በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ መሆን ጥቅም አለው

ታማኝ መሆን ጥቅም አለው

ታማኝ መሆን ጥቅም አለው

በአንዳንድ አገሮች የሚገኙ ልጆች በጓደኛቸው ሹራብ ላይ ጭጎጎት ለጥፈው የሚፈጠረውን ሁኔታ እያዩ መሳቅ ያስደስታቸዋል። ጭጎጎቶቹ በሹራቡ ላይ ሙጭጭ ብለው ስለሚጣበቁ ልጁ የፈለገውን ቢያደርግ ለምሳሌ ቢሄድ፣ ቢሮጥ፣ ቢወራጭ ወይም ቢዘል እንኳ ከላዩ ላይ አይራገፉም። ከልብሱ ላይ ማስለቀቅ የሚቻለው አንድ በአንድ በመልቀም ብቻ ነው። ይህ ለልጆች ትልቅ ጨዋታ ነው።

እርግጥ ልብሱ ላይ ጭጎጎት ቢለጠፍ ደስ የሚለው ሰው አይኖርም፤ ሆኖም ሁላችንም ለማለት ይቻላል ጭጎጎት ባለው የመጣበቅ ችሎታ መደነቃችን አይቀርም። ታማኝ የሆነም ሰው ተመሳሳይ ባሕርይ አለው። ከአንድ ሰው ጋር ያለው ዝምድና ዘላቂ እንዲሆን በጣም ተቀራርቦ ይኖራል። ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜ እንኳ ከግለሰቡ ጋር በመጣበቅ ዝምድናው የሚያስከትልበትን ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ በታማኝነት ይወጣል። “ታማኝነት” የሚለው ቃል እንደ እውነተኝነት፣ ሐቀኝነትና አፍቃሪነት ያሉትን መልካም ባሕርያት እንድናስታውስ ያደርገናል። ሰዎች ታማኝ ሲሆኑልህ በጣም ትደሰት ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አንተ ለሰዎች ታማኝ ለመሆን የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ አለህ? ከሆነ፣ ታማኝ መሆን ያለብህ ለማን ነው?

ታማኝነት በትዳር ውስጥ መሠረታዊ ነገር ነው

ታማኝነት በጣም የሚያስፈልግበት አንደኛው ቦታ ትዳር ነው፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ ባለ ትዳሮች ታማኝ አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነው። ለጋብቻ ቃለ መሐላቸው ታማኝ የሚሆኑ ባልና ሚስት በሌላ አነጋገር ሳይለያዩ አብረው የሚኖሩና አንዳቸው የሌላውን ጥቅም ለማስቀደም ጥረት የሚያደርጉ ባለ ትዳሮች ደስታና ሰላም ለማግኘት የሚረዳቸውን ትልቅ እርምጃ ወስደዋል ለማለት ይቻላል። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች በተፈጥሯቸው ከሌላው ታማኝነት የመጠበቅም ሆነ ታማኝነት የማሳየት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ነው። የአዳምና የሔዋን ጋብቻ በዔድን የአትክልት ስፍራ ሲከናወን አምላክ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል” ብሎ ነበር። ይህ መመሪያ ለሚስትም ይሠራል፤ እርሷም ከባልዋ ጋር መጣመር ወይም መጣበቅ ይኖርባታል። ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑና እርስ በርስ እንዲደጋገፉ ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:3-9

እርግጥ ይህ የሆነው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ነበር። ይህ ሲባል ታዲያ በዛሬው ጊዜ በትዳር ውስጥ ታማኝ መሆን ጊዜ አልፎበታል ማለት ነው? የአብዛኛው ሰው መልስ አይደለም የሚል ነው። በጀርመን የሚገኙ ተመራማሪዎች እንዳመለከቱት፣ ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ለትዳር ታማኝ መሆን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በወንዶችና በሴቶች ዘንድ በጣም ተፈላጊ ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ አንድ ሌላ ጥናት ተደርጎ ነበር። ወንዶቹ ሴቶች ቢኖሯቸው በጣም የሚያስደስታቸውን አምስት ባሕርያት ጽፈው የሰጡ ሲሆን ሴቶቹም እንዲሁ ወንዶች ቢኖሯቸው ይበልጥ የሚያስደስቷቸውን አምስት ግሩም ባሕርያት ዘርዝረው ነበር። ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ በጣም የወደዱት ባሕርይ ታማኝነት ነበር።

አዎን፣ የተሳካ ትዳር የሚያስፈልገውን ጠንካራ መሠረት ለመገንባት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ታማኝነት ነው። በፊተኛው ርዕስ ላይ እንዳየነው ግን ታማኝነት በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በተግባር የማይውል ባሕርይ ነው። ለምሳሌ፣ በብዙ አገሮች የሚታየው ከፍተኛ የፍቺ ቁጥር ታማኝነትን ማጉደል እንደተስፋፋ ማስረጃ ይሆናል። ታዲያ ባልና ሚስቶች ይህን አዝማሚያ ተቋቁመው አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ሆነው መጽናት የሚችሉት እንዴት ነው?

ታማኝነት ትዳርን ዘላቂ ያደርጋል

ታማኝነት በትዳር ውስጥ የሚታየው ባልና ሚስቱ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ፈልገው ሲጠቀሙበት ነው። ለአብነት ያህል፣ “የኔ” ከማለት ይልቅ “የኛ” ማለትም “ጓደኞቻችን፣” “ልጆቻችን፣” “ቤታችን፣” “ተሞክሯችን” እና የመሳሰሉትን እያሉ መናገር አብዛኛውን ጊዜ የተሻለ ይሆናል። ቤትን፣ ሥራን፣ ልጅ ማሳደግን፣ መዝናኛን፣ እረፍትን ወይም የሃይማኖት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ አንድ ባልና ሚስት እቅድ ሲያወጡም ሆነ ውሳኔ ሲያደርጉ አንዳቸው የሌላውን ስሜትና ዝንባሌ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 11:14፤ 15:22

እያንዳንዱ ባለ ትዳር የትዳር ጓደኛው ተፈላጊና ተወዳጅ እንደሆነ እንዲሰማው ሲያደርግ ታማኝነት በትዳር ውስጥ ግልጽ ሆኖ ይታያል። አንድ ባለ ትዳር ከሌላ ተቃራኒ ጾታ ጋር ከልክ በላይ ከተቀራረበ የትዳር ጓደኛው ስጋት ያድርባታል። መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶች ‘ከልጅነት ሚስቶቻቸው ጋር’ እንዲጣበቁ ይመክራል። አንድ ባል ከሚስቱ በስተቀር የሌሎች ሴቶችን አድናቆት ለማግኘት መመኘት አይኖርበትም። ከሌላ ሴት ጋር መባለግ እንደሌለበት እሙን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል” በማለት ያስጠነቅቃል። ታማኝነት የሚጠይቀው ከፍተኛ የአቋም ደረጃ ከሚስትም ይጠበቃል።—ምሳሌ 5:18፤ 6:32

በትዳር ውስጥ ታማኝ ለመሆን መጣር ጥቅም አለው? በእርግጥ አለው። የትዳር ቁርኝቱን ይበልጥ ጠንካራና ዘላቂ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ በግለሰብ ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ባል ለሚስቱ ደህንነት የሚያስፈልገውን ሁሉ በታማኝነት ሲያደርግ የመረጋጋት ስሜት ስለሚሰማት ያሏት ግሩም ባሕርያት ጎልተው ይወጣሉ። ለባልም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ባል ለሚስቱ ታማኝ ለመሆን ቁርጥ አቋም መውሰዱ በማንኛውም የሕይወቱ ዘርፍ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ይረዳዋል።

አንድ ባልና ሚስት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው እንኳ ታማኝ መሆናቸው የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። በሌላ በኩል ታማኝነት በሌለበት ትዳር ውስጥ ችግር ሲያጋጥም አብዛኛውን ጊዜ የሚወሰደው እርምጃ መለያየት አሊያም ፍቺ ይሆናል። እንዲህ ያለው እርምጃ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ብዙውን ጊዜ ሌላ ጣጣ ያስከትላል። ታዋቂ የሆነ አንድ የፋሽን አማካሪ በ1980ዎቹ ዓመታት ሚስትና ልጆቹን ትቶ ሄዶ ነበር። ታዲያ ነጠላ መሆኑ ደስታ አስገኝቶለታል? ከቤተሰብ በመለያየቱ ያተረፈው ነገር ቢኖር “ብቸኝነትና መረበሽ እንዲሁም [ልጆቹን] ‘ደህና እደሩ’ ብሎ ይተኛ የነበረበትን ጊዜ በማሰብ እንቅልፍ አጥቶ ማደር” እንደሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ ተናግሯል።

በወላጆችና በልጆች መካከል ሊኖር የሚገባው ታማኝነት

ወላጆች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ በሚሆኑበት ጊዜ ልጆቻቸው ይህንኑ ባሕርይ ለመውረስ ያላቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። ታማኝና አፍቃሪ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ትልቅ ከሆኑ በኋላ የትዳር ጓደኞቻቸውንም ይሁን በዕድሜ መግፋት ምክንያት የደከሙ ወላጆቻቸውን በኃላፊነት መንከባከብ ቀላል ይሆንላቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8

ይህ ሲባል ግን ሁልጊዜ ተረጂ የሚሆኑት ወላጆች ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ልጆችም በታማኝነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚያስገድድ ሁኔታ ያጋጥማቸው ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ኸርበርት እና ጌርትሩት የተባሉ ባልና ሚስት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ልጃቸው ዲትማር ከሕፃንነቱ አንስቶ መስኪዩላር ዲስትሮፊ በተባለ ጡንቻን የሚያዳክም በሽታ ይሰቃይ ነበር። ዲትማር በኅዳር 2002 ከመሞቱ በፊት ባሉት ሰባት ዓመታት ሌት ተቀን ክትትል ያስፈልገው ነበር። ወላጆቹም በፍቅር ተነሳስተው ለልጁ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ አድርገውለታል። እንዲያውም ለልጃቸው እንክብካቤ ለማድረግ ሲሉ የሕክምና መሣሪያዎችን ቤታቸው እስከ ማስገጠምና የሕክምና ሥልጠና እስከ መውሰድ ደርሰዋል። በእርግጥም ይህ በቤተሰብ ውስጥ ሊታይ ለሚገባው ታማኝነት ግሩም ምሳሌ ነው!

ታማኝነት ለጓደኛሞች በጣም ያስፈልጋል

ብርጅት የተባለች አንዲት ሴት “አንድ ሰው ትዳር ሳይኖረው ደስተኛ ሊሆን ይችላል፤ ያለ ጓደኛ ደስተኛ መሆን ግን በጣም ከባድ ነው” ስትል ተናግራለች። ምናልባት አንተም በዚህ አባባል ትስማማ ይሆናል። ያገባህም ሆንክ ያላገባህ ጓደኛህ ታማኝ መሆኑን ስታይ ልብህ ይረካል፣ ሕይወትህም ይለመልማል። እርግጥ ነው፣ ያገባህ ከሆንክ የቅርብ ጓደኛህ ሚስትህ ልትሆን ይገባል።

የምታውቀው ሰው ሁሉ ጓደኛህ ነው ማለት አይደለም። ጎረቤቶቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን እናውቅ ይሆናል። እውነተኛ ጓደኝነት ጊዜን፣ ጉልበትንና ስሜትን መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። የአንድ ሰው ጓደኛ መሆን ክብር ነው። ጓደኝነት ጥቅሞች አሉት፤ ይሁን እንጂ ኃላፊነት ጭምር ያስከትላል።

ከጓደኞቻችን ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረጋችን ወሳኝ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የግድ መነጋገር የሚያስፈልግበት ወቅት ይኖራል። ብርጅት “ከሁለት አንዳችን ችግር ካጋጠመን በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ እንደዋወላለን። ጓደኛዬ ለችግሬ እንደምትደርስልኝና ልታዳምጠኝ ፈቃደኛ መሆኗን ማወቄ በጣም ያጽናናኛል” ብላለች። ጓደኝነትን ርቀት አይገድበውም። ጌርዳ እና ሄልጋ የተባሉ ጓደኛሞች በሺህ በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው የሚኖሩ መሆናቸው ከ35 ለሚበልጡ ዓመታት ጥሩ ጓደኛሞች ከመሆን አላገዳቸውም። ጌርዳ “አስደሳች ሆኑም አልሆኑ ስላጋጠሙን ነገሮች እንዲሁም የልባችንን በየጊዜው እንጻጻፋለን። ከሄልጋ የሚደርሰኝ ደብዳቤ ከመጠን በላይ ያስደስተኛል። ስሜታችን ሁሉ ተመሳሳይ ነው” ብላለች።

ጓደኝነት እየጠነከረ እንዲሄድ ታማኝ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው። የክህደት ድርጊት የረጅም ጊዜን ወዳጅነት ሳይቀር ሊያፈርስ ይችላል። ጓደኛሞች ምስጢር እንኳ ሳይቀር ማውራታቸው የተለመደ ነው። ጓደኛሞች ይሳቅብኛል ወይም ምስጢሬ ይባክንብኛል ብለው ሳይፈሩ የልባቸውን አውጥተው ይጨዋወታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ይገልጻል።—ምሳሌ 17:17

የምንይዛቸው ጓደኞች በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችንና በተግባራችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ከእኛ ጋር የሚመሳሰል የሕይወት አቅጣጫ ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጓደኛ የምታደርጋቸው ሰዎች እንዳንተው ዓይነት እምነት፣ የሥነ ምግባር አቋም እንዲሁም ትክክልና ስህተት ስለሆነው ጉዳይ ተመሳሳይ የአቋም ደረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ አትዘንጋ። እንዲህ ያሉት ወዳጆች ወደ ግብህ እንድትደርስ ይረዱሃል። ታዲያ በሥነ ምግባር አቋሙ ከማይመስልህ ሰው ጋር መቀራረብ የምትፈልግበት ምን ምክንያት ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል” ብሎ በመናገር ጥሩ ጓደኞች መምረጥ ያለውን ጠቀሜታ ገልጿል።—ምሳሌ 13:20

ታማኝነትን መማር ይቻላል

አንድ ልጅ በሰው ልብስ ላይ ጭጎጎት እየለጠፈ መጫወትን አንዴ ካወቀ ደግሞ ደጋግሞ ሊያደርገው ይፈልግ ይሆናል። ታማኝ ስለሆነም ሰው ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ታማኝነትን ባሳየን ቁጥር ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ እየቀለለን ይመጣል። አንድ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በቤተሰብ ውስጥ ታማኝ መሆንን ከተማረ፣ በኋላ ላይ ታማኝነት የሚንጸባረቅበት ጓደኝነት መመሥረት አይከብደውም። እንዲህ ያለው ጠንካራና ዘላቂ ወዳጅነት ውሎ አድሮ በትዳር ውስጥ ለሚኖረው ታማኝነት መንገድ ይጠርጋል። በተጨማሪም ትልቅ ዋጋ ለሚሰጠው ወዳጅነት ታማኝ እንዲሆን ይረዳዋል።

ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ይሖዋ አምላክን በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን መውደድ እንዳለብን የሚገልጸው እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:30) በሌላ አነጋገር ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ታማኝ ልንሆንለት ይገባል ማለት ነው። ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆናችን ብዙ በረከት ያስገኝልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በሚመለከት “እግዚአብሔር ታማኝ ነው” ስለሚል ፈጽሞ ፊቱን አያዞርብንም ወይም አያሳዝነንም። (1 ቆሮንቶስ 10:13) በእርግጥም ለአምላክ ታማኝ መሆን የዘላለም በረከት ያስገኛል።—1 ዮሐንስ 2:17

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጓደኛህ ታማኝ መሆኑን ስታይ ልብህ ይረካል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታማኝ የሆኑ የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው ይተሳሰባሉ