በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!

መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!

መጥፎ አስተሳሰብን ተዋጉ!

በኢዮብ ላይ የደረሰውን ከባድ መከራ ሰምተው ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉት ሦስቱ ጓደኞቹ ሊያስተዛዝኑትና ሊያጽናኑት ወደ እርሱ መጡ። (ኢዮብ 2:11) ከሦስቱ ተደማጭነት ያለውም ሆነ ምናልባትም በዕድሜ የሚበልጣቸው ኤልፋዝ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ በቅድሚያ የተናገረውም ሆነ ብዙ ሐሳብ የሰጠው እርሱ ነበር። ኤልፋዝ ባደረጋቸው ሦስት ንግግሮች ላይ ያንጸባረቀው ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው?

ኤልፋዝ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ተአምራዊ የሆነ ክስተት በማስታወስ እንዲህ አለ:- “መንፈስ ሽው ብሎ በፊቴ አለፈ፤ የገላዬም ጠጒር ቆመ። እርሱም ቆመ፣ ምን እንደሆነ ግን መለየት አልቻልሁም፤ አንድ ቅርጽ በዐይኔ ፊት ነበረ፤ በእርጭታ ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” (ኢዮብ 4:15, 16) በኤልፋዝ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ አድርጎ የነበረው ምን ዓይነት መንፈስ ነው? ቀጥሎ የተናገረው ነቀፋ አዘል ንግግር፣ መንፈሱ ከአንድ ታማኝ የይሖዋ መልአክ የመነጨ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል። (ኢዮብ 4:17, 18) ተጽዕኖ ያሳደረበት ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ ውሸት በመናገራቸው ኤልፋዝንና ሁለቱን ጓደኞቹን ይገስጻቸው ነበር? (ኢዮብ 42:7) በእርግጥም፣ ኤልፋዝ ይናገር የነበረው በአጋንንት ተጽዕኖ ነው። የተናገራቸው ሐሳቦች አምላካዊ አስተሳሰብን አያንጸባርቁም።

ኤልፋዝ የተናገራቸው ቃላት ምን ዓይነት ሐሳብ ያስተላልፋሉ? ራሳችንን ከአፍራሽ አስተሳሰብ መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለመቋቋምስ ምን እርምጃ መውሰድ ይገባናል?

‘በአገልጋዮቹ ላይ እምነት አይጥልም’

ኤልፋዝ በሦስቱም ንግግሮቹ ላይ አምላክ ከአገልጋዮቹ ብዙ ነገር ስለሚጠብቅ በሚያደርጉት ነገር አይደሰትም የሚል ሐሳብ አቅርቧል። ኤልፋዝ ለኢዮብ ‘እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ ላይ እምነት አይጥልም፣ መላእክቱንም በስህተታቸው ይወቅሳቸዋል’ ብሎታል። (ኢዮብ 4:18) ቆየት ብሎም “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በእርሱ ፊቱ ንጹሓን አይደሉም” ብሏል። (ኢዮብ 15:15) “አንተ ጻድቅ ብትሆን ሁሉን የሚችለውን አምላክ ምን ደስ ታሰኘዋለህ?” በማለትም ጠይቆታል። (ኢዮብ 22:3) በልዳዶስም ይህን ሐሳብ በመጋራት ‘በፊቱ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለችም፣ ከዋክብትም ንጹሓን አይደሉም’ በማለት አክሎ ተናገረ።—ኢዮብ 25:5

እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያደርግብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ አምላክ ከእኛ በጣም ብዙ ነገር እንደሚፈልግ አድርገን ወደ ማሰብ ሊመራን ይችላል። ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ያበላሸዋል። ከዚህም በላይ፣ እንዲህ ባለው አመለካከት ከተሸነፍን አስፈላጊ የሆነ ተግሣጽ ቢሰጠን እንኳ የምንሰጠው ምላሽ ምን ይሆናል? የተሰጠንን ተግሣጽ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ልባችን ‘በእግዚአብሔር ላይ ማማረር’ ሊጀምርና በእርሱ ቅር ልንሰኝ እንችላለን። (ምሳሌ 19:3) ይህ ደግሞ አስከፊ መንፈሳዊ አደጋ ያስከትልብናል!

“ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን?”

አምላክ ከፍጡራኑ ብዙ ይጠብቃል የሚለው አመለካከት ሰዎችን እንደማይረቡ አድርጎ ይመለከታቸዋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር በጣም ይዛመዳል። ኤልፋዝ በሦስተኛ ንግግሩ ላይ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቧል:- “ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን? ጠቢብ እንኳ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል?” (ኢዮብ 22:2) ኤልፋዝ፣ ሰው ለአምላክ ምንም አይጠቅመውም ማለቱ ነበር። በተመሳሳይም በልዳዶስ “ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፣ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ይችላልን?” በማለት የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርቧል። (ኢዮብ 25:4) በዚህ አባባል መሠረት ሟች የሆነው ኢዮብ በአምላክ ዘንድ ንጹሕ አቋም ይኖረኛል ብሎ እንዴት ሊያስብ ይችላል?

