በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ መሆን ያዋጣል?

ታማኝ መሆን ያዋጣል?

ታማኝ መሆን ያዋጣል?

ሙሉጌታ ጓደኛውን ታደሰን “አሁን የምትሠራበት ድርጅት በቂ ገንዘብ ስለማይከፍልህ ከዚያ መውጣት አለብህ። a ሌላ ቦታ ብትገባ እኮ ከዚህ የተሻለ ደሞዝ ማግኘት ትችላለህ” አለው።

ታደሰ “ያልከው ትክክል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እዚህ ድርጅት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ስሠራ ቆይቻለሁ። ሰዎቹም ብዙ ውለታ ውለውልኛል፤ ስለዚህ ለእነርሱ ታማኝ መሆን እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብሎ መለሰለት።

ሙሉጌታም በመቀጠል “ታማኝነት በጣም ጥሩ ባሕርይ ነው። የሆነ ሆኖ ታማኝ ልሁን ብለህ ብዙ ገንዘብ እያጣህ ነው!” አለው።

ሙሉጌታ ያለው ነገር ትክክል ነው። ለአንድ ሰው ታማኝ መሆን አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ ሊያስወጣ ይችላል። ከዚህም ባሻገር ጊዜን፣ ጉልበትንና ስሜትን መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። ታማኝ ለመሆን ይህን ያህል መሥዋዕት መክፈል አስፈላጊ ነው?

በጣም የሚወደድ ብዙ ጊዜ ግን የማይተገበር

በጀርመን የሚገኘው የአለንስባክ የምርምር ተቋም ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት ታማኝነት ተፈላጊ ባሕርይ መሆኑን ተናግረዋል። ይኸው ተቋም ከ18 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶች ላይ ያደረገው ሌላ ጥናት እንደሚጠቁመው ከተጠየቁት ሦስት ወጣቶች መካከል ሁለቱ ታማኝነትን ተወዳጅ ባሕርይ አድርገው ይመለከቱታል።

ብዙ ሰዎች የታማኝነትን ባሕርይ ቢወዱትም ታማኝ ሆኖ መገኘት ግን ይከብዳቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በብዙ የአውሮፓ አገሮች የሚገኙ ባልና ሚስቶች ወይም የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ለሌላው እምብዛም ታማኝ ሆነው አይገኙም። ጓደኛሞችም አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርሳቸው ታማኝ አይደሉም። ቀደም ባሉት ጊዜያት ቀጣሪና ተቀጣሪን ወይም ሻጭና ደንበኛን እንደ ሰንሰለት ያስተሳስር የነበረው ታማኝነት ደግሞ ይበልጡኑ ጠፍቷል። ለምን?

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሕይወታቸው በሩጫ የተሞላ መሆኑ ያሉባቸውን ግዴታዎች በታማኝነት ለመወጣት የሚያስፈልገው ጊዜም ሆነ የመንፈስ ጥንካሬ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት አንድ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሰዎች ከዚያ በኋላ ለሌሎች ታማኝ መሆን ያስፈራቸዋል። ሌሎች ደግሞ ታማኝነት የሚጠይቅ ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት አይፈልጉ ይሆናል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ታማኝነት በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በተግባር የማይውል ባሕርይ ነው። በዚህም ምክንያት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን ተገቢ ነው:- ታማኝ መሆን ያዋጣል? የሚያዋጣ ከሆነ፣ ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው? በየትኞቹስ መንገዶች? ታማኝ መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ያሉት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ታማኝነት በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በተግባር የማይውል ባሕርይ ነው