በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ

የአምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ

የአምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ

በ1971 በጀርመንኛ በታተመው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። a ሆኖም መለኮታዊውን ስም ለመጠቀም ይህ የመጀመሪያው ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። ከ500 ዓመታት በፊት ዮሐን ኢክ የሚባል ታዋቂ የሮማ ካቶሊክ የሃይማኖት ምሑር የተረጎመው ጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተጠቀመ ይገመታል።

ዮሐን ኢክ በ1486 በደቡባዊው የጀርመን ክፍል ተወለደ። በ24 ዓመቱ በኢንግልሽታት ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆነ ሲሆን በ1543 እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስም በዚሁ ማዕረግ አገልግሏል። ኢክና ማርቲን ሉተር ይኖሩ የነበረው በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከመሆኑም በላይ ለተወሰነ ጊዜ ጓደኛሞች ነበሩ። ሆኖም የኋላ ኋላ ሉተር የተሐድሶ እንቅስቃሴ ዋና አቀንቃኝ ሲሆን ኢክ ግን ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥብቅና መቆሙን ቀጠለ።

በኋላ ላይ የባቫሪያው መስፍን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጀርመንኛ እንዲተረጉም ኢክን አዘዙት፤ ይህም ትርጉም በ1537 ለሕትመት በቃ። ኪሪችላይሸስ ሃንድላክሲከን እንደሚለው ከሆነ የኢክ ትርጉም የጥንቱን ቅጂ በጥብቅ የተከተለ ሲሆን “እስካሁን ካለው የበለጠ እውቅናም ሊሰጠው ይገባል።” በዚህ ትርጉም ላይ ዘፀአት 6:3 እንደሚከተለው ተቀምጧል:- “ሁሉን የሚችል አምላክ ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ እና ለያዕቆብ የተገለጥሁላቸው ጌታ ነኝ፤ ነገር ግን አዶናይ በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውም።” ለጥቅሱ ያሰፈረው የኅዳግ ማስታወሻ “አዶናይ ይሖዋ የተባለው ስም” ይላል። በጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ የግል ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ እንደሆነ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ያምናሉ።

ይሁንና የአምላክ የግል ስም ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲታወቅና በሥራ ላይ ሲውል ቆይቷል። “ይሖዋ” የሚለው ስም በቀዳሚነት የተዘገበው በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዘዳግም 6:4) የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ኢየሱስ የአምላክን ስም እንዳሳወቀ የተናገረው ሐሳብ በግሪክኛ ቋንቋ ተመዝግቧል። (ዮሐንስ 17:6) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህ ስም በበርካታ ቋንቋዎች ታትሟል። መዝሙር 83:18 በቅርቡ ፍጻሜውን ሲያገኝ ደግሞ ስሙ ይሖዋ የሆነው እሱ ብቻ በምድር ላይ ሉዓላዊ እንደሆነ ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። ይህ ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝኛ የታተመው በ1961 ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰነው ክፍል ከ50 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዘፀአት 6:3 ላይ ለሚገኘው ለይሖዋ ስም የኅዳግ ማስታወሻ ያሰፈረውና የ1558 እትም የሆነው የኢክ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም