች ሳቢያ ያለማቋረጥ ችግሮች ይደርሱባቸዋል። አንተም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወይም ሌላ ዓይነት ችግር እየደረሰብህ ይሆናል። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ፊቱን እንዳዞረብህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” የሚሉትን በዮሐንስ 3:16 ላይ የሚገኙትን ቃላት አሳምረህ ታውቃቸዋለህ። ሆኖም አለምንም ፋታ ሥቃይ ሲደርስብህ ‘አምላክ በእርግጥ እኔንም ይወደኛል? የሚደርሱብኝን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ ያያል? በግለሰብ ደረጃስ ያስብልኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

4. ጳውሎስ ከምን ችግር ጋር እየታገለ መኖር አስፈልጎት ነበር? ይህ ሁኔታ እኛንስ እንዴት ሊነካን ይችላል?

4 እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንዳጋጠመው ተመልከት። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት።” ይሖዋ የጳውሎስን ልመና የሰማ ቢሆንም ለችግሩ ተአምራዊ መፍትሔ እንደማይሰጠው ነግሮት ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ያለበትን ‘የሥጋ መውጊያ’ መቋቋም እንዲችል የአምላክ ኃይል እንደሚረዳው መተማመን ነበረበት። b (2 ቆሮንቶስ 12:7-9) አንተም እንደ ጳውሎስ መፍትሔ የሌለው የሚመስል ችግር ይኖርብህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ‘ይሖዋ እየደረሰብኝ ላለው ችግር ምንም መፍትሔ አለመስጠቱ ያለሁበትን ሁኔታ እንደማያውቅ ወይም ስለ እኔ እንደማያስብ የሚያሳይ ነው?’ የሚል ጥያቄ ታነሳ ይሆናል። መልሱ በጭራሽ አይደለም የሚል ነው! ይሖዋ ለእያንዳንዱ ታማኝ አገልጋዩ ከልብ እንደሚያስብ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከመረጣቸው ከጥቂት ጊዜ በኋላ በነገራቸው ነገር ላይ ጎላ አድርጎ ገልጾታል። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በዚህ ዘመን ያለነውን እንዴት እንደሚያበረታቱን እንመልከት።

“አትፍሩ”—ለምን?

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ሐዋርያቱ ወደፊት የሚያጋጥማቸውን ነገር በተመለከተ መፍራት እንደሌለባቸው ያስረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ ይሖዋ እንደሚያስብለት እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። ይህም “ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን” መቀበላቸውን ይጨምራል። እንዲህ ሲባል ግን ምንም ዓይነት መከራና ችግር አይገጥማቸውም ማለት አልነበረም። እንዲያውም በተቃራኒው ስለሚደርሱባቸው አንዳንድ ችግሮች ኢየሱስ ዝርዝር መግለጫ ሰጥቷቸዋል። ይሁንና “ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ” ሲል አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 10:1, 16-22, 28

6 ኢየሱስ ሐዋርያቱ ለምን መፍራት እንደሌለባቸው ለማስረዳት ሁለት ምሳሌዎችን ተጠቀመ። እንዲህ አላቸው:- “በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።” (ማቴዎስ 10:29-31) ኢየሱስ እዚህ ላይ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ አለመፍራትን፣ በግለሰብ ደረጃ ይሖዋ ያስብልኛል ብሎ ከመተማመን ጋር አያይዞ እንደገለጸው አስተውል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ እምነት እንደነበረው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?” (ሮሜ 8:31, 32) አንተም ለይሖዋ ታማኝ እስከሆንክ ድረስ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምህ እርሱ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ በጥልቅ እየመረመርን ስንሄድ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ በግልጽ መረዳት ትችላለህ።

የአንዲት ድንቢጥ ዋጋ

7, 8. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን ድንቢጦች እንዴት ይታዩ ነበር? (ለ) ኢየሱስ በማቴዎስ 10:29 ላይ ትንንሽ ድንቢጦችን የሚያመለክት ግሪክኛ ቃል የተጠቀመው ለምን ሊሆን ይችላል?

