በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለን

በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለን

በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለን

“አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” Nw] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክያስ 4:5

1. በኖኅ ዘመን ሰዎች በሥነ ምግባር ረገድ እንዴት ነበሩ? ኖኅ የተለየ የነበረው እንዴት ነው?

 አካሄዱን ከአምላክ ጋር እንዳደረገ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው ሄኖክ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኖኅ ነው። ዘገባው “ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:9) በጥቅሉ ሲታይ በኖኅ ዘመን ሰዎች ከንጹሕ አምልኮ ርቀው ነበር። መጥፎ የነበረው የጊዜው ሁኔታ የባሰ እንዲከፋ ያደረገው ደግሞ ከሃዲ መላእክት ከተፈጥሯቸው ውጪ ሴቶችን በማግባት “በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ” ኔፊሊም የሚባሉ ልጆችን መውለዳቸው ነው። ስለዚህ ምድር በዓመጽ መሞላቷ ምንም አያስገርምም! (ዘፍጥረት 6:2, 4, 11) የሆነ ሆኖ ኖኅ ጻድቅ መሆኑን ከማረጋገጡም በተጨማሪ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) አምላክ፣ ኖኅ ሕይወቱን የሚያተርፍበት መርከብ እንዲያዘጋጅ በነገረው ጊዜ “ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22) በእርግጥም ኖኅ ከአምላክ ጋር ሄዷል።

2, 3. ኖኅ በዛሬው ጊዜ ላለነው ምን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ ምሥክሮችን በዘረዘረ ጊዜ ስለ ኖኅም እንዲህ ብሏል:- “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።” (ዕብራውያን 11:7) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ኖኅ የይሖዋ ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ ስለነበረ የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ሀብቱን ሰውቷል። ዛሬም በተመሳሳይ ይህ ዓለም ለሚከፍትላቸው አጋጣሚዎች ጀርባቸውን ሰጥተው ይሖዋን ለመታዘዝ ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን የሚሰዉ ብዙ ሰዎች አሉ። የእነዚህ ሰዎች እምነት የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት የሚያድን በመሆኑ ላቅ ያለ ዋጋ አለው።—ሉቃስ 16:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16

3 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው እንደ ኖኅ ቅድመ አያት እንደ ሄኖክ ሁሉ ኖኅና ቤተሰቦቹ በእምነት ለመመላለስ ከብዷቸው መሆን አለበት። ልክ እንደ ሄኖክ ዘመን በኖኅ ዘመንም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፤ ታማኝነታቸው የተረጋገጠውና ከጥፋት ውኃ የተረፉት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ኖኅ ዓመጸኛ በነበረውና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ ጽድቅን ይሰብክ ነበር። ከዚህም በላይ እርሱና ቤተሰቦቹ የእንጨት መርከብ በመሥራት ዓለም አቀፍ ለሆነው የጥፋት ውኃ ተዘጋጅተው ነበር፤ ይሁንና ከዚያ በፊት ዝናብ ሲዘንብ ያየ ማንም ሰው አልነበረም። በመሆኑም ይመለከቷቸው የነበሩት ሰዎች ነገሩ እንግዳ ሳይሆንባቸው አልቀረም።

4. ኢየሱስ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች የፈጸሙትን የትኛውን ስህተት ነው?

4 የሚገርመው ነገር ዓመጽ፣ የሐሰት ሃይማኖትና መጥፎ ሥነ ምግባር አሳፋሪ ድርጊቶች ቢሆኑም ኢየሱስ ስለ ኖኅ ዘመን በተናገረበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች አልጠቀሰም። ኢየሱስ ስህተት እንደሆነ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው ሕዝቡ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ እርምጃ አለመውሰዱን ነበር። “ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ” ኢየሱስ ተናግሯል። መብላትና መጠጣት፣ ማግባትና መጋባት ስህተት ነው? ሰዎቹ ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው የተለመደውን ኑሮ ይመሩ ነበር! ነገር ግን የጥፋት ውኃ መምጫው ተቃርቦ ነበር፤ ኖኅም ጽድቅን ይሰብክ ነበር። የሚነግራቸው ነገርና አኗኗሩ ማስጠንቀቂያ ሊሆናቸው ይገባ የነበረ ቢሆንም ‘እስከዚያ ጊዜ ድረስ ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ አጥለቅልቋቸዋል።’—ማቴዎስ 24:38, 39

5. ኖኅና ቤተሰቡ ምን ዓይነት ባሕርያትን ማዳበር አስፈልጓቸው ነበር?

