በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሜኖናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ

ሜኖናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ

ሜኖናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ

በኅዳር 2000 አንድ ቀን ጠዋት በቦሊቪያ የሚገኙ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን በትንሿ ቤታቸው መስኮት ወደ ውጪ ሲያዩ እንደነገሩ የለበሱ ወንዶችና ሴቶች በፍርሃት ተውጠው በበራቸው ላይ ቆመው ተመለከቱ። ሚስዮናውያኑ በሩን በከፈቱበት ጊዜ እንግዶቹ በመጀመሪያ የተናገሯቸው ቃላት “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማወቅ እንፈልጋለን” የሚሉ ነበሩ። ሰዎቹ ሜኖናውያን ሲሆኑ ወንዶቹ ቱታ ለብሰዋል፤ ሴቶቹ ደግሞ ጥቁር ሽርጥ አሸርጠዋል። እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩት በጀርመን ቀበሌኛ ነው። ፊታቸው ላይ ፍርሃት ይነበብ የነበረ ከመሆኑም በላይ የተከተላቸው ሰው መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ አሁንም አሁንም ይገላመጡ ነበር። እንዲህም ሆኖ ወደ ቤት ለመግባት ደረጃውን እየወጡ ሳሉ ከወጣቶቹ ወንዶች አንዱ “በአምላክ ስም የሚጠቀሙ ሰዎችን ማወቅ እፈልጋለሁ” በማለት ተናገረ።

እንግዶቹ ወደ ቤት ገብተው የሚቀማምሱት ነገር ሲቀርብላቸው መረጋጋት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የመጡት ርቀው ከሚገኙ ገለልተኛ የእርሻ ክልሎች ነው። ከዚያ በፊት ለስድስት ዓመት መጠበቂያ ግንብ መጽሔት በፖስታ ሲደርሳቸው ቆይቷል። “ምድር ገነት እንደምትሆን አንብበናል። ይህ እውነት ነው?” የሚል ጥያቄ አነሱ። የይሖዋ ምሥክሮቹም ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ አሳዩዋቸው። (ኢሳይያስ 11:9፤ ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:7, 13፤ ራእይ 21:3, 4) ከገበሬዎቹ አንዱ አብረውት ለነበሩት “አያችሁ! እውነት ነው። ምድር ገነት ትሆናለች” አለ። ሌሎቹም በተደጋጋሚ “እውነትን ያገኘን ይመስለኛል” ይሉ ነበር።

ሜኖናውያን እነማን ናቸው? ምንስ ብለው ያምናሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወደ 16ኛው መቶ ዘመን መለስ ብለን መመልከት አለብን።

ሜኖናውያን እነማን ናቸው?

በ1500ዎቹ ዓመታት አውሮፓ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ በሚናገራቸው ቋንቋዎች ለመተርጎምና ለማተም የተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎታቸው እንደገና እንዲቀሰቀስ አድርጎ ነበር። ማርቲን ሉተርና ሌሎች ለውጥ አራማጆች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸውን በርካታ ትምህርቶች ተቃውመዋል። ይሁንና አዲስ የተቋቋሙት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ብዙ ልማዶችን መከተላቸውን አላቆሙም ነበር። ለምሳሌ ያህል አብዛኞቹ እያንዳንዱ ሕፃን እንደተወለደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠመቅ እንዳለበት ያምኑ ነበር። ሆኖም እውነትን የማወቅ ዓላማ ይዘው መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አንድ ሰው የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን የሚችለው ከመጠመቁ በፊት ባገኘው እውቀት ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ ማድረግ ሲችል ብቻ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ እምነት የነበራቸው ቀናተኛ ሰባኪዎች በከተሞችና በመንደሮች እየተጓዙ በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምሩና ያጠምቁ ጀመር። በዚህ ምክንያት አናባብቲስቶች ማለትም “ለሁለተኛ ጊዜ የሚያጠምቁ” ተባሉ።