7 ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ እንደሚያስብ በሚገባ ያስገነዝባሉ። እስቲ መጀመሪያ ስለ ድንቢጦች እንመልከት። በኢየሱስ ዘመን ድንቢጦች ለምግብነት ይውሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሰብል ያጠፉ ስለነበር በአብዛኛው እንደ ተባይ ተደርገው ይታዩ ነበር። ድንቢጦች በብዛት የሚገኙና ርካሽ የነበሩ በመሆኑ በአሁኑ ገንዘብ መሠረት ሁለቱን ከአምስት ሳንቲም ባነሰ ዋጋ መግዛት ይቻል ነበር። የዚህ እጥፍ ከተከፈለ ደግሞ አራት ብቻ ሳይሆን አምስት ድንቢጦች መግዛት ይቻላል። አንደኛዋ ወፍ እንዲያው ምንም ዋጋ የሌላት ይመስል ምራቂ ተደርጋ ትሰጣለች!—ሉቃስ 12:6

8 የዚህችን ወፍ መጠንም ተመልከት። ለአካለ መጠን የደረሰች ድንቢጥ እንኳን ከሌሎች የወፍ ዝርያዎች ጋር ስትወዳደር በጣም ትንሽ ነች። እንዲህም ሆኖ በማቴዎስ 10:29 ላይ “ድንቢጦች” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በቀጥታ የሚናገረው ስለ ትንንሽ ድንቢጦች ነው። ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከቁም ነገር የማትቆጠር አንዲት ትንሽ ወፍ ወደ አእምሯቸው እንዲያመጡ ፈልጎ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

9. ኢየሱስ የጠቀሰው የድንቢጦቹ ምሳሌ ምን ቁም ነገር ይዟል?

9 ኢየሱስ ስለ ድንቢጦች የተናገረው ምሳሌ ትልቅ ቁም ነገር ይዟል፤ ይኸውም በሰዎች ዘንድ ምንም ዋጋ እንደሌለው ተደርጎ የሚታየውን ነገር ይሖዋ አምላክ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ኢየሱስ የዚህን ጉዳይ እውነትነት ይበልጥ ለማጉላት ሲል ትንሿ ድንቢጥ ያለ ይሖዋ ፈቃድ “ምድር ላይ አትወድቅም” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። c ትምህርቱ ግልጽ ነው። ይሖዋ አምላክ በጣም ትንሽ ለሆነችና ማንም ከቁም ነገር ለማይቆጥራት ወፍ ትኩረት ከሰጠ እርሱን ማገልገል የሚፈልግ ሰው ስለሚገጥመው ሁኔታ ምን ያህል ያስብ!

10. “የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው” የሚለው አነጋገር ምን ቁም ነገር ይዟል?

10 ኢየሱስ ስለ ድንቢጦቹ ከተናገረው ምሳሌ በተጨማሪ “የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው” ሲል ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 10:30) ይህ አጭር ሆኖም ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ዓረፍተ ነገር ኢየሱስ ስለ ድንቢጦቹ የተናገረውን ምሳሌ ነጥብ በጥልቅ ለመረዳት ያስችላል። እስቲ አስበው፤ በአንድ ሰው ራስ ላይ በአማካይ 100,000 የሚያህሉ ፀጉሮች ይገኛሉ። በአብዛኛው አንዷ ነጠላ ፀጉር ከሌላው ጋር በጣም ስለምትመሳሰል አንዷ ፀጉራችን ልዩ ትኩረት ሊደረግላት ይገባል ብለን አናስብም። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ለእያንዳንዱ ፀጉራችን ትኩረት ከመስጠቱም በተጨማሪ በራሳችን ላይ ያሉትን ፀጉሮች አንድም ሳይቀር ቆጥሯቸዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ይሖዋ ስለ ሕይወታችን የማያውቀው ነገር ይኖራል? ይሖዋ የእያንዳንዱን አገልጋዩን ባሕርይ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ምንም አያጠራጥርም። አልፎ ተርፎም “ልብን ያያል።”—1 ሳሙኤል 16:7

11. ዳዊት በግለሰብ ደረጃ ይሖዋ እንደሚያስብለት ያለውን እምነት የገለጸው እንዴት ነው?

