በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ወታደር በመሆን መጽናት

የክርስቶስ ወታደር በመሆን መጽናት

የሕይወት ታሪክ

የክርስቶስ ወታደር በመሆን መጽናት

ዩሪ ካፕቶላ እንደተናገረው

“በእርግጥ እምነት እንዳለህ አሁን ተረድቻለሁ!” እነዚህ ቃላት የተሰነዘሩት በፍጹም ካልጠበቅሁት ሰው ነበር። ይህን የተናገረው አንድ የሩሲያ የጦር መኮንን ሲሆን ለእኔም በተገቢው ጊዜ የተለገሰ ማበረታቻ ሆኖልኛል። በወቅቱ የረጅም ጊዜ እስር ይጠብቀኝ ስለነበር ይሖዋ እንዲረዳኝ ከልብ ጸለይኩ። ጽናትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የብዙ ዓመታት ትግል ይጠብቀኝ ነበር።

የተወለድኩት ጥቅምት 19, 1962 ሲሆን ያደግኩት ደግሞ በምዕራብ ዩክሬን ነበር። በዚሁ ዓመት እንደ እኔው ዩሪ የሚባለው አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝ። ብዙም ሳይቆይ በመንደሪቱ ውስጥ የመጀመሪያው የይሖዋ አምላኪ ሆነ። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወሙ የነበሩት ባለ ሥልጣናት አባቴ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሚገባ ያውቁ ነበር።

ያም ሆኖ ብዙዎቹ ጎረቤቶቻችን ወላጆቼ በነበራቸው ክርስቲያናዊ ባሕርያትና ለሌሎች በሚያሳዩት አሳቢነት ምክንያት ያከብሯቸው ነበር። ወላጆቼ ገና ከልጅነታችን ጀምረው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በእኔና በሦስቱ እህቶቼ ልብ ውስጥ የአምላክን ፍቅር ለመትከል ይጥሩ ነበር። ይህም በትምህርት ቤት የሚደርሱብኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድቋቋም ረድቶኛል። አንደኛው ፈተና ያጋጠመኝ ተማሪዎች ሁሉ ‘የሌኒን የጥቅምት ልጆች’ መሆናቸውን የሚያሳውቅ መለያ ባጅ እንዲያደርጉ በተጠየቁበት ጊዜ ነበር። በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ የተነሳ ይህንን ባጅ ስለማላደርግ ከሌሎች ልጆች ተለይቼ እታይ ነበር።—ዮሐንስ 6:15፤ 17:16

የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ደግሞ ሁሉም ተማሪዎች ‘ወጣት አቅኚዎች’ ተብሎ የሚጠራው የኮሚኒስት ወጣት ማኅበር አባል እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ነበር። አንድ ቀን የክፍላችን ተማሪዎች በሙሉ ለማኅበሩ አባልነት ምዝገባ ሥነ ሥርዓት ወደ ትምህርት ቤቱ ሜዳ ተወሰድን። ፌዝና ተግሳጽ ይከተለኛል ብዬ ስላሰብኩ በጣም ፈራሁ። ከእኔ በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች ከቤት ያመጡትን የወጣት አቅኚዎች መለያ የሆነውን አዲስ ቀይ ያንገት ልብስ ይዘዋል። ከዚያም በትምህርት ቤታችን ርዕሰ መምህር፣ በአስተማሪዎቻችንና በክፍል ከእኛ የሚበልጡ ተማሪዎች ፊት ተሰለፍን። ትልልቆቹ ተማሪዎች ቀዩን ጨርቅ አንገታችን ላይ እንዲያስሩ ሲነገራቸው ማንም እንደማያየኝ ተስፋ በማድረግ አንገቴን ደፍቼ መሬት መሬቱን ማየት ጀመርኩ።

ሩቅ ወደሆኑ እስር ቤቶች ተወሰድኩ

አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ የተነሳ የሦስት ዓመት እስራት ተበየነብኝ። (ኢሳይያስ 2:4) የመጀመሪያውን የእስር ዓመት ያሳለፍኩት በዩክሬን፣ ቪንትስካያ አውራጃ ባለችው የትሩዱቮይ ከተማ ነበር። በዚያም 30 ከሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት ችዬ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ አንዳችን ከሌላው ጋር እንዳንገናኝ በማሰብ ሁለት ሁለት አድርገው የተለያየ የሥራ ምድብ ሰጡን።