እውነትን ለማግኘት ባደረገው ፍለጋ የአናባብቲስቶችን እምነት የተቀበለው አንዱ ሰው፣ ቀደም ሲል በሰሜን ኔዘርላንድ በምትገኝ ቪትማርሰም የተባለች መንደር የካቶሊክ ቄስ የነበረው ሜኖ ሳይመንስ ነበር። ይህ ሰው በ1536 ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በማቋረጡ ምክንያት የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለ ሥልጣናት ያሳድዱት ጀመር። በ1542፣ የቅዱስ ሮማ ገዢ የነበረው ቻርልስ አምስተኛ ሳይቀር ሜኖን ላገኘ ሰው 100 ጊልደር እንደሚሸልም ቃል ገብቶ ነበር። የሆነ ሆኖ ሜኖ ጥቂት አናባብቲስቶችን በመሰብሰብ ጉባኤዎችን አቋቋመ። ብዙም ሳይቆይ እርሱና ተከታዮቹ ሜኖናውያን ተብለው ይጠሩ ጀመር።

በዘመናችን ያሉ ሜኖናውያን

ከጊዜ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜኖናውያን በስደት ምክንያት ከምዕራብ አውሮፓ ወደ ሰሜን አሜሪካ ጎረፉ። በዚያም እውነትን መፈለጋቸውን የመቀጠልና መልእክታቸውን ለበርካታ ሰዎች የመንገር አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ አያት ቅደመ አያቶቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና ለሕዝብ ለመመሥከር የነበራቸው ዓይነት ኃይለኛ ቅንዓት አልነበራቸውም። አብዛኞቹ ‘አምላክ ሥላሴ ነው፣’ ‘የሰው ነፍስ አትሞትም’ እና ‘ሲኦል ማቃጠያ ስፍራ ነው’ እንደሚሉት ባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶች በጥብቅ ያምኑ ነበር። (መክብብ 9:5፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ ማርቆስ 12:29) በዘመናችን የሚገኙት የሜኖናውያን ሚስዮናውያን ከወንጌላዊነት ይልቅ ሕክምናና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠቱ ላይ ያተኩራሉ።

በአሁኑ ጊዜ በ65 አገሮች ውስጥ 1,300,000 ገደማ የሚሆኑ ሜኖናውያን እንዳሉ ይገመታል። ይሁን እንጂ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በፊት ሜኖ ሳይመንስ ይል እንደነበረው በዘመናችን ያሉ ሜኖናውያንም አንድነት እንደሌላቸው በምሬት ይናገራሉ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስለተነሱት ግጭቶች በነበራቸው የተለያየ አመለካከት ምክንያት በመካከላቸው ከባድ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። በሰሜን አሜሪካ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሜኖናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ የሚያስጥስ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁንና አን ኢንትሮዳክሽን ቱ ሜኖናይት ሂስትሪ እንዲህ ይላል:- “በ1914፣ በምዕራብ አውሮፓ በሚገኙ የሜኖናውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በወታደራዊ አገልግሎት ያለመካፈሉ ጉዳይ በታሪክነቱ የሚወሳ ነገር ብቻ ሆኖ ነበር።” በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የሜኖናውያን ቡድኖች ይነስም ይብዛ ዘመናውያን ናቸው። ሌሎቹ ግን ልብሳቸውን እንኳ የሚቆልፉት በአዝራር ሳይሆን ጥንት አባቶቻቸው በሚቆልፉበት መንገድ ነው፤ እንዲሁም ወንዶች ጺማቸውን መላጨት አይኖርባቸውም ብለው ያምናሉ።

ከዘመናዊው ዓለም ለመለየት የቆረጡ ጥቂት የሜኖናውያን ቡድኖች ደግሞ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ለመኖር ሲሉ ማኅበረሰባቸውን ይዘው ያሉበት አገር መንግሥት ወደ ፈቀደላቸው ቦታዎች ሰፍረዋል። ለምሳሌ ያህል በቦሊቪያ 38,000 ገደማ የሚሆኑ ሜኖናውያን ርቀው በሚገኙ በርካታ ክልሎች ይኖራሉ፤ እያንዳንዱ መንደር የራሱ የሆነ የሥነ ምግባር ሕግ አለው። በአንዳንዶቹ መንደሮች ውስጥ መጓጓዝ የሚቻለው በፈረስና በጋሪ ብቻ ነው፤ መኪና መጠቀም አይፈቀድም። ሌሎች መንደሮች ውስጥ ራዲዮ ማዳመጥ፣ ቲቪ ማየትና ሙዚቃ መስማት ክልክል ነው። እንዲያውም በአንዳንዶቹ መንደሮች የሚኖሩበትን አገር ቋንቋ መማር ክልክል ነው። የአንዱ መንደር ነዋሪ “ሰባኪዎቹ ከቁጥጥራቸው ሥር እንዳንወጣ ለማድረግ ሲሉ ስፓንኛ ቋንቋ እንድንማር አይፈቅዱልንም” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ብዙዎቹ እንደተጨቆኑ ይሰማቸዋል፤ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ያገለን ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ደግሞ ከዚህ ማኅበረሰብ ተለይቶ ለማያውቅ ሰው ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ነገር ነው።

የእውነት ዘር የተዘራው እንዴት ነው?

እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ይኖር የነበረ ዮሃን የተባለ ሜኖናዊ ገበሬ ጎረቤቶቹ ቤት መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ያያል። ዮሃንና ቤተሰቦቹ ከካናዳ ወደ ሜክሲኮ ከዚያ ወደ ቦሊቪያ ተሰድደው የሄዱ ናቸው። እንዲህም ሆኖ ዮሃን ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመፈለግ የሚያስችለውን እርዳታ ለማግኘት ይመኝ ነበር። ጎረቤቶቹ መጽሔቱን እንዲያውሱት ጠየቃቸው።

ቆየት ብሎም ዮሃን የግብርና ምርቱን ለመሸጥ ከተማ ሲወጣ በገበያ ቦታ መጠበቂያ ግንብ በማበርከት ላይ ከነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘ። ይቺ እህት ጀርመንኛ ከሚናገር ሚስዮናዊ ወንድም ጋር እንዲገናኝ ካደረገችው በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ በፖስታ ቤት ይደርሰው ጀመር። እያንዳንዱ እትም እስኪቀዳደድ ድረስ በሚገባ ይጠና እንዲሁም ከአንዱ ቤተሰብ ወደ ሌላው ይተላለፍ ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ የተለያዩ ቤተሰቦች አንድ ላይ ይሰባሰቡና ጥቅሶችን እያወጡ በማንበብ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ መጠበቂያ ግንቡን ያጠኑ ነበር። ዮሃን በዓለም ዙሪያ በአንድነት የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች መሆን አለባቸው የሚል እምነት ነበረው። ይህ ሰው ከመሞቱ በፊት ለሚስቱና ለልጆቹ “ምንጊዜም ቢሆን መጠበቂያ ግንብ ማንበብ አለባችሁ። መጽሔቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ እንድትረዱ ያግዛችኋል” ብሏቸው ነበር።

አንዳንዶቹ የዮሃን ቤተሰብ አባላት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሯቸውን ነገሮች ለጎረቤቶቻቸው ይነግሩ ጀመር። “ምድር አትጠፋም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ገነት ያደርጋታል። እንዲሁም አምላክ ሰዎችን በሲኦል ውስጥ አያሠቃያቸውም” በማለት ይናገሩ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የዮሃን ቤተሰቦች እንዲህ እያሉ እንደሚሰብኩ የቤተ ክርስቲያን ሰባኪዎች ጆሮ ስለደረሰ መናገራቸውን ካላቆሙ እንደሚያወግዟቸው አስፈራሯቸው። አንድ ቀን ቤተሰቡ ተሰብስቦ ሜኖናውያን ሽማግሌዎች የሚያደርጉባቸውን ተጽዕኖ በተመለከተ እየተወያዩ ሳሉ አንዱ ወጣት እንዲህ ብሎ ተናገረ:- “ለምን በቤተ ክርስቲያናችን ሽማግሌዎች ላይ እንደምናጉረመርም አልገባኝም። እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤ ቢሆንም ምንም እርምጃ አልወሰድንም።” የወጣቱ አባት ልጁ በተናገራቸው ቃላት ልባቸው ተነካ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አሥር የቤተሰቡ አባላት በምስጢር የይሖዋ ምሥክሮችን ለመፈለግ ጉዞ አደረጉና ሚስዮናውያኑ ቤት ደረሱ።

በሚቀጥለው ቀን ሚስዮናውያኑ አዲስ ወደተዋወቋቸው ጓደኞቻቸው መንደር ሄዱ። በመንገዱ ላይ የሚታየው የሚስዮናውያኑ መኪና ብቻ ነበር። በፈረስ በሚጎተቱ ጋሪዎች መካከል መኪናቸውን በዝግታ እየነዱ በሚጓዙበት ጊዜ ከነዋሪዎቹ ጋር በግርምት ይተያዩ ነበር። ከዚያም የሁለት ቤተሰቦች አባላት ከሆኑ አሥር ሜኖናውያን ጋር አንድ ቤት ውስጥ ተሰበሰቡ።