11 በርካታ ችግሮች ይፈራረቁበት የነበረው ዳዊት ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጠው እምነት ነበረው። “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 139:1, 2) አንተም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያውቅህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ኤርምያስ 17:10) ‘ሁሉን የሚመለከተው ይሖዋ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያየኝ የሚያስችል ብቃት ፈጽሞ የለኝም’ ብለህ ለመደምደም አትቸኩል!

‘እንባዬን በአቊማዳህ አጠራቅም’

12. ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚደርስባቸውን ችግር በሚገባ እንደሚገነዘብ እንዴት መረዳት እንችላለን?

12 ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ ከማወቅም አልፎ ምን ችግር እየደረሰባቸው እንዳለ በሚገባ ይገነዘባል። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን በባርነት ሲሰቃዩ ይሖዋ ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር:- “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።” (ዘፀአት 3:7) ያጋጠመንን ችግር በጽናት ለመቋቋም ስንጣጣር ይሖዋ እንደሚመለከተንና ጩኸታችንንም እንደሚሰማ ማወቁ እንዴት ያጽናናል! ይሖዋ የሚደርስብንን ችግር ፈጽሞ በግድየለሽነት አይመለከትም።

13. ይሖዋ በእርግጥ የአገልጋዮቹን ስሜት እንደሚጋራ የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 ይሖዋ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት ለመሠረቱ ሰዎች ምን ያህል አሳቢ እንደሆነ ለእስራኤላውያን ከነበረው ስሜት ሰፊ ግንዛቤ ማግኘት ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ለችግር ይዳርጋቸው የነበረው የራሳቸው አንገተ ደንዳናነት ቢሆንም፣ ኢሳይያስ “በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ” በማለት ስለ ይሖዋ ስሜት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 63:9) የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን፣ ሥቃይ በሚደርስብህ ጊዜ እርሱም አብሮህ እንደሚሠቃይ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ይህን ማወቅህ የሚያጋጥሙህን መከራዎች ያለ ፍርሃት እንድትጋፈጥና አቅምህ በፈቀደው ሁሉ ይሖዋን ማገልገልህን እንድትቀጥል አላነሳሳህም?—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

14. መዝሙር 56 በተቀናበረበት ወቅት ሁኔታዎቹ ምን ይመስሉ ነበር?

14 ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚያስብለትና በሥቃዩ ጊዜ አብሮት እንደሚሠቃይ እምነት እንደነበረው መዝሙር 56 ያሳያል። ዳዊት ይህንን መዝሙር ያቀናበረው ሊገድለው ከሚፈልገው ከንጉሥ ሳኦል ፊት በመሸሽ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ዳዊት ወደ ጌት ሸሽቶ ሄዶ ነበር፤ ይሁንና ፍልስጥኤማውያን ማንነቱን በማወቃቸው ምክንያት እንዳይዙት ፍራቻ አደረበት። ዳዊት “ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በላዬ ቆሙ፤ በትዕቢት የሚዋጉኝ ብዙዎች ናቸውና” በማለት ጽፏል። የነበረበት ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ ምክንያት ፊቱን ወደ ይሖዋ አዞረ። እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቀኑን ሙሉ ቃሌን ያጣምሙታል፤ ዘወትርም ሊጐዱኝ ያሤራሉ።”—መዝሙር 56:2, 5

15. (ሀ) ዳዊት እንባውን በአቁማዳው እንዲያጠራቅምለት ወይም ደግሞ በመዝገቡ እንዲይዝለት ይሖዋን ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? (ለ) እምነትን ከሚፈታተን ሁኔታ ጋር እየታገልን ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