ዛሬ ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ባላቸው አፍራሽ አስተሳሰብ የተነሳ ይሠቃያሉ። ለዚህ መንስኤ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ አስተዳደግ፣ የኑሮ ውጣ ውረድ ወይም የዘር አሊያም የጎሳ ጥላቻ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ሰይጣንና አጋንንቱ አንድ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ሲመለከቱ ደስ ይሰኛሉ። አንድ ሰው የፈለገውን ነገር ቢያደርግ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሊያስደስተው እንደማይችል እንዲሰማው ማድረግ ከቻሉ ግለሰቡ በከንቱነት ስሜት የመሸነፉ አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ያለው ግለሰብ ከሕያው አምላክ ሊርቅ ብሎም ሊኮበልል ይችላል።—ዕብራውያን 2:1፤ 3:12

የዕድሜ መግፋትና የጤና ችግሮች አቅማችንን ሊገድቡብን ይችላሉ። ወጣት፣ ጤነኛና ጠንካሮች ሳለን እናደርገው ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን በመንግሥቱ አገልግሎት የምናበረክተው ድርሻ ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰይጣንና አጋንንቱ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት በቂ አይደለም ብለን እንድናስብ እንደሚፈልጉ ማወቃችን በጣም ይጠቅመናል! እንዲህ ያለውን አመለካከት መዋጋት አለብን።

አፍራሽ የሆነን አስተሳሰብ መዋጋት የሚቻለው እንዴት ነው?

ኢዮብ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ መከራ ቢያመጣበትም እንኳ “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5 የ1954 ትርጉም) ኢዮብ አምላክን ስለሚወድ የመጣው ቢመጣ ፍጹም አቋሙን ጠብቆ ለመኖር ወስኖ ነበር። አፍራሽ አስተሳሰብን ለመዋጋት ቁልፉ ይህ ነው። ስለ አምላክ ፍቅር ትክክለኛ እውቀት ማዳበርና ልባዊ አድናቆት መኮትኮት ይኖርብናል። ለእርሱ ያለንን ፍቅር ማሳደግም ይገባናል። እንዲህ ማድረግ የሚቻለው የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናትና በተማርነው ላይ በጸሎት በማሰላሰል ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ 3:16 “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” ይላል። ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር ዓለም ጥልቅ ፍቅር ያለው ሲሆን ይህም ባለፉት ዘመናት ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ታይቷል። ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለይሖዋ ያለንን አድናቆት የሚገነባልን ከመሆኑም ሌላ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ያሳድግልናል፤ ይህ ደግሞ መጥፎ ወይም አፍራሽ አስተሳሰብን እንድንቋቋም ይረዳናል።

ለምሳሌ ያህል፣ ሰዶምና ገሞራ ጥፋት ተደቅኖባቸው በነበረበት ወቅት ይሖዋ አብርሃምን እንዴት እንዳነጋገረው እንመልከት። አብርሃም፣ ያስተላለፈውን ፍርድ አስመልክቶ ለይሖዋ ስምንት ጊዜ ጥያቄ አቅርቧል። ይሖዋ በዚያን ወቅት የተቆጣበት ወይም የተበሳጨበት ጊዜ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሰጠው መልስ አብርሃምን አጽናንቶታል እንዲሁም አበረታቶታል። (ዘፍጥረት 18:22-33) ከዚያም በኋላ ቢሆን አምላክ ሎጥንና ቤተሰቡን ከሰዶም ሲያወጣቸው ሎጥ ወደ ተራሮቹ ከመሄድ ይልቅ በቅርብ ወዳለችው ከተማ ለመሸሽ ጥያቄ አቀረበ። ይሖዋም “ይሁን እሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም” በማለት መለሰለት። (ዘፍጥረት 19:18-22) እነዚህ ዘገባዎች ይሖዋን ኃይለኛ፣ ጨካኝ፣ ወይም ፈላጭ ቆራጭ ገዥ እንደሆነ አድርገው ነው የሚገልጹት? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ የእርሱን ትክክለኛ ማንነት ማለትም አፍቃሪ፣ ደግ፣ መሐሪና የሰው ችግር የሚገባው ገዥ መሆኑን ያሳያሉ።

አምላክ እንከን የሚፈላልግና ሰዎች በሚያደርጉት ነገር የማይረካ ነው የሚለውን አመለካከት ውድቅ ለማድረግ በጥንቷ እስራኤል የነበሩትን የአሮንን፣ የዳዊትንና የምናሴን ምሳሌ መመልከት ይቻላል። አሮን ሦስት ከባድ መጥፎ ድርጊቶች ፈጽሟል። እነዚህም የወርቅ ጥጃ መሥራቱ፣ ከማርያም ጋር ተባብሮ ሙሴን መቃወሙ እንዲሁም በመሪባ አምላክን ሳይቀድስና ለእርሱ ክብር ሳይሰጥ መቅረቱ ናቸው። የሆነ ሆኖ ይሖዋ አሮን ያለውን ጥሩ ባሕርይ በማየት እስኪሞት ድረስ በሊቀ ካህንነት እንዲያገለግል ፈቅዶለታል።—ዘፀአት 32:3, 4፤ ዘኍልቍ 12:1, 2፤ 20:9-13

ንጉሥ ዳዊት በግዛት ዘመኑ ከባድ ኃጢአቶች ሠርቷል። እነርሱም ምንዝር መፈጸሙ፣ አንድ ንጹሕ ሰው እንዲገደል ማድረጉና ተገቢ ያልሆነ የሕዝብ ቆጠራ ማካሄዱ ናቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ዳዊት የገባውን ንስሐ የተመለከተ ከመሆኑም በተጨማሪ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በንግሥናው እንዲቀጥል በመፍቀድ የመንግሥት ቃል ኪዳኑ እንዲጸና አድርጓል።—2 ሳሙኤል 12:9፤ 1 ዜና መዋዕል 21:1-7

የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ለበዓል መሠዊያ የሠራና ልጆቹን በእሳት አሳልፎ የሰጠ ከመሆኑም በላይ መናፍስታዊ ድርጊቶች እንዲስፋፉ አድርጓል። በተጨማሪም በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሐሰት አማልክት መሠዊያዎች ሠርቷል። ይሁን እንጂ ልባዊ ንስሐ በመግባቱ ይሖዋ ይቅር ብሎታል፤ እንዲሁም ከምርኮ እንዲለቀቅ በማድረግ ወደ ንግሥናው መልሶታል። (2 ዜና መዋዕል 33:1-13) አምላክ ሰዎችን እንደ ከንቱ ነገር የሚቆጥራቸው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያደርግላቸው ነበር? በፍጹም!

ተጠያቂው ሐሰተኛው ከሳሽ ራሱ ነው

ሰይጣን፣ ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት እንዳሉት አድርጎ ቢከሰውም እንኳ የእነዚህ መጥፎ ባሕርያት ባለቤት እርሱ ራሱ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። ሰይጣን ጨካኝና በቃኝ የማያውቅ ነው። ይህንንም ጥንት ከሐሰት አምልኮ ጋር በተያያዘ ሕፃናትን መሥዋዕት ያደርጉበት ከነበረው ልማድ በግልጽ ማየት ይቻላል። ከሃዲ የሆኑት እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳልፈው ይሰጡ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ በይሖዋ ልብ ውስጥ ፈጽሞ የለም።—ኤርምያስ 7:31

በሰዎች ላይ እንከን የሚፈላልገው ሰይጣን እንጂ ይሖዋ አይደለም። በራእይ 12:10 ላይ ሰይጣን “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ” ተብሏል! በሌላ በኩል ደግሞ መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቆጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 130:3, 4

አፍራሽ አስተሳሰብ የማይኖርበት ጊዜ

ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ከሰማይ ሲጣሉ መላእክት ምን ያህል እፎይታ ተሰምቷቸው ይሆን! (ራእይ 12:7-9) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን በይሖዋ መላእክታዊ ቤተሰብ ላይ የሚያደርሱት ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የለም።—ዳንኤል 10:13

በቅርቡ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ደስ ይላቸዋል። የጥልቁን መክፈቻና ታላቅ ሠንሰለት በእጁ የያዘ ከሰማይ የሚመጣ መልአክ በቅርቡ ሰይጣንና አጋንንቱን አስሮ ምንም ማድረግ በማይችሉበት ጥልቅ ውስጥ ይጥላቸዋል። (ራእይ 20:1-3) በዚያን ጊዜ እንዴት ያለ ታላቅ ግልግል ይሆናል!

እስከዚያው ድረስ ግን ከመጥፎ አስተሳሰብ ራሳችንን እንጠብቅ። አፍራሽ ወይም መጥፎ የሆኑ አስተሳሰቦች ወደ አእምሯችን በሚመጡበት ጊዜ የይሖዋን ፍቅር በማሰብ እነዚህን አስተሳሰቦች ልንቋቋማቸው ይገባል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ‘ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችንንና ሐሳባችንን ይጠብቃል።’—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ አፍራሽ አስተሳሰብን ተቋቁሟል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎጥ፣ ይሖዋ የሰው ችግር የሚገባው ገዥ መሆኑን ተረድቶ ነበር