በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል መመስገን ይወዳል። ምስጋና ጥሩ ነገር እንደሠራን እንዲሰማን ስለሚያደርግ ደስታ ይሰጠናል። የሌሎችን አድናቆት ማግኘታችን የሥራችንን ጥራት ለማሻሻል ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርግም ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች እንደማይወዱን ስንገነዘብ ደስ አይለንም። ጥሩ ምላሽ ሳናገኝ ስንቀር ወይም ነቀፋ ሲሰነዘርብን መንፈሳችን ሊደቆስ ይችላል። ሌሎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት ስለ ራሳችን ባለን ግምት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል።

ሌሎች ለእኛ ስላላቸው አመለካከት ትኩረት አለመስጠት ስህተት ነው። እንዲያውም ሌሎች ስለ እኛ ያላቸውን አመለካከት እንዲነግሩን መጠየቃችን ይጠቅመናል። ሰዎች የሚሰጡን አስተያየት ላቅ ባለ የሥነ ምግባር መሥፈርት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ማስተካከያ እንድናደርግ የሚያነሳሳ በጎ ኃይል ሊሆነን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:31-33) ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የብዙኃኑ አመለካከት ሚዛኑን የሳተ ነው። የካህናት አለቆችና ሌሎች ሰዎች “‘ስቀለው! ስቀለው!’ እያሉ ይጮኹ” በነበረ ጊዜ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል የተዛባ አመለካከት እንደነበራቸው አስብ። (ሉቃስ 23:13, 21-25) በተሳሳተ መረጃ ወይም በቅናት አሊያም በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ አመለካከቶችን ችላ ብሎ ማሳለፍ ሊያስፈልግ ይችላል። ስለዚህ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀምና ሌሎች ለሚሰነዝሩት አስተያየት ማስተዋል የተሞላበት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

ትልቅ ግምት የሚሰጠው የማን አመለካከት ነው?

በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ባሉ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንፈልጋለን። እነዚህም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የቤተሰባችንን አባሎች እንዲሁም ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ያጠቃልላሉ። (ሮሜ 15:2፤ ቈላስይስ 3:18-21) የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያሳዩን ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ‘እርስ በርስ መበረታታት’ መቻላችን ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። (ሮሜ 1:11, 12) ‘ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ በትሕትና’ እናስባለን። (ፊልጵስዩስ 2:2-4) ከዚህም በተጨማሪ ተቀባይነት ማግኘት የምንፈልገው ‘በመሪዎቻችን’ ማለትም በጉባኤ ሽማግሌዎች ዘንድ ነው።—ዕብራውያን 13:17

እንዲሁም “በውጭ ባሉት ዘንድ መልካም ምስክርነት” ማትረፍ አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:7) እምነታችንን የማይጋሩ ዘመዶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንና ጎረቤቶቻችን በአክብሮት የሚያዩን መሆኑ በጣም ያበረታታል! ደግሞስ ምሥራቹን የምንሰብክላቸው ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ እንዲሰጡ ስንል ለእኛ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ጥረት እናደርግ የለ? በኅብረተሰቡ ዘንድ ንጹሕ ሥነ ምግባር የምንከተል፣ ጽድቅ ወዳድና ሐቀኛ ሰዎች እንደሆንን መታወቃችን ለአምላክ ክብር ያመጣል። (1 ጴጥሮስ 2:12) ይሁን እንጂ በሌሎች ዘንድ ለመወደድ ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጣስ ወይም ለእኛ አድናቆት እንዲኖራቸው ብለን ማስመሰል አንፈልግም። ሁሉንም ሰው ማስደሰት እንደማንችል ማወቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደ ሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለዚሁ ነው።” (ዮሐንስ 15:19) በሚቃወሙን ሰዎች ዘንድ አክብሮት ለማትረፍ ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራል?

የተቃዋሚዎችን አክብሮት ማግኘት

ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።” (ማቴዎስ 10:22) እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ አንዳንድ ጊዜ ኃይለኛ ነቀፋ ያስከትልብናል። የተዛባ አመለካከት ያላቸው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት “ሕዝቡን ለዓመጽ እንደምናነሳሳ” ወይም “ሥልጣናቸውን እንደምናዳክም” ይናገሩ ይሆናል። በግልጽ የሚቃወሙን ሰዎች መታገድ ያለብን ችግር ፈጣሪ ኑፋቄ እንደሆንን ሊናገሩ ይችላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 28:22) አንዳንድ ጊዜ እነዚህን የሐሰት ክሶች መና ማስቀረት እንችላለን። እንዴት? “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት” የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር በመከተል ነው። (1 ጴጥሮስ 3:15) ከዚህ በተጨማሪ “የማይነቀፍ ጤናማ አነጋገር [በማሳየት] . . . ተቃዋሚ ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር በማጣት እንዲያፍር” ማድረግ ይኖርብናል።—ቲቶ 2:8

ስማችንን ከነቀፋ ለማጽዳት ጥረት የምናደርግ ቢሆንም እንኳ አግባብ ባልሆነ መንገድ ስማችን ሲጠፋ ተስፋ መቁረጥ ወይም በሐዘን መዋጥ አይኖርብንም። ፍጹም የነበረው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ እንኳ አምላክን ተሳድቧል፣ ቄሳርን ተቃውሟል አልፎ ተርፎም አጋንንት አለበት በሚል ተወንጅሏል። (ማቴዎስ 9:3፤ ማርቆስ 3:22፤ ዮሐንስ 19:12) ሐዋርያው ጳውሎስ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶበታል። (1 ቆሮንቶስ 4:13) ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ ለእንዲህ ዓይነቱ ትችት ቦታ ሳይሰጡ ሥራቸውን በትጋት አከናውነዋል። (ማቴዎስ 15:14) ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ስለሆነ’ በጠላቶቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንደማይችሉ ያውቁ ነበር። (1 ዮሐንስ 5:19) በዛሬው ጊዜ እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመናል። እኛን የሚጠሉን ተቃዋሚዎች የውሸት ወሬ ቢያስወሩብን በፍርሃት መሸማቀቅ አይኖርብንም።—ማቴዎስ 5:11

ትክክለኛ ማንነታችን የሚለካው በማን አመለካከት ነው?

ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት በውስጣዊ ዝንባሌያቸውና ስለ እኛ በሰሙት ነገር ላይ የተመካ ስለሆነ በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ሲያመሰግኑንና ሲያከብሩን ሌሎች ደግሞ ይሰድቡናል እንዲሁም ይጠሉናል። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እስከተመራን ድረስ ደስተኛ የምንሆንበትና ሰላማችንን ጠብቀን የምንኖርበት በቂ ምክንያት አለን።

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በማንኛውም ነገር በአምላክ ቃል የምንመራ ከሆነ የይሖዋ አምላክንና የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። ደግሞም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይሖዋና ልጁ ለእኛ ያላቸው አመለካከት ነው። እነርሱ ለእኛ ያላቸው አመለካከት የእኛን ትክክለኛ ማንነት ያሳያል። በመጨረሻም፣ ሕይወታችን የተመካው በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘታችን ላይ ነው።—ዮሐንስ 5:27፤ ያዕቆብ 1:12

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ምስጋና የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ስላለኝ ሰዎች ሲያመሰግኑኝ እፍረት ይሰማኛል።”ሕንዳዊው ገጣሚ ራቢንድራናት ታጎር

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእምነት ባልደረቦቻችን ስለ እኛ ያላቸውን አመለካከት መስማታችን ይጠቅመናል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Culver Pictures