15 ዳዊት በመዝሙር 56:8 ላይ የሚከተሉትን ትኩረት የሚስቡ ቃላት ተናግሯል:- “ሰቆቃዬን መዝግብ፤ እንባዬን በዕቃህ [‘በአቊማዳህ፣’ የግርጌ ማስታወሻ] አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?” የይሖዋን ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳይ እንዴት ያለ መግለጫ ነው! በውጥረት ውስጥ ስንሆን ለይሖዋ ከእንባ ጋር ልመና ማቅረብ እንችላለን። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ እንኳን እንዲህ አድርጎ ነበር። (ዕብራውያን 5:7) ዳዊት፣ ይሖዋ እንባውን በአቁማዳ ያጠራቀመለት ያህል ወይም ደግሞ በመዝገብ ያሰፈረለት ያህል እንደሚከታተለውና ሥቃዩን እንደሚያስታውስ እምነት ነበረው። d ምናልባት የአንተ እንባ ያን አቁማዳ እንደሚሞላው ወይም የመዝገቡን በርካታ ገጾች እንደሚይዝ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—መዝሙር 34:18

የአምላክ የቅርብ ወዳጅ መሆን

16, 17. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ግድየለሽ እንዳልሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ይሖዋ ሕዝቦቹ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት እንዲችሉ ምን አድርጓል?

16 ይሖዋ ‘የራሳችንን ጠጒር እንኳ አንድ ሳይቀር’ የመቁጠሩ ሐቅ፣ በትኩረት የሚያየንንና የሚያስብልንን አምላክ እያመለክን እንዳለን መጠነኛ እውቀት እንድንገበይ አስችሎናል። ሙሉ ለሙሉ ከሥቃይና ከችግር የምንገላገልበትን ቃል የተገባልንን አዲስ ዓለም መጠበቅ ቢኖርብንም ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ጭምር ለእኛ ለሕዝቦቹ አንድ ግሩም ነገር እያደረገልን ነው። ዳዊት “እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤ ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 25:14

17 ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ።’ ይህ ፍጹም ላልሆኑ የሰው ልጆች የማይመስል ነገር ሊሆን ይችላል! ይሁንና ይሖዋ የሚፈሩት ሰዎች እንግዳ ሆነው በእርሱ ድንኳን ውስጥ እንዲያድሩ ይጋብዛቸዋል። (መዝሙር 15:1-5) ታዲያ ይሖዋ ለእንግዶቹ ምን ያደርግላቸዋል? ዳዊት እንደገለጸው ኪዳኑን ያሳውቃቸዋል። ይሖዋ ስለሚተማመንባቸው በነቢያቱ በኩል “ምስጢሩን” ይገልጥላቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ዓላማዎቹ ምን እንደሆኑና ከዓላማዎቹ ጋር ተስማምተው ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ማወቅ ይችላሉ።—አሞጽ 3:7

18. ይሖዋ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንድንመሠርት የሚፈልግ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

18 እኛ ፍጹማን ያልሆንን የሰው ልጆች የልዑሉ አምላክ የይሖዋ የቅርብ ወዳጆች መሆን እንደምንችል ማወቃችን በእውነትም ልብን የሚነካ ነው። እርሱም እንዲህ እንድናደርግ ነግሮናል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 4:8) ይሖዋ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይፈልጋል። እንዲያውም ይሖዋ እንዲህ ያለውን ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችል እርምጃ ወስዷል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለንን በር ከፍቶልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” ይላል።—1 ዮሐንስ 4:19

19. በትዕግሥት መጽናት ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲጠናከር የሚረዳን እንዴት ነው?

