በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሮያል ባይብል—ለትርጉም ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መጽሐፍ ቅዱስ

ሮያል ባይብል—ለትርጉም ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መጽሐፍ ቅዱስ

ሮያል ባይብል—ለትርጉም ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መጽሐፍ ቅዱስ

መርከቧ በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ከስፔይን ተነስታ ወደ ኢጣሊያ እያመራች ነበር። በ1514 እና በ1517 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ከታተመውና በርካታ ቋንቋዎች ከያዘው ኮምፕሉቴንስ ከሚባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብዛኛውን ጭና ነበር። ድንገት ኃይለኛ ማዕበል ተነሳ። መርከበኞቹ መርከቧን ለማዳን ብርቱ ተጋድሎ ቢያደርጉም ጥረታቸው መና ቀረ። መርከቧ የጫነችውን በዋጋ የማይተመን መጽሐፍ ይዛ ሰጠመች።

ይህ አደጋ በርካታ ቋንቋዎች የያዘ መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ፈጥሯል። በመጨረሻም በሕትመት ሙያ የላቀ ችሎታ ያለው ክሪስቶፍ ፕላታ ይህን ከባድ ሥራ ለመጀመር ወሰነ። ለዚህ ግዙፍ ሥራ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሀብታም ሰው ያስፈልገው ስለነበር የስፔይኑን ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕን ወጪውን እንዲሸፍን ጠየቀው። ንጉሡ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በርካታ የስፔይን ምሑራንን ያማከረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ታዋቂው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ቤኒቶ አርያስ ሞንታኖ ይገኝበታል። ሞንታኖ ንጉሥ ፊሊፕን እንዲህ አለው:- “ይህ ሥራ ለአምላክ የቀረበ አገልግሎት ተደርጎ የሚቆጠርና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ከመሆኑም በተጨማሪ ግርማዊነትዎ ከፍተኛ ክብር እንዲቀዳጅና ዝናዎም እንዲገንን ያደርጋል።”

በርካታ ቋንቋዎች የያዘው ኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ታርሞ በድጋሚ መታተሙ ራሱን የቻለ ትልቅ እመርታ እንደሆነ በመገንዘብ ንጉሡ ለፕላታ ፕሮጀክት ያልተቆጠበ ድጋፍ ለመስጠት ተስማማ። በመጨረሻ ሮያል ባይብል ወይም አንትወርፕ ፖሊግሎት የሚል ስያሜ ያገኘውን በርካታ ቋንቋዎች የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ለሕትመት የማዘጋጀቱን ከባድ ኃላፊነት ለአርያስ ሞንታኖ ሰጠው። a

ፊሊፕ የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ዝግጅት ከፍተኛ ጉጉት ስላሳደረበት እያንዳንዱ ገጽ ለማጣሪያ ንባብ እንዲላክለት ጠየቀ። ፕላታ እያንዳንዱ ገጽ ከአንትወርፕ ወደ ስፔይን ተልኮ፣ በንጉሡ ተነብቦና ታርሞ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ብዙ ጊዜ ስለሚባክን በነገሩ እንዳልተደሰተ መገመት አያዳግትም። በመሆኑም ፊሊፕ የተላከለት ታትሞ የወጣው የመጀመሪያው ገጽና ምናልባትም መጀመሪያ ላይ የታተሙ የተወሰኑ ገጾች ብቻ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ግን ሞንታኖ በሉቫን የሚኖሩ ሦስት ፕሮፌሰሮችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው የአታሚው ሴት ልጅ ባደረጉለት ጠቃሚ እርዳታ በመታገዝ ዋናው የማጣሪያ ንባብ በፍጥነት እንዲካሄድ አደረገ።

የአምላክን ቃል የሚወድ ሰው

አርያስ ሞንታኖ በአንትወርፕ ከሚኖሩ ምሑራን ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው። ሰፊ አመለካከት ያለው ሰው መሆኑ በፕላታ ዘንድ ያስወደደው ከመሆኑም ሌላ በሁለቱ መካከል የነበረው ጓደኝነትና ትብብር በቀሪው የሕይወታቸው ዘመንም ሊዘልቅ ችሏል። ሞንታኖ የተማረ ሰው በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአምላክ ቃል በነበረው ከፍተኛ ፍቅርም ይታወቃል። b በወጣትነት ዕድሜው፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በቶሎ አጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ጥልቅ ጥናት የማካሄድ ፍላጎት ነበረው።

አርያስ ሞንታኖ መጽሐፍ ቅዱስ በተቻለ መጠን ቃል በቃል መተርጎም አለበት የሚል እምነት ነበረው። የመጀመሪያውን ጽሑፍ እንዳለ ለመተርጎም ጥረት ያደረገ ሲሆን አንባቢው ትክክለኛውን የአምላክ ቃል እንዲያገኝ አድርጓል። ሞንታኖ፣ “የአምላክ ቃል መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ስለ ክርስቶስ መስበክ” እንዳለባቸው የሃይማኖት ምሑራንን ያሳስብ የነበረውን የኢራስመስን መርህ ተከትሏል። ሰዎች በላቲን የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ይከብዳቸው ስለነበር ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያ የተጻፉባቸው ቋንቋዎች የሚያስተላልፉትን መልእክት ለብዙ ዘመናት መረዳት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አንትወርፕ መጽሐፍ ቅዱስን ማቀናበር

አልፎንሶ ደ ዛሞራ ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎትን ለማሳተም ያዘጋጃቸውና እርማት ያደረገባቸው ረቂቅ ጽሑፎች በሙሉ አርያስ ሞንታኖ እጅ የገቡ ሲሆን እርሱም ሮያል ባይብልን ለማዘጋጀት ተጠቀመባቸው። c

መጀመሪያ ላይ ሮያል ባይብል የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት ሁለተኛ እትም እንደሚሆን ታስቦ የነበረ ቢሆንም ከተራ መሻሻል እጅግ የበለጠ ለውጥ ተደርጎበታል። ከኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰብዓ ሊቃናት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፍ የተወሰደ ሲሆን ከዚያም ከሌሎች አዳዲስ ትርጉሞች በተጨማሪ ትንታኔ የቀረበበት ሰፊ ክፍል ታክሎበታል። በመጨረሻም አዲሱ ፖሊግሎት በስምንት ጥራዞች ለመዘጋጀት በቅቷል። የሕትመት ሥራው ከ1568 እስከ 1572 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም ከሥራው ውስብስብነት አንጻር ሲታይ በጣም አጭር ጊዜ ነው። በመጨረሻም መጽሐፉ በ1,213 ቅጂዎች ለመታተም በቃ።

በ1517 የተዘጋጀው ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት “በሕትመት ሥራ ጥበብ ረገድ ለአብነት” የሚጠቀስ ቢሆንም አዲሱ አንትወርፕ ፖሊግሎት ግን በጥራቱም ሆነ በይዘቱ ከእርሱ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ጽሑፍ በሕትመት ሥራ ታሪክ፣ በይበልጥ ደግሞ ጥራት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት የሚረዳ ሌላው ምዕራፍ ከፋች ሆኖ ተገኝቷል።

የአምላክ ቃል ጠላቶች የሰነዘሩት ጥቃት

ብዙም ሳይቆይ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳይዘጋጅ የሚፈልጉ ሰዎች ተቃውሞ ያሰሙ ጀመር፤ ይህ ደግሞ የሚያስገርም አይደለም። አንትወርፕ ፖሊግሎት የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ የጳጳሱን ፈቃድ ያገኘና አርያስ ሞንታኖ ደግሞ ታላቅ ምሑር የሚል የተከበረ ስም ያተረፈ ቢሆንም እንኳ ተቃዋሚዎቹ ኢንክዊዝሽን በሚባለው የሮማ ካቶሊክ ችሎት ፊት ቀርበው ከሰሱት። ተቃዋሚዎች የሞንታኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ ተሻሽሎ የተዘጋጀው የሳንቴስ ፓንዪኖ የላቲን ጽሑፍ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ከተዘጋጀው ከቩልጌት በተሻለ ከመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች ጋር የሚቀራረብ ትክክለኛ ትርጉም ነው የሚል አንድምታ ያዘለ ነው ሲሉ ክስ ሰንዝረዋል። በተጨማሪም ሞንታኖ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ከነበረው ፍላጎት የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የመጀመሪያዎቹን ቋንቋዎች አመሳክሯል በሚል ወንጅለውታል። በእነርሱ አመለካከት እንዲህ ማድረጉ የሚያስወግዝ ነበር።

ሌላው ቀርቶ ችሎቱ “ንጉሡ ለሥራው የገንዘብ ድጋፍ መስጠቱ ያስገኘለት ክብር የለም” ሲል ገልጿል። ሞንታኖ ቤተ ክርስቲያኗ ለተቀበለችው ለቩልጌት ተገቢውን እውቅና አለመስጠቱ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህን ክሶች ቢሰነዝሩም እንኳ ሞንታኖንም ሆነ በርካታ ቋንቋዎች የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመኮነን የሚያበቃ በቂ ማስረጃ አላገኙም። በመጨረሻ ሮያል ባይብል ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ ከመሆኑም ሌላ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀባይነት ያገኘ ሥራ ለመሆን በቅቷል።

