በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሞት በድል ተዋጠ”

“ሞት በድል ተዋጠ”

“ሞት በድል ተዋጠ”

አንዲት ልጅ ሕይወቷን አጠፋች ብሎ ከሚጀምር ርዕስ ይልቅ ከላይ ያለውን በማለት የሚጀምር የጋዜጣ ርዕስ ብታነብ ምን ይሰማሃል? እውነት ነው፣ እንዲህ ብሎ የሚጀምር ጋዜጣ እስከዛሬ ድረስ ታይቶ አያውቅም። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ባስቆጠረ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ።

በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሞት በግልጽ ተብራርቷል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ለምን እንደምንሞት ብቻ ሳይሆን ሙታን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ተስፋ እንዳላቸው ያብራራል። በመጨረሻም፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የሚታወጅበት ታላቅ ቀን እንደሚመጣ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 15:54

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት በሚያብራራበት ወቅት ለመረዳት የሚያዳግቱ አባባሎችን ሳይሆን የተለመዱ መግለጫዎችን ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ በብዙ ቦታዎች ላይ ሞትን ‘ከእንቅልፍ’ ጋር የሚያዛምደው ሲሆን የሞቱ ሰዎችን ደግሞ “አንቀላፍተው” እንዳሉ አድርጎ ይናገራል። (መዝሙር 13:3፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13፤ ዮሐንስ 11:11-14) ሞት “ጠላት” እንደሆነ ተደርጎም ተገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሞት ለምን በእንቅልፍ እንደተመሰለ፣ የሰውን ዘር የሚያጠቃበትን ምክንያትና ይህ ጠላት በመጨረሻ እንዴት እንደሚወገድ እንድናውቅ ያስችለናል።

የምንሞተው ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን የፈጠረውና በገነት ውስጥ ያኖረው እንዴት እንደሆነ ይዘግባል። (ዘፍጥረት 2:7, 15) ከዚያም የሚሠራው ሥራና አንድ ጥብቅ መመሪያ ተሰጠው። አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ ከሚገኙት ዛፎች መካከል አንዱን በተመለከተ እንዲህ አለው:- “[ከእርሱ] አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” a (ዘፍጥረት 2:17) ስለዚህ አዳም ሞትን ሳይቀምስ በሕይወት መቀጠል እንደሚችል ተረድቶ ነበር። የሚሞተው የአምላክን ሕግ ከጣሰ ብቻ ነው።

የሚያሳዝነው አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ዓመጹ። የፈጣሪያቸውን ፈቃድ ሆን ብለው በመጣሳቸው ይህ ድርጊት የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጨድ ተገድደዋል። አምላክ የፈጸሙት ኃጢአት የሚያስከትልባቸውን ውጤት ሲገልጽ “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” ብሏቸዋል። (ዘፍጥረት 3:19) በዚህም ምክንያት ከባድ እክል ይኸውም አለፍጽምና ወረሱ። አለፍጽምና መውረሳቸው ወይም ኃጢአተኛ መሆናቸው ለሞት ይዳርጋቸዋል።

ይህ እክል ማለትም ኃጢአት ለአዳምና ለሔዋን ዘሮች ይኸውም ለሰው ዘር በሙሉ ተላልፏል። ሁኔታው በዘር ከሚተላለፍ በሽታ ጋር ይመሳሰላል። አዳም ከሞት ፍርሃት ነፃ የሆነ ሕይወት ከማጣቱ በተጨማሪ ለዘሮቹም አለፍጽምናን አውርሷል። የሰው ዘር በሙሉ የኃጢአት ምርኮኛ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።”—ሮሜ 5:12

‘ኀጢአት ወደ ዓለም ገባ’

ይህ በዘር የሚተላለፍ እክል ወይም ኃጢአት በማጉያ መነጽር የሚታይ ነገር አይደለም። “ኀጢአት” የሚለው ቃል ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የወረስነውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እክል የሚያመለክት ሲሆን በአካላችን ላይም የሚያስከትላቸው ጉዳቶች አሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ መፍትሔ እንዳዘጋጀ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 6:23) በተጨማሪም ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ “ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) ይህ ተስፋ ለእርሱ ከፍተኛ ትርጉም ነበረው።

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኃጢአትንና ሞትን በማስወገድ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ወደ ምድር የመጣው ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት’ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ያደረገው ነገር ታፍኖ የተወሰደን ሰው ለማስለቀቅ የግድ የተወሰነ ክፍያ መክፈል ከሚጠይቀው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አለው። እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚያወጣን ቤዛ የኢየሱስ ፍጹም ሕይወት ነው። bየሐዋርያት ሥራ 10:39-43

አምላክ የቤዛውን ዋጋ ለመክፈል፣ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ከመሞቱ በፊት ‘ስለ እውነት መስክሯል።’ (ዮሐንስ 18:37) በተጨማሪም አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ስለ ሞት እውነቱን ለማሳወቅ አንዳንድ አጋጣሚዎችን ተጠቅሟል።

“ልጅቱ ተኝታለች”

ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ ሞት ለእርሱ እንግዳ ነገር አልነበረም። የሚያውቃቸውን ሰዎች በሞት ሲያጣ ያዝን የነበረ ሲሆን እርሱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሞት ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 17:22, 23) ኢየሱስ ከመገደሉ ከጥቂት ወራት በፊት የቅርብ ወዳጁ የነበረው አልዓዛር ሞተ። ያ ክስተት ኢየሱስ ስለ ሞት ያለውን አመለካከት እንድናስተውል ይረዳናል።

ኢየሱስ የአልዓዛርን መሞት ከሰማ በኋላ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አልዓዛር አሞት ተኝቶ ከሆነ ተሽሎት ይነሳል ብለው አሰቡ። ስለዚህ ኢየሱስ በግልጽ “አልዓዛር ሞቶአል” አላቸው። (ዮሐንስ 11:11-14) ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር እንዳመሳሰለው ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። ሞት ምን እንደሆነ መረዳት ሊከብደን ቢችልም ስለ እንቅልፍ ግን በሚገባ እናውቃለን። ድብን ያለ እንቅልፍ ሲወስደን ምን ያህል ሰዓት እንዳለፈና በአካባቢያችን ምን እየተፈጸመ እንዳለ እንኳ አናውቅም፣ ምክንያቱም ለጊዜውም ቢሆን ራሳችንን ስለማናውቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ የሚገልጸው በዚህ መልክ ነው። መክብብ 9:5 “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” ይላል።

ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር ያዛመደበት ሌላው ምክንያት ሰው ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሁሉ ሙታንም በይሖዋ ኃይል አማካኝነት ሊነሡ ስለሚችሉ ነው። ኢየሱስ በአንድ አጋጣሚ ትንሽ ልጃቸው በመሞቷ ምክንያት ተጨንቆ የነበረ ቤተሰብ ቤት ሄዶ ነበር። ኢየሱስ “ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ከዚያም ወደ ሞተችው ልጅ ቀረበና እጅዋን ያዘ፤ ልጅቱም “ተነሥታ ቆመች።” በሌላ አባባል ከሞት ተነሣች።—ማቴዎስ 9:24, 25

በተመሳሳይ ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። ይሁን እንጂ ይህን ተአምር ከመሥራቱ በፊት የአልዓዛርን እህት ማርታን “ወንድምሽ ይነሣል” ብሎ አጽናንቷታል። እርሷም በትምክህት “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” በማለት መለሰችለት። (ዮሐንስ 11:23, 24) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ወደፊት የሆነ ወቅት ላይ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ትጠብቅ ነበር።

ትንሣኤ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? “ትንሣኤ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አናስታሲስ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “መነሣት” ማለት ነው። ይህም ከሞት መነሣትን ያመለክታል። አንዳንዶች ይህን ማመን ይከብዳቸው ይሆናል፤ ሆኖም ኢየሱስ ሙታን ድምጹን እንደሚሰሙ ከተናገረ በኋላ “በዚህ አትደነቁ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:28) ኢየሱስ ምድር ሳለ የፈጸመው ትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱስ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ለረጅም ዓመታት “ተኝተው” ያሉት እንደሚነሱ በሚናገረው ተስፋ በእርግጠኝነት እንድናምን ያስችለናል። ራእይ 20:13 “ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም [መቃብር] በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ” በማለት ትንቢት ይናገራል።

እነዚህ ትንሣኤ ያገኙ ሙታን ልክ እንደ አልዓዛር ከሞት ከተነሱ በኋላ አርጅተው እንደገና ይሞታሉ? ይህ የአምላክ ዓላማ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሞት የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣና ማንም አርጅቶ እንደማይሞት ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ራእይ 21:4

ሞት ጠላት ነው። የሰው ዘር እንደ በሽታና እርጅና የመሳሰሉ ከባድ ሥቃይ የሚያስከትሉ ሌሎች ብዙ ጠላቶችም አሉት። አምላክ በመጨረሻ በሰው ልጆች ታላቅ ጠላት ላይ የፍርድ ውሳኔ በማስተላለፍ እነዚህን ሁሉ ለማጥፋት ቃል ገብቷል። “የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:26

