በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን ከአምላክ ጋር መሄድ

ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን ከአምላክ ጋር መሄድ

ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን ከአምላክ ጋር መሄድ

“ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም።”—ዘፍጥረት 5:24

1. ዘመናችንን አስጨናቂ ያደረጉት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

 ሁከት የነገሠበት ዘመን! እነዚህ ቃላት መሲሐዊው መንግሥት ከተቋቋመ ከ1914 ወዲህ የሰው ልጆች የሚኖሩበትን ሽብርና ዓመጽ የበዛበት ጊዜ በሚገባ ይገልጻሉ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ይገኛል። በዚህ ዘመን ውስጥ የሰው ልጅ እንደ ረሐብ፣ ቸነፈር፣ የምድር መናወጥና ጦርነት ባሉት መቅሰፍቶች ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ከፍተኛ መጠን ተጠቅቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ራእይ 6:1-8) የይሖዋ አምላኪዎችም ከችግሮቹ አላመለጡም። ይነስም ይብዛ ሁላችንም ያለንበት ዓለም የሚያደርስብንን መከራና አለመረጋጋት ተቋቁመን መኖር ይገባናል። ኑሮን በጣም ካከበዱት ነገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወንጀልና ሕመም ይገኙበታል።

2. የይሖዋ አገልጋዮች ምን ፈተናዎች ተጋርጠውባቸዋል?

2 በተጨማሪም በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ሰይጣን “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ” ሰዎች ላይ የከፈተውን ውጊያ ባለማቆሙ ምክንያት በተደጋጋሚ የሚደርስባቸውን የስደት ማዕበል ተቋቁመው ለማሳለፍ ተገድደዋል። (ራእይ 12:17) ሁላችንንም ቀጥተኛ ስደት ያጋጥመናል ማለት ባይቻልም እውነተኛ ክርስቲያኖች በአጠቃላይ ሰይጣን ዲያብሎስንና በሰው ልጆች መሃል የዘራውን መንፈስ ለመቋቋም መታገል አለባቸው። (ኤፌሶን 2:2፤ 6:12) ይህ መንፈስ ለንጹሕ አምልኮ አድናቆት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ሁልጊዜ በምንገናኝባቸው በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በሌሎችም ስፍራዎች ተንሰራፍቶ ስለሚገኝ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ዘወትር መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ከአሕዛብ ጋር ሳይሆን ከአምላክ ጋር መሄድ

3, 4. ክርስቲያኖች ከዓለም የሚለዩት በምን መንገድ ነው?

3 በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ የዚህን ዓለም መንፈስ በብርቱ ታግለዋል፤ ይህም ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ካሉት ሰዎች ፈጽሞ የተለዩ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ ልዩነታቸውን ገልጿል:- “ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም። እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቦናቸው ጨልሞአል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል። ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኵሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።”—ኤፌሶን 4:17-19

4 እነዚህ ቃላት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ድቅድቅ ጨለማ የዋጠውን የጳውሎስንና የእኛን ዘመን እንዴት ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ! በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ ዛሬም የአምላክ አገልጋዮች ‘እንደ አሕዛብ አይመላለሱም።’ ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር የመሄድ ታላቅ መብት አግኝተዋል። አንዳንዶች ‘እዚህ ግባ የማይባለውና ፍጽምና የሌለው የሰው ልጅ ከይሖዋ ጋር መሄድ ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ እሙን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እንደሚቻል ይገልጻል። እንዲያውም ይሖዋ የሰው ልጆች ከእርሱ ጋር እንዲሄዱ ይፈልግባቸዋል። ነቢዩ ሚክያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የሚከተሉትን ቃላት አስፍሯል:- “ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8

ከአምላክ ጋር መሄድ ያለብን እንዴትና ለምንድን ነው?

5. ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር መሄድ የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ሁሉን ቻይ ከሆነውና ከማይታየው አምላክ ጋር መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? ከሰዎች ጋር እንደምንሄደው አለመሆኑ ግልጽ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መሄድ” ተብሎ የተገለጸው ቃል “አንድን ዓይነት አሠራር ወይም አካሄድ መከተል” ማለት ሊሆን ይችላል። a ይህንን በአእምሯችን ከያዝን አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የሚሄደው እርሱ የሚፈልገውንና የሚደሰትበትን የሕይወት ጎዳና በመከተል መሆኑን እንገነዘባለን። እንዲህ ዓይነት አካሄድ መከተላችን በዙሪያችን ካሉት አብዛኞቹ ሰዎች የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። ሆኖም ክርስቲያኖች ሊጓዙበት የሚገባው ብቸኛ መንገድ ይሄ ነው። ለምን? በርካታ ምክንያቶች አሉ።

6, 7. ከአምላክ ጋር መሄድ ከሁሉ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ፈጣሪያችን ማለትም የሕይወታችን ምንጭ እንዲሁም ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ የሚሰጠን አምላክ ነው። (ራእይ 4:11) በመሆኑም አካሄዳችንን የመምራት መብት ያለው እርሱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ከአምላክ ጋር ከመሄድ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ሌላ አካሄድ የለም። ይሖዋ ከእርሱ ጋር የሚሄዱ የኃጢአት ሥርየት የሚያገኙበትን ዝግጅት አድርጓል፤ እንዲሁም እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ዘርግቶላቸዋል። ከዚህም በላይ አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ከእርሱ ጋር የሚሄዱት ሰዎች ፍጽምና የሚጎድላቸውና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የተሳካ ሕይወት ለመምራት የሚያስችላቸውን ጠቃሚ ምክር ይሰጣቸዋል። (ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15, 16፤ 1 ዮሐንስ 1:8፤ 2:25፤ 5:19) ከአምላክ ጋር የምንሄድበት ሌላው ምክንያት ከእርሱ ጋር ለመሄድ ፈቃደኛ መሆናችን ለጉባኤው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ ነው።—ቆላስይስ 3:15, 16

7 የመጨረሻውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከአምላክ ጋር ስንሄድ ጥንት በዔድን የአትክልት ስፍራ ተነስቶ በነበረው ትልቅ ጉዳይ ማለትም ሉዓላዊነትን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ላይ ከማን ጎን እንደቆምን እናሳያለን። (ዘፍጥረት 3:1-6) በአኗኗራችን ሙሉ በሙሉ ከይሖዋ ጎን መቆማችንን እናሳያለን፤ እንዲሁም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት ያለው እርሱ ብቻ እንደሆነ በድፍረት እናውጃለን። (መዝሙር 83:18) በዚህ መንገድ የአምላክ ስም እንዲቀደስና ፈቃዱ እንዲፈጸም ከምናቀርበው ጸሎት ጋር የሚስማማ ተግባር እንፈጽማለን። (ማቴዎስ 6:9, 10) ከአምላክ ጋር ለመሄድ የመረጡ ሰዎች ምንኛ ጥበበኞች ናቸው! ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” አምላክ በመሆኑ እነዚህ ሰዎች ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘው እየተጓዙ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። እርሱ ፈጽሞ አይሳሳትም።—ሮሜ 16:27

8. የሄኖክና የኖኅ ዘመን ከእኛ ጊዜ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

8 ታዲያ ሁከት በነገሠበትና በርካታ ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል በማይፈልጉበት ጊዜ ውስጥ እየኖሩ እንዴት ክርስቲያናዊ ኑሮ መምራት ይቻላል? በጥንት ዘመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እንኳን ጽኑ አቋማቸውን ያላላሉ ታማኝ ሰዎችን ታሪክ ስንመለከት መልሱን እናገኛለን። ከእነዚህ መካከል ሄኖክና ኖኅ ይገኙበታል። ሁለቱም የኖሩት ከእኛ ዘመን ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነበር። በወቅቱ ክፋት በዝቶ ነበር። በኖኅ ዘመን ምድር በዓመጽና በሥነ ምግባር ብልግና ተሞልታ ነበር። ቢሆንም ሄኖክና ኖኅ በእነርሱ ዘመን የነበረውን ዓለም መንፈስ ተቋቁመው ከይሖዋ ጋር ሄደዋል። ይህንን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንድንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ የሄኖክን ምሳሌ እንመለከታለን። በሚቀጥለው ርዕስ ደግሞ የኖኅን ታሪክ እናያለን።

ሄኖክ ሁከት በነገሠበት ዘመን ከአምላክ ጋር ሄዷል

9. ሄኖክን በተመለከተ ምን የተጠቀሰ ነገር አለ?

9 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከአምላክ ጋር እንደሄደ የተነገረለት የመጀመሪያው ሰው ሄኖክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር [አደረገ]” ይላል። (ዘፍጥረት 5:22) ዘገባው በዚያን ጊዜ ከነበረው ዕድሜ አንጻር ሲታይ አጭር፣ ከእኛ የሕይወት ዘመን ጋር ሲወዳደር ግን ረጅም የሆነውን የሄኖክ ዕድሜ ከገለጸ በኋላ “ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም” ይላል። (ዘፍጥረት 5:24) ይሖዋ፣ ሄኖክ በጠላቶቹ እጅ ላይ እንዳይወድቅ በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ ከሕያዋን ምድር ወሰደው። (ዕብራውያን 11:5, 13) ከዚህ አጭር መግለጫ በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሄኖክ በሌሎች ጥቂት ቦታዎች ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ያም ሆነ ይህ ከዚህና ከሌሎችም ማስረጃዎች በመነሳት የሄኖክ ዘመን ሁከት የነገሠበት ነበር ብለን መናገር እንችላለን።

10, 11. (ሀ) አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ ምግባረ ብልሹነት የተስፋፋው እንዴት ነው? (ለ) ሄኖክ ምን የሚል ትንቢታዊ መልእክት ይሰብክ ነበር? ምንስ ዓይነት ምላሽ እንዳጋጠመው እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

10 ለምሳሌ ያህል አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ምግባረ ብልሹነት ምን ያህል በፍጥነት ተዛምቶ እንደነበር ተመልከት። የአዳም የበኩር ልጅ የሆነው ቃየን ወንድሙን አቤልን በመግደል የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 4:8-10) አቤል በጭካኔ ከተገደለ በኋላ አዳምና ሔዋን ሌላ ልጅ ወልደው ስሙን ሴት አሉት። ስለ እርሱ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ።” (ዘፍጥረት 4:25, 26) የሚያሳዝነው “የእግዚአብሔርን ስም መጥራት” የጀመሩት በክህደት መልክ ነበር። b ሄኖስ ከተወለደ በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላ የቃየን ዘር የሆነው ላሜህ ያቆሰለውን አንድ ወጣት እንደገደለ የሚገልጽ መዝሙር ለሁለት ሚስቶቹ ተቀኝቶላቸው ነበር። እንዲሁም “ቃየንን የሚገድል ሰባት ጊዜ ቅጣት ካገኘው፣ የላሜሕ ገዳይማ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል” በማለት አስጠንቅቆ ነበር።—ዘፍጥረት 4:10, 19, 23, 24

11 ሰይጣን በዔድን ገነት ያስጀመረው ምግባረ ብልሹነት የአዳም ዘሮች ክፋት በፍጥነት እየተስፋፋ እንዲሄድ መንገድ እንደከፈተ ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱት እውነታዎች ያሳያሉ። ሄኖክ ይህን ይመስል በነበረው ዓለም ውስጥ የይሖዋ ነቢይ ሆኖ በሚያገለግልበት ወቅት በመንፈስ አነሳሽነት የተናገራቸው ከባድ ቃላት በእኛም ዘመን እንኳን ሳይቀር ያስተጋባሉ። ሄኖክ “እነሆ፤ ጌታ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤ ይህም፣ በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመፀኞችን ሁሉ በክፋት መንገድ በሠሩት የዐመፅ ሥራና በክፋት በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ አጥፊነታቸውን ይፋ ለማድረግ ነው” በማለት ትንቢት እንደተናገረ ይሁዳ ዘግቧል። (ይሁዳ 14, 15) እነዚህ ቃላት የመጨረሻ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በአርማጌዶን ነው። (ራእይ 16:14, 16) ይሁንና በሄኖክ ዘመንም ቢሆን እርሱ የተናገረው ትንቢት ያበሳጫቸው በርካታ “ዐመፀኞች” እንደነበሩ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይሖዋ እነዚህ ዓመጸኞች እንዳይጎዱት ነቢዩን መውሰዱ እንዴት ያለ የፍቅሩ መግለጫ ነው!

ሄኖክ ከአምላክ ጋር እንዲሄድ የረዳው ምንድን ነው?

12. ሄኖክን በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች የሚለየው ምንድን ነው?

