ይሖዋ መንገዱን የሚጠብቁትን አትረፍርፎ ይባርካቸዋል
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ መንገዱን የሚጠብቁትን አትረፍርፎ ይባርካቸዋል
ሮሙአልት ስታፍስኪ እንደተናገረው
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መስከረም 1939 ሲጀምር ሰሜናዊ ፖላንድ ከባድ ውጊያዎች የሚደረጉበት የጦር አውድማ ሆነ። በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ልጅ የነበርኩ ሲሆን ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ጦር ሜዳ ሄድኩ። የተመለከትኩት ሁሉ በጣም የሚዘገንን ነበር። በየቦታው አስከሬን ይታያል፤ አየሩም በሚያፍን ጭስ ተሞልቷል። በጣም ያሳሰበኝ ወደ ቤት በሰላም የመድረሴ ጉዳይ ቢሆንም “አምላክ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ሁኔታ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? የሚደግፈውስ የትኛውን ጎራ ይሆን?” የሚሉት ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ መጡ።
የጦርነቱ ማብቂያ ሲቃረብ ወጣቶች የጀርመንን መንግሥት እንዲያገለግሉ ይገደዱ ጀመር። ይህን ለመቃወም የቃጣ ማንኛውም ሰው “ከሐዲ” ወይም “ሴረኛ” የሚል ጽሑፍ ደረቱ ላይ ተለጥፎ በዛፍ አሊያም በድልድይ ላይ ይሰቀል ነበር። የምንኖርበት ከተማ ገዲንያ በሁለት ተፋላሚ ወገኖች መካከል ይገኝ ነበር። ውኃ ለመቅዳት ከከተማ በምንወጣበት ወቅት ጥይትና ቦምብ በዙሪያችን ይርከፈከፍ ነበር። በዚሁም ሳቢያ ታናሽ ወንድሜ ሄንሪክ ክፉኛ ቆሰለና ሞተ። ሁኔታው አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እናቴ ለደህንነታችን በማሰብ እኔን ጨምሮ አራት ልጆቿን ይዛ ምድር ቤት ውስጥ መኖር ጀመረች። በዚያም የሁለት ዓመቱ ወንድሜ ኢጁኒየሽ በዘጊ አናዳ በሽታ ለሞት ተዳረገ።
በዚህ ጊዜም “አምላክ የት አለ? ይህን ሁሉ ሥቃይ ለምን ዝም ብሎ ይመለከታል?” እያልኩ ራሴን እጠይቅ ጀመር። ቤተ ክርስቲያን አዘውትሬ የምሄድ ቀናተኛ ካቶሊክ የነበርኩ ቢሆንም እንኳ ለጥያቄዎቼ ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበልኩ
ካልተጠበቀ ምንጭ ለጥያቄዎቼ ምላሽ አገኘሁ። ጦርነቱ በ1945 አበቃ፤ በ1947 መጀመሪያ ላይ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ገዲንያ ወደሚገኘው ቤታችን መጣች።
ምሥክሯን ያነጋገረቻት እናቴ ስትሆን እኔም የሚነጋገሩትን በትንሹ መስማት ችዬ ነበር። ነገሩ ምክንያታዊ ይመስላል፤ ስለሆነም ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሙሉ በሙሉ ባልረዳም ከወር በኋላ በአካባቢው ከነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ጋር በመሆን ከጦርነትና ከግፍ ነፃ ስለሚሆነው የተሻለ ዓለም ለሌሎች መስበክ ጀመርኩ። ይህ ትልቅ ደስታ አስገኝቶልኛል።በመስከረም 1947 ሶፖት ውስጥ በተደረገ የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። በግንቦት ወር ላይ የዘወትር አቅኚ ሆንኩና ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በመስበክ ብዙ ጊዜዬን አሳልፍ ጀመር። የአካባቢው ቀሳውስት ሥራችንን አጥብቀው ይቃወሙና ዓመጽ ይቀሰቅሱብን ነበር። በአንድ ወቅት በቁጣ የገነፈሉ ሰዎች የድንጋይ ናዳ አወረዱብን እንዲሁም ክፉኛ ደበደቡን። በሌላ ጊዜ ደግሞ የአካባቢው መነኮሳትና ቀሳውስት ብዛት ያላቸውን ሰዎች ጥቃት እንዲያደርሱብን ገፋፏቸው። እኛም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሸሸን፤ ያም ሆኖ ግን ሕዝቡ ሕንጻውን በመክበብ እኛን ለመደብደብ ይጋበዝ ጀመር። በመጨረሻም ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል በመምጣቱ ታጅበን ወደ ሌላ ቦታ ተወሰድን።
በእነዚህ ጊዜያት በምንሰብክበት አካባቢ ጉባኤ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ጫካ ውስጥ እናድር ነበር። ሁኔታዎቹ አስቸጋሪ ቢሆኑም እንኳ የስብከቱን ሥራ ማከናወናችን ደስታ አስገኝቶልናል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ጠንካራ ጉባኤዎች ይገኛሉ።
የቤቴል አገልግሎትና እስር
በ1949 ውች በሚገኘው የቤቴል ቤት እንዳገለግል ተጋበዝኩ። እንዲህ ባለ ቦታ ማገልገል መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የሚያሳዝነው ግን፣ በዚያ የቆየሁት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። በሰኔ 1950 ሥራችን በይፋ ከመታገዱ አንድ ወር ቀደም ብሎ ቤቴል ይገኙ ከነበሩ ሌሎች ወንድሞች ጋር ተያዝኩና ወደ እስር ቤት ተወሰድኩ፤ እዚያም ጭካኔ የተሞላበት ምርመራ ይደረግብኝ ጀመር።
አባቴ ወደ ኒው ዮርክ በሚመላለስ መርከብ ላይ ይሠራ ስለነበር መርማሪዎቹ የአሜሪካ ሰላይ ነው ብዬ እንዳምን ሊያስገድዱኝ ሞከሩ። በዚህ ሳቢያ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ምርመራ ይደረግብኝ ነበር። በተጨማሪም አራት መርማሪዎች በፖላንድ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት ሲቆጣጠር በነበረው ወንድም ቪልኸልም ሻይደር ላይ በሐሰት እንድመሠክር ለማድረግ ይጥሩ ጀመር። ይህ አልሳካ ሲላቸው ውስጥ እግሬን ገረፉኝ። ደም በደም ሆኜ ወለሉ ላይ ተዘረጋሁና ከዚህ በላይ እንደማልችል ሆኖ ስለተሰማኝ “ይሖዋ፣ እርዳኝ!” ስል ጮኽኩ። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ገረማቸውና ድብደባቸውን አቆሙ፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም እንቅልፍ ያዟቸው ሄደ። እኔም እፎይ አልኩ፤ ጥንካሬዬም ተመለሰልኝ። ይህ ሁኔታ ይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮቹ ወደ እርሱ በሚጮሁበት ጊዜ ፍቅራዊ ምላሽ እንደሚሰጣቸው እንዳምን አደረገኝ። ከዚህም በላይ እምነቴ ይበልጥ እንዲጠነክር ረድቶኛል፤ እንዲሁም በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን እንዳለብኝ አስተምሮኛል።
በምርመራው የማጠቃለያ ሪፖርት ላይ እኔ እንደሰጠሁት በማስመሰል የተጻፈ የሐሰት የምሥክርነት ቃል ተካትቶ ነበር። ተቃውሞ ሳሰማ አንድ መርማሪ “ሁኔታውን ችሎት ፊት ታስረዳለህ!” አለኝ። አብሮኝ ታስሮ የነበረ አንድ ተግባቢ ሰው፣ የመጨረሻውን ሪፖርት ትክክለኛነት ወታደራዊ አቃቤ ሕግ ስለሚያጣራ የዚያን ጊዜ የሐሰት የምሥክርነት ቃል መሆኑን ማስረዳት እንደምችል በመንገር አረጋጋኝ። የሆነውም እንደዚሁ ነበር።
የወረዳ ሥራ ጀመርኩ ከዚያም እንደገና ታሰርኩ
በጥር 1951 ከእስር ተፈታሁ፤ ከወር በኋላም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። እገዳው
እንደቀጠለ ቢሆንም እንኳ ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ጉባኤዎችን ለማጠናከርና በደህንነት ሠራተኞች እንቅስቃሴ ምክንያት ተበታትነው የነበሩትን ክርስቲያኖች ለመርዳት ጥረናል። ወንድሞች አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ እናበረታታቸውም ነበር። በቀጣዮቹ ዓመታት፣ እነዚህ ወንድሞች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በድፍረት ከመደገፋቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በድብቅ በማተሙና በማሰራጨቱ ሥራ ላይ ተካፍለዋል።በሚያዝያ 1951 አንድ ቀን ከስብሰባ በመመለስ ላይ እያለሁ በዓይነ ቁራኛ ሲከታተሉኝ በነበሩ ደህንነቶች ተያዝኩና ታሰርኩ። ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልነበርኩ ወደ ቤድጎሽ እስር ቤት ከወሰዱኝ በኋላ የዚያኑ ዕለት ማታ ይመረምሩኝ ጀመር። ፊቴን ወደ ግድግዳ አዙሬ እንድቆም ታዘዝኩ፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በሲጋራ ጭስ በታፈነ ክፍል ውስጥ አለምንም ውሃና ምግብ ለስድስት ቀንና ሌሊት እንድቆም አደረጉኝ። ከዚህም በላይ በቆመጥ ይደበድቡኝና በሲጋራ ያቃጥሉኝ ነበር። ራሴን ስቼ ስወድቅ ውኃ ይደፉብኝና ስነቃ እንደገና ምርመራቸውን ይቀጥላሉ። እኔም ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠኝ ይሖዋን እለምነው ነበር፤ እርሱም ደግፎኛል።