19 አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲደርሱብን በትዕግሥት መጽናታችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት እንዲጠናከር ያደርጋል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:4) መከራን በትዕግሥት ወይም በጽናት ማሳለፍ የሚፈጽመው “ሥራ” ምንድን ነው? ጳውሎስ የነበረበትን ‘የሥጋ መውጊያ’ አስታውስ። ጳውሎስ በትዕግሥት መጽናቱ ምን ስኬት አስገኝቶለታል? “የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና” በማለት ስለነበረበት ችግር ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10) የጳውሎስ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይሖዋ አስፈላጊውን ኃይል ሰጥቶታል፤ እንዲያውም ከወትሮው የተለየ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ያገኘበት ጊዜም አለ። በዚህ ምክንያት በችግሩ ለመጽናት ችሏል። ይህ ደግሞ ከክርስቶስና ከይሖዋ አምላክ ጋር ይበልጥ እንዲቀራረብ አድርጎታል።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:11-13

20. ይሖዋ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ እንደሚደግፈንና እንደሚያጽናናን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

20 ምናልባት ይሖዋ ያለብህ ችግር እንዲቀጥል ሊፈቅድ ይችላል። ሁኔታህ እንዲህ ከሆነ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” በማለት እርሱን ለሚፈሩት የገባውን ቃል ምንጊዜም አስታውስ። (ዕብራውያን 13:5) ይህን የመሰለ ድጋፍና መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። ይሖዋ ‘የራስ ጠጒርህን እንኳ አንድ ሳይቀር’ ቆጥሮታል። ትዕግሥትህን ይመለከታል፣ ሥቃይህ ይሰማዋል እንዲሁም በጥልቅ ያስብልሃል። ከዚህም በላይ ‘ሥራህንና ስለ ስሙ ያሳየኸውን ፍቅር አይረሳም።’—ዕብራውያን 6:10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጻድቁ ዳዊትና ታማኞቹ የቆሬ ልጆች ተመሳሳይ የሆኑ አገላለጾችን ተጠቅመዋል።—መዝሙር 10:1፤ 44:24

b መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስ የነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ምን እንደሆነ በግልጽ አይናገርም። ምናልባትም አጥርቶ የማየት ችግርን የመሰለ አንድ ዓይነት አካላዊ ሕመም ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ “የሥጋዬ መውጊያ” ብሎ የጠራቸው፣ ሐሰተኛ ሐዋርያትንና የእርሱን ሐዋርያነትም ሆነ አገልግሎቱን የሚቃወሙ ሌሎች ሰዎችን ሊሆን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 11:6, 13-15፤ ገላትያ 4:15፤ 6:11

c አንዳንድ ምሁራን የድንቢጧ መውደቅ መሞቷን ብቻ የሚያመለክት ላይሆን እንደሚችል አስተያየት ይሰጣሉ። ጥቅሱ በመጀመሪያ በተጻፈበት ግሪክኛ ቋንቋ የተጠቀሰው ቃል ወፏ ምግብ ለመለቃቀም መሬት ላይ ማረፏን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል ይላሉ። ይህ አባባላቸው እውነት ከሆነ አምላክ የወፏን መሞት ብቻ ሳይሆን ለምታደርገው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ትኩረት ይሰጣል እንዲሁም ያስብላታል ማለት ነው።—ማቴዎስ 6:26

d በጥንት ዘመን የበግ፣ የፍየልና የከብት ቆዳ በማልፋት አቁማዳ ይዘጋጅ ነበር። አቁማዳ ለወተት፣ ለቅቤ፣ ለአይብ ወይም ለውኃ መያዣነት ያገለግል ነበር። ቆዳው በደንብ ከለፋ ደግሞ ዘይት ወይም ወይን ጠጅ መያዝ ይችላል።

ታስታውሳለህ?

• አንድ ሰው አምላክ ፊቱን ያዞረበት እንዲመስለው የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ኢየሱስ ስለ ድንቢጦችና የራስ ጠጉራችን ስለ መቆጠሩ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ምን ትምህርት እናገኛለን?

• የአንድ ሰው እንባ በይሖዋ ‘አቊማዳ’ ወይም “መዝገብ” መያዙ ምን ያመለክታል?

• ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ጳውሎስ የነበረበትን ‘የሥጋ መውጊያ’ ያላስወገደለት ለምንድን ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ስለ ድንቢጦች ከተናገረው ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

© J. Heidecker/VIREO

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በማንበብ አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን የሚያሳይ ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን