በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ ፈቃደኛ ነህ?

የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ ፈቃደኛ ነህ?

የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ ፈቃደኛ ነህ?

‘እኛም የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እናንጸባርቃለን።’2 ቆሮንቶስ 3:18

1. ሙሴ ምን ተመለከተ? ይህስ ምን አስከተለ?

 ማንም ሰው አይቶት የማያውቅ እጅግ አስደናቂ ራእይ ነበር። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ብቻውን እያለ ላቀረበው ለየት ያለ ጥያቄ ምላሽ ተሰጠው። ማንም ሰው አይቶት የማያውቀውን የይሖዋን ክብር እንዲመለከት ተፈቀደለት። እርግጥ ሙሴ ይሖዋን ፊት ለፊት አልተመለከተውም። የአምላክ ገጽታ በጣም ድንቅ በመሆኑ የትኛውም ሰው ቢሆን እርሱን አይቶ በሕይወት ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ይሖዋ እስኪያልፍ ድረስ ሙሴን ‘በእጁ’ (በአንድ መልአክ በመጠቀም ሳይሆን አይቀርም) ጋረደው። ከዚያም እርሱ ካለፈ በኋላ ሙሴ ክብሩን ከጀርባው እንዲመለከት ፈቀደለት። ከዚህም በላይ ይሖዋ ሙሴን በመልአክ አማካኝነት አነጋግሮታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጸመ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ሙሴ . . . ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ [ያበራ ነበር]።”—ዘፀአት 33:18 እስከ 34:7, 29

2. ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ስለሚያንጸባርቁት ክብር ምን በማለት ጽፏል?

2 ከሙሴ ጋር በተራራው ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ዕፁብ ድንቅ የሆነውን ሁሉን የሚችለውን አምላክ ክብር መመልከትና እርሱ ሲናገር መስማት እንዴት ያለ አስደሳች ነገር ነው! የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ ከሆነው ከሙሴ ጋር ሆኖ ከተራራው መውረድስ ምንኛ ታላቅ መብት ነው! ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች በአንዳንድ መንገዶች ከሙሴ በላቀ ሁኔታ የአምላክን ክብር እንደሚያንጸባርቁ ታውቃለህ? ይህ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይገኛል። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች “የጌታን ክብር እንደ መስተዋት [እንደሚያንጸባርቁ]” በደብዳቤው ላይ ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 3:7, 8, 18) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም በተወሰነ መንገድ የአምላክን ክብር ያንጸባርቃሉ።

ክርስቲያኖች የአምላክን ክብር የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

3. ይሖዋን ከሙሴ በተለየ መንገድ እኛ ልናውቀው የቻልነው እንዴት ነው?

3 የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? እኛ እንደ ሙሴ የይሖዋን ክብር አልተመለከትንም ወይም ሲናገር አልሰማነውም። ሆኖም ከሙሴ በተለየ መንገድ ይሖዋን እናውቀዋለን። ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ የመጣው ሙሴ ከሞተ ወደ 1,500 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር። በመሆኑም ሙሴ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት የጭቆና ቀንበር ነፃ ለማውጣት ሕይወቱን አሳልፎ በሰጠው በኢየሱስ ላይ ሕጉ የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ማወቅ አይችልም ነበር። (ሮሜ 5:20, 21፤ ገላትያ 3:19) ከዚህም በላይ ሙሴ በመሲሐዊው መንግሥት ላይ ስላተኮረው የይሖዋ ታላቅ ዓላማ እንዲሁም ይህ መንግሥት በምድር ላይ ስለሚያመጣው ገነት የተረዳው በጥቂቱ ብቻ ነበር። እኛ ግን በሥጋዊ ዓይናችን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ በተመሠረተ የእምነት ዓይን የይሖዋን ክብር ማየት ችለናል። ከዚህም በላይ በመልአክ አማካኝነት ባይሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም የኢየሱስን ትምህርቶችና አገልግሎት ግሩም በሆነ መንገድ በዘገቡት የወንጌል መጻሕፍት በኩል የይሖዋን ድምፅ ሰምተናል።

4. (ሀ) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች የአምላክን ክብር የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው? (ለ) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

4 ክርስቲያኖች የአምላክን ክብር ሲያንጸባርቁ ፊታቸው ቃል በቃል ባያበራም ድንቅ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያትና ዓላማዎች ለሰዎች ሲናገሩ ፊታቸው ይፈካል። ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ዘመናችን ሲናገር የአምላክ አገልጋዮች “በሕዝቦችም መካከል [ስለ ይሖዋ ክብር] ይናገራሉ” ብሏል። (ኢሳይያስ 66:19) ከዚህም በተጨማሪ 2 ቆሮንቶስ 4:1, 2 እንዲህ ይላል:- “ይህ አገልግሎት ስላለን . . . ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ አናታልልም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋር አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን።” ጳውሎስ ይህንን ሲናገር “የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች” ስለሆኑት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች መግለጹ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 3:6) ይሁን እንጂ እነዚህ ቅቡዓን ያከናወኑት አገልግሎት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ባላቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች የሚያከናውኑት አገልግሎት በማስተማር ብቻ ሳይሆን በአኗኗርም ጭምር የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅን ያካተተ ነው። የልዑሉን አምላክ ክብር እንደ መስተዋት ማንጸባረቅ ኃላፊነታችንም መብታችንም ነው!

5. መንፈሳዊ ብልጽግናችን ለምን ነገር ማስረጃ ይሆናል?

5 ኢየሱስ እንደተነበየው በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ሁሉ ላይ እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ምሥራቹን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲሉ በሕይወታቸው ላይ ለውጥ አድርገዋል። (ሮሜ 12:2፤ ራእይ 7:9) እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እነዚህ ሰዎችም ያዩትንና የሰሙትን ከመናገር ወደኋላ አይሉም። (የሐዋርያት ሥራ 4:20) በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የአምላክን ክብር እያንጸባረቁ ነው። አንተስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ነህ? የአምላክ ሕዝቦች ያገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደባረካቸውና ከክፉም እንደጠበቃቸው ያሳያል። በእኛ ላይ የተነሱብንን ኃይሎች ስንመለከት የይሖዋ መንፈስ እንደሚደግፈን ይበልጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የይሖዋ መንፈስ ድጋፍ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ እንመልከት።

የአምላክን ሕዝቦች ዝም ማሰኘት አይቻልም

6. ከይሖዋ ጎን ለመቆም እምነትና ድፍረት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

6 በአንድ ጨካኝ ወንጀለኛ ላይ እንድትመሠክር ፍርድ ቤት ቀርበሃል እንበል። ወንጀለኛው ትልቅ ድርጅት እንዳለውና እንዳታጋልጠው ለመከላከል የማይቆፍረው ጉድጓድ እንደማይኖር ታውቃለህ። እንደዚህ ባለው ወንጀለኛ ላይ ለመመሥከር ድፍረት ሊኖርህ እንዲሁም ባለ ሥልጣናቱ ይህ ሰው ጥቃት እንዳያደርስብህ ጥበቃ ሊያደርጉልህ እንደሚችሉ ልትተማመን ይገባል። እኛም ያለንበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ስንመሠክር ሰይጣን ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይና ዓለምን ሁሉ እያሳተ ያለ ውሸታም መሆኑን በማጋለጥ በእርሱ ላይ መመሥከራችን ነው። (ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 12:9) ዲያብሎስን በመቃወም ከይሖዋ ጎን መቆም እምነትና ድፍረት ይጠይቃል።

7. ሰይጣን ምን ያህል ኃይል አለው? ምን ለማድረግስ ይጥራል?

7 ይሖዋ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ በመሆኑ ከሰይጣን እጅግ በጣም የላቀ ኃይል እንዳለው ግልጽ ነው። በታማኝነት የምናገለግለው ከሆነ ለእኛ ጥበቃ ለማድረግ አቅሙም ፍላጎቱም እንዳለው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ያም ቢሆን ግን አጋንንትንም ሆነ ከአምላክ የራቀውን የሰው ዘር ኅብረተሰብ የሚገዛው ሰይጣን ነው። (ማቴዎስ 12:24, 26፤ ዮሐንስ 14:30) በምድር አካባቢ ተወስኖ እንዲቆይ የተደረገውና “በታላቅ ቊጣ” የተሞላው ሰይጣን የይሖዋን አገልጋዮች አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን ምሥራቹን የሚያውጁትን ሰዎች ሁሉ አፍ ለማዘጋት በእርሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ይጠቀማል። (ራእይ 12:7-9, 12, 17) ይህንን የሚያደርገው እንዴት ነው? ቢያንስ በሦስት መንገዶች ይጠቀማል።

8, 9. ሰይጣን ለየትኞቹ ነገሮች ፍቅር እንዲያድርብን በማድረግ ሊያስተን ይሞክራል? ወዳጆቻችንን በጥበብ መምረጥ የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?

8 ሰይጣን ትኩረታችንን ለመከፋፈል የኑሮ ሐሳቦችን እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ገንዘብን፣ ራሳቸውንና ተድላን የሚወዱ ሲሆን ለአምላክ ግን ፍቅር የላቸውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ስለሚጠመዱ ለምንነግራቸው የምሥራች ትኩረት አይሰጡም። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማር ምንም ፍላጎት የላቸውም። (ማቴዎስ 24:37-39) እንደዚህ ያለው ዝንባሌ በቀላሉ ሊጋባብንና በመንፈሳዊ ግዴለሾች እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። የቁሳዊ ነገሮችና የተድላ ፍቅር ካደረብን ለአምላክ ያለን ፍቅር እየቀዘቀዘ ይሄዳል።—ማቴዎስ 24:12

9 በዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች ወዳጆቻቸውን በጥንቃቄ ይመርጣሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 13:20) እኛም የአምላክን ክብር ከሚያንጸባርቁት ጋር ‘መሄድ’ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ ምንኛ አስደሳች ነው! ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በስብሰባዎችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ስንገናኝ በፍቅራቸው፣ በእምነታቸው፣ በደስተኝነታቸውና በጥበባቸው እንበረታታለን። እንዲህ ያለው ጤናማ ወዳጅነት በአገልግሎታችን እንድንጸና ያጠናክረናል።

10. ሰይጣን የአምላክን ክብር የሚያንጸባርቁ ሰዎችን ለማጥቃት በፌዝ የተጠቀመው እንዴት ነው?

10 ሰይጣን ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክን ክብር ማንጸባረቃቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ የሚጠቀምበት ሁለተኛው መንገድ ፌዝ ነው። ሰይጣን በዚህ መንገድ መጠቀሙ ሊያስገርመን አይገባም። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሰዎች አፊዘውበት፣ ስቀውበት፣ አላግጠውበት፣ ተሳልቀውበት፣ ተዘባብተውበትና ተፍተውበት ነበር። (ማርቆስ 5:40፤ ሉቃስ 16:14፤ 18:32) የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ይፌዝባቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:13፤ 17:32) በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ተመሳሳይ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች እንደ ሐሰተኛ ነቢያት እንደሚቆጠሩ ተናግሯል። “በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ ‘“እመጣለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? . . . ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) የአምላክ ሕዝቦች አመለካከታቸው ከገሃዱ ዓለም የራቀ ነው በሚል ይፌዝባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ኋላ ቀር እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። የምንሰብከው መልእክት ለብዙዎች ሞኝነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:18, 19) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ አንዳንድ ጊዜም በቤተሰብ ውስጥ ጭምር ይፌዝብን ይሆናል። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ስለምናውቅ በሚደርስብን ፌዝ ሳንበገር በስብከቱ ሥራችን የአምላክን ክብር ማንጸባረቃችንን እንቀጥላለን።—ዮሐንስ 17:17

11. ሰይጣን ክርስቲያኖችን ዝም ለማሰኘት በስደት የተጠቀመው እንዴት ነው?

11 ዲያብሎስ እኛን ዝም ለማሰኘት የሚጠቀምበት ሦስተኛው ዘዴ ተቃውሞ ወይም ስደት ነው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 24:9) በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን በተለያዩ የምድር ክፍሎች ጭካኔ የተሞላበት ስደት አጋጥሞናል። ይሖዋ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደተናገረው በአምላክ አገልጋዮችና በሰይጣን ዲያብሎስ አገልጋዮች መካከል ጠላትነት እንደሚኖር እናውቃለን። (ዘፍጥረት 3:15) እንዲሁም መከራ ቢያጋጥመንም እንኳ በታማኝነት መጽናታችን የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ትክክለኛ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ተገንዝበናል። ይህንን ማወቃችን በጣም ከባድ ስደት ቢያጋጥመንም እንኳ መጠንከር እንድንችል ይረዳናል። የአምላክን ክብር ለማንጸባረቅ ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን ምንም ዓይነት ስደት ቢደርስብን ለዘለቄታው ዝም አያሰኘንም።

12. ሰይጣን የሚያደርስብንን ተቃውሞ በታማኝነት ስንወጣ የምንደሰተው ለምንድን ነው?

12 ዓለም የሚያቀርባቸውን መደለያዎች፣ የሚሰነዝርብንን ፌዝና የሚያደርስብንን ስደት ትቋቋማለህ? ከሆነ ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት አለህ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል:- “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና።” (ማቴዎስ 5:11, 12) መጽናትህ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በአንተ ላይ እንደሚሠራና የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ እንድትችል እየረዳህ መሆኑን ያሳያል።—2 ቆሮንቶስ 12:9

ከይሖዋ በሚገኝ እርዳታ መጽናት

13. በአገልግሎታችን እንድንጸና የሚያደርገን ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

13 በአገልግሎታችን የምንጸናበት ዋናው ምክንያት ይሖዋን ስለምንወደውና የእርሱን ክብር ማንጸባረቅ ስለሚያስደስተን ነው። የሰው ልጆች የሚወዷቸውንና የሚያከብሯቸውን ሰዎች የመምሰል ዝንባሌ አላቸው፤ ደግሞም ከይሖዋ የበለጠ ልንመስለው የሚገባን አካል የለም። ይሖዋ ለሰው ልጆች ታላቅ ፍቅር ስላለው ለእውነት እንዲመሠክርና ታዛዥ የሰው ዘሮችን እንዲቤዥ ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። (ዮሐንስ 3:16፤ 18:37) እንደ አምላክ ሁሉ እኛም ሁሉም ዓይነት ሰዎች ንስሐ ገብተው ለመዳን እንዲበቁ እንፈልጋለን፤ ምሥራቹን የምንሰብከውም ለዚህ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9) ይህ ፍላጎታችን አምላክን ለመምሰል ካለን ምኞት ጋር ተዳምሮ በአገልግሎታችን የእርሱን ክብር ማንጸባረቃችንን እንድንቀጥል ይገፋፋናል።

14. ይሖዋ በአገልግሎታችን እንድንጸና የሚያጠናክረን እንዴት ነው?

14 በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ለመጽናት የሚያስችለንን ኃይል በዋነኝነት የምናገኘው ግን ከይሖዋ ነው። በመንፈሱ፣ በድርጅቱና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይደግፈናል እንዲሁም ያጠናክረናል። ይሖዋ የእርሱን ክብር ለማንጸባረቅ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ‘ብርታት ይሰጣል።’ ለጸሎቶቻችን ምላሽ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ችግሮችን ለመቋቋም እንድንችል ያበረታናል። (ሮሜ 15:5፤ ያዕቆብ 1:5) ከዚህም በላይ ይሖዋ ልንቋቋመው ከምንችለው በላይ መከራ እንዲደርስብን አይፈቅድም። በይሖዋ ከታመንን የእርሱን ክብር ማንጸባረቃችንን እንድንቀጥል ከፈተናው መውጫ መንገዱን ያዘጋጅልናል።—1 ቆሮንቶስ 10:13

15. መጽናት እንድንችል የሚረዳን ምንድን ነው?

