በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

“እርሱ ብቻ ኢመዋቲ ነው” እንዲሁም “እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም” እንደሚሉት ያሉት ሐረጎች የሚያመለክቱት ይሖዋ አምላክን ሳይሆን ኢየሱስን ነው ለማለት የሚያስችል ምን መሠረት አለ?

ሐዋርያው ጳውሎስ “ያም መገለጥ፣ የተባረከውና ብቻውን ገዥ የሆነው የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ . . . በራሱ ጊዜ የሚያሳየው ነው፤ እርሱ ብቻ ኢመዋቲ ነው፤ ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም” ሲል ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16

ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ‘“እርሱ ብቻ ኢመዋቲ ነው፣” “ብቻውን ገዥ የሆነው” እንዲሁም “እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም” የሚሉት አገላለጾች ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ በስተቀር ማንን ሊያመለክቱ ይችላሉ?’ የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ቃላት ይሖዋን ለመግለጽ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ሆኖም ጳውሎስ በ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16 ላይ እየተናገረ ያለው ስለ ኢየሱስ መሆኑን በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ በግልጽ ያሳያል።

ጳውሎስ በቁጥር 14 መጀመሪያ ላይ ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ’ ጠቅሷል። (1 ጢሞቴዎስ 6:14) በመሆኑም ጳውሎስ ቁጥር 15 ላይ “ያም መገለጥ፣ የተባረከውና ብቻውን ገዥ የሆነው የነገሥታት ንጉሥ፤ የጌቶችም ጌታ . . . በራሱ ጊዜ የሚያሳየው ነው” ሲል የጻፈው የይሖዋ አምላክን ሳይሆን የኢየሱስን መገለጥ ለማመልከት ነው። ታዲያ “ብቻውን ገዥ” የተባለው ማን ነው? ጳውሎስ ገዥ ብሎ የጠቀሰው ኢየሱስን ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይመስላል። ለምን? ጳውሎስ ኢየሱስን ያወዳደረው ከሰብዓዊ ገዢዎች ጋር እንደሆነ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ በግልጽ ያሳያል። በእርግጥም ጳውሎስ እንደጻፈው ኢየሱስ “የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ” ነው። a ከእነዚህ ሰብዓዊ ነገሥታት ጋር ሲወዳደር ኢየሱስ “ብቻውን ገዥ” ነው። ለእርሱም ‘ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጥቶታል፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦችም ይሰግዱለታል።’ (ዳንኤል 7:14) ማንኛውም ሰብዓዊ ገዥ እንዲህ የመሰለ መብት ሊኖረው አይችልም!

“እርሱ ብቻ ኢመዋቲ ነው” ስለሚሉት ቃላትስ ምን ለማለት ይቻላል? እዚህም ላይ እየተነጻጸሩ ያሉት ኢየሱስና ሰብዓዊ ነገሥታት ናቸው። ከኢየሱስ በስተቀር ያለመሞት ባሕርይ ተሰጥቶኛል ሊል የሚችል ምድራዊ ገዥ የለም። ጳውሎስ “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጒልበት አይኖረውም” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 6:9) ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የማይሞት ሕይወት እንደተሰጠው የተገለጸው ኢየሱስ ነው። በእርግጥም ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የማይጠፋ ሕይወት ያገኘው ኢየሱስ ብቻ ነበር።

ከዚህም በላይ ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት ኢየሱስ ያለመሞት ባሕርይ ተላብሶ ስለነበር ‘ይህ ባሕርይ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው’ ቢል ስሕተት ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። ይሁንና ጳውሎስ ከምድራዊ ገዥዎች ጋር በማወዳደር ኢየሱስ ብቻ የማይሞት እንደሆነ ተናግሯል።

በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም” መባሉ በእርግጥ ትክክል ነው። እውነት ነው፣ በመንፈስ የተቀቡ ደቀ መዛሙርቱ ከሞቱና እነርሱም መንፈሳዊ ኣካል ይዘው ወደ ሰማይ ካረጉ በኋላ ኢየሱስን ያዩታል። (ዮሐንስ 17:24) ሆኖም ማንኛውም በምድር ላይ የሚኖር ሰው ኢየሱስን በክብራማ ቦታው ላይ ሆኖ ማየት አይችልም። ስለሆነም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳና ካረገ በኋላ እርሱን ያየ “ማንም የለም” ተብሎ መገለጹ ተገቢ ነው።

በ⁠1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16 ላይ ያለው መግለጫ ላይ ላዩን ሲታይ የሚናገረው ስለ አምላክ ሊመስል ይችላል። ይሁንና በጥቅሱ ዙርያ ያለው ሐሳብ ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ ጥቅሶች ጋር ተዳምሮ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ⁠1 ቆሮንቶስ 8:5, 6፤ በ⁠ራእይ 17:12, 14 እና ራእይ 19:16 ላይም ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ተመሳሳይ አገላለጾች ይገኛሉ።