በዚያን ዕለት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለማጥናት አራት ሰዓት ፈጅተዋል። a ገበሬዎቹ እያንዳንዱን አንቀጽ በሚያጠኑበት ጊዜ ከዚህ በፊት የማያውቋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሲመለከቱ የጥቅሶቹን ሐሳብ በትክክል ተረድተው እንደሆነ ለማረጋገጥ ይጥራሉ። ከእያንዳንዱ ጥያቄ በኋላ በርከት ላሉ ደቂቃዎች መጠበቅ ያስፈልግ ነበር፤ ምክንያቱም ሜኖናውያኑን ወክሎ የሚናገረው ሰው መልሱን በስፓንኛ ከመመለሱ በፊት ገበሬዎቹ በሰሜን ጀርመን አካባቢ በሚነገረው ጀርመንኛ ቋንቋ ይመካከራሉ። ዕለቱ ትልቅ ትዝታ ትቶ ያለፈ ነበር፤ ይሁንና የስደት ማዕበል መቀስቀሱ አልቀረም። ወደ አምስት መቶ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ሜኖ ሳይመንስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መፈለግ ሲጀምር አጋጥሞት የነበረውን ዓይነት ችግር መጋፈጥ ነበረባቸው።

ለእውነት ሲባል ችግሮችን መጋፈጥ

ከጥቂት ቀናት በኋላ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመወያየት ላይ ወደነበሩት የዮሃን ቤተሰቦች ሄደው እንደሚከተለው በማለት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጧቸው:- “የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችሁ መጥተው እንደነበር ሰምተናል። ተመልሰው እንዳይመጡ መከልከል አለባችሁ፤ ጽሑፎቻቸውንም አምጥታችሁ እንዲቃጠሉ ካላደረጋችሁ በስተቀር ትወገዛላችሁ።” በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠኑት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረ በመሆኑ ይህ ለእነርሱ ከባድ ፈተና ነው።

ከቤተሰቦቹ ራሶች አንዱ “እንዳላችሁት ማድረግ አንችልም። እነዚህ ሰዎች የመጡት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስተምሩን ነው” በማለት መልስ ሰጠ። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎቹ ምን አደረጉ? መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው ምክንያት አወገዟቸው! እንዴት ያለ የጭካኔ ድርጊት ነው። የመንደሩ አይብ ፋብሪካ ንብረት የሆነ ጋሪ የአንዱን ቤተሰብ ወተት ሳይወስድ ትቶ አለፈ፤ ይህም ብቸኛ የገቢ ምንጫቸው ተቋረጠ ማለት ነው። አንዱ የቤተሰብ ራስ ከሥራው ተባረረ። ሌላውም እንዲሁ ከመንደሩ መደብር እቃ እንዳይገዛ ከመከልከሉም በላይ የአሥር ዓመት ልጁ ከትምህርት ቤት ተባረረች። የአንዱ ወጣት ጎረቤቶች ደግሞ ከተወገዘ ባል ጋር መኖር የለባትም በሚል ሚስቱን ለመውሰድ ቤቱን ከብበው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩት ቤተሰቦች የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩባቸውም እንኳን እውነትን ለማግኘት የሚያደርጉትን ፍለጋ አላቋረጡም ነበር።