በነሐሴ 1982 ሌሎች እስረኞችን ጨምሮ እኔና ኤድዋርድ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለእስረኞች የተዘጋጀ ፉርጎ ባለው ባቡር ላይ ተጭነን ወደ ሰሜናዊ ዩራል ተራሮች ተወሰድን። በጣም በሚሞቅና ትፍግፍግ ባለ ሁኔታ ተጉዘን ከስምንት ቀናት በኋላ ፕሪምስካያ አውራጃ ወደሚገኘው ሶሊካመሰክ እስር ቤት ደረስን። ከዚያም እኔና ኤድዋርድ በተለያየ ክፍል ውስጥ ታሰርን። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ አሁንም በስተ ሰሜን አቅጣጫ በክራስኖቪሺርስኪ ክልል ወደምትገኘው ቫዮልስ ወደምትባል መንደር ተወሰድኩ።

መጓጓዣችን ወደ ሥፍራው የደረሰው እኩለ ሌሊት ላይ ስለነበር አካባቢው በድቅድቅ ጨለማ ተውጧል። አንድ ባለ ሥልጣን እኔንና አብረውኝ የነበሩትን ሌሎች እስረኞች በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ጀልባ ተሳፍረን ወንዝ እንድንሻገር አዘዘን። ይሁንና እንኳን ጀልባው ወንዙም አይታየንም ነበር! ያም ሆኖ እንደምንም ዳብሰን ጀልባውን ማግኘትና እየፈራንም ቢሆን ወንዙን ማቋረጥ ቻልን። ወንዙን ከተሻገርን በኋላ በአቅራቢያው ባለ ኮረብታ ላይ ወደሚታይ መብራት አቀናን፤ በዚያም ጥቂት ድንኳኖችን አገኘን። ይህ እንግዲህ አዲሱ መኖሪያችን መሆኑ ነው። እኔ እኖርበት የነበረው ድንኳን ከሌሎች ጋር ሲወዳደር በመጠኑ ሰፋ ያለ ሲሆን በድንኳኑ ውስጥ 30 የሚሆኑ ሌሎች እስረኞችም ነበሩ። በክረምት ወቅት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ስለሚደርስ የምንኖርበት ድንኳን እምብዛም አይረዳንም ነበር። ዋናው ሥራችን ዛፍ መቁረጥ ቢሆንም እኔ ግን ለእስረኞች የሚሆን ጎጆ ከሚሠሩት ጋር ተመደብኩ።

በሰፈርንበት ገለልተኛ ቦታ መንፈሳዊ ምግብ ደረሰ

በሰፈራ ጣቢያው ውስጥ ከእኔ ሌላ የይሖዋ ምሥክር አልነበረም፤ ያም ሆኖ ይሖዋ አልተወኝም። አንድ ቀን በምዕራብ ዩክሬን ከምትኖረው እናቴ የተላከ አንድ ጥቅልል ደረሰኝ። ጠባቂው ጥቅልሉን በፈታው ጊዜ በመጀመሪያ ዓይኑ ውስጥ የገባው የተላከልኝ ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። እርሱም መጽሐፍ ቅዱሱን አንስቶ ገጾቹን መገላለጥ ጀመረ። ይህን መንፈሳዊ ሀብት ከመወረስ ለማዳን ምን ማለት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ። ጠባቂው “ይህ ምንድን ነው?” ሲል በቁጣ ጠየቀኝ። ምን እንደምመልስ እንኳ በቅጡ ሳላስብ በአቅራቢያችን ቆሞ የነበረ አንድ ተቆጣጣሪ “እሱማ፣ መዝገበ ቃላት ነው!” ሲል መለሰለት፤ እኔ ግን ትንፍሽ አላልኩም። (መክብብ 3:7) ከዚያም ተቆጣጣሪው ቀሪውን እቃ ከፈተሸ በኋላ ውድ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ ሁሉንም አስረከበኝ። እኔም በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ከተላከልኝ ለውዝ ላይ ጥቂት ሰጠሁት። የዚህ ጥቅልል መድረስ ይሖዋ እንዳልተወኝ እንድገነዘብ ረዳኝ። በእነዚህ ወቅቶች ሁሉ የይሖዋ እንክብካቤ ያልተለየኝ ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ፍላጎቴን አሟልቶልኛል።—ዕብራውያን 13:5

ያለማሰለስ መስበክ

ከጥቂት ወራት በኋላ 400 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ካለ አንድ ወንድም ደብዳቤ ሲደርሰኝ በጣም ተደነቅሁ። ደብዳቤው ወንድም አንድ ፍላጎት ያለው ሰው እንዳነጋገረና ምናልባትም ይህ ሰው እኔ የምኖርበት ካምፕ ውስጥ ሊኖር ስለሚችል ፈልጌ እንዳገኘው የሚገልጽ ነበር። የሚላኩልን ደብዳቤዎች ሳንሱር ይደረጉ ስለነበር እንዲህ ዓይነቱን ነገር በግልጽ መጻፍ ጥበብ አልነበረም። ስለሆነም አንድ ባለ ሥልጣን ወደ ቢሮው አስጠርቶ እንዳልሰብክ በጥብቅ ካስጠነቀቀኝ በኋላ እምነቴን ለሌሎች ማካፈል እንደማቆም በሚገልጽ አንድ ሰነድ ላይ እንድፈርም አዘዘኝ። እኔም ሁሉም ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስለሚያውቅ እንዲህ ዓይነቱን ሰነድ የመፈረሙ አስፈላጊነት እንዳልገባኝ ገለጽኩለት። ሌሎች እስረኞችም ቢሆኑ የታሰርኩበትን ምክንያት ለማወቅ መጠየቃቸው እንደማይቀር ከነገርኩት በኋላ ‘በዚህ ጊዜ ምን ልበላቸው?’ ስል ጠየቅሁት። (የሐዋርያት ሥራ 4:20) ባለ ሥልጣኑ ሊያስፈራራኝ እንዳልቻለ ሲገነዘብ ከዓይኑ ሊያርቀኝ ወሰነ። በመሆኑም ወደ ሌላ ካምፕ ተላክሁ።

የተላክሁት 200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ቫያ የተባለች መንደር ነበር። በሥፍራው የነበረው ተቆጣጣሪ ክርስቲያናዊ አቋሜን በማክበር ከውትድርና አገልግሎት ጋር ግንኙነት የሌለው ሥራ ላይ መደበኝ። መጀመሪያ ላይ አናጺ ቀጥሎም የኤሌትሪክ ሠራተኛ ሆንኩ። ሆኖም እነዚህም ሥራዎች የራሳቸው የሆነ ችግር ነበራቸው። በአንድ ወቅት ላይ መሣሪያዎቼን ይዤ ወደ መንደሪቱ መዝናኛ ክበብ እንድሄድ ተነገረኝ። እዚያም ስደርስ በክበቡ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች እኔን በማየታቸው ተደሰቱ። የተለያዩ ወታደራዊ አርማዎችን እንዲያደምቁ ታሰበው የተዘጋጁት መብራቶች በትክክል ባለ መሥራታቸው ተቸግረው ነበር። ወታደሮች የቀዩ ጦር ዓመታዊ ክብረ በዓልን ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ ስለነበር ችግሩን ለማስተካከል እንድረዳቸው ጠየቁኝ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ በጸሎት ካሰብኩ በኋላ እንዲህ ዓይነት ሥራ መሥራት እንደማልችል ነገርኳቸው። ከዚያም መሣሪያዎቼን ሰጥቻቸው ሄድኩ። ያደረግሁት ነገር ለምክትል ዲሬክተሩ ሪፖርት ተደረገ፤ የሚገርመው ምክትል ዲሬክተሩ የቀረበብኝን ክስ ካዳመጠ በኋላ “ይህን በማድረጉ አከብረዋለሁ። የራሱ የሆነ አቋም ያለው ሰው ነው” ሲል መለሰላቸው።