12 አዳምና ሔዋን በዔድን ገነት ሳሉ ሰይጣን ያላቸውን በመስማታቸው አዳም በይሖዋ ላይ ዓመጸ። (ዘፍጥረት 3:1-6) ልጃቸው አቤል ግን ከዚህ የተለየ መንገድ ተከትሏል፤ ይሖዋም ሞገሱን ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 4:3, 4) የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ የአዳም ዘሮች እንደ አቤል አልሆኑም። ይሁን እንጂ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የተወለደው ሄኖክ እንደ አቤል ዓይነት ሰው ነበር። በሄኖክና በብዙዎቹ የአዳም ዝርያዎች መካከል ምን ልዩነት ነበረ? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ከዚህ ዓለም በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ዕብራውያን 11:5) ሄኖክ ግሩም የእምነት ምሳሌ ከተዉልን ‘እንደ ደመና ያሉ [የቅድመ ክርስትና] ምስክሮች’ አንዱ እንደሆነ ጳውሎስ ጠቅሷል። (ዕብራውያን 12:1) ሄኖክ በዛሬው ጊዜ አብዛኞቻችን ከሚኖረን ዕድሜ ከሦስት እጥፍ በላይ ማለትም ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት በመልካም አኗኗሩ ጸንቶ እንዲመላለስ ያስቻለው እምነቱ ነው!

13. ሄኖክ ምን ዓይነት እምነት ነበረው?

13 ጳውሎስ “እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው” በማለት ስለ ሄኖክና ስለ ሌሎች ምሥክሮች እምነት ገልጿል። (ዕብራውያን 11:1) አዎን፣ እምነት ማለት በተስፋ የምንጠባበቃቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ መሆን ማለት ነው። እምነት ተስፋ የምናደርገው ነገር እውን ሆኖ እንዲታየን ከማድረጉ የተነሳ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ በምንሰጠው ነገር ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል። ሄኖክ የነበረው እንዲህ ያለ እምነት በዙሪያው ከነበረው ዓለም ተለይቶ ከአምላክ ጋር እንዲሄድ አስችሎታል።

14. የሄኖክ እምነት የተገነባው በምን ዓይነት ትክክለኛ እውቀት ላይ ሊሆን ይችላል?

14 እውነተኛ እምነት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። ሄኖክ ምን እውቀት ነበረው? (ሮሜ 10:14, 17፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4) በዔድን የአትክልት ሥፍራ ስለተፈጸሙት ነገሮች እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባትም በዔድን ገነት ውስጥ ኑሮ ምን ይመስል እንደነበረ ሰምቶ ይሆናል፤ እንዲሁም ሰዎች እንዳይገቡ ይከልከሉ እንጂ በእርሱም ዘመን ዔድን ገነት ሳትኖር አትቀርም። (ዘፍጥረት 3:23, 24) ከዚህም በላይ አምላክ የአዳም ዘሮች ምድርን እንዲሞሏትና መላዋን ፕላኔት መጀመሪያ እንደተፈጠረችው ገነት እንዲያስመስሏት ዓላማ እንዳለው ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በተጨማሪም ይሖዋ የሰይጣንን ራስ የሚቀጠቅጥና የእርሱ የማታለል ድርጊት ያስከተላቸውን አስከፊ መዘዞች ፈጽሞ የሚያስወግድ ዘር እንደሚያስገኝ የሰጠውን ተስፋ ከፍ አድርጎ ይመለከት እንደነበረ አያጠያይቅም። (ዘፍጥረት 3:15) በእርግጥም በይሁዳ መጽሐፍ ውሰጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ሄኖክ በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረው ቃል ይሖዋ የሰይጣንን ዘር እንደሚያጠፋ ይተነብያል። ሄኖክ እምነት ስለነበረው ይሖዋን ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ እንደሚሰጥ’ አምላክ አድርጎ ያመልከው እንደነበር እናውቃለን። (ዕብራውያን 11:6) ስለዚህ ሄኖክ ምንም እንኳን እኛ ያገኘነውን ያህል እውቀት ባይኖረውም ጠንካራ እምነት ለመገንባት መሠረት የሚሆን በቂ እውቀት ነበረው። እንዲህ ያለው እምነት ሁከት በነገሠበት ዘመን ጽኑ አቋሙን እንዲጠብቅ አስችሎታል።

የሄኖክን ምሳሌ ኮርጁ

15, 16. የሄኖክን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

15 እኛም ሁከት በነገሠበት በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ማስደሰት ስለምንፈልግ የሄኖክን ምሳሌ መከተል ይገባናል። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና የቀሰምነው እውቀት እንዳይጠፋብን መጠንቀቅ ይገባናል። ይሁን እንጂ ሌላም የሚያስፈልገን ነገር አለ። ይህ ትክክለኛ እውቀት አካሄዳችንን እንዲመራልን መፍቀድ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:101፤ 2 ጴጥሮስ 1:19) በአምላክ አስተሳሰብ መመራት ይገባናል፤ እንዲሁም በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ሁሉ እርሱን ለማስደሰት መጣጣር ያስፈልገናል።