ሚስዮናውያኑ እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በየሳምንቱ በመኪናቸው ረጅም ጉዞ ማድረጋቸውን ቀጠሉ። እነዚህ ቤተሰቦች ጥናታቸው ምን ያህል አበረታች ሆኖ እንዳገኙት መገመት ይቻላል! አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት በፈረስና በጋሪ ለሁለት ሰዓት ተጉዘው በጥናቱ ላይ ይገኙ ነበር። ቤተሰቦቹ፣ አንዱ ሚስዮናዊ እንዲጸልይ የጋበዙበት ዕለት በጣም አስደሳች ነበር። በእነዚህ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩት ሜኖናውያን በጭራሽ ጮክ ብለው አይጸልዩም፤ በመሆኑም ከዚያን ጊዜ በፊት ሌላ ሰው እነርሱን ወክሎ ሲጸልይ ሰምተው አያውቁም። ወንዶቹ እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። በመንደሩ ሙዚቃ መስማት ፈጽሞ የተከለከለ ስለሆነ ሚስዮናውያኑ ቴፕ ይዘውላቸው ሲሄዱ ምን ያህል ብርቅ እንደሆነባቸው መገመት ትችላለህ! ውብ የሆኑት የመንግሥቱ ጣዕመ ዜማዎች በጣም ስላስደሰቷቸው ሁልጊዜ ከጥናታቸው በኋላ ለመዘመር ወሰኑ! እስቲ ያጋጠማቸውን አዲስ ሁኔታ እንዴት እንዳሳለፉ እንመልከት።

አፍቃሪ የወንድማማች ኅብረት

ቤተሰቦቹ ከማኅበረሰቡ ተለይተው የራሳቸውን አይብ ማምረት ጀመሩ። ሚስዮናውያኑም ገዢዎችን በማፈላለግ ይረዷቸው ነበር። በደቡብ አሜሪካ በሚገኝ የሜኖናውያን መንደር ያደገና ለብዙ ጊዜያት ይሖዋን ያገለገለ በሰሜን አሜሪካ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እነዚህ ቤተሰቦች እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ሲሰማ እነርሱን የመርዳት ከፍተኛ ጉጉት አደረበት። ስለ እነርሱ በሰማበት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሊያያቸው ወደ ቦሊቪያ ተጓዘ። ይህ ወንድም ከፍተኛ መንፈሳዊ ማበረታቻ ያካፈላቸው ከመሆኑም ሌላ አነስተኛ የጭነት መኪና እንዲገዙ ረዳቸው፤ መኪና መግዛታቸው በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘትና የእርሻ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማጓጓዝ ያስችላቸዋል።

አንዱ የቤተሰቡ አባል “ከማኅበረሰቡ ከተገለልን በኋላ ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ወደ መንግሥት አዳራሽ የምንሄደው ፊታችን ጭፍግግ ብሎ ነበር። የምንመለሰው ግን ፍልቅልቅ እያልን ነበር” በማለት ትዝታውን ተናግሯል። በዚያ አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ቢሆኑ በራሳቸው ተነሳሽነት እነዚህ ሰዎች ያጋጠማቸውን ችግር እንዲወጡ አስፈላጊውን እርዳት አድርገዋል። አንዳንዶቹ ጀርመንኛ የተማሩ ሲሆን ይህን ቋንቋ መናገር የሚችሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ከአውሮፓ ወደ ቦሊቪያ በመሄድ በጀርመንኛ ክርስቲያናዊ ስብሰባ እንዲደረግ እርዳታ አበርክተዋል። ብዙም ሳይቆይ የሜኖናውያን ማኅበረሰብ አባላት የነበሩ 14 ሰዎች ለሌሎች የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ጀመሩ።

ጥቅምት 12, 2001 ቀድሞ አናባብቲስት ከነበሩት ውስጥ አሥራ አንዱ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት በድጋሚ ተጠመቁ፤ ይህም ሜኖናውያኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚስዮናውያኑ ቤት ከሄዱ ከአንድ ዓመት ከማይበልጥ ጊዜ በኋላ መሆኑ ነው። ከዚያም በኋላ ተጨማሪ ሰዎች ተጠምቀዋል። “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስለተማርን ነጻ እንደወጣ ባሪያ የሆንን ያህል ተሰምቶናል” በማለት አንዱ አስተያየት ሰጥቷል። ሌላው ደግሞ “በርካታ ሜኖናውያን በማኅበረሰቡ መካከል ፍቅር ባለመኖሩ ያማርራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ግን እርስ በርሳቸው ይተሳሰባሉ። በመካከላቸው ስሆን ደህንነት ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል። አንተም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል ፍለጋ እያደረግክ ከሆነ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲረዳህ ከጠየቅከው እንዲሁም እነዚህ ቤተሰቦች እንዳደረጉት እምነትና ድፍረት ካሳየህ አንተም ሊሳካልህና ደስታ ልታገኝ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጀርመንኛ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማግኘታቸው ተደስተዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙዚቃ ክልክል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠኑ በኋላ ይዘምራሉ