በቤድጎሽ እስር ቤት ያደረግሁት ቆይታ መልካም ጎንም ነበረው። በሌላ መንገድ ሊገኙ ለማይችሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማካፈል ችያለሁ። ለመመስከር የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። እስረኞቹ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለነበሩ ጆሯቸውንና ልባቸውን ከፍተው ምሥራቹን በደስታ ያዳምጡ ነበር።
ሁለት ትልልቅ ለውጦች አደረግሁ
በ1952 ከእስር ከተለቀቅኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኔላ ከተባለች ቀናተኛ አቅኚ እህት ጋር ተዋወቅሁ። ኔላ ደቡብ ፖላንድ ውስጥ በአቅኚነት ታገለግል ነበር። ቆየት ብላም “ዳቦ መጋገሪያ” ብለን በምንጠራው ጽሑፎቻችን በድብቅ በሚታተሙበት ቤት ሠርታለች። ይህ ሥራ ንቃትና ራስን መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። በ1954 ጋብቻችንን የፈጸምን ሲሆን ሊዲያ የተባለችው ሴት ልጃችን እስክትወለድ ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ችለን ነበር። ከዚያም እኔ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ መቀጠል እንድችል ኔላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን በማቆም ሴት ልጃችንን ለመንከባከብ ወደ ቤት እንድትመለስ ወሰንን።
በዚሁ ዓመት ሌላ ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ገጠመን። የፖላንድ አንድ ሦስተኛ በሆነ ክልል ውስጥ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጠየቅሁ። ሁኔታውን በጸሎት አሰብንበት። በእገዳ ሥር ያሉትን ወንድሞች ማበረታታት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ። በጊዜው በርካታ ወንድሞች ይታሰሩ ስለነበር መንፈሳዊ ማበረታቻ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ የኔላ እገዛ ታክሎበት ሥራውን ተቀበልኩ። ለቀጣዮቹ 38 ዓመታት በዚህ ሥራ ላይ ማገልገል እንድችል ይሖዋ ረድቶኛል።
“የዳቦ መጋገሪያዎቹ” ኃላፊ ሆንኩ
በእነዚህ ጊዜያት አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች በተመደበበት ክልል ውስጥ የሚገኙትን “ዳቦ መጋገሪያዎች” የመቆጣጠር ኃላፊነት ነበረበት። ፖሊሶች ጽሑፎቻችንን የት እንደምናትም ለማወቅና ለማስቆም እግር በእግር ይከታተሉን ነበር። የተሳካላቸው ጊዜያት ቢኖሩም የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በጭራሽ አጥተን አናውቅም። ይሖዋ እየተንከባከበን እንዳለ በግልጽ ይታይ ነበር።
አንድ ሰው አስቸጋሪና አደገኛ በሆነው የኅትመት ሥራ ላይ ለመካፈል ታማኝ፣ ንቁ፣ ራሱን መሥዋዕት የሚያደርግና ታዛዥ መሆን ነበረበት። “ዳቦ መጋገሪያው” ያለምንም ችግር መሥራቱን የቀጠለው እዚያ የሚሠሩት ወንድሞች እነዚህ ግሩም ባሕርያት ስለነበሯቸው ነው። ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ደግሞ በድብቅ ለሚካሄደው የኅትመት
ሥራ ተስማሚ የሆነ ሥፍራ ማግኘት ነበር። አንዳንድ አካባቢዎች አመቺ ቢመስሉም ወንድሞች ያን ያህል ጥንቁቅ አልነበሩም። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሁኔታው የተገላቢጦሽ ይሆናል። ያም ሆኖ ወንድሞች አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች ነበሩ። በእነዚያ ወቅቶች አብሬያቸው የመሥራት መብት ላገኘሁት ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ጥልቅ የአድናቆት ስሜት አለኝ።ለምሥራቹ ጥብቅና መቆም
በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ታደርጋላችሁ እንዲሁም በመንግሥት ላይ ታሴራላችሁ በሚል ሰበብ በተደጋጋሚ እንከሰስና ችሎት ፊት እንቀርብ ነበር። ችሎት ፊት ቀርበው የሚከራከሩልን ጠበቆች ስላልነበሩ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነበር። የሐዘኔታ ስሜት ያሳዩን ጥቂት ጠበቆች ቢኖሩም እንኳ ብዙዎቹ በሌሎች ዘንድ የእኛ ደጋፊ ሆነው መታወቅና ባለ ሥልጣናቱን ማስከፋት አይፈልጉም ነበር። የሆነ ሆኖ ይሖዋ ፍላጎታችንን ያውቅ ስለነበር በተገቢው ሰዓት ሁኔታዎችን አስተካክሎልናል።
በክራኮ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል የነበረው አሎይዝ ፕሮስታክ በምርመራ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት እስር ቤት ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰደ። ይህ ወንድም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም እንኳ ያሳየው የአቋም ጽናት በሆስፒታሉ በመታከም ላይ በነበሩ እስረኞች ዘንድ ክብርና አድናቆት አትርፎለታል። ከእነዚህ እስረኞች ውስጥ አንዱ ጠበቃ የነበረው ቪቶልድ ሌስኦልሼቪስኪ ሲሆን ወንድም ፕሮስታክ ባሳየው ድፍረትም እጅግ ተደንቆ ነበር። ጠበቃው ወንድምን በተደጋጋሚ ጊዜያት ካነጋገረው በኋላ “ከእስር ተፈትቼ ሥራዬን እንድቀጥል ሲፈቀድልኝ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅና እቆማለሁ” ሲል ቃል ገባለት። ልክ እንዳለውም አደረገ።
ሚስተር ሌስኦልሼቪስኪ ራሱን የቻለ አንድ የጠበቆች ቡድን ነበረው። እነዚህ ጠበቆች እኛን ለመርዳት የገቡትን ቃል ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። ተቃውሞ ይበልጥ በሚፋፋምበት ወቅት ላይ በወር 30 ለሚያህሉ ክሶች ጥብቅና ይቆሙልን ነበር፤ ይህም በቀን አንድ ማለት ነው! ሚስተር ሌስኦልሼቪስኪ ስለ ክሶቹ በደንብ ማወቅ ይፈልግ ስለነበር በቅርብ ሆኜ እንድረዳው ተመደብኩ። በዚህ ሁኔታ በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ያህል አብሬው ሠርቻለሁ።
በእነዚህ ጊዜያት ሕግ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች ብዙ ነገሮችን መገንዘብ ችያለሁ። በበርካታ ችሎቶች ላይ ተገኝቻለሁ፤ ለድጋፍም ይሁን ለተቃውሞ የተሰነዘሩ የጠበቆችን ሐሳብ፣ ሕጋዊ መከላከያ ማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ እንዲሁም ተከሰው የቀረቡ ክርስቲያኖች የሰጡትን ቃል የመከታተል አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ይህ ሁሉ፣ ወንድሞች በተለይም ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ለምሥክርነት የተጠሩት መናገር ያለባቸውንና የሌለባቸውን እንዲያውቁ በመርዳት ረገድ በእጅጉ ጠቅሞኛል።
አንድ ክስ መታየት ከጀመረ ሚስተር ሌስኦልሼቪስኪ የሚያድረው ወንድሞች ቤት ነበር። ይህን የሚያደርገው በሆቴል ውስጥ ለማረፍ የሚያስችል አቅም ስለሌለው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ወቅት “ከችሎቱ በፊት መንፈሳችሁ ትንሽ እንዲጋባብኝ እፈልጋለሁ” በማለት ምክንያቱን ተናግሮ ነበር። እሱ ባደረገልን ድጋፍ የተነሳ በርካታ የፍርድ ሂደቶች በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቀዋል። ለእኔም ብዙ ጊዜ ጥብቅና የቆመልኝ ቢሆንም በጭራሽ አስከፍሎኝ አያውቅም። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ 30 ለሚያህሉ ፍርድ ነክ ጉዳዮች ክፍያ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ለምን? “ለምታከናውኑት ሥራ ጥቂትም ብትሆን አስተዋጽኦ ማድረግ እፈልጋለሁ” ሲል ተናግሯል። ሆኖም የተወልን ገንዘብ ቀላል አልነበረም። የሚስተር ሌስኦልሼቪስኪ ቡድን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ዓይን የተሰወረ ባይሆንም ቡድኑ እኛን ከመርዳት ወደኋላ አላለም።
ጉዳያችን በፍርድ ቤት ይታይ በነበረባቸው በእነዚያ ወቅቶች ወንድሞች የሰጡትን ግሩም ምሥክርነት በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ብዙዎች የፍርድ ሂደቱን ለመከታተልና ተከሰው የቀረቡትን ለማበረታታት ወደ ፍርድ ቤት ይመጡ ነበር። የክሱ መጠን ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ላይ በአንድ ዓመት ብቻ እስከ 30,000 የሚያህሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር። በእርግጥም የምሥክሮቹ ቁጥር እጅግ ታላቅ ነበር!