5 ያንን ዘመን መለስ ብለን ስናስብ ኖኅ ጥበብ ያለበት ኑሮ ይመራ እንደነበር ማየት እንችላለን። ይሁን እንጂ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት ጊዜያት ከሌሎች የተለዩ ሆኖ መኖር ድፍረት ይጠይቅ ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ትልቅ መርከብ ለመገንባትና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን ወደ መርከቡ ለማስገባት ጠንካራ እምነት አስፈልጓቸዋል። ከእነዚህ ጥቂት ታማኞች መካከል አንዳንዶቹ የሰዎችን ትኩረት ሳይስቡ እንደሌሎቹ ሰዎች የተለመደውን ኑሮ ለመኖር የተመኙበት ጊዜ ይኖር ይሆን? እንዲህ ያለ ሐሳብ መጥቶባቸው ሊሆን ቢችልም ጽኑ አቋማቸውን አላላሉም። ኖኅ የነበረው እምነት፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ማናችንም ከሚኖረን ዕድሜ በላይ ቆይቶ ከመጣው የጥፋት ውኃ ለመትረፍ አስችሎታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የተለመደውን ዓይነት ኑሮ ሲመሩ የነበሩትንና በምን ዓይነት ጊዜ ውስጥ እየኖሩ እንዳሉ ያላስተዋሉትን ሰዎች ሁሉ የቅጣት ፍርድ ፈጽሞባቸዋል።

ምድር እንደገና በዓመጽ ተሞላች

6. ከጥፋት ውኃ በኋላም ቢሆን ምን ያልተወገደ ነገር ነበር?

6 የጥፋት ውኃው ከደረቀ በኋላ የሰው ልጅ አዲስ ኑሮ ጀመረ። ይሁን እንጂ ከዚያም በኋላ ቢሆን የሰው ልጅ ፍጹም ስላልሆነ “ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” መሆኑ አልቀረም። (ዘፍጥረት 8:21) ከዚህም በላይ አጋንንት እንደ ቀድሟቸው ሥጋ አይልበሱ እንጂ በሰው ዘር ላይ ተጽዕኖ ማድረጋቸውን አላቆሙም ነበር። አምላክ የለሽ የሆነው ዓለም “በክፉው ሥር እንደ ሆነ” ወዲያውኑ የታየ ከመሆኑም በተጨማሪ ልክ እንደዛሬው ሁሉ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ” መታገል ነበረባቸው።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ኤፌሶን 6:11, 12

7. ከጥፋት ውኃ በኋላ በዓለም ላይ ዓመጽ እየተባባሰ የመጣው እንዴት ነው?

7 ከጥፋት ውኃ በኋላ፣ ቢያንስ ቢያንስ ከናምሩድ ዘመን ጀምሮ ምድር በድጋሚ በዓመጽ ተሞላች። የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የቴክኖሎጂው መሻሻል ዓመጹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንዲሄድ አድርጓል። ቀደም ባሉት ዘመናት የሰው ልጅ ከሰይፍ፣ ከጦር፣ ከደጋንና ከቀስት እንዲሁም ከሰረገላ ያለፈ መሣሪያ አልነበረውም። ከዚያ በኋላ ነፍጥና መድፍ የተፈለሰፉ ሲሆን በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ደግሞ ጠመንጃና ሌሎች እጅግ የተራቀቁ ከባድ የጦር መሣሪያዎች ብቅ ብለዋል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ እንደ አውሮፕላን፣ ታንክ፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከብና የመርዝ ጋዝ የመሰሉ አስፈሪ የሆኑ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ታይተውበታል። በጦርነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ መሣሪያዎች ተጨፍጭፈዋል። ይህ የተከሰተው እንዲያው በአጋጣሚ ነው? በጭራሽ።

8. ራእይ 6:1-4 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በ1914 የአምላክ መንግሥት ገዢ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ‘የጌታ ቀን’ ጀምሯል። (ራእይ 1:10) ኢየሱስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ድል እያደረገ እንደሚጋልብ ንጉሥ ሆኖ እንደታየ በራእይ መጽሐፍ ላይ ተዘግቧል። በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን የተለያየ ዓይነት መቅሰፍት የሚወክሉ ሌሎች ጋላቢዎችም ይከተሉት ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ፍም በሚመስል ቀይ ፈረስ ላይ የሚጋልብ ፈረሰኛ ሲሆን ለእርሱም “ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድና ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅም ሰይፍ ተሰጠው።” (ራእይ 6:1-4) ይህ ፈረስና ጋላቢው ጦርነትን ሲያመለክቱ ትልቁ ሰይፍ ደግሞ በኃይለኛ የጦር መሣሪያዎች የሚካሄዱት የዘመናችን ጦርነቶች ታይቶ በማይታወቅ መጠን እያደረሱ ያሉትን ውድመት ያመለክታል። በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች መካከል በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ለማጥፋት የሚያስችሉ የኑክሌር መሣሪያዎች፣ በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ዒላማን ለመምታት የሚያስችሉ ኑክሌር ተሸካሚ ሮኬቶች እንዲሁም በጣም የተራቀቁ ጅምላ ጨራሽ ኬሚካላዊና ባዮሎጂያዊ መሣሪያዎች ይገኙበታል።

ለይሖዋ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን

9. ያለንበት ዘመን ከጥፋት ውኃ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ በኖኅ ዘመን የሰው ልጆችን ያጠፋው ክፉ ሰዎች በኔፊሊሞች ገፋፊነት ከባድ ዓመጽ በመፈጸማቸው ምክንያት ነበር። ዛሬስ በምድር ላይ የሚፈጸመው ነገር በዚያ ዘመን ከነበረው ያንሳል? በፍጹም አያንስም! በተጨማሪም በኖኅ ዘመን እንደነበረው በዛሬው ጊዜ ሰዎች የዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸውን በማከናወን የተለመደውን ኑሮ ለመምራት ይሯሯጣሉ፤ እየተሰጡ ያሉትንም ማስጠንቀቂያዎች ሰምተው እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም። (ሉቃስ 17:26, 27) ይሖዋ በድጋሚ የሰው ልጆችን አያጠፋም ብለን የምንጠራጠርበት ምክንያት ይኖራል? በጭራሽ።

10. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ በተደጋጋሚ ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ብቸኛው የጥበብ አካሄድ ምንድን ነው?

10 ሄኖክ የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በዘመናችን ስለሚደርሰው ጥፋት ተንብዮአል። (ይሁዳ 14, 15) ኢየሱስም ስለመጪው “ታላቅ መከራ” ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:21) ሌሎች ነቢያትም እንዲሁ ስለዚያ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። (ሕዝቅኤል 38:18-23፤ ዳንኤል 12:1፤ ኢዩኤል 2:31, 32) እንዲሁም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የመጨረሻውን ጥፋት በሚመለከት ሕያው መግለጫ ተሰጥቷል። (ራእይ 19:11-21) እኛም በግለሰብ ደረጃ የኖኅን ምሳሌ በመኮረጅ በትጋት ጽድቅን እንሰብካለን። ለይሖዋ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን፣ ጎረቤቶቻችንም እንዲሁ እንዲያደርጉ በፍቅር ተነሳስተን እንረዳቸዋለን። በመሆኑም ልክ እንደ ኖኅ ከአምላክ ጋር እንሄዳለን። ሕይወትን የሚፈልግ ማንም ሰው ከአምላክ ጋር መሄዱን መቀጠል እንዳለበት የተረጋገጠ ነው። የሚያስጨንቅ ነገር በየዕለቱ እያጋጠመንም እንኳን እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ዓላማ እንደሚፈጸም ጠንካራ እምነት በማዳበር ነው።—ዕብራውያን 11:6

ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን ከአምላክ ጋር መሄዳችሁን ቀጥሉ

11. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን የምንኮርጀው በምን መንገድ ነው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘መንገዱን’ ይከተሉ እንደነበር ተገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 9:2) መላ አኗኗራቸው በይሖዋና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ላይ ያተኮረ ነበር። ጌታቸው የሄደበትን ፈለግ ተከትለዋል። ዛሬም ታማኝ ክርስቲያኖች እንዲሁ ያደርጋሉ።

12. ኢየሱስ በርካታ ሰዎችን በተአምር ከመገበ በኋላ ምን ተከሰተ?

12 የእምነት አስፈላጊነት በኢየሱስ አገልግሎት ወቅት በተፈጸመ አንድ ክንውን ላይ ታይቷል። ኢየሱስ አንድ ጊዜ 5,000 የሚያክሉ ወንዶችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መገበ። ሰዎቹ በሁኔታው ተደነቁ፣ በጣምም ተደሰቱ። ይሁን እንጂ ቀጥሎ የሆነውን ነገር ልብ በል:- “ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ፣ ‘ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው’ አሉ። ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።” (ዮሐንስ 6:10-15) በዚያው ምሽት ወደ ሌላ ቦታ ተጓዘ። ኢየሱስ ንጉሥ ለመሆን አለመፈለጉ ብዙዎችን ቅር ሳያሰኝ አልቀረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ለንግሥና የሚያበቃ ጥበብና የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ይሁን እንጂ ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ ይሖዋ የቀጠረው ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ከዚህም በላይ የኢየሱስ መንግሥት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለም።

13, 14. ብዙዎች ምን አመለካከት እንደነበራቸው አሳይተዋል? እምነታቸውስ የተፈተነው እንዴት ነው?

13 የሆነ ሆኖ ሰዎቹ ኢየሱስን ለመከተል ቆርጠው ስለነበር ዮሐንስ እንደገለጸው “ከባሕሩ ማዶ” አገኙት። ኢየሱስን ለማንገሥ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸው እያወቁ ለምን ተከተሉት? ብዙዎቹ ይሖዋ በሙሴ ዘመን በምድረ በዳ ስላደረጋቸው ቁሳዊ ዝግጅቶች በቀጥታ በመናገር አመለካከታቸው ሥጋዊ እንደሆነ አሳይተዋል። ኢየሱስ ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል የፈለጉ ይመስላል። ኢየሱስ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ መሆኑን በማስተዋሉ አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት መንፈሳዊ እውነት ያስተምራቸው ጀመር። (ዮሐንስ 6:17, 24, 25, 30, 31, 35-40) አንዳንዶቹ ግን በተለይ የሚከተለውን ምሳሌ ሲነግራቸው አጉረመረሙ:- “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”—ዮሐንስ 6:53, 54

14 ብዙውን ጊዜ የኢየሱስ ምሳሌዎች ሰዎች በእርግጥ ከአምላክ ጋር ለመሄድ መፈለግ አለመፈለጋቸውን እንዲያሳዩ የሚያደርጉ ነበሩ። ይህም ምሳሌ ከዚህ የተለየ ዓላማ አልነበረውም። በመሆኑም ተቃውሞ አስነስቷል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ ‘ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?’ አሉ።” ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት መንፈሳዊ ትርጉም ለመረዳት እንዲሞክሩ ሲያበረታታቸው እንዲህ አለ:- “መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው።” አብዛኞቹ ሰዎች ግን ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ዘገባው እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።”—ዮሐንስ 6:60, 63, 66

15. አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ምን ዓይነት ትክክለኛ አመለካከት ነበራቸው?

15 ይሁን እንጂ ወደኋላ የተመለሱት ሁሉም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አልነበሩም። ታማኞቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ እንዳልተረዱት አይካድም። ቢሆንም በእርሱ ላይ የነበራቸው እምነት አልቀነሰም። ከታማኞቹ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ የሆነው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት የሌሎቹንም ስሜት ገልጿል። (ዮሐንስ 6:68) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ የሚሆን አስተሳሰብ ነው!

16. በምን መንገድ ልንፈተን እንችላለን? ምንስ ዓይነት ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር አለብን?

16 እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ተከታዮች ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እኛ እንዳሰብነው በፍጥነት ባለመፈጸሙ ቅር ይለን ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው በሚታተሙ ጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡት ማብራሪያዎች ለመረዳት የሚያስቸግሩ እንደሆኑ ሊሰማን ይችላል። እንዲሁም የክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ባሕርይ ያበሳጨን ይሆናል። ታዲያ በእነዚህ ወይም ተመሳሳይ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ከአምላክ ጋር መሄዳችንን ብናቆም ትክክል ይሆናል? በፍጹም ትክክል አይሆንም! ኢየሱስን ከመከተል ወደኋላ ያፈገፈጉት ደቀ መዛሙርት ሥጋዊ አስተሳሰብ እንደነበራቸው ታይቷል። እኛም እንደነርሱ እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል።

“ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም”

17. ከአምላክ ጋር መሄዳችንን እንድንቀጥል የሚረዳን ምንድን ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” እያለ በግልጽ ይነግረናል። (ኢሳይያስ 30:21) የአምላክን ቃል መታዘዛችን ‘ለአካሄዳችን እንድንጠነቀቅ’ ይረዳናል። (ኤፌሶን 5:15 NW) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና ባጠናናቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ‘በእውነት መመላለሳችንን እንድንቀጥል’ እገዛ ያደርግልናል። (3 ዮሐንስ 3) በእርግጥም ኢየሱስ እንዳለው “መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም።” እርምጃችንን ለማቅናት የሚረዳ አስተማማኝ መመሪያ ሊሆነን የሚችለው ከይሖዋ ቃል፣ ከመንፈሱና ከድርጅቱ የሚመጣው መንፈሳዊ መመሪያ ብቻ ነው።

18. (ሀ) አንዳንዶች ምን ጥበብ የጎደለው ድርጊት ይፈጽማሉ? (ለ) እኛስ እንዴት ያለ እምነት መኮትኮት አለብን?

18 ዛሬ በሥጋዊ አመለካከት ምክንያት ወይም የጠበቁት ነገር ሳይፈጸምላቸው በመቅረቱ ቅር ተሰኝተው ወደኋላ ያሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይህ ዓለም ሊሰጥ የሚችለውን ሁሉ ለማግኘት ይፈልጋሉ። የጥድፊያ ስሜታቸውን በማጣታቸው ‘ነቅተው መጠበቅ’ እንደማያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ጉዳዮች ከማስቀደም ይልቅ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ ግቦችን መከታተል ይመርጣሉ። (ማቴዎስ 24:42) እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው። “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል። (ዕብራውያን 10:39) እንደ ሄኖክና እንደ ኖኅ ሁሉ እኛም ሁከት በነገሠበት ዘመን የምንኖር ብንሆንም ልክ እንደ እነርሱ ከአምላክ ጋር የመሄድ አጋጣሚ ተከፍቶልናል። በዚህ አጋጣሚ ከተጠቀምን የይሖዋ ዓላማ ሲፈጸም፣ ክፋት ሲወገድና ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ሲመጣ የማየት የተረጋገጠ ተስፋ ይኖረናል። እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው!

19. ሚክያስ የእውነተኛ አምላኪዎችን ሁኔታ የገለጸው እንዴት ነው?

19 ነቢዩ ሚክያስ በመንፈስ ተነሳስቶ አሕዛብ “በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ” በማለት ተናግሮ ነበር። ከዚያም ስለ ራሱና ስለ ሌሎች ታማኝ አምላኪዎች ሲናገር “እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን” ብሏል። (ሚክያስ 4:5) የአንተም ቁርጥ ውሳኔ ይህ ከሆነ የምንኖርበት ዘመን ምንም ያህል ሁከት የነገሠበት ቢሆን ከይሖዋ ጋር ተጣበቅ። (ያዕቆብ 4:8) እያንዳንዳችን አሁንና ከዘላለም እስከ ዘላለም ከአምላካችን ከይሖዋ ጋር ለመሄድ ልባዊ ፍላጎት ይኑረን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የኖኅን ዘመንና የእኛን ዘመን የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ኖኅና ቤተሰቦቹ ምን ዓይነት አካሄድ ተከትለዋል? እምነታቸውንስ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

• የኢየሱስ ተከታዮች ምን የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው ታይቷል?

• እውነተኛ ክርስቲያኖች ለማድረግ የቆረጡት ነገር ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ሰዎች በዛሬው ጊዜ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ተወጥረዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንደመሆናችን መጠን ‘ወደ ኋላ ከሚያፈገፍጉት አይደለንም’