ካልጠበቅሁት ሰው ማበረታቻ አገኘሁ

በሰኔ 8, 1984 ልክ በታሰርኩ በሦስት ዓመቴ ከእስር ተለቀቅሁ። ወደ ዩክሬን እንደተመለስኩ ሚሊሻዎች ዘንድ በመሄድ ታስሬ እንደነበር መመዝገብ ነበረብኝ። ባለ ሥልጣናቱ በስድስት ወር ውስጥ እንደገና ለፍርድ መቅረቤ ስለማይቀር አውራጃውን ጨርሶ ብለቅ የተሻለ እንደሚሆን ነገሩኝ። ስለሆነም ዩክሬንን ለቅቄ ወጣሁ፤ ብዙም ሳይቆይ በላትቪያ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። በዚያም ለተወሰኑ ጊዜያት በዋና ከተማው በሪጋ እና በአካባቢው ካሉ አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ወንድሞች ጋር አብሬ ማገልገልና መሰብሰብ ቻልኩ። ሆኖም ከአንድ ዓመት በኋላ ለወታደራዊ አገልግሎት እንድመለመል በድጋሚ ጥሪ ደረሰኝ። በዚህ ጊዜ በምልመላ ቢሮ ውስጥ ለነበረው ባለ ሥልጣን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኔን ከዚህ በፊት እንዳሳወቅሁ ነገርኩት። በምላሹም “ምን እያደረግህ እንደሆነ በእርግጥ ታውቀዋለህ? ለሌተና ኮሎኔሉ ምን እንደምትል እስቲ እናያለን!” ሲል ጮኸብኝ።

ከዚያም ሁለተኛ ፎቅ ላይ በሚገኝ ረጅም ጠረጴዛ ባለው አንድ ክፍል ውስጥ ወደተቀመጡት ሌተና ኮሎኔል ወሰደኝ። ኮሎኔሉ ያለኝን አቋም ስገልጽ በጥሞና ካዳመጡኝ በኋላ የምልመላ ኮሚቴ ፊት ከመቅረቤ በፊት ውሳኔዬን ለመለወጥ የሚያስችል ጊዜ እንዳለኝ ነገሩኝ። የሌተና ኮሎኔሉን ቢሮ ለቅቀን ስንወጣ ቀደም ሲል ተቆጥቶኝ የነበረው ባለ ሥልጣን “በእርግጥ እምነት እንዳለህ አሁን ተረድቻለሁ!” አለኝ። በወታደራዊ ምልመላ ኮሚቴ ፊት በመቅረብ የገለልተኝነት አቋሜን በድጋሚ ካረጋገጥኩ በኋላ ለጊዜው እንድሄድ ፈቀዱልኝ።

በወቅቱ የምኖረው በኪራይ ቤት ውስጥ ነበር። አንድ ምሽት ላይ የቤቴ በር በቀስታ ሲንኳኳ ሰማሁ። በሩን ስከፍት አንድ ሙሉ ልብስ የለበሰና ቦርሳ የያዘ ሰው ደጃፌ ላይ ቆሞ አገኘሁ። ሰውየው “የደህንነት ሠራተኛ ነኝ። ችግር እንደገጠመህና ችሎት ፊት ልትቀርብ መሆኑን አውቄያለሁ” ሲል ራሱን አስተዋወቀኝ። እኔም “አዎን ልክ ነህ” ስል መለስኩለት። ቀጠል አድርጎም “ለእኛ የምትሠራልን ከሆነ ልንረዳህ እንችላለን” አለኝ። ምላሼም “በፍጹም አላደርገውም፤ ለክርስቲያናዊ እምነቶቼ ታማኝ መሆን እሻለሁ” የሚል ነበር። እኔን ለማሳመን ሌላ ምንም ተጨማሪ ጥረት ሳያደርግ ካለሁበት ጥሎኝ ሄደ።

በድጋሚ ብታሰርም መስበኬን ቀጥያለሁ

በነሐሴ 26, 1986 የሪጋ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ከጉልበት ሥራ ጋር የአራት ዓመት እስራት ፈረደብኝ፤ ከዚያም ወደ ሪጋ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወሰድኩ። በአንድ ሰፊ ክፍል ውስጥ ከሌሎች 40 እስረኞች ጋር አብሬ ታሰርኩ። እኔም ለእያንዳንዱ እስረኛ ለመመሥከር ጥረት አደርግ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በአምላክ እናምናለን ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ያፌዙ ነበር። የኋላ ኋላ ሰዎቹ በቡድን ተከፋፍለው እንደሚሰባሰቡ አስተዋልኩ። ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ የቡድኖቹ መሪዎች በጽሑፍ ባይሰፍሩም እንኳ መተዳደሪያ ደንቦቻቸውን ስለማልከተል መስበክ እንደማይፈቀድልኝ ነገሩኝ። እኔም በዚሁ ምክንያት እንደታሰርኩና የምመራበት ሌላ ዓይነት ሕግ እንዳለኝ ገለጽኩላቸው።

ከዚያም በጥንቃቄ መስበኬን ቀጠልኩ፤ ይህም መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘትና ከአራቱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አስቻለኝ። በውይይታችን ወቅት መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ያሰፍሩ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ በኤሌትሪክ ሠራተኛነት እንዳገለግል ተመድቤ ቫልማይራ ወደሚገኝ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ካምፕ ተላክሁ። በዚያም ለአንድ የኤሌትሪክ ባለ ሙያ መጽሐፍ ቅዱስን አስጠና ጀመር፤ ከአራት ዓመት በኋላ ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቅቷል።

በመጋቢት 24, 1988 ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበት ከነበረው ካምፕ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሰፈራ ጣቢያ ተዛወርኩ። የተሻለ ነፃነት ማግኘት ስለቻልኩ ይህ ለእኔ እውነተኛ በረከት ነበር። በተለያዩ የግንባታ ሥፍራዎች እንድሠራ ስለምመደብ ለመስበክ የሚያስችሉኝን አጋጣሚዎች ለማግኘት ያለመታከት እጥር ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜያት ከካምፑ ውጪ በመሄድ እስከ ምሽቱ ድረስ እሰብክ የነበረ ቢሆንም ወደ ሰፈራ ጣቢያው በምመለስበት ወቅት በጭራሽ ችግር ገጥሞኝ አያውቅም።

ይሖዋ ጥረቴን ባርኮልኛል። በሰፈራ ጣቢያው አቅራቢያ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ቢሆንም ከተማው ውስጥ ግን ቪልማ ክሩሚንያ የተባሉ በዕድሜ የገፉ እህት ብቻ ነበሩ። እኔና እኚህ እህት በርካታ ወጣቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን። አልፎ አልፎ ወንድሞችና እህቶች ከሪጋ ድረስ እየመጡ በአገልግሎቱ ይካፈሉ ነበር፤ ከሌኒንግራድም (ከአሁኗ ሴይንት ፒተርስበርግ) አንዳንድ ዘወትር አቅኚዎች ይመጡ ነበር። በይሖዋ እርዳታ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ቻልን፤ ብዙም ሳይቆይ እኔም አቅኚ በመሆን በስብከቱ ሥራ ላይ በወር 90 ሰዓት ማሳለፍ ጀመርኩ።

በሚያዝያ 7, 1990 ጉዳዬ ቫልሚራ በሚገኘው የሕዝብ ሸንጎ ፊት በድጋሚ እንዲታይ ተደረገ። ችሎቱ መሰማት ሲጀምር አቃቤ ሕጉ ማን እንደሆነ አስታወስኩ። ከዚህ ወጣት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አድርገን ነበር! እሱም አስታውሶኝ ኖሮ ፈገግ አለ ሆኖም ምንም ቃል አልተናገረም። በዚያች ቀን በዋለው ችሎት ላይ ዳኛው የተናገሯቸውን የሚከተሉትን ቃላት መቼም አልረሳቸውም:- “ዩሪ፣ ከአራት ዓመት በፊት እንድትታሰር የተላለፈብህ ውሳኔ ሕገ ወጥ ነበር። መጀመሪያውኑም ሊወነጅሉህ ባልተገባ።” ሳይታሰብ ነፃ ወጣሁ!

የክርስቶስ ወታደር

በሰኔ 1990 በሪጋ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ወደ ምዝገባው ቢሮ በድጋሚ ሄድኩኝ። ከአራት ዓመት በፊት በወታደራዊ አገልግሎት እንደማልካፈል በገለጽኩላቸው ረጅም ጠረጴዛ ባለው ክፍል ውስጥ በሚሠሩት ሌተና ኮሎኔል ፊት እንደገና ቀረብኩ። በዚህ ወቅት ግን ሰላም ሊሉኝ ከመቀመጫቸው ተነስተው እጄን በመጨበጥ “ያ ሁሉ እንዲደርስብህ መደረጉ አሳፋሪ ነው። እንደዚያ በመሆኑ አዝኛለሁ” አሉኝ።

እኔም “የክርስቶስ ወታደር እንደመሆኔ መጠን የተጣለብኝን ተልእኮ መወጣት አለብኝ። እርስዎም ቢሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ቃል ከገባላቸው አስደሳችና ዘላለማዊ ሕይወት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ” ስል መለስኩላቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ኮሎኔሉም “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቼ እያነበብኩ ነው” አሉኝ። በወቅቱ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ይዤ ነበር። a ስለሆነም ስለ መጨረሻው ጊዜ ምልክቶች የሚናገረውን ምዕራፍ በመግለጥ ካሳየኋቸው በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ካሉት ክንውኖች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ አስረዳኋቸው። ልባዊ በሆነ የምስጋናና የአድናቆት ስሜት ተሞልተው እጄን ጨበጡና ሥራዬ የተሳካ እንዲሆንልኝ መልካም ምኞታቸውን ገለጹልኝ።

በወቅቱ በላትቪያ ያለው ማሳ አዝመራው ነጥቶ ለአጨዳ ደርሶ ነበር። (ዮሐንስ 4:35) በ1991 የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ በመላው አገሪቱ የተሾሙት የጉባኤ ሽማግሌዎች ብዛት ሁለት ብቻ ነበር! ከዓመት በኋላ በላትቪያ ይገኝ የነበረው አንድ ጉባኤ የላትቪያ ተናጋሪና የሩሲያ ተናጋሪ ጉባኤ በመባል ለሁለት ተከፈለ። እኔም የሩሲያ ተናጋሪ በሆነው ጉባኤ ውስጥ የማገልገል መብት አገኘሁ። የነበረው እድገት እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በቀጣዩ ዓመት ጉባኤያችን ለሦስት ተከፈለ! ወደኋላ መለስ ብዬ ሳየው ይሖዋ ራሱ በጎቹን ወደ ድርጅቱ ይመራቸው እንደነበር ግልጽ ነው።

በ1998 ከሪጋ በስተ ደቡብ ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የልጋቫ ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። በዚሁ ዓመት ሴይንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ ሶልኔችኖዬ ውስጥ በሩሲያ ቋንቋ ይሰጥ በነበረው የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። በዚህ ትምህርት ቤት ለመሠልጠን ከላትቪያ ውስጥ የመጀመሪያው ሰው ነበርኩ። ትምህርት ቤቱ በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ሰዎችን በፍቅር መያዙ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንድገነዘብ ረዳኝ። በትምህርት ቤቱ ከተማርናቸው በርካታ ቁም ነገሮች ይበልጥ እኔን የነካኝ የቤቴል ቤተሰቦችና አስተማሪዎቻችን ያሳዩን የነበረው ፍቅርና አሳቢነት ነበር።

በ2001 ካሪና የተባለች ተወዳጅ ክርስቲያን ባገባሁ ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ካሪናም እንደኔ ልዩ አቅኚ ሆነች፤ በየዕለቱ ከአገልግሎት ስትመለስ የሚታይባት የደስታ ስሜት ለእኔም ማበረታቻ ሆኖኛል። በእርግጥም ይሖዋን ማገልገል ታላቅ ደስታ ያስገኛል። በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ያሳለፍኩት አስቸጋሪ ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ በእርሱ መታመን እንዳለብኝ አስተምሮኛል። ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና ሉዓላዊነቱን ለመደገፍ የቱንም ያህል መሥዋዕት ቢከፈል አያስቆጭም። ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳቴ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል። “እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር” ይሖዋን ማገልገል በመቻሌ ከፍ ያለ ክብር ይሰማኛል።—2 ጢሞቴዎስ 2:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር ለአራት ዓመት እንድታሰር ተፈርዶብኝ ወደ ሪጋ ማዕከላዊ እስር ቤት ተላክሁ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከካሪና ጋር ስናገለግል