በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በጥንቷ እስራኤል በማደሪያው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚታየው እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ሸኪና ተብሎ የሚጠራው ተአምራዊ ብርሃን ምን ያመለክት ነበር?

ይሖዋ አፍቃሪ አባትና የሕዝቡ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን እስራኤላውያን በመካከላቸው መገኘቱን በግልጽ እንዲያውቁ ያደርግ ነበር። ይህን ያደረገበት አንደኛው መንገድ ከአምልኮ ቦታው ጋር በቅርብ ተዛማጅነት ያለውን አንጸባራቂ ደመና በመጠቀም ነበር።

ይህ አንጸባራቂ ብርሃን ይሖዋ በዓይን በማይታይ ሁኔታ በቦታው መገኘቱን ያመለክት ነበር። ብርሃኑ በማደሪያው ድንኳንም ሆነ ሰሎሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይታይ ነበር። ይህ ተአምራዊ ብርሃን ይሖዋ በአካላዊ ሁኔታ መገኘቱን አያመለክትም። አምላክ ሰው በሠራው በማንኛውም ዓይነት ሕንጻ ውስጥ ሊቀመጥ አይችልም። (2 ዜና መዋዕል 6:18፤ የሐዋርያት ሥራ 17:24) ይህ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚታየውና ከሰው በላይ ከሆነ ኃይል የመነጨው ደማቅ ብርሃን ሊቀ ካህኑና በእርሱ አማካኝነት ደግሞ መላው እስራኤል ይሖዋ በዚያ እንደሚገኝና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ በኋላ በነበሩት ዘመናት ይህ ብርሃን በአረማይክ ቋንቋ ሸኪና (shekhi·nahʹ) ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ቃሉ “የሚኖርበት” ወይም “መኖሪያው” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይኖርም በአረማይክ ቋንቋ በተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግን ይገኛል፤ እነዚህ ትርጉሞች ታርገም በመባልም ይታወቃሉ።

ይሖዋ ለሙሴ የማደሪያውን ድንኳን እንዲሠራ መመሪያ በሰጠው ጊዜ እንዲህ ብሏል:- “የስርየት መክደኛውን በታቦቱ አናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ። በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋር እገናኛለሁ።” (ዘፀአት 25:21, 22) ከላይ የተጠቀሰው ታቦት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሚገኝ በወርቅ የተለበጠ ሣጥን ነበር። በታቦቱ መክደኛ ላይ ሁለት የወርቅ ኪሩቤል ነበሩ።

ታዲያ ይሖዋ የሚናገረው ከየት ነበር? “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመና ውስጥ እገለጣለሁ” በማለት ለሙሴ ከሰጠው መመሪያ መልሱን እናገኛለን። (ዘሌዋውያን 16:2) ደመናው ከቅዱሱ ታቦት በላይ በሁለቱ የወርቅ ኪሩቤል መካከል ይታይ ነበር። ደመናው ከኪሩቦቹ በላይ ምን ያህል ከፍ ብሎ እንደሚገኝና ወደ ጎን ምን ያህል ቦታ እንደሚሸፍን መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም።

ይህ አንጸባራቂ ደመና ለቅድስተ ቅዱሳኑ ብርሃን ይሰጠዋል። እንዲያውም በዚያ ስፍራ የነበረው ብቸኛ የብርሃን ምንጭ ይህ ደመና ነበር። ሊቀ ካህኑ በሥርየት ቀን ወደ ውስጠኛው ክፍል ሲገባ ይህ ብርሃን ለማየት ይረዳዋል። በዚያም ካህኑ በይሖዋ ፊት እንደቆመ ያህል ነበር።

ይህ ተአምራዊ ብርሃን ለክርስቲያኖች የያዘው ቁም ነገር ይኖራል? ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከታት ከተማ በውስጧ ‘ሌሊት እንደሌለ’ ገልጿል። ከተማዋ ከሙታን ተነስተው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙትን ቅቡዓን ያቀፈችውን አዲሲቱ ኢየሩሳሌምን ታመለክታለች። ይህች ምሳሌያዊ ከተማ ብርሃን የምታገኘው ከፀሐይ ወይም ከጨረቃ አይደለም። ሸኪና ተብሎ የተጠራው አንጸባራቂ ደመና በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንደሚያበራ ሁሉ የይሖዋ አምላክ ታላቅ ክብርም ለዚህች ድርጅት ብርሃን ይሰጣታል። በጉ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስም ለከተማይቱ “መብራቷ” ነው። “ከተማዋ” ደግሞ ከብሔራት ሁሉ ለተዋጁት ሕዝቦች መንፈሳዊ ብርሃን የምትፈነጥቅ ከመሆኗም በላይ መመሪያ በመስጠት ሞገስ ታሳያቸዋለች።—ራእይ 21:22-25

የይሖዋ አገልጋዮች ከአምላክ በጣም ብዙ በረከት ስለሚያገኙ ይሖዋ ጥበቃ የሚያደርግላቸው እረኛቸውና አፍቃሪ አባታቸው መሆኑን እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።