15 በአገልግሎታችን መጽናታችን የአምላክ መንፈስ እየረዳን እንዳለ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። አንድ ምሳሌ እንውሰድ:- አንድ ሰው ከቤት ወደ ቤት እየሄድክ ዳቦ በነፃ እንድታድል ጠየቀህ እንበል። ሥራውን የምታከናውነው በራስህ ወጪ ከመሆኑም በላይ ጊዜህን መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልግሃል። ብዙም ሳትቆይ ግን ዳቦውን የሚፈልጉት በጣም ጥቂቶች እንደሆኑና እንዲያውም አንዳንዶች የምታደርገውን ጥረት እንደሚቃወሙ ትገነዘባለህ። በዚህ ሥራ ከወር እስከ ወር ብሎም ከዓመት እስከ ዓመት የምትቀጥል ይመስልሃል? ላትቀጥል ትችላለህ። ምሥራቹን ለመስበክ ግን ጊዜህንና ገንዘብህን መሥዋዕት አድርገህ ለዓመታት አልፎ ተርፎም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጥረት ስታደርግ ቆይተሃል። እንዲህ የምታደርገው ለምንድን ነው? ይሖዋን ስለምትወደው እንዲሁም በመንፈሱ አማካኝነት ጥረትህን በመባረክ መጽናት እንድትችል ስለረዳህ አይደለም? ምንም ጥርጥር የለውም!

ምንጊዜም የማይረሳ ሥራ

16. በአገልግሎታችን መጽናታችን ለእኛም ሆነ ለሚሰሙን ሰዎች ምን ጥቅም ያስገኛል?

16 የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋይ መሆን ተወዳዳሪ የሌለው ስጦታ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በተመሳሳይም ሌሎች በጎች በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱት ክርስቲያናዊ አገልግሎት ውድ መብት ነው። በአገልግሎት ጸንተህ ከቀጠልክ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት ላይ እንደገለጸው “ራስህንና የሚሰሙህን ታድናለህ።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ይህ ምን ትርጉም እንዳለው እስቲ አስበው። አንተ የምትሰብከው የምሥራች ሰዎች ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በመንፈሳዊ ከምትረዳቸው ሰዎች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ። ስለ አምላክ እንዲማሩ ከረዳሃቸው ሰዎች ጋር በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ምንኛ አስደሳች እንደሆነ እስቲ አስበው! እነርሱን ለመርዳት ያደረግኸውን ጥረት ፈጽሞ እንደማይረሱት ጥርጥር የለውም። ይህ በእርግጥም እርካታ ያስገኛል!

17. አሁን ያለንበትን ወቅት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

17 የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ለየት ባለ ጊዜ ላይ ነው። ምሥራቹ ከአምላክ ለራቀው ኅብረተሰብ ከአሁን በኋላ አይሰበክም። ኖኅ እንደዚህ ባለው ዓለም ውስጥ የኖረ ሲሆን በዚያን ጊዜ የነበረው ኅብረተሰብ ሲጠፋ ተመልክቷል። አምላክ መርከብ እንዲሠራ የሰጠውን ኃላፊነት በታማኝነት እንደተወጣና ይህንንም በማድረጉ እርሱና ቤተሰቡ ከጥፋት መትረፍ እንደቻሉ ሲገነዘብ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! (ዕብራውያን 11:7) አንተም እንዲህ ዓይነት ደስታ ልታገኝ ትችላለህ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሆነህ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ያከናወንከውን ሥራ መለስ ብለህ ስትመለከትና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ የቻልከውን ያህል እንዳደረግህ ስትገነዘብ ምን እንደሚሰማህ አስብ።

18. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ዓይነት ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል?

18 እንግዲያው የአምላክን ክብር ማንጸባረቃችንን እንቀጥል። ይህ ለዘላለም የማንረሳው ሥራ ይሆናል። ይሖዋም ሥራችንን አይረሳውም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማበረታቻ ይሰጠናል:- “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።”—ዕብራውያን 6:10-12

ልታብራራ ትችላለህ?

• ክርስቲያኖች የአምላክን ክብር የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

• ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች ዝም ለማሰኘት የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?

• የአምላክ መንፈስ ከእኛ ጋር እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሙሴ ፊት የአምላክን ክብር አንጸባርቋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎታችን የአምላክን ክብር እናንጸባርቃለን