ለትርጉም ሥራ የሚያገለግል ጠቃሚ መሣሪያ

አንትወርፕ ፖሊግሎት ለብዙኃኑ ተብሎ የተዘጋጀ ባይሆንም ብዙም ሳይቆይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ጠቃሚ መሣሪያ ለመሆን በቅቷል። ከዚህ በፊት እንደተዘጋጀው ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት ሁሉ ይህም በወቅቱ የነበሩትን ቅዱሳን ጽሑፎች ግልጽ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያዎቹን ቋንቋዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ አስችሏቸዋል። በአውሮፓ በሚነገሩ በርካታ ዋና ዋና ቋንቋዎች የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች የዚህ የትርጉም ሥራ ተጠቃሚ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሰፊው የሚታወቀውና በ1611 የተዘጋጀው ኪንግ ጄምስ ቨርሽን ወይም ኦቶራይዝድ ቨርሽን የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የጥንቶቹን ቋንቋዎች ለመተርጎም አንትወርፕ ፖሊግሎት በጣም ጠቅሟቸዋል ሲል ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል ዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪ ሮያል ባይብል በ17ኛው መቶ ዘመን ለተዘጋጁ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱሶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።—“በርካታ ቋንቋዎች የያዙ መጽሐፍ ቅዱሶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አንትወርፕ ፖሊግሎት ካሉት ጠንካራ ጎኖች መካከል አንዱ የአውሮፓ ምሑራን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሶርያ ቋንቋ እንዲያገኙ ማድረጉ ነው። በሶርያ ቋንቋ የተተረጎመው ጽሑፍ በላቲን ከተዘጋጀው ጥሬ ትርጉም ጎን ሠፍሯል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከተዘጋጁባቸው ቀደምት ቋንቋዎች መካከል አንዱ የሶርያ ቋንቋ ስለሆነ ይህ መካተቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው። ከአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት ወዲህ በሶርያ ቋንቋ የተዘጋጁት ትርጉሞች በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተዘጋጁ ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዳለው ከሆነ “ፐሺታ የሚባለው [በሶርያ ቋንቋ የተዘጋጀው] መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራዎችን ጥራት ለመገምገም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በሰፊው ይታወቃል። ይህ ትርጉም ስለ ጥንታዊ ልማዶች መረጃ የያዘ፣ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውና በጣም የቆዩ ከሚባሉት መጻሕፍት መካከል የሚቆጠር ነው።”

በኃይለኛ ማዕበል የተናወጠው ባሕርም ሆነ የስፔይኑ የሮማ ካቶሊክ ችሎት ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት ተሻሽሎና ተጨማሪ ገጽታዎች ይዞ በ1572 በሮያል ባይብል መልክ እንዳይወጣ ሊያግደው አልቻለም። በርካታ ቋንቋዎች የያዘው የአንትወርፕ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች የአምላክን ቃል ለመጠበቅ ያደረጉትን ጥረት የሚያሳይ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

እነዚህ ለሥራው ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ሰዎች አወቁትም አላወቁት ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ባከናወኑት ሥራ ኢሳይያስ የተናገረው የትንቢት ቃል እውነት መሆኑን አሳይተዋል። ይህ ነቢይ ከሦስት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ሲል ጽፏል።—ኢሳይያስ 40:8

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a መጽሐፉ ሮያል ባይብል የተባለው ወጪውን የሸፈነው ንጉሥ ፊሊፕ በመሆኑ ሲሆን አንትወርፕ ፖሊግሎት የተባለው ደግሞ በወቅቱ የስፔይን ግዛት በነበረችው በአንትወርፕ ከተማ በመታተሙ ነው።

b አንትወርፕ ፖሊግሎት የተዘጋጀባቸውን አምስት ዋና ዋና ቋንቋዎች ይኸውም አረብኛን፣ ግሪክኛን፣ ዕብራይስጥን፣ ላቲንንና የሶርያን ቋንቋ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የአርኪኦሎጂ፣ የሕክምና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና የመንፈሳዊ ትምህርት ሰፊ እውቀት የነበረው ሲሆን ይህም የመጽሐፍ ቅዱሱን ተጨማሪ ክፍል ለማዘጋጀት ጠቅሞታል።

c በርካታ ቋንቋዎች የያዘውን የኮምፕሉቴንስን መጽሐፍ ቅዱስ በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 15, 2004ን መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በርካታ ቋንቋዎች የያዙ መጽሐፍ ቅዱሶች