16 በሄኖክ ዘመን ይሖዋን የሚያገለግል ሌላ ሰው እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም፤ ይሁንና ሄኖክ ብቻውን አሊያም ደግሞ ከአንድ አነስተኛ ቡድን ጋር ሆኖ አምላክን ያገለግል እንደነበር ግልጽ ነው። በዓለም ዙሪያ የእኛም ቁጥር በጣም ትንሽ ነው፤ ሆኖም ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ አያደርገንም። የሚቃወመን ማንም ቢሆን ይሖዋ ይደግፈናል። (ሮሜ 8:31) ሄኖክ ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች እንደሚጠፉ በድፍረት አስጠንቅቆ ነበር። እኛም ፌዝ፣ ተቃውሞና ስደት ቢያጋጥመንም ‘ይህንን የመንግሥት ወንጌል’ በድፍረት እንሰብካለን። (ማቴዎስ 24:14) ሄኖክ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች ያህል ረጅም ዕድሜ አልኖረም። የሆነ ሆኖ በዚያን ጊዜ በነበረው ዓለም ላይ ተስፋ አላደረገም። ትኩረቱን ከዚያ በሚበልጥ ነገር ላይ አድርጎ ነበር። (ዕብራውያን 11:10, 35) እኛም ትኩረታችንን በይሖዋ ዓላማ ፍጻሜ ላይ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ ምክንያት በዚህ ዓለም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ጥረት አናደርግም። (1 ቆሮንቶስ 7:31) ከዚህ ይልቅ በአንደኛ ደረጃ ጉልበታችንንና ሀብታችንን የምናውለው ለይሖዋ አገልግሎት ነው።

17. ሄኖክ ያልነበረው ምን እውቀት አለን? ስለዚህ ምን ማድረግ ይገባናል?

17 ሄኖክ፣ እንደሚመጣ ይሖዋ የተናገረለት ዘር አምላክ በፈቀደው ጊዜ እንደሚገለጥ እምነት ነበረው። አስቀድሞ የተነገረለት ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ቤዛውን በማቅረብ ለእኛም ሆነ እንደ ሄኖክ ላሉ የጥንት ታማኝ ምሥክሮች የዘላለም ሕይወት ለመውረስ የሚያስችል መንገድ ከከፈተ ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። አሁን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን ዙፋን ላይ ተቀምጦ ያለው ይህ ዘር ሰይጣንን ከሰማይ ወደ ምድር አባረረው፤ በዚህ ምክንያት በመላው ዓለም ላይ እየደረሰ ያለውን ሁከት በዓይናችን እያየን ነው። (ራእይ 12:12) አዎን፣ ሄኖክ ከነበረው እጅግ በጣም የሚበልጥ እውቀት አግኝተናል። ስለዚህ እርሱ የነበረው ዓይነት ጠንካራ እምነት ይኑረን። የምናደርገው ነገር በሙሉ ይሖዋ የሰጠን ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ጠንካራ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ይሁን። የምንኖረው ሁከት በነገሠበት ዘመን ቢሆንም ልክ እንደ ሄኖክ ከአምላክ ጋር እንሂድ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 220 አንቀጽ 6ን ተመልከት።

b ይሖዋ ሄኖስ ከኖረበት ዘመን በፊት ከአዳም ጋር ተነጋግሮ ነበር። አቤልም ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ለይሖዋ አቅርቧል። አልፎ ተርፎም አምላክ ቃየን በቅንዓት ተቆጥቶ ግድያ ከመፈጸሙ በፊት አነጋግሮታል። ስለዚህ ሰዎች “የእግዚአብሔርን ስም መጥራት” የጀመሩት ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ለየት ባለ መንገድ መሆን አለበት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው?

• ከአምላክ ጋር መሄድ የተሻለ አማራጭ የሆነው ለምንድን ነው?

• ሄኖክ ሁከት በነገሠበት ዘመንም እንኳን ከአምላክ ጋር ለመሄድ ያስቻለው ምንድን ነው?

• ሄኖክን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄኖክ በእምነት “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ”

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም በጥብቅ እናምናለን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በቀኝ በኩል ከበስተ ኋላ ያለችው ሴት:- FAO photo/B. Imevbore; እየወደቀ ያለው ሕንፃ:- San Hong R-C Picture Company