በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በልብ ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ

በልብ ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ

በልብ ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ

“ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ።”—ኤርምያስ 31:33

1, 2. (ሀ) በዚህ ርዕስ ሥር የምናጠናው ስለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ የተገለጠው እንዴት ነው?

 ባለፉት ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ የይሖዋን ክብር በማንጸባረቅ ያበራ እንደነበረ ተምረናል። ሙሴ ፊቱ ላይ አድርጎት ስለነበረው መሸፈኛም ተመልክተናል። በዚህ ርዕስ ሥር ደግሞ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ትርጉም ያለው ከዚህ ጋር የተያያዘ ነጥብ እናጠናለን።

2 ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እያለ ከይሖዋ መመሪያ ተቀበለ። እስራኤላውያን በሲና ተራራ ፊት ለፊት ተሰብስበው ሳለ የአምላክን መገለጥ የሚያመለክቱ አስደናቂ ነገሮች ተመለከቱ። “ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጎድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ። . . . የሲና ተራራ እግዚአብሔር በእሳት ስለወረደበት በጢስ ተሸፍኖ ነበር። ጢሱ ከምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ወደ ላይ ተትጐለጐለ፤ ተራራውም በሙሉ በኀይል ተናወጠ።”—ዘፀአት 19:16-18

3. ይሖዋ አሥርቱን ትእዛዛት ለእስራኤላውያን የሰጣቸው በማን በኩል ነበር? ሕዝቡስ ምን ነገር ተገነዘቡ?

3 ይሖዋ ሕዝቡን በአንድ መልአክ አማካኝነት ያነጋገራቸው ሲሆን አሥርቱ ትእዛዛት በመባል የሚታወቁትን ሕግጋት ሰጣቸው። (ዘፀአት 20:1-17) ይህም ሕግጋቱን የሰጣቸው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ራሱ መሆኑን አለምንም ጥርጥር ያረጋግጣል። ይሖዋ እነዚህን ትእዛዛት በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፤ እነዚህ ጽላቶች ሙሴ እስራኤላውያን ከወርቅ የተሠራውን ጥጃ ሲያመልኩ ሲመለከት ወርውሮ የሰባበራቸው ናቸው። ስለዚህ ይሖዋ ሕግጋቱን እንደገና በድንጋይ ላይ ጻፋቸው። በዚህ ጊዜ ሙሴ ጽላቶቹን ይዞ ከተራራው ሲወርድ ፊቱ ያበራ ነበር። ሕዝቡ በሙሉ ይህን ሲመለከቱ እነዚህ ሕግጋት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መሆናቸውን ተገነዘቡ።—ዘፀአት 32:15-19፤ 34:1, 4, 29, 30

4. አሥርቱ ትእዛዛት ትልቅ ቦታ የተሰጣቸው ለምንድን ነው?

4 አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለት ጽላቶች በመገናኛው ድንኳን (በኋላም በቤተ መቅደሱ) ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን በተባለው ክፍል በሚገኘው የቃል ኪዳን ታቦት ውስጥ ተቀመጡ። በእነዚህ ጽላቶች ላይ የተጻፉት ሕግጋት የሙሴን ሕግ ቃል ኪዳን ዋነኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች የያዙ ከመሆናቸውም በላይ የእስራኤል ብሔር በአምላካዊ አገዛዝ የሚተዳደርበት መሠረት ጥለዋል። እንዲሁም ይሖዋ ሕዝቡን ለይቶ እንደመረጣቸው ማስረጃ ይሆናሉ።

5. አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት ለእነርሱ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት ነው?

5 እነዚያ ሕግጋት ስለ ይሖዋ በተለይም ለሕዝቡ ስላለው ፍቅር ብዙ የሚገልጹት ነገር አለ። ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ውድ ስጦታ ነበሩ! አንድ ምሑር “እነዚህ አሥር የአምላክ ቃሎች ከመሰጠታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ . . . እነርሱን ሊተካከል ወይም ሊበልጥ ቀርቶ ሊደርስባቸው እንኳ የሚችል በሰው ልጆች የተዘጋጀ የሥነ ምግባር ሕግ የለም” ሲሉ ጽፈዋል። ይሖዋ ሙሉውን የሙሴን ሕግ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ።”—ዘፀአት 19:5, 6

በልብ ላይ የተጻፈ ሕግ

6. በድንጋይ ላይ ከተጻፉት ሕግጋት የሚበልጠው የትኛው ሕግ ነው?

6 በእርግጥም እነዚያ መለኮታዊ ሕግጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበራቸው አይካድም። ሆኖም በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በድንጋይ ላይ ከተጻፉ ሕግጋት የሚበልጥ ነገር እንዳላቸው ታውቃለህ? ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር ካደረገው የሕግ ቃል ኪዳን በተለየ መልኩ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ” ብሏል። (ኤርምያስ 31:31-34) የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ የሆነው ኢየሱስ ለተከታዮቹ በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ አልሰጣቸውም። በንግግሩና በድርጊቱ የይሖዋ ሕግ በደቀ መዛሙርቱ አእምሮና ልብ ውስጥ እንዲቀረጽ አድርጓል።

7. ‘የክርስቶስ ሕግ’ መጀመሪያ የተሰጠው ለእነማን ነበር? በኋላስ ይህንን ሕግ እነማን ተቀብለውታል?

7 ይህ ሕግ ‘የክርስቶስ ሕግ’ ተብሎ ይጠራል። ሕጉ በመጀመሪያ የተሰጠው የያዕቆብ ዘሮች ለሆኑት ሥጋዊ እስራኤላውያን ሳይሆን ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ ለተባለው መንፈሳዊ ብሔር ነው። (ገላትያ 6:2, 16፤ ሮሜ 2:28, 29) የአምላክ እስራኤል በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈ ብሔር ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋን ማምለክ የሚፈልግ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጣ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከዚህ ብሔር ጋር ተቀላቅሏል። (ራእይ 7:9, 10፤ ዘካርያስ 8:23) እነዚህ ሁለቱም ቡድኖች ‘በአንድ እረኛ’ የሚመራ ‘አንድ መንጋ’ እንደመሆናቸው መጠን “የክርስቶስን ሕግ” የሚቀበሉ ከመሆኑም በላይ ሕጉ በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው እንዲመራቸው ይፈቅዳሉ።—ዮሐንስ 10:16

8. በሙሴ ሕግና በክርስቶስ ሕግ መካከል ምን ልዩነት ነበረ?

8 እስራኤላውያን ሆነው በመወለዳቸው የሙሴን ሕግ የመታዘዝ ግዴታ ከነበረባቸው ከሥጋዊ እስራኤላውያን በተለየ መልኩ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ሕግ የሚገዙት በገዛ ፈቃዳቸው ሲሆን እንደ ዘርና የትውልድ ሥፍራ የመሳሰሉት ነገሮች ምንም ቦታ አይሰጣቸውም። ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ የሚማሩ ሲሆን ፈቃዱን ለመፈጸምም ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች የአምላክ ሕግ “በልባቸው” የተጻፈ ያህል “በልቡናቸው” ውስጥ ስላለ አምላክን የሚታዘዙት እንዳይቀጣቸው በመፍራት ወይም መታዘዝ ግዴታቸው ስለሆነ አይደለም። እርሱን እንዲታዘዙ የሚገፋፋቸው ከዚህ በጣም የላቀና ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ምክንያት አላቸው። ሌሎች በጎችም እንዲሁ አምላክን የሚታዘዙት የአምላክ ሕግ በልባቸው ውስጥ ስላለ ነው።

በፍቅር ላይ የተመሠረቱ ሕግጋት

9. ኢየሱስ የይሖዋ ሕግጋት መንፈስ ፍቅር መሆኑን የጠቆመው እንዴት ነው?

9 የሁሉም የይሖዋ ሕግጋትና ሥርዓቶች ዋና መንፈስ ፍቅር በሚለው አንድ ቃል ሊጠቃለል ይችላል። ቀደም ባሉት ዘመናት ፍቅር የእውነተኛው አምልኮ ዋነኛ ክፍል የነበረ ሲሆን ወደፊትም ቢሆን ይህ ሁኔታ ይቀጥላል። ኢየሱስ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ” በማለት መልሷል። ሁለተኛው ደግሞ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:35-40) ስለዚህ ኢየሱስ አሥርቱ ትእዛዛትም ሆኑ አጠቃላይ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በፍቅር ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ገልጿል።

10. ፍቅር የክርስቶስ ሕግ ዋነኛ መሠረት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

10 በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የተጻፈው ሕግም ለአምላክና ለጎረቤት ፍቅር በማሳየት ላይ የተመሠረተ ነው? አዎን! የክርስቶስ ሕግ አምላክን ከልብ መውደድን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ሌላ አዲስ ትእዛዝም ያካተተ ነው፤ ክርስቲያኖች በመካከላቸው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ሊኖር ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደወደዳቸውና ሕይወቱን ለወዳጆቹ በፈቃዱ አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እነርሱም በመካከላቸው እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሊኖር ይገባል። ደቀ መዛሙርቱ አምላክን እንዲወዱና እርሱ እንደወደዳቸው እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አስተምሯቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚታወቁበት ዋነኛ መለያ አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩት የላቀ ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:12, 13) ኢየሱስ ከዚያም አልፎ ጠላቶቻቸውንም ጭምር እንዲወድዱ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 5:44

11. ኢየሱስ ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

11 ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። በሰማይ ይኖር የነበረው ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ፍጡር አባቱ ለምድር ያለውን ፈቃድ እንዲፈጽም የቀረበለትን አጋጣሚ በደስታ ተቀብሏል። የሰው ልጆች ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ሲል ሰብዓዊ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠትም ባሻገር ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው አሳይቷቸዋል። ትሑት፣ ደግና አሳቢ እንዲሁም ሸክማቸው የከበዳቸውንና የተጨቆኑትን የሚረዳ ሰው ነበር። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ በመርዳት ‘የዘላለምን ሕይወት ቃል’ ነግሯቸዋል።—ዮሐንስ 6:68

12. ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለሰዎች ከምናሳየው ፍቅር ለይቶ ማየት አይቻልም የምንለው ለምንድን ነው?

12 በእርግጥ ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለሰዎች ከምናሳየው ፍቅር ለይቶ ማየት የማይቻል ነገር ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “ፍቅር ከእግዚአብሔር [ነው]። . . . ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።” (1 ዮሐንስ 4:7, 20) ይሖዋ የፍቅር ምንጭና ተምሳሌት ነው። ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው። እኛም የተፈጠርነው በእርሱ አምሳል በመሆኑ ሌሎችን ማፍቀር እንችላለን። (ዘፍጥረት 1:27) ሰዎችን በማፍቀር አምላክን እንደምንወደው እናሳያለን።

ፍቅር በመታዘዝ ይገለጻል

13. አምላክን ለማፍቀር እንድንችል መጀመሪያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 የማናየውን አምላክ እንዴት ልናፈቅረው እንችላለን? አምላክን ለማፍቀር የመጀመሪያው እርምጃ እርሱን ማወቅ ነው። የማናውቀውን አካል ልናፈቅረው ወይም ልንተማመንበት አንችልም። በዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል በጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እንዲሁም ይሖዋን ከሚያውቁትና ከሚወድዱት ሰዎች ጋር በመሰብሰብ አምላክን እንድናውቀው ያበረታታናል። (መዝሙር 1:1, 2፤ ፊልጵስዩስ 4:6፤ ዕብራውያን 10:25) አራቱ የወንጌል መጻሕፍት ኢየሱስ ክርስቶስ በአኗኗሩና በአገልግሎቱ የይሖዋን ባሕርያት እንዴት እንዳንጸባረቀ ስለሚገልጹ ስለ አምላክ እንድናውቅ ከፍተኛ እገዛ ያደርጉልናል። አምላክን የበለጠ ስናውቀውና ለእኛ ያሳየንን ፍቅር ስናደንቅ እርሱን ለመታዘዝና ባሕርያቱን ለመኮረጅ ያለን ፍላጎት ይበልጥ እያደገ ይሄዳል። አዎን፣ አምላክን መውደድ መታዘዝንም ይጨምራል።

14. የአምላክ ሕግጋት ከባዶች አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?

14 የምናፈቅራቸው ሰዎች ምን እንደሚወዱና ምን እንደሚጠሉ እናውቃለን፤ በዚሁ መሠረትም ፍላጎታቸውን እናከብርላቸዋለን። የምንወዳቸውን ሰዎች ልናሳዝናቸው አንፈልግም። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) የአምላክ ትእዛዛት ከባድ ወይም በጣም ብዙ አይደሉም። ፍቅር አካሄዳችንን ይመራልናል። እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን በተመለከተ ዝርዝር ሕግጋትን ማጥናት አያስፈልገንም፤ ለአምላክ ያለን ፍቅር በምናደርገው ነገር ሁሉ ይመራናል። አምላክን የምንወደው ከሆነ ፈቃዱን ማድረግ ያስደስተናል። እንዲህ በማድረጋችን ደግሞ የአምላክን ሞገስ የምናገኝ ከመሆኑም በላይ ራሳችንን እንጠቅማለን፤ ምክንያቱም የአምላክ መመሪያዎች ምንጊዜም ቢሆን ለእኛ ጠቃሚ ናቸው።—ኢሳይያስ 48:17

15. ይሖዋን እንድንመስል የሚገፋፋን ምንድን ነው? አብራራ።

15 ለአምላክ ያለን ፍቅር ባሕርያቱን እንድንኮርጅ ያነሳሳናል። አንድን ሰው ስንወድ ባሕርያቱን የምናደንቅ ከመሆኑም በላይ እንደ እርሱ ለመሆን እንፈልጋለን። በይሖዋና በኢየሱስ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ እንመልከት። አባትና ልጅ ምናልባትም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት በሰማይ አብረው በመኖራቸው በመካከላቸው ንጹሕና ጥልቅ የሆነ ፍቅር ተመሥርቷል። ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን ሙሉ በሙሉ ይመስል ስለነበረ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ብሎ ሊናገር ችሏል። (ዮሐንስ 14:9) ይሖዋንና ልጁን ይበልጥ ስናውቃቸውና ለእነርሱ ያለን አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ እነርሱን ለመምሰል እንገፋፋለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ከሚያደርግልን እርዳታ ጋር ተዳምሮ ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቀን በመጣል አዲሱን ሰው እንድንለብስ’ ይረዳናል።—ቆላስይስ 3:9, 10፤ ገላትያ 5:22, 23

ፍቅር በተግባር ሲገለጽ

16. በስብከቱና በማስተማሩ ሥራችን ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ያለንን ፍቅር የምናሳየው እንዴት ነው?

16 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ብሎም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንካፈል ያነሳሳናል። እንዲህ ስናደርግም “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” የሚፈልገውን ይሖዋ አምላክን እናስደስታለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በዚህ መንገድ ሌሎች ሰዎችም የክርስቶስ ሕግ በልባቸው ላይ እንዲጻፍ በመርዳት ደስታ እናገኛለን። ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ተለውጠው የይሖዋን መለኮታዊ ባሕርያት ሲያንጸባርቁ መመልከት ያስደስተናል። (2 ቆሮንቶስ 3:18) በእርግጥም ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት ልንሰጣቸው ከምንችላቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው። የይሖዋ ወዳጆች ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ከእርሱ ጋር የዘላለም ጓደኝነት መመሥረት ይችላሉ።

17. ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማዳበሩ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

17 በዓለም ላይ ቁሳዊ ነገሮች ከፍ ተደርገው የሚታዩ ከመሆኑም በላይ በሰዎች ዘንድ ይወደዳሉ። ሆኖም ቁሳዊ ነገሮች ዘላቂ አይደሉም። ሊሰረቁ ወይም ከጊዜ ብዛት ሊያልቁ ይችላሉ። (ማቴዎስ 6:19) መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ያስጠነቅቀናል። (1 ዮሐንስ 2:16, 17) አዎን፣ ይሖዋም ሆነ እርሱን የሚወዱና የሚያገለግሉት ሰዎች ለዘላለም ይኖራሉ። ይህ ከሆነ ታዲያ ዓለም የሚያቀርባቸውን ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮች ከማሳደድ ይልቅ አምላክንና ሰዎችን ማፍቀር ይበልጥ ጠቃሚ አይሆንም?

18. አንዲት ሚስዮናዊት እህት የራሷን ጥቅም መሥዋዕት እስከ ማድረግ የሚያደርስ ፍቅር እንዳላት ያሳየችው እንዴት ነው?

18 ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣሉ። በሴኔጋል የምትኖረውን ሶንያ የተባለች ሚስዮናዊት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሶንያ፣ ሃይዲ ከተባለች በማያምን የትዳር ጓደኛዋ ምክንያት ለኤች አይ ቪ ከተጋለጠች አንዲት ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ነበር። ሃይዲ ባለቤቷ ከሞተ በኋላ ተጠመቀች፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ጤንነቷ በማሽቆልቆሉና የኤድስ ሕመምተኛ በመሆኗ ሆስፒታል ገባች። ሶንያ እንዲህ ትላለች:- “የሆስፒታሉ ሠራተኞች የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቢጥሩም በቁጥር በጣም ትንሽ ነበሩ። በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተው እንዲንከባከቧት ተጠየቀ። ሆስፒታል በገባች በሁለተኛው ሌሊት አልጋዋ አጠገብ ምንጣፍ ላይ ያደርኩ ሲሆን እስከሞተችበት ዕለት ድረስም ተንከባከብኳት። ሁኔታዋን ይከታተል የነበረው ሐኪም ‘ዋነኛው ችግራችን የሕመምተኛው ዘመዶችም እንኳን በሽታው ኤድስ መሆኑን ሲያውቁ ግለሰቡን የሚርቁት መሆኑ ነው። ታዲያ አንቺ ዘመድሽም ሆነ የአገርሽ ሰው ላልሆነችና ሌላው ቀርቶ የቆዳችሁ ቀለም እንኳ ለማይመሳሰል ሴት ስትይ ሕይወትሽን አደጋ ላይ ለመጣል ፈቃደኛ የሆንሽው ለምንድን ነው?’ አለኝ። እኔም ሃይዲን ከአንድ አባትና ከአንድ እናት የተወለድን እህቴ ያህል እንደምቀርባት ነገርኩት። እንደ እህቴ ስለማያት እርሷን መንከባከብ ያስደስተኛል።” በነገራችን ላይ ሶንያ በፍቅር ተነሳስታ ለሃይዲ ባደረገችው እንክብካቤ ሳቢያ በጤናዋ ላይ ምንም እክል አላጋጠማትም።

19. የአምላክ ሕግ በልባችን የተጻፈ በመሆኑ ምን ለማድረግ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ልንጠቀምባቸው ይገባል?

19 የይሖዋ አገልጋዮች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ፍቅር እንደሚያሳዩ የሚጠቁሙ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። በዛሬው ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች የሚመራቸው የተጻፈ ሕግ የለም። ከዚህ ይልቅ በዕብራውያን 8:10 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ትንቢት ሲፈጸም እንመለከታለን:- “ከዚያን ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሮአቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” ፍቅር ለማሳየት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ይሖዋ በልባችን የጻፈውን የፍቅር ሕግ ሁልጊዜ ከፍ አድርገን እንመልከተው።

20. የክርስቶስ ሕግ በዋጋ ሊተመን የማይችል ሀብት የሆነው ለምንድን ነው?

20 ለአምላክ ፍቅር እንዳላቸው ከሚያሳዩ በዓለም ዙሪያ ከሚኖሩ ወንድሞቻችን ጋር ሆኖ ይሖዋን ማገልገል ምንኛ አስደሳች ነው! የክርስቶስ ሕግ በልባቸው ላይ የተጻፈላቸው ሰዎች ፍቅር በራቀው በዚህ ዓለም ውስጥ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብት አላቸው። ይሖዋ የሚወዳቸው ከመሆኑም በላይ ከወንድሞቻቸው ጋር ባላቸው ጠንካራ ፍቅር ይደሰታሉ። “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ አገሮች የሚኖሩና በርካታ ቋንቋዎች የሚናገሩ እንዲሁም የተለያየ ባሕል ያላቸው ቢሆኑም በመካከላቸው ተወዳዳሪ የሌለው ሃይማኖታዊ አንድነት አለ። ይህ አንድነት የይሖዋን ሞገስ ያስገኛል። መዝሙራዊው “በዚያ [በፍቅር በተሳሰረ ሕዝብ መካከል] እግዚአብሔር በረከቱን፣ ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዞአልና” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 133:1-3

መመለስ ትችላለህ?

• አሥርቱ ትእዛዛት ምን ያህል አስፈላጊ ነበሩ?

• በልብ ላይ የተጻፈው ሕግ ምንድን ነው?

• “በክርስቶስ ሕግ” ውስጥ ፍቅር ምን ሚና ይጫወታል?

• ለአምላክና ለሰዎች ያለንን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን በድንጋይ ጽላቶች ላይ የተጻፉ ሕግጋት ተሰጥተዋቸው ነበር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች የአምላክ ሕግ በልባቸው ላይ ተጽፎላቸዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶንያ የሴኔጋል ተወላጅ ከሆነች አንዲት ልጅ ጋር በ2004 የአውራጃ ስብሰባ ላይ