ፌዴሪኮ ፔሬዝ ካስትሮ የተባሉት ስፔይናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱስ ምንባቡን በተለያየ ቋንቋ የያዘ መጽሐፍ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “ቀደም ሲል ግን ቃሉ ቅዱሳን ጽሑፎችን መጀመሪያ በተጻፉባቸው ቋንቋዎች የያዙ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማመልከት ይሠራበት ነበር። የቃሉን ትርጉም እንዲህ ካጠበብነው ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱሶች በቁጥር በጣም ጥቂት ይሆናሉ።”

1. ኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት (1514-17)፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ የሸፈኑት ካርዲናል ዚስናሮስ ሲሆኑ መጽሐፉ የታተመው በአልካላ ቴ ኤናሬስ፣ ስፔይን ነበር። ስድስት ጥራዞች ያሉት ይህ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በአራት ቋንቋዎች የያዘ ሲሆን እነዚህም ዕብራይስጥ፣ ግሪክ፣ አረማይክና ላቲን ናቸው። በ16ኛው መቶ ዘመን ለነበሩ ተርጓሚዎች ለሥራቸው ጠቃሚ የሆኑ የዕብራይስጥና የአረማይክ ቅዱሳን ጽሑፎች አስገኝቶላቸዋል።

2. አንትወርፕ ፖሊግሎት (1568-72)፣ በኮምፕሉቴንስ ምንባብ ላይ በሶርያ ቋንቋ የተዘጋጁት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲሁም በጆናታን የተዘጋጀውንና ታርገም የሚባለውን የአረማይኩን ጽሑፍ ጨምሮ በቤኒቶ አርያስ ሞንታኖ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አናባቢ ምልክቶችና በትክክል ለማንበብ የሚረዱ ሥርዓተ ነጥቦች ያሉት የዕብራይስጡ ምንባብ ከጄኮብ ቤን ሃዪም በተገኘው የዕብራይስጥ ጽሑፍ መሠረት ታርሟል። ከዚህም የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመተርጎም የሚጠቀሙበት መደበኛ ጽሑፍ ለመሆን በቅቷል።

3. የፓሪሱ ፖሊግሎት (1629-45)፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ የሸፈነው ፈረንሳዊው ጠበቃ ጊ ሚሼል ለ ዤ ነው። ምንም እንኳ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሰማርያ ቋንቋና በአረብኛ የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎችን የያዘ ቢሆንም ለዚህ መጽሐፍ መታተም ምክንያት የሆነው አንትወርፕ ፖሊግሎት ነበር።

4. የለንደኑ ፖሊግሎት (1655-57)፣ በብራየን ዋልተን የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ቅዱስም በአንትወርፕ ፖሊግሎት ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህ ፖሊግሎት ወደ ኢትዮጵያና ወደ ፋርስ ቋንቋ የተተረጎሙ ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱሶችን ያካተተ ቢሆንም እነዚህ ትርጉሞች ጽሑፉን ግልጽ ለማድረግ ያበረከቱት ያን ያህል የጎላ አስተዋጽኦ የለም።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ባነሩ እና አንትወርፕ ፖሊግሎት (ከሥር ያሉት ሁለቱ):- Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid; አንትወርፕ ፖሊግሎት (ከላይ ያለው):- By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen; የለንደኑ ፖሊግሎት:- From the book The Walton Polyglot Bible, Vol. III, 1655-1657

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስፔይን ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ

[ምንጭ]

ዳግማዊ ፊሊፕ:- Biblioteca Nacional, Madrid

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርያስ ሞንታኖ

[ምንጭ]

ሞንታኖ:- Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንትወርፕ፣ ቤልጅየም የሚገኙ የድሮ ማተሚያ መሣሪያዎች

[ምንጭ]

የማተሚያ መሣሪያ:- By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተ ግራ:- ክሪስቶፍ ፕላታ እና የአንትወርፕ ፖሊግሎት 2ኛ ገጽ

[ምንጭ]

የመጽሐፉ 2ኛ ገጽ እና ፕላታ:- By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ:- ዘፀአት ምዕራፍ 15 በአራት አምዶች የሚገኝበት ገጽ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የመጽሐፉ 2ኛ ገጽ እና ፕላታ:- By courtesy of Museum Plantin-Moretus/Stedelijk Prentenkabinet Antwerpen

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid