በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሞት የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት

ሞት የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት

ሞት የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት

“የስድስት ዓመት ልጅ ሕይወቷን አጠፋች።” ይህ አስደንጋጭ አርዕስተ ዜና ጃኪ የተባለች የስድስት ዓመት ልጅ በአሳዛኝ ሁኔታ መሞቷን የሚተርክ ነው። እናቷ በማይድን በሽታ ተይዛ በቅርቡ ሞታባታለች። ጃኪ ባቡር ሥር ዘላ ከመግባቷ በፊት ለወንድሞቿና ለእህቶቿ ‘መልአክ ሆና ከእናቷ ጋር አብራ መሆን’ እንደምትፈልግ ነግራቸው ነበር።

ኢየን አባቱ በካንሰር የሞተበትን ምክንያት አንድ ቄስ እንዲያስረዳው በጠየቀበት ወቅት የ18 ዓመት ልጅ ነበር። ቄሱ፣ አባቱ ጥሩ ሰው ስለነበር አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲሆን ወደ ሰማይ እንደወሰደው ለኢየን ነገረው። ኢየን ይህን ማብራሪያ ከሰማ በኋላ እንዲህ ያለውን ጨካኝ አምላክ ማወቅ እንደማይፈልግ ወሰነ። ሕይወት ትርጉም አልባ ስለሆነበት ኢየን ተድላ ለማሳደድ ቆርጦ ተነሳ። ስለዚህም የአልኮልና የአደንዛዥ መድኃኒቶች ሱሰኛ ከመሆኑም ሌላ የፆታ ብልግና ይፈጽም ጀመር። ከዚህ በኋላ ሕይወቱ ከቁጥጥር ውጭ ሆነበት።

“ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉ”

እነዚህ ሁለት አሳዛኝ ሁኔታዎች ሞት፣ በተለይ ደግሞ ሳይታሰብ የተከሰተ ከሆነ በሰዎች ሕይወት ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትል ያሳያሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና” በማለት የተናገረውን ሐቅ ሁላችንም እንደምናውቀው ግልጽ ነው። (መክብብ 9:5) ይሁን እንጂ ብዙዎች ይህን መራራ ሐቅ ገሸሽ ማድረግ ይመርጣሉ። አንተስ? የሕይወት ውጣ ውረድ ጊዜያችንንና ትኩረታችንን በጣም ስለሚሻማብን ብዙውን ጊዜ እንሞታለን የሚለው ሐሳብ ወደ አእምሯችን አይመጣም።

“አብዛኞቹ ሰዎች ሞትን ስለሚፈሩ ጭራሽ ስለ ሞት ማሰብ አይፈልጉም” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። የሆነ ሆኖ ከባድ አደጋ ሲያጋጥመን ወይም የማይድን በሽታ ሲይዘን በድንገት ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንፋጠጣለን። ወይም ደግሞ የዘመድ ወይም የጓደኛችን ቀብር ላይ ስንገኝ ሞት ለሁሉም የሰው ዘር የማይቀር ነገር መሆኑን ለማሰብ እንገደዳለን።

ይሁንና በቀብር ቦታዎች ላይ የተገኙ ሰዎች “ከሞት የሚቀር የለም” ሲሉ ብዙ ጊዜ እንሰማለን። ይህ ደግሞ እውነት ነው። እንዲያውም እድሜያችን እንዴት እንዳለፈ እንኳ ሳናውቀው እናረጅና ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ያጋጥሙናል። እዚያ ደረጃ ላይ ስንደርስ ሞት ሩቅ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ለረጅም ጊዜ አብረውን ያሳለፉ የቅርብ ወዳጆቻችንን በማጣት ብዙ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘታችን አይቀርም። በርካታ አረጋውያን “የእኔስ ተራ መቼ ይሆን?” የሚለው እረፍት የሚነሳ ጥያቄ በአእምሯቸው ይመላለሳል።

ታላቅ ምስጢር

የሞትን አይቀሬነት ማንም የማያስተባብለው ቢሆንም ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ ግን ትልቅ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ሞትን አስመልክቶ የሚቀርቡ እርስ በርስ የሚጋጩ ማብራሪያዎች ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች ጉዳዩ መልስ ስለሌለው ነገር በመጠየቅ የሚደረግ ከንቱ ውዝግብ እንደሆነ እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል። ባዩት ነገር ብቻ የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ “ሌላ ሕይወት የለ፣” በተቻለ መጠን ዛሬ ባለህ ተደሰት ይላሉ።

በተቃራኒው ደግሞ ሞት የሁሉ ነገር ማብቂያ ነው የሚለውን አባባል የሚቃወሙ አሉ። ይሁን እንጂ እነርሱም ቢሆኑ ከሞት በኋላ ስላለው ነገር ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም። አንዳንዶች ሕይወት ከሥቃይ ነፃ በሆነ ቦታ ላይ ይቀጥላል ብለው የሚያምኑ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ወደፊት በሆነ ወቅት ላይ በድጋሚ እንደሚኖሩና ምናልባትም ሌላ ሰው ሆነው እንደሚመጡ ያምናሉ።

ዘመድ የሞተባቸው ሰዎች “ሙታን የት ናቸው?” ብለው ምንጊዜም ይጠይቃሉ። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የአንድ የእግር ኳስ ቡድን አባላት በሚኒ ባስ ተጭነው ለግጥሚያ እየሄዱ ሳለ ድንገት አንድ የጭነት መኪና ገጫቸውና ሚኒ ባሷ ተሽከርክራ መንገድ ስታ ወጣች። በዚህም ምክንያት አምስት ተጫዋቾች ሞቱ። በአደጋው ከሞቱት መካከል የአንዱ እናት ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሕይወቷ ተመሰቃቀለባት። ልጄ የት ይሆን የሚለው ጥያቄ ዘወትር ያሳስባት ነበር። በየጊዜው ወደ መቃብሩ በመሄድ ድምጿን እያሰማች ለሰዓታት ታወራለች። “ከሞት በኋላ ምንም ነገር የለም ብሎ ማመን በጣም ይከብደኛል፣ ነገር ግን እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት ትናገራለች።

በግልጽ እንደሚታየው ለሞት ያለን አመለካከት በሕይወታችን ላይ አንድ ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል። ሞት ከሚያስከትለው ከባድ ጉዳት በመነሳት ሰዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። እስቲ አንተ ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ አስብ። ስለ ሞት ማሰብ ትተን ስለ ሕይወት ብቻ እናስብ? የሞት ፍርሃት ሕይወታችንን እንዲያበላሽብን መፍቀድ ይኖርብናል? አንድ ሰው በሞት ያጣቸው የሚወዳቸው ዘመዶቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በማሰብ ከመጨነቅ ሌላ አማራጭ የለውም? ሞት ምስጢር ሆኖ ይቀር ይሆን?