ይህ ተስፋ ሲፈጸም ሰዎች ኃጢአትና ሞት ሊያጎድፈው የማይችል ፍጹም ሕይወት አግኝተው ይደሰታሉ። እስከዚያው ድረስ ግን በሞት የተለዩን ወዳጆቻችን እረፍት ላይ እንዳሉ ማወቃችን ያጽናናል፤ በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ ደግሞ እርሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ከሞት ይነሳሉ።

ስለ ሞት ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ያስችላል

ስለ ሞትና ሙታን ስላላቸው ተስፋ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን ለሕይወት ያለን አመለካከት እንዲለወጥ ያደርጋል። በፊተኛው ርዕስ ላይ የተመለከትነው ኢየን በሃያዎቹ እድሜ ውስጥ እያለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት የሚሰጠውን ማብራሪያ ተማረ። “አባቴ አንድ ቦታ ይኖራል ብዬ እንዲያው ተስፋ አደርግ ነበር” በማለት ተናግሯል። “በመሆኑም በሞት አንቀላፍቶ እንደሚገኝ ስማር መጀመሪያ ላይ በጣም አዘንኩ።” ይሁን እንጂ ኢየን አምላክ የሰጠውን የትንሣኤ ተስፋ በሚያነብበት ወቅት አባቱን በድጋሚ እንደሚያገኝ ማወቁ በጣም አስደሰተው። “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ውስጣዊ ሰላም አገኘሁ” በማለት ያስታውሳል። ስለ ሞት ያገኘው ትክክለኛ ግንዛቤ መንፈሱ እንዲረጋጋ ያስቻለውን የአእምሮ ሰላም አስገኝቶለታል።

ክላይቭና ብሬንዳ በፊተኛው ርዕስ ላይ በተጠቀሰው የመኪና አደጋ የ21 ዓመት ልጃቸውን ስቲቨንን በሞት አጥተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት የሚናገረውን ነገር ካወቁ በኋላም እንኳ ልጃቸውን በድንገት በማጣታቸው ከደረሰባቸው ሐዘን በቀላሉ መጽናናት አልቻሉም። ደግሞም ሞት ጠላት ከመሆኑም ሌላ የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚሰጠውን ትምህርት ማወቃቸው ሐዘናቸው ቀስ በቀስ እንዲቀላቸው አድርጓል። ብሬንዳ እንዲህ ብላለች:- “ስለ ሞት ያገኘነው እውቀት ሕይወትን በአዲስ መልክ እንድንጀምርና ወደተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እንድንመለስ አድርጎናል። ይሁን እንጂ ስቲቨን ከእንቅልፉ የሚነሳበትን ቀን ሳናስብ ውለን አናውቅም።”

“ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?”

ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በግልጽ ማወቁ ለሕይወት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን እንደሚረዳን ግልጽ ነው። ሞት ምስጢር ሆኖ መቅረት የለበትም። ይህ ጠላት የሚያሳድረው ከባድ ፍርሃት ሳያሸማቅቀን ተደስተን መኖር እንችላለን። ለዘላለም ሞተን እንደማንቀር ማወቃችን “ሕይወት በጣም አጭር ነው” በሚል እምነት ተድላን ከማሳደድ እንድንቆጠብ ያደርገናል። በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ሆነው ትንሣኤ የሚያገኙበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ማወቃችን የሚያጽናና ከመሆኑም በተጨማሪ የተለመደ ሕይወታችንን የመቀጠል ፍላጎታችንን ያቀጣጥልልናል።

አዎን፣ ሕይወት ሰጪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ሞትን ለዘላለም የሚያጠፋበትን ጊዜ በእርግጠኝነት መጠባበቅ እንችላለን። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” ብለን መጠየቅ ለምንችልበት ጊዜ መብቃት እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!—1 ቆሮንቶስ 15:55

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው እዚህ ቦታ ላይ ነው።

b የተከፈለው የቤዛው ዋጋ አዳም ያጠፋው ዓይነት ፍጹም ሕይወት ነው። ኃጢአት ሁሉንም የሰው ዘር ስለበከለ ፍጽምና የሚጎድለው የትኛውም ሰው ቤዛ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ አምላክ ለዚሁ ዓላማ ሲል ልጁን ከሰማይ ወደ ምድር ላከ። (መዝሙር 49:7-9) በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአዳምና የሔዋን አለመታዘዝ ሞት አመጣ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የሞተችውን ልጅ እጅ ይዞ ከሞት አስነሳት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልዓዛር እንደተነሳው ሁሉ ብዙዎች በሞት ያጧቸው የሚወዷቸው ሰዎች ከእንቅልፍ እስኪነቁ ይጠብቃሉ