አዲስ የሥራ ምድብ
ሥራችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በ1989 ተነሳ። ከሦስት ዓመት በኋላም አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቶ ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ። እኔም የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ተጋበዝኩ፤ የሐዋርያት ሥራ 15:29
የተሰጠኝንም ኃላፊነት በደስታ ተቀበልኩ። ሦስት ሆነን ከደም ጋር በተያያዘ ችግር ላጋጠማቸው ወንድሞቻችን ድጋፍ እንሰጥ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ሕሊናቸው ተጠቅመው ስለ አቋማቸው መልስ መስጠት እንዲችሉ እንረዳቸው ነበር።—እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ለሰዎች ምሥክርነት በመስጠት ይሖዋን የማገልገል ልዩ መብት በማግኘታችን እጅግ አመስጋኞች ነን። ኔላ ዘወትር ታበረታታኝና ትደግፈኝ ነበር። በመንፈሳዊ ሥራ ተጠምጄም ይሁን በእስር ምክንያት ብዙውን ጊዜ ከቤት ብርቅ አማርራ አታውቅም። ለዚህም አመስጋኝ ነኝ። በአስቸጋሪ ጊዜያት በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ ሌሎችን ታጽናና ነበር።
ለምሳሌ ያህል፣ በ1974 ከሌሎች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር ታስሬ ነበር። ሁኔታውን የሰሙ ወንድሞች ለባለቤቴ ቀስ ብለው ሊነግሯት ወሰኑ። እንዳገኟት “እህት ኔላ አሳዛኝ ዜና ለመስማት ተዘጋጅተሻል? ሲሉ ጠየቋት። መጀመሪያ ላይ የእኔን መሞት ሊያረዷት ስለመሰላት በድንጋጤ ክው አለች። ሁኔታውን ስትረዳ ግን እፎይታ ተሰምቷት “በሕይወት ይኑር እንጂ ሲታሰር እኮ ይህ የመጀመሪያው አይደለም” በማለት መለሰችላቸው። ወንድሞች ባሳየችው አዎንታዊ አመለካከት እጅግ መደነቃቸውን በኋላ ላይ ገለጹልኝ።
ባለፉት ጊዜያት አንዳንድ አስጨናቂ ሁኔታዎች የገጠሙን ቢሆንም መንገዶቹን በመጠበቃችን ይሖዋ አትረፍርፎ ክሶናል። ሊዲያ የተባለችው ሴት ልጃችንና ባለቤቷ አልፍሬት ዴሩሻ ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ምንኛ ደስተኞች ነን። ክሪስተፈርና ጆናተን የተባሉ ወንዶች ልጆቻቸውን ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ አሠልጥነው ማሳደጋቸው ለደስታችን ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ወንድሜ ራይሻርድና እህቴ ኧርሱላ ታማኝ ክርስቲያኖች በመሆን ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል።
ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ተለይቶ አያውቅም፤ እኛም ብንሆን እሱን በሙሉ ልብ ማገልገላችንን መቀጠል እንፈልጋለን። በመዝሙር 37:34 ላይ የሰፈሩት “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል” የሚሉት ቃላት እውነተኛ መሆናቸውን ከግል ተሞክሯችን ማየት ችለናል። ይህ የሚሆንበትን ጊዜ በሙሉ ልባችን እንጠባበቃለን።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ ወንድም ግቢ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ፣ ክራኮ፣ 1964
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1968 ከባለቤቴ ከኔላ እና ከሴት ልጃችን ከሊዲያ ጋር
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ከሚደረግለት ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ልጅ ጋር
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ2002 ከኔላ ጋር
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በካታቪትሳ ሆስፒታል ያለ ደም በሚከናወን የልጆች የልብ ቀዶ ጥገና ዋና ቀዶ ሐኪም ከሆነው ከዶክተር ዊትስ ጋር